አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ ወሳኝ የተባለ የኒውክሌር ስምምነት ተፈራረሙ

የሳዑዲው መሪ እና ፕሬዚዳንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በስምምነቱ መሠረት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሳዑዲ አቻቸው መሀመድ ቢን ሳልማን ለእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ እውቅና እንዲሰጡ እንልጠየቁ ተዘግቧል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ሳዑዲ አረቢያ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል የኒውክሌር ፕሮግራም መጀመር የሚያስችላትን ስምምነት ከአሜሪካ ጋር ተፈራረመች።

ስምምነቱ "ሰላማዊ የኒውክሌር ትብብር ስምምነት" ተብሎ የተገለጸ ሲሆን "ለአሜሪካ ኩባንያዎች በሳዑዲ የኒውክሌር ኃይል ፕሮግራም ውስጥ ትልቅ ዕድልን ይሰጣል" ሲል የአሜሪካ የኢነርጂ መስሪያ ቤት አስታውቋል።

የስምመነቱ ዝርዝር ነጥቦች ለሕዝብ ይፋ ባይደረግም የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ግን ሳዑዲ አረቢያ ወደፊት ዩራኒየምን እንድታበለጽግ ሊፈቅድላት እንደሚችል ዘግበዋል። ይህም ለኃይል ማመንጫዎች ብቻ ሳይሆን የኒውክሌር ቦምቦችንም ለማምረት ሊያገለግል ይችላል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ ቀድሞውንም ባልተረጋጋ ቀጣና ውስጥ የኒውክሌር መስፋፋት አደጋ ሊያስከትል የሚችል ነው።

የአሜሪካ የኢነርጂ ሚኒስቴር ከትብብር ስምምነቱ ጋር "የሁለትዮሽ ጥበቃ ስምምነት" መፈረሙን አስታውቋል።

"እነዚህ ሁለት ስምምነቶች በአንድ ላይ ለአስርተ ዓመታት የሚቆይ፣ በርካታ ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ አጋርነት፣ የኒውክሌር መስፋፋትን ጨምሮ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ስትራቴጂካዊ ዓላማዎችን የሚያራምድ ሕጋዊ መሠረት ይጥላሉ" ሲል በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

የሳዑዲ መንግሥትም ስምምነቱ "ሁለቱ አገራት በኢነርጂ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማደጉን የሚያመለክት" መሆኑን በመግለጽ መግለጫ አውጥቷል።

ሁለቱ አገራት ከስምመነት ላይ የደረሱት የሳዑዲው መሪ ባለፈው ኅዳር ወር ዋሽንግተንን ከጎበኙ በኋላ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ስምምነት የተፈረመው በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው ጦርነት እየተባባሰ በመጣበት ወቅት ነው። ለረዥም ጊዜ የአሜሪካ አጋር የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ በኢራን ጥቃቶች ዒላማ የተደረጉ በርካታ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ታስተናግዳለች።

በየመን የኢራን አጋር የሆኑት ሁቲዎች ሰኞ ዕለት በሳዑዲ ላይ "የባሕር ላይ እገዳ" ጥለዋል።

የኒውክሌር ስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች ባይገለጹም ቀደም ሲል ሳዑዲ ከአሜሪካ ጋር የጋራ ጥናት ካደረገች በኋላ ከውጭ በሚመጣ ነዳጅ ላይ ከመመካት ይልቅ በግዛቷ ዩራኒየምን ለማበልጸግ ሊፈቀድላት እንደሚችል መገናኛ ብዙኃን ዘግበው ነበር።

ይህ ለአሜሪካ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሊያስገኝላት ይችላል። ኩባንያዎቿ ለኃይል ማመንጫዎች እንዲሁም የኒውክሌር ቦምቦችንም ለማምረት የሚያስችል የበለፀገ ዩራኒየም ለማምረት የሚያስችል ተቋም በመገንባት ላይ ሊሳተፉ እንደሚችሉም ተዘግቧል።

