ቀጥታ , ከኢትዮጵያ ሞያሌ ግጭት ሸሽተው ወደ ኬንያ የገቡ ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ ደረሰ

በኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ የተከሰተውን ግጭት በመሸሽ ወደ ሰሜናዊ ኬንያ የተሻገሩ ሰዎች ቁጥር ወደ 50 ሺህ መድረሱን ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) አስታወቀ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ከሞያሌ ግጭት ሸሽተው ወደ ኬንያ የገቡ ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ ደረሰ

    ወደ ሰሜን ኬንያ የገቡ የሞያሌ ነዋሪዎች
    የምስሉ መግለጫ, ወደ ሰሜን ኬንያ የገቡ የሞያሌ ነዋሪዎች

    በኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ የተከሰተውን ግጭት በመሸሽ ወደ ሰሜናዊ ኬንያ የተሻገሩ ሰዎች ቁጥር ወደ 50 ሺህ መድረሱን ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) አስታወቀ።

    በኢትዮጵያ በኩል ያለው ሁኔታ ባለመረጋጋቱ ተጨማሪ ሰዎች ተፈናቅለው ሊመጡ እንደሚችሉ የተሰጋ ሲሆን፣ የኬንያ መንግሥት እና የሰብዓዊ ድጋፍ አጋሮች እስከ 80 ሺህ ለሚደርሱ ሰዎች የሚሆን የእርዳታ ዕቅድ እያዘጋጁ ነው።

    በኬንያ የአይኦኤም ኃላፊ ኖማጉጉ ንኩቤ እንዳሉት “በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ኬንያ ተሻግረዋል፤ አብዛኞቹም በአካባቢው ማኅበረሰቦች ጋር ተጠልለው ይገኛሉ። ሁኔታው የሚለዋወጥ በመሆኑ በሚቀጥሉት ቀናት ተጨማሪ ሰዎች ሊመጡ ይችላሉ።”

    እስከ ሐሙስ ጥቅምት 19 ድረስ ከኢትዮጵያ ተሻግረው በሰሜናዊ ኬንያ ወደ ምትገኘው ማርሳቢት ግዛት ሞያሌ ከተማ የገቡት ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ መድረሱ ተመዘግቧል። ከእነዚህ መካከልም አንዳንዶቹ በድንበር አካባቢ ከሚኖሩ ማኅበረሰቦች ጋር ሲቆዩ፣ ሌሎች ደግሞ በአምስት ጊዜያዊ መጠለያ ሥፍራዎች መቀመጣቸውን ድርጅቱ ገልጿል።

    ከኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ ተፈናቅለው ወደ ኬንያ ግዛት መግባታቸው የተነገረው ሰዎች ቁጥር አሁንም የመጀመሪያ ደረጃ ግምት እንደሆነ እና ተጨማሪ መረጃ ሲገኝ አሃዙ ሊለወጥ እንደሚችል አይኦኤም አመልክቷል።

    አይኦኤም ከኬንያ መንግሥት እና ከግዛቲቱ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከአጋር ተቋማት ጋር በመሆን የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ዕቅድ እያዘጋጀ መሆኑን እና ይህም መጠለያ፣ ሌሎች መሠረታዊ አቅርቦት እና ሕክምና ለማቅረብ ግምገማ እና ክትትልን እደያረገ ነው ተብሏል።

    ተያያዥ ዜና

  2. ሩሲያ በዩክሬን የባቡር ጣቢያ ላይ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት ቢያንስ 13 ሰዎች ተገደሉ

    በድኒፕሮ ከተፈፀመ ጥቃት በኋላ አንድ ካሜራ ውስጥ ያልገባ የተጎዳብ ሰው ከባቡር ጣቢያው ሲያወጡ የሚታዩ ወንዶች

    በዩክሬን ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው በሰዎች የተጨናነቀ የባቡር ጣቢያ ላይ ሩሲያ በፈፀመችው የድሮን ጥቃት 13 ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ገለፁ።

    በጥቃቱ ከተገደሉት በተጨማሪ የ11 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ ቢያንስ 10 ሰዎች መቁሰላቸውን ጥቃቱ የተፈፀመበት የድኒፕሮፔትሮቭስክ ግዛት አስተዳዳሪ ኦሌክሳንደር ሃንዛ ተናግረዋል።

    የዩክሬን የባቡር አስተዳደር ድርጅት እንደገለፀው፣ ወደ ዛፖሪዥያ በመጓዝ ላይ የነበረው ባቡር በድኒፕሮ ከሚገኙ ጣቢያዎች በአንዱ ላይ ሳለ ነበር በድሮኑ የተመታው።

    ሞስኮ የዩክሬንን ሰፊ የባቡር አውታረ መረብ በተደጋጋሚ ዒላማ ብታደርግም፣ ሲቪሎች ላይ ሆን ብላ ጥቃት እንደምትፈፅም የሚቀርብባትን ክስ ታስተባብላለች።

    በሌላ በኩል በሰሜን ዩክሬን በምትገኘው ቼርኒሂቭ ከተማ ማዕከል ላይ በተፈፀመ የሩሲያ ሚሳዔል ጥቃት ሁለት የ15 ዓመት ልጃገረዶች መገደላቸውን የክልሉ አስተዳዳሪ ቪያቼስላቭ ቻውስ ገልፀዋል። ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 11 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ተናግረዋል።

    በድኒፕሮ ከተማ፣ የሐሙሱ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ከፍተኛ የስጋት ማስጠንቀቂያ መታወጁን የዩክሬን ባቡር ኃላፊ ኦሌክሳንደር ፐርትሶቭስኪ ገልፀዋል።

  3. ቱርክ እና ግብፅ በሜዲትራኒያን ላይ የባሕር ኃይል ልምምድ ሊያደርጉ ነው

    የቱርክ መርከብ (ፎቶ ፋይል)

    ቱርክ እና ግብፅ በሜዲትራኒያን ላይ የባሕር ኃይል ወታደራዊ ልምምድ ለማካሄድ ያቀዱ ሲሆን ቱርክ ከግብፅ ጋር ያላትን የባሕር ላይ ድንበርን ለመወሰን ከስምምነት ለመድረስ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች።

