'በሳቅ የተሸፈነ ድብርት' ምንድን ነው? እንዴትስ መለየት እንችላለን?

ደስተኛ ያልሆነች እና ፊቷን በሚስቅ ፊት ማስክ የከለለችን ሴት የሚያሳይ ምሥል
የምስሉ መግለጫ, 'በሳቅ የተሸፈነ ድብርት' የሚታወቅ ሕክምና ባይኖረውም ባለፉት አምስት ዓመታት ስለችግሩ ማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር 50 በመቶ ጨምሯል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ብዙ ጊዜ በድብርት የሚሰቃይ ሰውን ስናስብ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ከአልጋው ላይ መነሳት ያቃተው ወይም በር ዘግቶ የሚቀመጥ ሰው ነው።

ምን አልባትም ደግሞ አልቃሻ የሆኑ፣ ከጓደኞቻቸው የተነጠሉ ወይም ቀኑን ለማሳለፍ የታከታቸውን ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በሰዎች መሃል ሆነው ቀልድ የሚፈጥሩ፣ አብዝቶ ተጨዋች፣ ራሳቸውን በማኅበራዊ ሕይወት ወይም በሥራ የጠመዱ ሰዎች በድብርት እየተሰቃዩ ሊሆን እንደሚችል አናስብም።

ሆኖም 'በሳቅ በተሸፈነ ድብርት' የተጠቁ ሰዎች እነዚህን ሰዎች ነው የሚመስሉት።

አንዳንድ ጊዜም በዚህ ሁኔታችሁ የሚሸወዱት ጓደኞቻችሁ፣ ባልደረቦቻችሁ ወይም የትዳር አጋራችሁ ላይሆኑ ይችላሉ። እናንተም በዚሁ ተሸፍናችሁ ሕይወታችሁን እየገፋችሁ ሊሆን ይችላል።

'በሳቅ የተሸፈነ ድብርት' ምንድን ነው?

አንዲት ተማሪ የምክር አገልግሎት ከሚሰጥ ግለሰብ ፊት ለፊት ተቀምጣ ትታያለች። የምክር አገልግሎት ሰጪው ጀርባውን ለካሜራ ሰጥቶ የተቀመጠ ሲሆን ፊቱ አይታይም።
የምስሉ መግለጫ, የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው በዓለም 322 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የድብርት ተጠቂ ናቸው

'በሳቅ የተሸፈነ ድብርት' በይፋ የታወቀ ሕክምና የለውም። ሆኖም ችግሩን በተለመለከተ ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ባለፉት አምስት ዓመታት በ50 በመቶ ጨምሯል።

ከውጪ ደስተኛ መስሎ ከውስጥ በድብርት መሰቃየት በሳቅ የተሸፈነ ድብርት (ስማይሊንግ ዲፕረሽን) እንደሚባል በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ጤና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ኦሊቪያ ሪምስ ይናገራሉ።

በእርግጥ ሁላችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ደስታ የማጣት ስሜት ይሰማናል። እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ በዓለም 322 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ይህ የመዳከም ስሜት ወደ ድብርት ከፍ ብሏል።

ድብርት የሚከሰተው ዘለቂ የሆነ ደስታ እና ለነገሮች ፍላጎት ማጣት ያሉ ስሜቶች ለሳምንታት ወይም ለወራት ሲቆዩ እና ሥራችንን፣ ግንኙነታችንን ፣ እንቅልፋችንን እንዲሁም የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ሲያውኩ ነው።

ሆኖም ድብርት ሁልጊዜም እንደምናስበው ላይሆን ይችላል። ድብርት ካጋጠማቸው ወደ 40 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ያልተለመዱ ሁኔታዎች እንደሚገጥሟቸው ጥናቶች አመልክተዋል። ለምሳሌ ለወትሮው ከሚያደርጉት በተለየ ሊመገቡ ወይም ሊተኙ ይችላሉ፤ የሆነ ጥሩ ወይም ደስ የሚል ነገር ሲገጥማቸውም ስሜታቸው በጊዜያዊነት ሊነቃቃ ይችላል።

ከዚህም በተጨማሪ የድብርት ተጠቂ የሆነ ሰው የሚያልፉበትን ነገር ሊደብቁ ወይም ሊሸፍኑ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ማስረጃዎችም አሉ።

ሰዎች ድብርትን የሚደብቁት ለምንድን ነው?

