በኦሮሚያ ክልል ቱሉ ገና ባለፈው ሳምንት በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሲቪሎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአዲሱ አደረጃጀት ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ውስጥ በተካተተው በቀድሞው ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አቤ ደንጎሮ ወረዳ ቱሉ ገና ከተማ እና አካባቢው ባለፈው ሳምንት "የኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች" በፈፀሙት ጥቃት በርካታ ሲቪሎች መገደላቸውን የቢቢሲ ምንጮች ገለፁ።
በተለያዩ ቀናት ያናገርናቸው ስድስት የቱሉ ገና ከተማ ነዋሪዎች፣ የተገደሉትን ሰዎች አሐዝ በተመለከተ የተለያዩ ቁጥሮችን ጠቅሰዋል።
ጥቃቱ የተፈፀመው ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 15 እና 16/2019 ዓ. ም. መሆኑን የገለፁት እማኞቹ፣ በአንድ ቀን ብቻ "በትንሹ 25 ሰዎች" መቀበራቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ቀናት ያናገርናቸው እማኞች የሟቾቹን ቁጥር እስከ 28 ሲያደርሱ፣ ዛሬ ጥቅምት 23 ያናገርናቸው ተጎጂዎች እና ነዋሪዎች ደግሞ ግድያ የተፈፀመባቸው ሲቪሎች 40 እንደሚሆኑ ገልፀዋል።
ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ጥቃቱን የፈፀሙት "ገዳ ኮማንዶ" በመባል የሚታወቁ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኃይሎች እንደሆኑ አስረድተዋል።
እነዚህ ታጣቂዎች በፋኖ ታጣቂዎች ላይ "አሰሳ እና ኦፐሬሽን እናደርጋለን" በሚል ከጊዳ አያና ተነስተው ፋኖዎች አሉ ብለው የሚያስቡበት ስፍራ ሲሔዱ እና ሲመለሱ ቱሉ ገናን አቋርጠው በሚጓዙበት ጊዜ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ጥቃቱን እንደፈፀሙ ገልፀዋል።
ቢቢሲ ስለተፈፀመው ጥቃት ከገለልተኛ አካል መረጃ አላገኘም። ለጥቃቱ ተጠያቂ የተደረገው "ገዳ ኮማንዶን" ስለመኖሩ እንዲሁም እንቅስቃሴ ስለማድረጉም ቢቢሲ በገለልተኛ ወገን አላጣራም።
ከኦሮሚያ ክልል በኩል ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረትም አልተሳካም።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በምሥራቅ ወለጋ ጊዳ አያና የነበረውን ጥቃት ሸሽተው ወደ ቱሉ ገና እና አካባቢው የሔዱ ተፈናቃዮች፣ እንዲሁም በስፍራው የሚኖሩ ሌሎች ሰላማዊ ሰዎች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን የቢቢሲ ምንጮች አመልክተዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ አንዱ ሲናገሩ፣ "ገዳ ኮማንዶዎች ወደ ጊዳ አያና መጥተው እሁድ ዕለት ተኩስ ተጀመረ፤ ብዙ ንፁሐንን ያዙ፤ ሰኞም ተኩሱ ቀጠለ፤ ብዙ ንፁሐን ተገደሉ፤ ብዙ ቤቶችም ተቃጠሉ" ብለዋል።
ሁለት ቀን የነበረው ተኩስ ቆሞ ማክሰኞ ጥቅምት 17 የተገደሉ ሰዎችን ለማንሳት ፍለጋ ሲጀመር "17 ሟቾች" መገኘታቸውን ገልፀዋል። "በአንድ ቦታ ያገኘናቸው ዘጠኝ ሰዎች ናቸው። ሰላማዊ ሰዎች ናቸው፤ አንደኛው እንዲያውም የማውቀው ነጋዴ ነበረ" ሲሉ ተናግረዋል።
ዘጠኙ ሟቾች በከተማዋ በምትገኘው ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በጅምላ መቀበራቸውን የገለፁት ግለሰቡ፣ ሌሎቹ ስድስት ሟቾች ደግሞ በመስጊድ መቀበራቸውን ገልፀዋል።
በቀጣይ ቀን ደግሞ ሁለት ሟቾች መገኘታቸውን እና ባጠቃላይ በሁለቱ ቀናት 11 ሰዎች በቤተ ክርስቲያኗ መቀበራቸውን ያለፈው ሳምንት ሀሙስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዙሪያው ባሉ ሌሎች አካባቢዎች የተገደሉትን ጨምሮ "28 ሲቪሎች እንደተገደሉ" መረጃ አለኝ ብለዋል።