    ለረጅም ጊዜ ግንኙነታቸው ሻክሮ የቆዩት ሁለቱ አገራት ከአንድ ሳምንት በኋላ በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ የጋራ ወደታራዊ ልምምድ ሊያደርጉ እንደሆነ የቱርክ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ሚኒስቴሩ እንዳመለከተው “ፍረንድሺፕ ሲ 2026” ተብሎ የተሰየመ የጋራ የባሕር ኃይል ልምምዱ የሚካሄደው ከጥቅምት 25 እስከ 30 ቀን 2019 ዓ.ም. በግብፅ የባሕር ዳርቻ ከተማ አሌክሳንድሪያ ነው።

    በምሥራቃዊ ሜዲትራኒያን ባሕር ላይ የባሕር ላይ ድንበር የሚጎራበቱት ሁለቱ አገራት በሚያካሂዱት ወታደራዊ ልምምድ የቱርክ እና የግብፅ የባሕር ኃይል ክፍሎች እና ወታደራዊ ሠራተኞች ይሳተፋሉ።

    የቱርክ መከላከያ ሚኒስቴር ጨምሮም በጋራ ጥቅምላይ በመመሥረት ቱርክ ከግብፅ ጋር ያላትን “የባሕር ድንበር ለመወሰን” ስምምነት ለመፈረም ዝግጁ መሆኗን አስታውቋል።

    ቱርክ በምሥራቃዊ ሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ያላትን ሕጋዊ መብቶች እና ጥቅሞች በዓለም አቀፍ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ማስጠበቋን እንደምትቀጥል የገለጸው የመከላከያ ሚኒስቴሩ፤ በተመሳሳይም ቱርክ ለቀጣናዊ ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋት ያላትን አስተዋፅኦ እንደምትቀጥል አስታውቋል።

    • ተያያዥ ዜና
  4. ዓመታዊው የቻይና የፖለቲካ ጉባዔ “የፓርቲ ሥነ ሥርዓት” ላይ ትኩረቱን ሲያደርግ፣ በታሪክ ከፍተኛ አባላት ተሰናበቱ

    የቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂንፒንግ
    የምስሉ መግለጫ, በዢ ጂንፒንግ የ14 ዓመታት የመሪነት ታሪክ ውስጥ በፓርቲ ጉባዔ ከ300 በታች አባላት ሲሳተፉ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው

    ቻይና ትልቁን ዓመታዊ የፖለቲካ ጉባዔ ስታጠናቅቅ፣ በኮሚኒስት ፓርቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 33 አባላት ከፓርቲው ተባረሩ።

    የፓርቲው ጉባዔ ላይ ከወትሮው በላይ ባዶ ወንበሮች ታይተዋል።

    በአምስተኛው የፓርቲው ጉባዔ 279 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተሳትፈዋል። ይህ ቁጥር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በጥቅምት 2025 በተካሄደው አራተኛ ጉባዔ ላይ ከተሳተፉ 315 አባላት እንዲሁም በሐምሌ 2024 በተካሄደው ሦስተኛ ጉባዔ ላይ ከነበሩት 364 ተሳታፊዎች በእጅጉ ያነሰ ነው።

    የቅርብ ዓመታት ጉባዔዎች በኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች እና በልማት ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ የነበሩ ሲሆን በዚህ ሳምንት የተካሄደው ስብሰባ ግን የፓርቲ ሥነ ሥርዓትን ዋነኛ አጀንዳው አድርጓል።

    ዢ ጂንፒንግ እአአ በ2012 ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ከሙስና ጋር የሚደረገውን ትግል የአስተዳደራቸው ዋና ጉዳይ አድርገዋል። ፕሬዝደንቱ ሙስና “የፓርቲው ትልቁ ስጋት” እንደሆነ ይገልፃሉ።

    በቤጂንግ በአንድ ሆቴል ውስጥ ለአራት ቀናት በዝግ የተካሄደው ስብሰባ ማብቂያ ላይ ከፓርቲው ከተባረሩት 33 አባላት ውስጥ 16ቱ የጦር ኃይሉ አባላት ስለመሆናቸው ዛሬ የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

    እነዚህ አባላት “ከባድ የሥነ ሥርዓትና የሕግ ጥሰቶች” እንደፈፀሙ ከቀረበባቸው ጠቅለል ያለ ክስ ውጭ፣ በዝርዝር የቀረበባቸው ውንጀላ ምን እንደሆነ በመግለጫው አልተብራራም። እንደዚህ ያሉ ጠቅለል ብለው የሚቀርቡ ክሶች በዢ ጂንፒንግ የፀረ ሙስና ዘመቻ የተለመዱ ሆነው ቀጥለዋል።

    • ተያያዥዜና
  5. ኤል ሳልቫዶር አራት የጠፉ ወታደሮችን ለመታደግ ከ2,000 በላይ ወታደሮችን ወደ ሄይቲ አሰማራች

    የኤል ሳልቫዶር ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በሄይቲ መዲና ፖርት ኦ ፕሪንስ
    የምስሉ መግለጫ, የኤል ሳልቫዶር ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች የሄይቲ መዲና ፖርት ኦ ፕሪንስ ገብተዋል

    ኤል ሳልቫዶር ከሁለት ሳምንታት ገደማ በፊት በሄይቲ የጠፉትን አራት ወታደሮቿን ሕይወት ለመታደግ ከ2,000 በላይ ወታደሮችን ወደ ሄይቲ መላኳን አስታወቀች።

    የኤል ሳልቫዶር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ወሳኝ የተባለው ይህን የወታደሮች ስምሪት በተመለከተ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ ለሄይቲው ጠቅላይ ሚኒስትር አሊክስ ዲዲዬር ፊልስ-አይሜ ገለፃ ማድረጋቸውን አስታውቋል።

    ፕሬዝዳንት ቡኬሌ ስምሪት የተጣቸው ከ 2,000 በላይ የሚሆኑት ወታደሮች በሄይቲ የወንበዴ ቡድኖች ላይ የሚደረገውን የፀጥታ ማስከበር ጥረት እንደሚያግዙም መናገራቸውን በመግለጫው ተመላክቷል። ይህ ስምሪት በተለያዩ አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተደገፈ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    በሄይቲ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በሚደግፈው ፀረ-ወንበዴ ተቋም ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ አራት የአየር ኃይል ቴክኒሻኖች መጥፋትን ተከትሎ በሁለቱ የመካከለኛው አሜሪካ አገራት መካከል ያለው ውጥረት ተባብሷል።

    በፀረ-ወንበዴ ኃይል ውስጥ አባል የሆኑት አራቱ ወታደሮች ጥይት በማይበሳው ተሽከርካሪ ወደ ጦር ሰፈራቸው እየተመለሱ ሳለ፣ በታጠቁ ቡድኖች ቁጥጥር ስር በሚገኝ አካባቢ ድንገተኛ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ሆኖም እስካሁን ድረስ ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን የለም።

    በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ፣ ሄይቲ የጠፉት ወታደሮች ናቸው በማለት አራት አስከሬን ለልዩ ኃይሎች ያስረከበች ቢሆንም፣ የኤል ሳልቫዶር ፕሬዝዳንት ቡኬሌ ግን አስከሬኖቹ ደብዛቸው ከጠፋ ወታደሮች ጋር እንደማይመሳሰል ገልጸዋል።

  6. የሆንግ ኮንግ አስተዳዳሪ 168 ሰዎች ለሞቱበት የእሳት አደጋ ይቅርታ ጠየቁ

    ጆን ሊ (መሀል ላይ ያሉት) እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዝቅ ብለው ይቅርታ ሲጠይቁ
    የምስሉ መግለጫ, ጆን ሊ (መሀል ላይ ያሉት) ከሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በጋራ ዝቅ ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል

    የሆንግ ኮንግ ዋና አስተዳዳሪ ጆን ሊ፣ ባለፈው ዓመት በከተማዋ በሚገኘው የዋንግ ፉክ ኮርት መኖሪያ ህንፃ ላይ ለተነሳውና የ168 ሰዎችን ሕይወት ለቀጠፈው ከፍተኛ የእሳት አደጋ ይቅርታ ጠየቁ።

    አስተዳዳሪው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ በእሳት አደጋው ክስተት “ጥልቅ ሀዘን” እንደተሰማቸው ገልፀው፣ በመንግሥታቸው ስም "ተጎጂዎችን እንዲሁም የከተማዋን ነዋሪዎች ይቅርታ እጠይቃለሁ" ብለዋል።

    በዚያው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ የተደረገ የገለልተኛ ኮሚቴ ሪፖርት፣ የእሳቱ መንስኤ “የግሉ ዘርፍ የሥነ-ምግባር ጉድለት" እንዲሁም “ለአስርት ዓመታት የዘለቀ የመንግሥት ተቋማት ውድቀት” መሆኑን አመልክቷል።

    በርካታ ሰዎች ያለቁበት የእሳት አደጋ የተከሰተው፣ በወቅቱ ሰፊ የእድሳት ስራ እየተካሄደበት በነበረው የአፓርታማ ህንፃ ውስጥ እንደ ሲጋራ ያለ ተቀጣጣይ ነገር የወረቀት ቁሳቁሶችን በማያያዙ እንደሆነ ጉዳዩን የመረመረው ገለልተኛ ኮሚቴ አስታውቋል።

    ጆን ሊ በበኩላቸው እንዲህ አይነቱ አደጋ ዳግም እንዳይከሰት ለማረጋገጥ በመንግሥት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

    አክለውም የከተማዋ የቤቶች አስተዳደር ዋና ጸሐፊ የነበሩት ዊኒ ሆ ለአደጋው ኃላፊነትን በመውሰድ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።

    በሆንግ ኮንግ ባለፈው ዓመት የተከሰተው የእሳት አደጋ፤ ከተማዋ በአስርት ዓመታት ውስጥ ካስተናገደቻቸው አደጋዎች ሁሉ እጅግ አሰቃቂውና የብዙ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ነው።

  7. አሜሪካ በሩዋንዳ መከላከያ ሚኒስቴር ላይ ማዕቀብ ጣለች

    ኤም23

    የሩዋንዳ መከላከያ ሚኒስቴር በምሥራቅ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እየተዋጋ ያለውን ኤም23 አማጺ ቡድን ይደግፋል በሚል በአሜሪካ ማዕቀብ ተጣለበት።

    ሩዋንዳ ወታደሮቿን ከአካባቢው እንድታስወጣ እና አማጺያኑን መደገፍ እንድታቆም ለማድረግ የተላለፈ ውሳኔ ነው።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ባሴት “ሩዋንዳ ለኤም23 የምትሰጠውን ድጋፍ ማቆም አለባት” ብለዋል።

    ከወራት በፊት በአሜሪካ አሸማጋይነት ዴሞክራቲክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ የሰላም ስምምነት ፈርመው ነበር።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት እንዳለው የሩዋንዳ መከላከያ ሚኒስቴር በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቹ ከኤም23 ጎን ተሰልፈው እንዲዋጉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

    የመሣሪያ፣ የመገልገያ፣ ሎጅስቲክስ እና የሥልጠና ድጋፍም አድርጓል።

    ኤም23 በማዕድን የበለፀጉትን የሰሜን እና ደቡብ ኪቭዩ አካባቢዎች ተቆጣጥሯል።

    አካባቢው በወርቅ እና ኮልታን ምርት ይታወቃል።

    አሜሪካ እንደምትለው ከሆነ አማጺያን ከሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች የሚወጣው ማዕድን ወደ ሩዋንዳ ገበያ ይገባል።

    ሩዋንዳ ከምታመርተው በላይ ማዕድን ኤክስፖርት እያደረገች መሆኑም ተመልክቷል።

  8. ማይክሮሶፍት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቹን ማሰናበቱን ባስታወቀ በቀናት ውስጥ ትርፉ አደገ

    የማይክሮሶፍት መሪ

    ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮሶፍት እስከ መስከረም ድረስ ያለው የሦስት ወራት ትርፉ ካለፈው ዓመት በ36.6 ቢሊዮን ዶላር ማደጉን ገለፀ።

    ኩባንያው ይህን ያለው ከሲሶ የሚበልጠውን የሰው ኃይሉን እንደሚቀንስ ካሳወቀ ከቀናት በኋላ ነው።

    በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ላይ ቢሊዮን ዶላሮችን እያፈሰሰ ያለው ኩባንያው ሰኞ ዕለት 60 ሺህ የሚሆኑ ሠራተኞቹን ወጪ ለመቀነስ ሲል እንደሚያሰናብት አስታውቋል።

    እንደ ሌሎች ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቹ ሁሉ ማይክሮሶፍት ኤአይ ላይ እየፈሰሰ ያለው ግዙፍ መዋዕለ ነዋይ አዋጭነት ላይ ጥያቄዎች ባልተመለሱበት ወቅት በኤአይ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ገንዘብ መድቧል።