በሳቅ የተሸፈነ ድብርት ተጠቂ የሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች ድብርት እንዳለባቸው ስለማያውቁ እየሸፈኑት እንደሆነም አያውቁም።

"የሚያሳዩዋቸው ምልክቶች በሥራ የመጠመዳቸው እና በውጥረት የተሞላው ሕይወታቸው ውጤት እንደሆነ ሊያስቡ ይችላሉ" ይላሉ ሪምስ።

ሌሎች ደግሞ እየታገሉ እንደሆነ ሊያውቁ፤ ነገር ግን ይህ እንዳይታይባቸው በሥራ ይጠመዳሉ። ይህ በተለይ ጥንቅቅ ባሉ ወይም ጎዶሎ ማየት በማይፈልጉ እና ግባቸውን ማሳካት በሚፈልጉ ሰዎች ዘንድ የተለመደ ነው።

"እነዚህ ሰዎች ከራሳቸው ብዙ ነገር ይጠብቃሉ፤ ሆኖም እየታገሉ እንዳለ ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ላያምኑ ይችላሉ" ይላሉ ተመራማሪዋ።

አንዳንድ ሰዎች ይህን የሚያደርጉት መገለልን ወይም በሌሎች ላይ ጫና ለመፍጠር ስለማይፈልጉ ነው።

ሌሎች ደግሞ እንዳይፈረጁ ወይም በሥራቸው እና በግንኙታቸው ውስጥ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመፍራት የሚሰማቸውን እንደሚደብቁ ጥናቶች ያሳያሉ። በባህል ወይም በቤተሰብ ከሚጠብቀው አንጻርም በግልጽ ለመናገር ይቸገራሉ።

ድብርትን መደበቅ የሚያስከትላቸው አደጋዎች

ባለሙያዎች እንደሚሉት ሁኔታን ደብቆ መቆየት አደገኛ ሊሆን ይችላል።

"ድብርት የሚነጥለን ሲሆን ብቸኛ እንደሆን እንዲሰማን ያደርጋል፤ ብዙ ጊዜ ከዚህ ስሜት ለመውጣት ከምናደርጋቸው ነገሮች አንዱ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት ነው" ይላሉ በዩኬ ኤክሰተር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ባርኒይ ደን። ይህ ማለት ሰዎች ማግኘት ያለባቸውን እርዳታም እያገኙ አይደለም ነው።

"እነዚህ የመጀመሪያ ምልክቶች ካልታከሙ ወደ የባሰ እና አስከፊ የሆነ ደረጃ ያድጋሉ፤ ይህም ራስን ወደ ማጥፋት አደጋን ሊጨምር እንደሚችል" ሪምስ ይናገራሉ።

ሰባት በቀላሉ የማይለዩ የድብርት ምልክቶች

ከላፕቶፑ ፊት ለፊት የተቀመጠ እና ጥቁር ፍሬም ያለው መነጽር ያደረገ ግለሰብ።
የምስሉ መግለጫ, ለትችት ወይም ተቀባይነት ለማጣት ከተለመደው በተለየ የበለጠ ስሱ መሆን የድብርት ምልክት ሊሆን ይችላል
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በስሜታችን ላይ የሚገጥሙን አንዳንድ ለውጦች በቀላሉ ላይለዩ ይችላሉ። እነዚህ በቀላሉ የማይታዩ የድብርት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።

1. በነገሮች መደሰት ማቆም

ብዙ ጊዜ ደስታ የሚሰጧችሁ ለምሳሌ ከጓደኛ ጋር መገናኘት፣ ጂምናዚየም መሄድ ወይም የምትወዱትን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማየት ሊሆን ይችላል። እነዚህ ለወትሮው ደስታ የሚሰጧችሁ ነገሮች ሥራ መስለው ከታዩዋችሁ ችግሩን ጠለቅ ብሎ መመርመር ያስፈልጋል።

2. እግር እና እጅ ከተለመደው በተለየ የመክበድ ስሜት

ይህ በሕክምናው ቋንቋ 'ሊድን ፓራሊይሲስ' ይባላል። እግር እና እጅ የመክበድ ስሜት እና ለማንቀሳቀስ መቸገር ነው። ለወትሮው በቀላሉ የምናከናውናቸው የእለት ተዕለት ተግባራትን ለማከናወን ጉልበት እንዲጠይቅ ያደርጋል። ይህ የተለየ የድብርት ምልክት ሊሆን ይችላል።