ከሟቾቹ መካከል የአንዱ እናት ለቢቢሲ ስለሁኔታው ሲያስረዱ፣ በግብርና እና በንግድ ሥራ ይተዳደር እንደነበረ የገለፁት ልጃቸው፣ በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ እንዳለ እሁድ ዕለት "በገዳ ኮማንዶ" ታጣቂዎች ከተወሰደ በኋላ "ተገድሎ" መገኘቱን ተናግረዋል።
እርሳቸው እና ቤተሰባቸው ባለፈው ነሐሴ ወር የነበረውን ጥቃት ተከትሎ ወደ ቱሉ ገና ተፈናቅለው ሔደው በኪራይ ቤት ይኖሩ እንደነበር የተናገሩት የሟች እናት፣ ልጃቸው በጊዳ አያና፣ አንዶዴ ዲቾ ነበረው ያሉት ወደ 600 ኩንታል የሚሆን የበቆሎ እህል ከነመጋዘኖቹ እንደተቃጠለበት አስታውሰዋል።
በተጨማሪም የልጃቸው እንዲሁም የቤተሰባቸው መኖሪያ ቤቶች በነሐሴው ጥቃት መቃጠላቸውን እና ከብቶችን ጨምሮ ንብረቶቻቸው መዘረፋቸውን ገልፀው፣ ከዛ ጥቃት ሸሽተን በምንገኝበት ነው "ልጄ የተገደለው" ብለዋል።
ልጃቸው በትጥቅ ትግል ውስጥ ከሚገኙ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያለው እንደሆነ የጠየቅናቸው የሟቹ እናት፣ "ጭራሽ ከሚዛንና ከማረሻ በቀር የሚያውቀው ነገር የለውም። የያዙት ከሸሸንበት ከቱሉ ገና ከመንገድ ላይ ነው" ሲሉ መልሰዋል።
ማክሰኞ ዕለት በቤተ ክርስቲያን እና በመስጊድ የቀብር ስፍራዎች በአንድ ቀን ተቀበሩ ያላቸውን 17 አስከሬኖች ጨምሮ እስከ ሐሙስ ድረስ "የ25 ሰዎች አስከሬን" መገኘቱን የቱሉ ገና ከተማ ነዋሪ የሆነ ሌላ አስተያየት ሰጭ ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ሸሽተን መጥተን ነው። እንዶዴ ነበርን። አሁን ሸሽተን ባለንበት ነው ግድያው የተፈፀመው" የሚለው ይህ እማኝ፣ የገዳ ኮማንዶ ታጣቂዎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ለመዋጋት "ሲሔዱ እና ሲመለሱ በመንገዳቸው ያገኙትን ሰውም እንስሳም ገድለው ነው የሚያልፉት" ሲል ሁኔታውን ያስረዳል።
ዛሬ ጥቅምት 23 ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ ሦስት የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ፣ በታጣቂዎች ተወስደው ጠፍተው የነበሩ ሰዎች አስከሬን በየዕለቱ እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰው በሁለቱ ቀናት ጥቃት ተገድለው የተገኙ ሲቪሎች ቁጥር እስከ አሁን 40 መድረሱን ገልፀዋል።
አንድ እማኝ "6 ሙስሊሞች በአንድ ቀን ቀብረናል። ባጠቃላይ 25 ሰዎች ነበሩ ተገድለዋል የተባለው። ኋላ ላይ ሳጣራ የተለያየ አካባቢ ከተገደሉት ጋር ወደ 40 ደርሷል" ብለዋል።
አሁንም የጠፉ ሰዎች በመኖራቸው የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተናግረዋል።
ጥቃቱ ከተፈፀመ ከቀናት በኋላ የተገኙ ሟቾች፣ አስከሬናቸው በአውሬ ተበልቶ የቀረ አካላቸው ተሰብስቦ መቀበራቸውን አብራርተዋል።
ከሟቾቹ መካከል አብዛኛው ወጣት ወንዶች እንደሆኑ እና የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሁለት ሰዎችም እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
ከሲቪሎች ግድያ በተጨማሪ በትንሹ 6 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ እንስሳትም መዘረፋቸውን እና መገደላቸውን አስተያየታቸውን ለቢቢሲ የሰጡ ተጎጂዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ገልፀዋል።
የክልሉ ታጣቂዎች ዒላማ "የአማራ ብሔር ተወላጆች" መሆናቸውን የተናገሩት እማኞቹ ይኸውም "ፋኖን ትደግፋላችሁ በሚል ጥርጣሬ" የሚፈፀም እንደሆነ ይገልፃሉ።
በቱሉ ገና ከተማ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እና የከተማ አስተዳደሩ፣ ጥቃቱን ለመከላከል "የተቻላቸውን ጥረት አድርገዋል" ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