    ረቡዕ ዕለት በኒው ዮርክ የአክሲዮን ገበያ በሰዓታት ውስጥ የማይክሮሶፍት ድርሻዎች ዋጋ በ2.9 በመቶ ጨምሯል።

    እንደ አማዞን፣ ሜታ እና አልፋቤት ያሉ ትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በዚህ ዓመት 700 ቢሊዮን ዶላር የኤአይ ቺፕ እና እንደ መረጃ ቋት ባሉ መሠረተ ልማቶች ላይ ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ማይክሮሶፍት የሩብ ዓመት ገቢው ካለፈው ዓመት በ19 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ወደ 92.3 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን አስታውቋል።

    ገቢው ከፍ ማለቱ የመረጃ ቋት ሥርዓቱ የመጣ መሆኑንም ጠቁሟል።

    በዚህ ሳምንት ኩባንያው “በፍላጎት ለውጥ” ምክንያት በካናዳ፣ ሕንድ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ የሚገኙ የተመረጡ ሠራተኞች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ማሰናበት እንደሚያደርግ አስታውቋል።

    በዚህ እርምጃ ለኩባንያው “ተለዋዋጭነትን” እንደሚሰጠው እና ለሠራተኞች ደግሞ የገንዘብ እና ቀጣይ የሥራ ድጋፍ እንደሚያቀርብ ገልጿል።

    ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም 220 ሺህ የሚሆኑ ሠራተኞች አሉት።

  9. የትራምፕን የማኅበራዊ ሚዲያ ፖስቶች ቀድሞ ለማግኘት 100 ሺህ ዶላር ሊጠየቅ ነው

    ትራምፕ እና ትሩዝ ሶሳል

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንብረት የሆነው ትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ፕሬዝዳንቱ በገጻቸው ላይ የሚያጋሯቸውን ፖስቶች የፋይናንስ ኩባንያዎች ቀድመው እንዲያገኙ የሚያስችል በወር እስከ 100 ሺህ ዶላር የሚያስከፍል አገልግሎት ለመጀመር ተስማማ።

    የመረጃ እና ዜና ምንጭ የሆኑት ብሉምበርግ እና ሁለት የዎል ስትሪት ፋይናንስ ተቋማት የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጸዋል።

    የዓለማችን ኃያል አገር አሜሪካ ፕሬዝዳንት የሆኑት የትራምፕ የሚሰጧቸው አስተያየቶች እና የሚያጋሯቸው መረጃዎች አንዳንድ ጊዜ በፋይናስ ገበያዎች ላይ ተጽእኖ ስለሚያሳድሩ፣ እነዚህን መረጃዎች ከሌሎች ቀድሞ ማግኘት ለንግድ ውሳኔዎች የተሻለ ዕድል ሊፈጥር ይችላል የሚል ዕምነት አለ።

    ይህ እርምጃ የጥቅም ግጭትን እና መንግሥታዊ መረጃ እኩል ባልሆነ መንገድ ለሰዎች እንዲደርስ ያደርጋል በሚል ተቃውሞ ያጋጠመው ሲሆን፤ ሁለት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትም በጉዳዩ ላይ ቅሬታ አቅርበዋል።

    የትራምፕ ተቋም ይህንን አገልግሎት ለሽያጭ ማቅረቡን በግልጽ ቃል ሳይክድ፣ ትሩዝ ሶሻል በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚታወቅ እና ከፍተኛ ፍላጎት ያለው አገልግሎት እየሰጠ ነው ብሏል።

    ነገር ግን ለትራምፕ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኘውን አገልግሎት በተመለከተ የወጣውን የሮይተርስ ዘገባን በስም ያልተገለጹ ምንጮች ላይ የተመሠረተ፣ ኩባንያውን፣ ደንበኞቹን እና የአክሲዮን ባለቤቶችን ለመጉዳት የታለመ አሳሳች መረጃ ነው ሲል አጣጥሎታል።

  10. የኔታኒያሁ ቡድን የእስራኤን ምርጫ እየመራ ቢሆንም አብላጫ ድምፅ ማግኘት አልቻለም

    ኔታኒያሁ

    በእስራኤል ጠቅላላ ምርጫ የወጡ ከፊል ውጤቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ምርጫውን እየመሩ መሆናቸውን አሳዩ።

    ኔታኒያሁ ዋነኛ ተቀናቃኛቸውን የቀድሞ የመከላከያ አዛዥ ጋዲ ኢስንኮትን እየመሩ ቢሆንም በፓርላማው አብላጫ ድምፅ እስካሁን አላገኙም።

    85 በመቶ በተቆጠረ ድምፅ የኔታኒያሁ ሊኩድ ፓርቲ እና የቀኝ ዘመም እና የአክራሪ ኦርቶዶክስ አይሁድ አጋሮቹ 120 ወንበሮች ባሉት ከነሴት (የእስራኤል ፓርላማ) 53 ወንበሮች አሸንፈዋል።

    የጋዲ ኢንስኮት ‘ያሸር’ የተባለው ፓርቲ እና ሌሎች ሦስት የአይሁድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች 58 መቀመጫዎችን በእጃቸው ማስገባታቸው እየተነገረ ነው።

    ሁለቱም መሪዎች ጥምር መንግሥት ለመቋቋም እንደሚሞክሩ ተናግረዋል።

    ያልተጠበቀ 19 ወንበሮችን ለማሸነፍ የተቃረቡት አረብ መር ፓርቲዎች ቀጣዩን የእስራኤል መሪ ለመወሰን ቁልፍ ሆነው ብቅ ሊሉ ይችላሉ።

    ይሁን እንጂ ከፓርቲዎቹ ውስጥ አንዱ ብቻ ከአይሁድ ፓርቲዎች ጋር በጋራ እንደሚሰራ አስታውቋል።

    እንደ ወታደሮች፣ ዲፕሎማቶች እና ሆስፒታል የተኙ ታካሚዎች ያሉ ከ430 ሺህ እስከ 480 ሺህ ድምፅ መስጠት ያልቻሉ መራጮች ድምፅ ገና አልተቆጠረም።

    የድምፅ ቆጠራው ከተረጋገጠ በኋላ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ከሁሉም የፖለቲካ ጥምረቶች ጋር ምክክር ያደርጋሉ።

    ፕሬዝዳንቱ መንግሥት ለመመስረት የተሻለ እድል አላቸው ብለው የሚያስቧቸውን መሪ ይጋብዛሉ። ይህ ሂደት ሳምንታትን ሊወስድ ይችላል።

