በትግራይ ክልል ያልመከነ የጦር መሣሪያ ፈንድቶ አምስት ሕጻናትን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, DW
በትግራይ ክልል፣ በአበርገለ የጭላ ወረዳ ያልመከነ የጦር መሣሪያ ፈንድቶ አምስት ሕጻናትን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ሞቱ።
በፍንዳታው አምስት አህዮችም ሕይወታቸው አልፏል።
ፍንዳታው የተከሰተው ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 17 ቀን 2019 ዓ. ም. በየጭላ ከተማ ልዩ ስሙ መአረይ ጣቢያ በሚባል አካባቢ ነው።
ፍንዳታው የተከሰተው ቁርጥራጭ ብረት የጫኑ አህዮች ከትግራይ ኃይሎች የጦር መሣርያ ማከማቻ ተነስተው ብረታ ብረት ወደሚገዙ ነጋዴዎች መውሰዳቸውን ተከትሎ መሆኑ ተገልጿል።
ከቁርጥራጭ ብረቶቹ ጋር አብሮ የተጫነ ቦምብን ጨምሮ ያልመከኑ የጦር መሣሪያዎችም መፈንዳታቸው ተመልክቷል።
በፍንዳታው የሁለት ዓመት ልጅን ጨምሮ አምስት ሕጻናት እና ሦስት አዋቂዎች መሞታቸውን ቢቢሲ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከነዋሪዎች እና ከሆስፒታል ምንጮች አረጋግጧል።
የየጭላ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዕርደይ አሰፋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በፍንዳታው 18 ሰዎች ተጐድተዋል፤ 15 ሰዎች ደግሞ ሆስፒታል ገብተዋል።
ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት ከ18ቱ ተጎጂዎች መካከል ሦስቱ ፍንዳታው ባጋጠመበት ቦታ ወድያውኑ ነበር የሞቱት።
በሆስፒታሉ 15 ተጎጂዎችን መቀበላቸውን እና ሁለቱ ሕክምና ሳይደረግላቸው መሞታቸውን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ ቀሪዎቹ ወደ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል እና ዓብይዓዲ ሆስፒታል በፍጥነት መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
"ከ18ቱ ተጎጂዎች ሦስቱ ወድያውኑ ነው የሞቱት። ሟቾች የሦስት፣ የአምስት፣ የስድስት እና የ12 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ናቸው" ብለዋል።
15 የተጎዱ ሰዎች ወደ ሆስፒታላቸው መወሰዳቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።
"ከ15ቱ ሁለቱ ብዙ ሳይቆዩ ሞተውብናል" ያሉት ሥራ አስኪያጁ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው፣ እጃቸው እና እግራቸው የተቆረጠ እና ሆዳቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሦስት ሰዎች ወደ ዓብይዓዲ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
ሰባት ተጎጂዎችን ደግሞ ወደ መቀለ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል መላካቸውን ተናግረዋል።
"ወደ ዓብይዓዲ ሪፈር ካልናቸው ሁለቱም ብዙ የሕክምና እርዳታ ሳያገኙ ሕይወታቸው አልፏል። ወደ ዓይደር ከላክናቸው ደግሞ ኣንዱ በ20 ደቂቃ ውስጥ ሞቷል" ብለዋል።
ሥራ አስኪያጁ ጨምረው እንዳሉት ቁርጥራጭ ብረቱን የሚገዙ ነጋዴዎች ማኅበረሰቡ በሚኖርበት የመኖሪያ አካባቢ ይሰበስባሉ።
በቤታቸው በር ላይ ሲጫወቱ የነበሩ አምስት ልጆችም ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ያልመከነውን ፈንጂ የያዙ አምስት አህዮች ወዲያውኑ ሞተዋል።
አቶ አዱኛ ገብረመድኅን የጭላ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ የሁለት ዓመት ከሁለት ወር ልጃቸው ባልመከነው የጦር መሣሪያ ሞቶባቸዋል።
የዘጠኝ ዓመት ልጃቸውም ተጎድቶ በዓብይዓዲ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል።

የፎቶው ባለመብት, Google Earth
"ልጆቼ በመንደራቸው እየተጫወቱ ሳሉ በፍንዳታው ተመቱ። የሞተው ልጄ ዕድሜው ሁለት ዓመት ከሁለት ወር ነበር። ተጎድቶ በሕይወት የተረፈው ልጄ ደግሞ ዘጠኝ ዓመቱ ነው። አንገቱ፣ እግሩ እና ዐይኑ ላይ ተጎድቷል። እኔ ከዓብይዓዲ ሆስፒታል የልጄ ሬሳ ይዤ ተመለስኩኝ።"
የስድስት ዓመት ሴት ልጃቸውን በፍንዳታው ያጡት ቄስ ገብረሥላሴ መረሳ አራት የቤተሰባቸው አባላትም ተጎድተዋል።
ቄስ ገብረሥላሴ ጨቅላ ልጃቸውን ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ብረታ ብረት የምትገዛው የመጀመሪያ ልጃቸው፣ ባለቤታቸው፣ የልጅ ልጃቸው እና የወንድማቸው ልጅም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ወደ መቀለ ወደሚገኘው የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ተልከዋል።
