ግጭት ከተቀሰቀሰባት ሞያሌ ወደ ኬንያ ድንበር "ሮኬቶች መተኮሳቸውን" የኬንያ ፖሊስ አስታወቀ

ሁለተኛ ሳምንቱን በያዘው የሞያሌ ግጭት ሦስት "አርፒጂ የጦር መሣሪያዎች" ከኢትዮጵያ ድንበር ወደ ኬንያ ድንበር መተኮሳቸውን የኬንያ ፖሊስ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገለጹ።
የሞያሌ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ጆርጅ ኪፕኮሮስ፤ ትናንት እሑድ ጥቅምት 22/2019 ዓ. ም. ሮኬቶቹ መተኮሳቸውን አረጋግጠዋል።
እስከ አሁን ድረስ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት አልተሰጠም።
የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ በኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ በኦሮሞ እና በሶማሌ ማኅበረሰቦች መካከል በተፈጠረው ግጭት 50,000 ገደማ ሰዎች ሸሽተው ወደ ኬንያ ግዛት መግባታቸውን አስታውቋል።
ስለ ግጭቱ ከኦሮሚያ ክልል፣ ከሶማሌ ክልል እንዲሁም ከኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የተሰጠ አስተያየት የለም።
የሞያሌ የፖሊስ አዛዥ የኬንያ መከላከያ ሠራዊት "ያለ ምንም ችግር ሦስት ሮኬቶችን አምክኗል" ብለዋል።
ሴሲ ሁለተኛ ደረጃ በሚባል ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ሮኬት መውደቁን ተናግረዋል። ሌሎቹ ሁለት ሮኬቶች ደግሞ በዚያው አካባቢ እንደወደቁ አክለዋል።
ኮማንደር ጆርጅ እንዳሉት በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ ነው። የፀጥታ ኃይሎች በድንበር ላይ መሰማራታቸውንም ገልጸዋል።
"መንግስት ፖሊስን፣ የኬንያ መከላከያ ኃይሎችን እና የድንበር ጠባቂዎችን አሰማርቷል" ብለዋል።
በተተኮሱት ሮኬቶች የተጎዱ ሰዎች እንደሌሉ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ትናንት እሑድ አንድ ሰው "ከኢትዮጵያ በኩል በተተኮሰ ተባራሪ ጥይት" መቁሰሉ ተዘግቧል።
ክስተቱ በድንበር አካባቢ በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ላይ የተፈጠረውን ስጋት እንዳባባሰው አክለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራት የኬንያ ሞያሌ ነዋሪ በግጭቱ ምክንያት "ሰላም ማጣታቸውን" ገልጻለች።
"ግጭት ያለው በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ነው። እኛ ኬንያ ውስጥ በሰላም የምንኖር ዜጎች ነን። ሌሊትም ቀንም ሰላም እየነሱን ነው። እየመጡ እየበጠበጡን ነው። የኬንያ መንግሥት እንዲያስቆምልን እንጠይቃለን" ብላለች።
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ የተከሰተው ይህ ግጭት በሶማሌ ክልል ሰንደቅ ዓላማ መሰቀል ውዝግብ የተነሳ መሆኑን የሁለቱም ክልል ከንቲባዎች እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ አስረድተዋል።
አስተያየታቸውን ለቢቢሲ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ከባድ መሣሪያዎችን ጨምሮ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ በርካታ ሰዎች መገደላቸው እና ነዋሪዎች ወደ ኬንያ መሰደዳቸውን አብራርተዋል።
እንደ ኬንያ ቀይ መስቀል መረጃ ከሆነ ግጭቱን በመሸሽ ወደ ኬንያ የሸሹ ግለሰቦች ቁጥር ከ40,000 በላይ ይደርሳል።
የሞያሌ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግጭቱ ከአንድ ሳምንት በላይ ቢቆይም፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ሆነ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት በከተማው ሰላምና መረጋጋት እንዲመለስ በቂ የፀጥታ ኃይል አላሰማሩም።
ወደ ኬንያ ከተሰደዱት መካከል 15,000 ያህሉ በተፈናቃዮች መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፣ ብዙዎቹ ደግሞ በአካባቢው ማኅበረሰቦች ቤት ማረፋቸው ተሰምቷል።
የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች እንደሚገልጹት፣ የተፈናቀሉት ሰዎች ምግብ፣ መጠለያ እና ሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች በአስቸኳይ ያስፈልጓቸዋል።
ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል በሚዋሰኑባት ሞያሌ ከተማ ግጭት የተቀሰቀሰው የኦሮሚያ ክልል ይገባኛል በሚለው አካባቢ የሶማሌ ክልል ባንዲራ ከተሰቀለ በኋላ ነው።
የኦሮሚያ ክልል የሞያሌ ከተማ ከንቲባ ገልማ ኮሮፊቻ፣ ግጭቱን "አሳዛኝ" ሲሉ ገልጸው፣ ከሶማሌ ክልል የመጡ የፀጥታ ኃይሎች ውጥረቱ እንዲባባስ አስተዋጽኦ አድርገዋል ሲሉ ወንጅለዋል።
ከንቲባው ግጭቱ የተከሰተው ለረዥም ጊዜ አብረው ሲኖሩ እና የቅርብ ማኅበራዊ እና ቤተሰባዊ ግንኙነቶች ባሏቸው የኦሮሞ እና የሶማሌ ማኅበረሰቦች መካከል መሆኑን ገልጸዋል።
በሶማሌ ክልል የሚገኘው የሞያሌ ከተማ ከንቲባ ኩላ አሊ አብዲራሕማን በበኩላቸው ክሱን ውድቅ አድርገው "ሰላም እያለን እና ምንም ዓይነት ግጭት ሳይኖር፣ ከእንቅልፋችን ነቅተን ራሳችንን በጦርነት መሃል አገኘን። ግጭቱ የተጀመረው በቅርቡ በከተማው ውስጥ በከፈትነው የአስተዳደር ቢሮ ምክንያት ነው" ብለዋል።
ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ የሞያሌ ነዋሪዎች፣ ከባድ ውጊያዎች ለቀናት ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸው በግጭቱ ላይ ጥቅም ላይ የዋሉ የጦር መሣሪያዎች ከአካባቢው አርብቶ አደር ማኅበረሰብ በላይ ያሉ ኃይሎች በግጭቱ ውስጥ ተሳትፈዋል የሚል ጥርጣሬ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በርካታ ነዋሪዎች፣ በግጭቱ ወቅት ጥቅም ላይ የዋሉ መሣሪያዎች ብቻ ሳይሆን የተሳተፉ ግለሰቦችም "የላቀ ወታደራዊ ሥልጠና" ያላቸው መሆናቸውን ይናገራሉ።
በተጨማሪ ከሌላ አካባቢ የመጡ ተዋጊዎች በዚህ ግጭት መሳተፋቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እንዳሏቸው ገልጿል።
ቢቢሲ ይህንን በገለልተኛ ወገን አላረጋገጠም።

