    ይህ ሂደት የሚከሽፍ ከሆነ በመጨረሻም ሌላ ዙር ምርጫ ወደማካሄድ ያመራል።

    ፕሬዝዳንት ሄርዞግ በእስራኤል ጠቅላላ ምርጫ 77 በመቶ መራጮች ድምፅ መስጠታቸውን አወድሰዋል። ይህም በአገሪቱ ከሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ትልቁ የመራጮች ቁጥር ነው ተብሏል።

    ይፋዊ ውጤት በሚቀጥለው ሳምንት እቀበላለሁ ብለው እንደሚጠብቁም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ውጤቱን ከተቀበሉ በኋላ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር ውይይት ይጀምራሉ።

  11. የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ለኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ደብዳቤ መላካቸውን ትራምፕ አረጋገጡ

    ጄዲ ቫንስ

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ለኢራን ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊ ሞህሲን ራይዚ ደብዳቤ መላካቸውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አረጋገጡ።

    ዋል ስትሪት ጆርናል ያወጣውን ዘገባ ተከትሎ ከጄዲ ቫንስ ደብዳቤ እንደተላከላቸው ራይዚ ይፋ አድርገዋል። ደብዳቤው መላኩን ያረጋገጡት ትራምፕ ይዘቱም መድኃኒት እና የሕክምና አቅርቦት መሆኑን ገልጸዋል።

    ደብዳቤው ከድርድር ጋር የተያያዘ ነው ቢባልም ትራምፕ እንዳሉት ግን የሕክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒት መላክል ይመለከታል።

    ራይዚ “የሕክምና መገልገያዎች ማቅረብ ይፈልጋሉ። ጄዲ ቫንስ ምን እንደማስብ ጠይቆኛል። ማድረግ ከፈለጋችሁ ትችላላችሁ ብዬዋለሁ። የታመሙ ሰዎችን ለመርዳት የሚውል ቁሳቁስ መቅረቡ መልካም ነው” ብለዋል።

    አክሲዮስ የአሜሪካ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆን ግን ደብዳቤው የሰላም ንግግርን ለማስቀጠል ያለመ ነው።

    ደብዳቤው የተጻፈው አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ እንዳትወስድ እና “በኒውክሌር ጉዳይ ለመወያየት ነው” ብሏል።

    ዋል ስትሪት ጆርናል ትናንት ረቡዕ ባወጣው ዘገባ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን ጠቅሶ ቫንስ ደብዳቤ መላካቸውን አስነብቧል።

    የደብዳቤው ዓላማ የሰላም ውይይት ማስቀጠል መሆኑም በዘገባው ተመልክቷል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤው መድረሱን በተመለከተ መረጃ አልሰጠም። ሆኖም ግን በያዝነው ሳምንት የቀጣናው ከፍተኛ አመራሮች እና ወታደራዊ ባለሥልጣኖች በብዛት ወደ ቴህራን እየተጓዙ ነው።

    ትራምፕ ለአጋማሽ ዘመን ምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ኢራን ላይ አዲስ ጥቃት መሰንዘር ሊጀምሩ እንደሆነ ሲያስጠነቅቁ ተደምጠዋል።

  12. በስፔን በደረሰ የባቡር መጋጨት አደጋ ቢያንስ 68 ሰዎች ሞቱ

    የተጋጩት ባቡሮች

    በስፔን በከፍተኛ ፍጥነት የሚጓዝ ባቡር ከሌላ ባቡር ጋር ተጋጭቶ ቢያንስ 68 ሰዎች ሞቱ።

    የባቡር መጋጨት አደጋው በአገሪቱ ታሪክ ከአውሮፓውያኑ 2013 ወዲህ የከፋው ነው ተብሏል።

    የአገሪቱ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ በመቆጣጠሪያ ክፍል የኮምፒውተር ችግር በመፈጠሩ አደጋው ተከስቷል።

    ኢርዮ የተባው የባቡር ተቆጣጣሪ እንዳለው ሬንፍሬ በተባለው ባቡር “ከኋላው ግጭት” ደርሶበታል።

    በሁለቱ ባቡሮች ውስጥ 500 ሰዎች እየተጓዙ ነበር።

    በአደጋው ሥፍራ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ስፔን “ሐዘን ላይ ናት” ሲሉ ተናግረዋል።

    አብዛኞቹ የአገሪቱ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ለማቋረጥ ወስነዋል።

    በአካባቢው የሚገኙ የዐይን እማኞች አደጋውን “አሰቃቂ” ሲሉ ገልጸዋል።

  13. ታንዛኒያ ከ10 ዓመት በኋላ በድጋሚ የተፈጥሮ ጋዝ ማግኘቷን አስታወቀች

    የምናዚ ቤይ አካባቢ

    ታንዛኒያ በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በሚገኘው የምናዚ ቤይ አካባቢ ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ ማግኘቷን አስታወቀች። ይህም ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው ግኝት ነው።

    የታንዛኒያ የኃይል ሚኒስትር ጁማ ሆሜራ የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ 6.3 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንደሚሆን ገልጸው፣ በነዳጅ እና ጋዝ ዘርፍ ውስጥ አነስተኛ እድገት ላላት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገር “ትልቅ ምዕራፍ ነው” በማለት ተናግረዋል።

    አዲስ የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ በሚቀጥለው ወር መጀመሪያ ላይ ምርት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ አቅርቦትን ለማሳደግ ከፍ ያለ ሚና አለው ተብሏል። ታንዛንያ 57.54 ትሪሊዮን ኪውቢክ ጫማ የሚደርስ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አላት።

    የተፈጥሮ ጋዝ “ግኝቱ በተለይም በኢንዱስትሪ እድገት እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ፍላጎት እየጨመረ በሄደበት ወቅት፣ ሀገሪቱ በተመጣጣኝ ዋጋ አስተማማኝ፣ ንፁህ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ኃይል እንዲኖራት ለማረጋገጥ አስፈላጊ ነው” ሲሉ የኃይል ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

    እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2024 የወጣው የመንግሥት ስታቲስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው የተፈጥሮ ጋዝ 80% የታንዛንያን የኃይል ምንጮች ይሸፍናል።

  14. በግድያ የተከሰሰው የእንግሊዝ ወታደር ለኬንያ መንግሥት ተላልፎ አለመሰጠቱ ቁጣ ቀሰቀሰ

    አግነስ ዋንጂሩ

    በኬንያ አንዲትን ወጣት በመግደል የተከሰሰው የቀድሞ የእንግሊዝ ወታደር ለኬንያ መንግሥት ተላልፎ አለመሰጠቱ በሟች ቤተሰብ ዘንድ ቁጣ ቀሰቅሷል።

