ኡጋንዳ ከ20 ዓመታት በኋላ ወታደሮቿን ከሶማሊያ ማስወጣት ጀመረች

ወታደሮች በአንድ ስፍራ ተሰባስበው
የምስሉ መግለጫ, ኡጋንዳ ለመጀመርያ ጊዜ ወታደሮቿን በሶማሊያ ያሰማራችው እንደ አውሮፓውያኑ በ2007 ነበር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኡጋንዳ ለ20 ዓመታት ያህል በሶማሊያ ሰላም በማስከበር ላይ ተሰማርተው የቆዩ ወታደሮቿን ማስወጣት ጀመረች።

የኡጋንዳ ጦር ኃይል አዛዥ ጄኔራል ሙሁዚ ካይነሩጋባ የጦሩን መውጣት ካስታወቁ በኋላ የመጀመሪያዎቹ 109 ወታደሮችን ያካተተው ቡድን ዓርብ ዕለት ከሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ መውጣቱ ተዘግቧል።

የኡጋንዳ ጦር ኃይል ተጠባባቂ ቃል አቀባይ ክሪስ ማጌዚ ቢቢሲ ላቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጡም።

ኡጋንዳ እንደ አውሮፓውያኑ በ2007 የተመሰረተው የአፍሪካ ኅብረት የሶማልያ ተልዕኮ (አሚሶም) ስር ወታደሮችን ወደ ሶማሊያ የላከች የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ነች።

ኢትዮጰያም የዚሁ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ አካል ነበረች።

የተልዕኮው ዋና ዓላማ የሶማሊያን የሽግግር መንግሥት ከእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ጥቃት መጠበቅ እና በአገሪቱ ውስጥ መረጋጋትን ማጠናከር ነበር።

ኡጋንዳ በሶማሊያ በአልሻባብ ላይ በተደረጉ ዘመቻዎች ውስጥ ቁልፍ ሚና ስትጫወት የቆየች ሲሆን፣ የወታደሮቹ መውጣት በቀጣይ የሶማሊያ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ምን ተጽእኖ ይኖረዋል የሚለው ትኩረት ስቧል።

ባለፈው ሳምንት የኡጋንዳ ጦር ኃይል አዛዥ ጄኔራል ሙሁዚ ካይነሩጋባ ኡጋንዳ ወታደሮቿን ከሶማሊያ ማስወጣት መጀመሯን እና የጸጥታ ኃላፊነቱን ለሶማሊያ የጸጥታ ኃይሎች እንደምታስረክብ ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"እንደገባነው ቃል ከሶማሊያ የኡጋንዳ መከላከያ ኃይሎችን ማስወጣት ጀምረናል። ከ20 ዓመታት ደምና መስዋዕትነት በኋላ የጸጥታ ኃላፊነቱን ለሶማሊያ ወንድሞቻችን እያስረከብን ነው" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

ኡጋንዳ ወታደሮቿ የማስወጣት ሂደትን የምታከናውነው ደረጃ በደረጃ ሲሆን፣ እስከ ነሐሴ 2027 ድረስ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

ኡጋንዳ እአአ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ስር በሶማሊያ የጸጥታ ማስከበር ውስጥ ስትሳተፍ ቆይታለች።

በዚህ ጊዜ ውስጥም በአልሻባብ ላይ በተደረጉ ዘመቻዎች ውስጥ ዋና ሚና ተጫውታለች። የጦሩ መውጣት የሶማሊያ መንግሥት የራሱን የጸጥታ ኃይሎች በማጠናከር የአገሪቱን ደህንነት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እየሞከረ ባለበት ወቅት የተጀመረ ነው።

ነገር ግን ኡጋንዳ በሶማሊያ ያላትን ወታደራዊ ተሳትፎ ሙሉ በሙሉ አላቋረጠችም። በተለየ ሁለትዮሽ የደህንነት ስምምነት መሠረት የተሰማሩ ወታደሮቿ በአገሪቱ ውስጥ መቆየታቸውን ይቀጥላሉ።

በሶማሊያ በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ስር የሚገኙ 4,500 የሚሆኑ ወታደሮች እንዳሉ ሲገመት፣ ተጨማሪ 2,000 ወታደሮች ደግሞ በሁለትዮሽ ስምምነቶች አማካኝነት ተሰማርተዋል።

በሶማሊያ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አልሻባብ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የማዕከላዊ መንግሥቱ ላይ ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።

የኡጋንዳ ጦር በ2007 ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሊያ የተሰማራ ሲሆን፣ አልሻባብን ከሞቃዲሾ እና ከሌሎች ዋና ዋና ከተሞች በማስወጣት ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

ወታደሮቹ ከሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ጋር በመሆን ቁልፍ ግዛቶችን መልሰው ለመቆጣጠር እና አስፈላጊ የመንግሥት ተቋማትን ለማስጠበቅ ተዋግተዋል።

የኡጋንዳ ጦር በተከታታይ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮዎች ስር ተሳትፎውን የቀጠለ ሲሆን፣ እአአ በ2022 የተጀመረውና የደህንነት ኃላፊነቶችን ቀስ በቀስ ወደ ሶማሊያ ለማስተላለፍ ባለመው የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮን (አትሚስ) ውስጥም ይሳተፋል።

አትሚስ እአአ በ2025 የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ተተክቷል። ይህ ተልዕኮ የሶማሊያን የደህንነት ተቋማት ለማጠናከርና የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ሙሉ የደህንነት ኃላፊነት እንዲወስዱ ማዘጋጀት ላይ ትኩረት ያደርጋል።

ሆኖም አውሶም በአሜሪካ እና በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ መቀነስ ምክንያት ለወደፊት በሚደረግለት የገንዘብ ድጋፍ ላይ እርግጠኛ ባለመሆኑ ፈተና ገጥሞታል።

በጥር ወር የሚጀምረው የ12 ወር የሽግግር እቅድ፣ ሶማሊያና አፍሪካ ኅብረት አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን እንዲፈልጉ ጊዜ ይሰጣቸዋል።