ይህ ባይሆን ኖሮ ጉዳቱ ከዚህም የከፋ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ህይወትን "በከፍተኛ ስጋት ውስጥ" እየመሩ እንደሆነ አመልክተዋል።
ጥቃቱን በተመለከተ በስልክ መረጃ የጠየቅናቸው የቱሉ ገና ከተማ ከንቲባ ገበየሁ ደረጀ፣ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
ከክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ምላሽ ለማግኘት ስልክ የደወልንላቸው እና በጽሁፍ የጠየቅናቸው የኮሙኒኬሽን ኃላፊው ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጡም።
ይሁን እንጂ፣ የክልሉ መንግሥት ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ይፈፅማሉ በሚል ከዚህ ቀደም የሚቀርቡ ውንጀላዎችን ሲያስተባብል ቆይቷል።
"ገዳ ኮማንዶ" በሚል ስያሜ የተቋቋመ ታጣቂ ኃይል አለ መባሉንም የክልሉ መንግሥት አይቀበልም።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት የሰላምና ደኅንነት ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ጄኔራል ኃይሉ ጎንፋ በቅርቡ ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት፣ "ገዳ ኮማንዶ የሚባል አደረጃጀት የለንም" ያሉ ሲሆን፣ በተለያዩ የወለጋ አካባቢዎች የተሰማሩ የክልሉ ታጣቂዎችም ሰላማዊ ሰዎችን ከመጠበቅ ባለፈ ጥቃት እንደማይፈፅሙባቸው ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ኃይሎች፣ "የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነት የሚነሱ" ባሏቸው በፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ እርምጃ እየወሰዱ እንደሚገኙ ተናግረው ነበር።
በሌላ በኩል የክልሉ መንግሥት ታጣቂዎችን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም የሚከሱት የቱሉ ገና ነዋሪዎች፣ በዛሬው ዕለትም "የገዳ ኮማንዶ" ያሏቸው የክልሉ ታጣቂዎች ከተማዋን አቋርጠው ማለፋቸውን በማንሳት፣ ሕዝቡ በድጋሚ መረበሹን ተናግረዋል።
"ከባድ ነገር ነው የገጠመን። አሁን ቀኑም ሕይወትም ጨለማ ሆኖብን ነው ያለነው። ከዛሬ ነገ ይገድሉናል እያልን። ሰዉ የት መሔድ እንዳለበት እንኳን አያውቅም። ወዴት እንደምንሔድ ግራ ገብቶን እየተንከራተትን ነው ያለነው። ዛሬ ራሱ መጡ ተብሎ መከላከያ ነው አካባቢውን የተወሰነ ያረጋጋው። እነሱም አልፈው ወደ ጫካ ሔዱ ሲመለሱ ይጨርሱን ይሆን እያለ ሰው በጭንቀት ነው ያለው" ብለዋል አንድ አስተያየት ሰጭ።
የጥቃቱ ዒላማ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በአብዛኛው ወደ አማራ ክልል እና ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለመሸሽ እየሞከሩ እንደሚገኙም አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም መንግሥት ባወጣቸው መግለጫዎች በአካባቢው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንዲሁም የፋኖ ታጣቂዎችም ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ሲገልጽ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንዲሁም ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማትም ንጹኃን ዜጎች በታጣቂዎች መገደላቸውን እንደሁም መጎዳታቸውን ገልጸዋል። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ንጹኃን ላይ የሚደርሰውን ግድያ፣ ጉዳት እና መፈናቀል ማውገዛቸው አይዘነጋም።

