    ከ14 ዓመት በፊት በተፈጸመ ግድያ የተጠረጠረው ወታደር ተላልፎ የሚሰጥበት ችሎች በአውሮፓውያኑ 2027 መቀጠሩን ተከትሎ የሟች ቤተሰቦች ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።

    እ.ኤ.አ. በ2012 የተገደለችው ወጣት አግነስ ዋንጂሩ አስክሬኗ የእንግሊዝ ጦር ማሰልጠኛ ካምፕ አቅራቢያ በሚገኝ የውኃ ማቆሪያ ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ ተገኝቷል።

    በዚህ ወንጀል ተከሰሽ የሆነው ወታደር ለኬንያ መንግሥት ተላልፎ የሚሰጥበት ችሎት በፍጥነት አለመጠናቀቁ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌው ነው ሲሉ የሟች ቤተሰቦች ተናግረዋል።

    የ21 ዓመቷን እናት በመግደል የተከሰሰው የቀድሞው የእንግሊዝ ወታደር ሮበርት ጄምስ ፐርኪስ ችሎት፣ በሚቀጥለው ወር ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት ነበር። ሆኖም አሁን ላይ ለሚቀጥለው ዓመት የግንቦት ወር እንዲዘዋወር ተደርጓል።

    በግድያ ወንጀል የተጠረጠረው ፐርኪስ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር በዩናይትድ ኪንግደም በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፣ ለኬንያ ተላልፎ እንዲሰጥ መባሉን በመቃወም የቀረበበትን ክስ ግን አስተባብሏል።

    የዋንጂሩ ቤተሰብ የሆነችው ኤስቴር ኞኪ ለቢቢሲ እንደገለጸችው፣ ቤተሰቡ የችሎቱን መራዘም ያወቀው በእንግሊዝ ኤምባሲ በኩል ሲሆን፣ ምንም ዓይነት ኦፊሴላዊ ማብራሪያ አልደረሰውም ብላለች።

    ይህን ጉዳይ የኬንያን ባለሥልጣናት አለማሳወቃቸውንም ቤተሰቡ ተችቷል። ኞኪ በሰጠችው ማብራሪያ “ለዓመታት ታግሰናል፣ አሁን ግን ይህ ትዕግስታችን አለአግባብ እየተወሰደ ነው” በማለት ቁጣዋን ገልጻለች።

  15. ኢትዮጵያ "ከሰሃራ በታች አገራት ቀዳሚ" የሚያደርጓትን የጦር ጄቶች ተረከበች

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ባለቤታቸው እና የአየር ኃይል አዛዥ ሜ/ጄነራል ይልማ
    የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ባለቤታቸው እና የአየር ኃይል አዛዥ ሜ/ጄነራል ይልማ

    ለሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ሞስኮ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እጅግ ዘመናዊ የጦር ጄቶች እና የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን መረከባቸውን አስታወቁ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል በተደረሰ ስምምነት መሠረት 12 ሱ-35 እጅግ ዘመናዊ የጦር ጄቶች እና አራት የኤስ-400 የአየር መከላከያ መሣሪያዎችን ኢትዮጵያ ተረክባለች።

    ዘመናዊ መሆናቸው የተነገረላቸውን እነዚህን የጦር ጄቶች በመታጠቅ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት "ቀዳሚ" እንደምትሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

    ሱ-35 የተባሉት የጦር ጄቶች አራተኛው ትውልድ የሚባሉ ዘመናዊ መሆናቸውን ያመለከቱት ዐቢይ፤ አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት የተቀበላቸው 12 የጦር አውሮፕላኖች የመጀመሪያው ዙር አቅርቦት መሆናቸውን ገልጸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎቹን የተረከቡት ሁለቱ አገራት ከተስማሙበት ጊዜ ከአንድ ዓመት አስቀድሞ መሆኑን ጠቅሰው "ፕሬዝዳንት ፑቲን አውሮፕላኖቹን እንድንረከብ ስላሳዩት ትጋት" አመስግነዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር
    የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጦር መሣሪያዎቹ መረከባቸውን በገለጹበት ጽሁፍ ላይ "የአገራችንን ሰላም እና ደኅንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የምናደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ዛሬ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል" ብለዋል።

    ጨምረውም ኢትዮጵያ "በመከላከያ ኃይል እያደረገች ያለው ዝግጁነት ጥቃትን ቀድሞ ማስቀረት የሚያስችላትን አቅም እያላበሳት ነው" በማለት "ታሪካዊ ስኬት" እንደሆነ ገልጸዋል።

    የአገራትን ወታደራዊ አቅም የሚያወዳድረው ግሎባል ፋየርፓወር በአውሮፓውያኑ 2026 በወታደራዊ ኃይል ኢትዮጵያን ከ145 አገራት መካከል በ47ኛ ቦታ አስቀምጧታል።

    በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ካላቸው አገራት መካከል እንደምትገኝ ተገልጿል።

    በአፍሪካ ደረጃ ኢትዮጵያ ከግብፅ፣ ከአልጄሪያ፣ ከናይጄሪያ እና ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ አምስተኛ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ያላት አገር ተብላለች።

    ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ከ500 ሺህ በላይ ወታደሮች ያሏት ሲሆን፣ ብዙ ታንኮች፣ የመድፍ መሣሪያዎች እና የጦር አውሮፕላኖችም አሏት።

    የግሎባል ፋየርፓወር መመዘኛ የወታደራዊ አቅምን ለመለካት የሰው ኃይል፣ መሣሪያ፣ የፋይናንስ አቅም፣ ሎጂስቲክስ እና የአገሮችን መልክዓ ምድራዊ ሁኔታ ጨምሮ ከ60 በላይ መለኪያዎችን ይጠቀማል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሩሲያ የሄዱት ሦስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ላይ ለመሳትፍ ሲሆን፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።

    የጦር አውሮፕላን
    የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያ ተረክባዋለች ከተባሉት አውሮፕላኖች መካከል
  16. ባለቤቷ የነበሩትን የዚምባብዌ ምክትል ፕሬዝዳንት ለመግደል በመሞከር የተወነጀለችው ተከሳሽ ተለቀቀች