የአሜሪካ የኢነርጂ ሚኒስትር ክሪስ ራይት በሰጡት መግለጫ ላይ "እርግጠኛ ነኝ፣ እነዚህ ስምምነቶች ከፍተኛውን የኒውክሌር ደህንነት ደረጃዎችን እና የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች መስፋፋት ቁጥጥርን ያከብራሉ፣ ነገር ግን እዚህ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተሰሩት እና በዓለም ላይ ላሉት ምርጥ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ እና ሳይንቲስቶችንም ይጠቀማሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

የኢነርጂ መሥሪያ ቤቱ እንዳስታወቀው ስምምነቱ "የአሜሪካን እና የቀጣናውን ደህንነት" የሚያሻሽል ሲሆን "ከፍተኛ የኒውክሌር ደህንነት፣ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መስፋፋትን የሚመለከቱ ደረጃዎችን የሚያከብር እና የዩናይትድ ስቴትስን በሲቪል የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነት የሚያጠናክር" ይሆናል ብሏል።

የኒውክሌር ባለሙያዎች እና የእስራኤል የቀድሞ ባለሥልጣናት ዕቅዱ በመጨረሻ ሳዑዲ አረቢያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንድታመርት ሊያደርጋት እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ብዙ ባለሙያዎች ደግሞ ይህንን ለማድረግ አስርት ዓመታትን የሚወስድ እና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተቃውሞ ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል።

በአሜሪካ የሚገኘው የመከላከያ የምርምር ተቋም የመካከለኛው ምስራቅ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሮዝሜሪ ኬላኒክ፣ ሳዑዲ አረቢያ ዩራኒየምን ለማበልጸግ የሚያስችሉ ተቋማት እንዲኖሯት ዩናይትድ ስቴትስን መፍቀድን የሚያካትት ስምምነት ካለ "በጣም አስደንጋጭ" እንደሚሆን ተናግረዋል።

"አሜሪካ ከዚህ በፊት እንዲህ አድርጋ አታውቅም፤ ሌላ አገር በራሱ ግዛት ውስጥ ዩራኒየም እንዲያበለጽግ ድጋፍ አድርጋ አታውቅም" ሲሉ ገልፀዋል።

ለዚህም ምክንያቱ "የራስህን የኒውክሌር ነዳጅ ማምረት ከቻልክ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ለመገንባት የበለጠ አደጋ ትሆናለህ" ሲሉ አብራርተዋል።

ስምምነቱ ወደ አሜሪካ ኮንግረስ ተልኳል።

ትራምፕ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር በርካታ እርምጃዎችን ወስደዋል።

አሜሪካ ከዚህ ስምምነት ጋር ተያይዞ ሊመጡ ከሚችሉት ስትራቴጂካዊ እና የንግድ ትርፎች በተጨማሪ አሁን ስምምነቱን ለመፈረም የወሰነችው ሩሲያ እና ቻይና በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ እየተወያዩ መሆናቸው በመሰማቱ ሊሆን ይችላል።

ስምምነቱ ለሳውዲ አረቢያ ትልቅ ድልን የሚያመላክት ሲሆን በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የኃይል ተለዋዋጭነት በረዥም ዓመት ቢሆንም እንደገና የመቀየር አቅም አለው።

አሜሪካ እና እስራኤል ከቴህራን ጋር በገቡት ጦርነት ውስጥ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ጉዳይ የንግግራቸው ማዕከል ሆኖ ቆይቷል።

ሁለቱ አገራት በየካቲት ወር ኢራንን ያጠቁበት አንዱ ምክንያት አገሪቱ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳታመርት ለመከላከል እንደሆነ ይናገራሉ፤ ቴህራን በበኩሏ የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ የሚለው መሆኑን ስትናገር ቆይታለች።

የሳውዲ አረቢያው ገዥ ልዑል አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን እአአ በ2018 ለሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት አገራቸው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የመታጠቅ ዕቅድ ባይኖራትም "ያለምንም ጥርጥር ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ካመረተች በተቻለ ፍጥነት እርምጃ እንወስዳለን" ብለዋል።