3. እቅዶችን በተደጋጋሚ መሰረዝ

አንዳንድ ጊዜ በሌሎች ዙሪያ ጥሩ መስለን ልንታይ እንችላለን፤ ግን ስሜታችን ሲለወጥ እቅዶቻችሁን ትሰርዛላችሁ። ስሜታችሁንም መደበቅ አትችሉም።

4. ብዙ ሰዓት ብትተኙም ድካም ይሰማችኋል

በጣም ሰልችቷችሁ የተለመደ እንቅስቃሴያችሁን ልታከናውኑ ትችላላችሁ። " ሁሉም ነገር አስቸጋሪ የሚሆነው በተወሰነ መልኩ ነው" የሚሉት ሪምስ፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች በመጨረሻ አስከፊ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። በመሆኑም ከተለመደው በተለየ ብዙ እንቅልፍ ሊፈልጉ ይችላሉ።

5. ለትችት ወይም ተቀባይነት ለማጣት ስሱ መሆን

እቅዳችሁን እንድትሰርዙ ከአለቃችሁ ወይም ከጓደኛችሁ የተወረወሩ አስተያየቶች ከተለመደው የበለጠ ሊያስከፏችሁ ይችላሉ። ኤዲኤችዲ ያለባቸው ሰዎችም ሊያጋጥማቸው የሚችለው ለትችት የበለጠ ስሱ እየሆኑ መምጣት የተለየ የድብርት ዓይነት ነው።

6. ሁልጊዜ ሳቂታ እና የሌሎች ረዳት መሆን

በድብርት የሚሰቃዩ ሰዎች ሁልጊዜ ራሳቸውን ማግለል አይፈልጉም። ብዙ ጊዜ ተቃራኒውን ሊያደርጉ ይችላሉ። ለምሳሌ ራሳቸውን በሥራ መጥመድ፣ ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት ከመስመራቸው መውጣት ይታይባቸዋል።

7. ከውስጣችሁ የሚወጣው ድምጽ ያለማቋረጥ አሉታዊ መሆን

በራሳችሁ የምትተማመኑ ልትመስሉ ትችላላችሁ በውስጣችሁ ግን በራሳችሁ ላይ ትችት የምትሰነዝሩ ትሆናላችሁ። በራስ መጠራጠር፣ ዋጋ የማጣት ስሜት ፣ ባዶነት መሰማት አሳሳቢ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

ከዚህ ለመውጣት ምን ሊረዳን ይችላል?

'በሳቅ የተሸፈነ ድብርት' ወይም በእንግሊዝኛ አጠራሩ "ስማይሊንግ ዲፕረሽን' የሚለውን ቃል መጠቀም የሚያከራክር ጉዳይ ነው።

ሆኖም ሰዎች እንዲረዱት እና እያለፉበት ላለው ነገር ስም እንዲሰጡ ሊረዳቸው ወይም ውስብስብ የሆነን እና እያለፉበት ያለውን ነገር ለማወቅ ሊያቃልል እንደሚችል ሬምስ ይናገራሉ።

ሳቅ የሚለው ቃል ከደስተኛነት እና ከተጨዋችነት ጋር በተያያዘ እንድታስቡት ሊያደርጋችሁ ይችላል፤ ሆኖም ከዚህ ጀርባ ያለው ነገር ተስፋ ማጣት ፣ ባዶነት እና ዋጋ አልባነት ሊሆን ይችላል።

ከዚህ ለመውጣት ለምታምኑት ሰው የሚሰማችሁን ስሜት በትንሹም ቢሆን በማጋራት መጀመር መልካም እንደሆነ የሥነ ልቦና ፕሮፌሰሩ ደን ይመክራሉ።

" ይህ ብዙ ጊዜ ግለሰቦች ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያጠናክርላቸው ፣ ያለመነጠል ስሜት እንዲሰማቸው እንዲሁም በዚህ ስሜት ብቻቸውን እንዳልሆኑ እንዲረዱ ያደርጋል" ይላሉ።

በዚህ ድብርት ውስጥ እየታገላችሁ ካላችሁም ሐኪም እንድታዩም ደን ይመክራሉ።

" ማውራት ፣ ድብርት የሚያቀሉ መድሃኒቶች እና ማኅበራዊ ሕክምናዎች ውጤታማ እንደሆኑ የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ" ብለዋል ደን።