"ከተቆራረጠ ብረት ጋር ያልመከነ የጦር መሣርያም በአህያ ጭነው መጡ። አህያው ከቤታችን ፊት ለፊት ወድቆ ከባድ ፍንዳታ ተከሰተ" ሲሉ የተፈጠረውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"አንድ ልጄ ሞተች፣ ብረት የምትገዛ ትልቋ ልጄ፣ የልጅ ልጄ፣ ባለቤቴ እና ልጄ ተጎድተው በዓይደር ሆስፒታል ነው ያሉት። ልጄ ከቤታችን ፊት ለፊት ብረት መግዛት ጀምራ ነበር። 'ይህ ያልተተኮሰ ጥይት የያዘ ነው አልገዛም' አለቻቸው። በዛ በመሃል አህያው የተሸከመው ከብዶት ወደቀ።"
የትግራይ ኃይሎች የጦር መሣሪያ ማከማቻ የሚገኘው በአበርገለ ወረዳ የጭላ ዓሪቋ በሚባል ልዩ ቦታ ነው።

የፎቶው ባለመብት, HAILE AYGISH
የአካባቢው አስተዳደር የፀጥታ ኃይሎች እና ሚሊሻዎች ጥበቃ ሲያደርጉለት ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ በትግራይ ኃይሎች እንዲሁም በፌዴራል መከላከያ ሠራዊት እና በአጋሩ የትግራይ የሰላም ኃይል መካከል ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ፣ በአበርገለ የጭላ ወረዳ የሚገኙ የአስተዳደር እና የፀጥታ ኃይሎች ከአካባቢው መውጣታቸው ይነገራል።
ጦሩ ከወጣ በኋላ ነዋሪዎች ብረታ ብረት ለመሰብሰብ ወደ አካባቢው መሄዳቸው ተገልጿል።
ቢቢሲ ያረጋገጣቸው ከፕላኔት ላብስ ፒቢሲ የተገኙ የሳተላይት ምሥሎች፣ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 22 ቀን በሰሜናዊ የጭላ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ እና ቃጠሎ መከሰቱን አሳይተዋል።
እነዚህ የሳተላይት ምሥሎች እሳቱ በአውሮፓውያኑ ከጥቅምት 22 እስከ 23 ባለው ጊዜ ውስጥ አብዛኛውን የጦር መሣሪያ ማከማቻ እንዳወደመ ያሳያሉ።
የቢቢሲ ምንጮቹ እንደገለጹት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ተገድለዋል።
በዓሪቋ የተከማቹት የጦር መሣሪያዎች ለማኅበረሰቡ አስጊ ናቸው። ነገር ግን በርካታ ነዋሪዎች የተቆራረጠ ብረታ ብረት ከመጋዘኑ አውጥተው ከመሸጥ ባሻገር ያልተተኮሱ የጦር መሳሪያዎች መፍታት እንደጀመሩም ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህም ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 12 በዓሪቋ በሚገኘው የጦር መሣሪያ ማከማቻ ውስጥ ለተነሳው የእሳት አደጋ መንስዔ እንደሆነም ይነገራል።
ቢቢሲ የእሳቱን መንስዔ በገለልተኛ ወገን አላረጋገጠም።
የዓሪቋ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ከኢትዮጵያ-ኤርትራ ጦርነት ጀምሮ የነበረ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Planet Labs PBC
የህወሓት አስተዳደር እና የፀጥታ ኃይሎች አካባቢውን ለቅቀው ሲወጡ በአካባቢው ምንም ዓይነት ይፋዊ አስተዳደር አልነበረም።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የተቋቋመው የትግራይ ባለ አደራ አስተዳደር እስካሁን ወደ አካባቢው አልገባም።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአበርገለ የጭላ ወረዳን ተቆጣጥሯል።
የሃይማኖት መሪዎች እና የአገር ሽማግሌዎች ነዋሪዎች ብረታ ብረት ለመውሰድ ወደ ጦር መሣሪያ ማከማቻው እንዳይሄዱ ግንዛቤ ለመፍጠር እየሠሩ ቢሆንም ብዙም ውጤት አልተገኘም።
በትግራይ ማእከላዊ ዞን፣ የአበርገለ የጭላ ወረዳ ሊቀ ጳጳስ ቄስ ገብረሕይወት ዓለኔ ከሕዝቡ ጋር በተደጋጋሚ ቢነጋገሩም "ምላሽ አለማግኘታቸውን" ይገልጻሉ።
ጥቅምት 12 የእሳት አደጋ ከተከሰተ በኋላም በአካባቢው ያሉ የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ነዋሪዎች ወደ ጦር መሣሪያ ማከማቻው እንዳይሄዱ እንዲቆጣጠሩ መንገራቸውን ገልጸዋል።
ጥቅምት 16 ወታደሮች ማኅበረሰቡ ወደ አካባቢው እንዳይሄድ እንዲጠብቁ አሳስበው ፍንዳታው በነጋታው ጥቅምት 17 መነሳቱን አስረድተዋል።
በአካባቢው ጦርነት ካሳደረው ጫና በተጨማሪ ድርቅም ማኅበረሰቡን እየፈተነው ይገኛል።
የየጭላ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዕርደይ አሰፋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ነዋሪዎች ችግሮቻቸውን ለመፍታት ብረታ ብረት ሰብስቦ በመሸጥ ሥራ ተሰማርተዋል።
"እነዚህ ፈንጂዎች በእያንዳንዱ ግለሰብ ቤት ውስጥ ይከማቹ ነበር። መጀመሪያ ላይ በኪሎ ግራም በ50 ብር ይሸጡ ነበር" ብለዋል።
ማኅበረሰቡን ከአደጋ ለመጠበቅ የተከማቹት የጦር መሣሪያዎች እንዲወገዱ ጠይቀዋል። የቤት ለቤት ፍተሻ ተደርጎ ያልፈነዱ መሣሪያዎች ተሰብስበው ደኅንነቱ በተጠበቀ ሥፍራ እንዲወገዱም አሳስበዋል።
