    የዚምባብዌ ምክትል ፕሬዝዳንት የቀድሞ ባለቤት ሜሪ ሙባይዋ
    የምስሉ መግለጫ, የዚምባብዌ ምክትል ፕሬዝዳንት የቀድሞ ባለቤት ሜሪ ሙባይዋ

    የግድያ ሙከራ በማድረግ ክስ ለሰባት ዓመታት የፍደድ ሂደት ላይ የነበረችው የዚምባብዌ ምክትል ፕሬዝዳንት የቀድሞ ባለቤት ከእስር ተለቀቀች።

    ሜሪ ሙባይዋ ክስ የተመሠረተባት በአውሮፓውያኑ 2019 የነበር። በወቅቱ ባለቤቷ የነበሩት ጄነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ በደቡብ አፍሪካ ሲያደርጉ የነበረውን የህክምና ክትትል ለማደናቀፍ እንደሞከረች በመግለጽ ከስሰዋት ነበር።

    ጉዳዩን ሲከታተሉ የቆዩት ዳኛ ተከሳሿ ሙባይዋ እንድትለቀቅ ትዕዛዝ የሰጡት ለዓመታት በዘለቀው የዳኝነት ሂደት በአእምሮ፣ አካል እና ፋይናንስ ተፅዕኖ እንደደረሰባት በመጥቀስ መሆኑን የአገሪቱ መንግሥት ዕለታዊ ጋዜጣ የሆነው ‘ዘ ሄራልድ’ ዘግቧል።

    ይህ ውሳኔ የተላለፈው ዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማነጋገር በሚል የፍርድ ሂደቱ ለአንድ ወር እንዲራዘም ከጠየቀ በኋላ ነው።

    የተከሳሿ ጠበቃ ውሳኔውን ዘግይቶ የመጣ ድል ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ የፍርድ ሂደቱ መጓተት ምክንያት የደንበኛቸው መብት መጣሱን ተናግረዋል።

    ማክሰኞ ዕለት በአገሪቱ መዲናዋ ሃራሬ የሚገኘው ፍርድ ቤት ደጅ ላይ ቃለ መጠይቅ የሰጡት ጠበቃዋ፣ መንግሥት አዲስ ክስ የሚመሠርት ከሆነ ጉዳዩ ሲከሰት እንደሚጋፈጡት አክለዋል።

    ሙባይዋ ክስ የቀረበባት፣ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና ላይ የነበሩትን ቺዌንጋን ለመግደል ሞክራለች በሚል ነው። ከዚያ በኋላ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ለአራት ወራት የህክምና ቆይታ ወደ ቻይና ተጉዘዋል።

    የዋስትና ጥያቄዋ ውድቅ የተደረገባት ሙባይዋ ለዓመታት በእስር ቆይታለች።

    ‘ኒው ዚምባብዌ’ የተሰኘው የዜና ድረ ገጽ እንደዘገበው፣ ሙባይዋ ፍርድ ቤቱ ደጅ ላይ ሆና በውሳኔው ደስታውን ስትገልጽ ታይታለች። በዚህ ውሳኔ ፍትሕ መረጋገጡን እና በጠበቃዋ እንደምትኮራም ተናግራለች።

    ምክትል ፕሬዝዳንት ቺዌንጋ በአውሮፓውያኑ 2017 የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን ከሥልጣን በተወገዱበት ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበቸራው።

  17. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ለመሳተፍ ሩሲያ ገቡ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሞስኮ ሲደርሱ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ረቡዕ በሚጀምረው ሦስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ሞስኮ መግባታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

    የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ከጉባኤው ጎን ለጎን አዲስ አበባ እና አሥመራን ለማሸማገል ፍላጎት ወዳሳየችው ሩሲያ ደርሰዋል።

    ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 18/2019 ዓ.ም. እና ነገ ሐሙስ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎችን ጨምሮ የ50 ገደማ የአፍሪካ አገራት ተወካዮች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

    ይህ ጉባኤ ግጭት ውስጥ የገቡት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ መድረክ ላይ የሚገኙበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

    የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ሞስኮ ጉባኤ ላይ ለመታደም ትናንት ማክሰኞ ሞስኮ መግባታቸውን የአገሪቱ ማስታወቂ ሚኒስቴር ገልጸዋል።

    ኢሳያስ በተጨማሪም ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ስለ “የሁለትዮሽ ትስስር” እና ለሁለቱ አገራት “የጋራ ጥቅም ባላቸው ሌሎች ጉዳዮች” ላይ እንደሚነጋገሩም አስታውቋል።

    የሩሲያ መንግሥት ከዚህ ጉባኤ ጎን የተባባሰ ቅራኔ ውስጥ የገቡትን ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ለማደራደር ዝግጁ መሆኗን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌይ ላቭሮቭ ትናንት ረቡዕ ገልጸዋል።

    ላቭሮቭ፣ "አሁን፣ ነገ ወይም ከነገ በስቲያ [ረቡዕ ወይም ሐሙስ] በሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሁለቱ አገራት መሪዎች ይህንን ዓይነት ፍላጎት ካሳዩ፣ በእርግጥም ግንኙነት እንዲያደርጉ ሁሉንም ዕድሎች እናመቻቻለን" ሲሉ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ላይ ተናግረዋል።

  18. ኪሊያን ምባፔ በቀድሞ ቻይና መሪ ላይ ቀልዷል በመባሉ ተቋማት ከተጫዋቹ ጋር የነበራቸውን የብራንድ ውል አቋረጡ

    ኪሊያን ምባፔ

    ታዋቂው የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ምባፔ የቻይና መሪ በነበሩት ማኦ ዜዱንግ ላይ ተሳልቋል መባሉን ተከትሎ በርካታ የንግድ ተቋማት ከእርሱ ጋር የነበራቸውን ውል አቋረጡ።

    ምባፔ “ዘ ብሪጅ” በተሰኘ የፈረንሳይ ፕሮግራም ላይ በነበረው ቆይታ በእሱ ላይ ከተሰሩ ቀልዶች ውስጥ “በጣም የሚያስቀኝ ቀልድ የአንድ ሰው ቪዲዮ ያለበት ነው፣ የቻይና አምባገነን መሪ ይመስለኛል” በማለት መናገሩ በበርካታ ቻይናውያን ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል።

    የሪያል ማድሪዱ የፊት መስመር ተጫዋች በንግግሩ የጠቀሰው ቀልድ፣ የእሱን ምስል እና የቻይናውን የቀድሞ መሪ ማኦን በማቀናበር የተሰራ ነው።

    ምባፔ በእግር ኳሱ ዓለም ባለው ከፍተኛ ተጽዕኖ የተነሳ ከተሰጠው “አምባገነኑ” ከሚለው ቅጽል ስሙ ጋር ተያይዞ እንደዚህ ዓይነት በምስል እና ቪሲዮ የተቀነባበሩ ቀልዶች (ሚም) ተሰርተዋል።

    ምንም እንኳን ማኦ ዜዱንግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፉ፣ ብዙ ጊዜም የኃይል እርምጃ የታከለበት አገዛዝ የመሩ ናቸው ቢባሉም፣ የኮሚኒስት ፓርቲ ዘንድ ከፍተኛ ክብር ባላቸው መሪ ላይ መቀለዱ ቻይናውያን አስቆጥቷል።

    ይህን ተከትሎ ከታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋች የሥራ ግንኙነት ያላቸው የቻይና ተቋማት ውላቸውን አቋርጠዋል።

    በቻይና ዘንድ ተወዳጅ የሆነውና በርካታ የብራንድ ማስተዋወቅ ውሎች ያሉት ምባፔ፣ “ከቻይና ገበያ ጥቅም እያገኘ ነገር ግን የቻይናን ህዝብ የሚያስቀይሙ አስተያየቶችን ይሰጣል” በሚል በቻይናውያን ደጋፊዎች ትችት እየቀረበበት ይገኛል።

  19. ከአልሸባብ ጋር በተደረገ ውጊያ በርካታ የሶማሊያ ወታደሮች ተገደሉ

    የአልሸባብ ታጣቂዎች

    በደቡባዊ ሶማሊያ የአገሪቱ ጦር እና አልሸባብ ትናንት ሰኞ ባደረጉት ከፍተኛ ውጊያ ወታደሮች መገደላቸውን የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ያነጋገራቸው የሶማሊያ ጦር አባላት የተገደሉት የወታደሮች በርካታ እንደሆኑ ገልጸዋል።

    አንድ ወታደር፣ የ40 የሞቱ ወታደሮችን አስከሬን እና ከ100 በላይ የቆሰሉ የሠራዊት አባላትን በመዲናዋ ሞቃዲሾ ወደሚገኙ ሆስፒታሎች ለማጓጓዝ መሳተፉን ለዜና ወኪሉ ተናግሯል።

    የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፣ ቡርሃከባ አውራጃ በሚገኘው ጃሜአ በተባለ አካባቢ በተካሄደው ውጊያ 75 ገደማ አልሸባብ ታጣቂዎች እንደተገደሉ እና 56 የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸውን ገልጿል።

    ታጣቂዎቹ የተገደሉት፣ “አልሸባብ አባላት መደበቂያ በሆነ ሥፍራ ላይ በተፈጸመ ከባድ ጥቃት” እንደሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተናግሯል።

    ሚኒስቴሩ በመግለጫው ምን ያህል የአገሪቱ ወታደሮች እንደተገሉ አልጠቀሰም። ይሁን እንጂ፣ በውጊያ ወቅት አልሸባብ ፈንጂ የተጫነባቸውን ተሽከርካሪዎች በመጠቀም ጥቃት መፈጸሙን አምኗል።

    በዚህም “በተወሰኑ የሠራዊቱ ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት” መድረሱን አረጋግጧል። ሮይተርስ ያነጋገረው ሌላ ወታደር፣ የአልሸባብ ፈንጂ የጫኑት መኪናዎች አምስት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ማውደማቸውን ገልጿል። በፍንዳታው በርካታ ወታደሮች ተገድለዋል የሚል ግምቱን አስቀምጧል።

    ባለፉት ቀናት በሶማሊያ ሳውዝ ዌስት ግዛት የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በአልሸባብ መካከል ውጊያ ሲደረግ ቆይቷል።

    ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት የተጣሉትን የክልሉ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የሚደግፉ ኃይሎች እና የመንግሥት ወታደሮችም ግጭት ውስጥ ናቸው።

    የአገሪቱ መንግሥት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኃይሎች ከአልሸባብ ጋር ተባብረው እንደሚያዋጉ በመግለጽ ይከስሳል።

    የክልሉ የቀድሞ ፕሬዝዳንትን የሚደግፉ ኃይሎች ግን በመንግሥት እና በአልሸባብ መካከል በሚደረጉ ውጊያዎች ውስጥ ምንም ተሳትፎ እንደሌላቸው በመግለጽ ክሱን ውድቅ ያደርጋሉ።

  20. ዮርዳኖስ ባለፈው ሳምንት ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ በሶሪያ ላይ የአፀፋ እርምጃ ወሰደች

    በአየር ጥቃት የወደመ ሕንፃ

    ዮርዳኖስ ባለፈው ሳምንት ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ በሶሪያ ላይ የአፀፋ እርምጃ ወሰደች።

    ባለፈው ሳምንት በቤተ ክርስቲያን ቀብር ላይ በተፈፀመ ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል።

    የዮርዳኖስ ጦር በሶሪያ “የሽብር ድርጅቶች” በተባሉት ዒላማዎች ላይ የአፀፋ እርምጃ ወስዷል።

    የሶሪያ የጤና ባለሥልጣናት ጥቃቱ በተፈፀመበት ዳራ ግዛት ሴቶች፣ ሕፃናትን እና አረጋዊያንን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

    ዮርዳኖስ ዝርዝር መጃ ሳትሰጥ የጦር አውሮፕላኖቿ “በርካታ አሸባሪዎችን” መግደላቸውን እና ማቁሰላቸውን አስታውቃለች።

    አገሪቱ ጥቃቱን ስትፈፅም ከሶሪያ ባመንግሥት ጋር መተባበሯን ገልፃለች። ይሁን እንጂ ሶሪያ የሰኞው ጥቃት ከመፈፀሙ አስቀድሞ እንዳውቅ አልተደረገም ብላለች።

    ይህ ጥቃት የተፈፀመው ባለፈው አርብ በዮርዳኖስ ካራክ አካባቢ በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈፀመ ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ከተገደሉ እና 34 ሰዎች ደግሞ ከቆሰሉ በኋላ ነው።

    ሶሪያ ለተፈፀመባት ጥቃት ከዮርዳኖስ ጋር የሚያገናኛትን ድንበር መዝጋቷን አስታውቃለች።

    የጥቃቱን ሙሉ ሁኔታ ለማረጋገጥም ምርመራ መጀመሩን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።