ሰላምን ለማስጠበቅ የሚሳሳሙት እና የሚተቃቀፉት ዝንጀሮዎች

ሁለት ዝንጀሮዎች ተቃቅፈው

የፎቶው ባለመብት, Jake Brooker / Chimfunshi Wildlife Orphanage Trust

የምስሉ መግለጫ, በዝንጀሮ መጠለያ ጄክ እና ጆዊ የተባሉ ታዳጊ ዝንጀሮዎች ተቃቅፈው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የጭንቀት ሁነቶች ከመምጣታቸው በፊት መተቃቀፍ፣ መነካካት እና መሳሳም አመኔታን ለመገንባት ጥንታዊ መንገድ ሳይሆን እንደማይቀር ተመራማሪዎች ተናገሩ።

ተመራማሪዎች የሰው ልጆች የቅርብ ዝርያ ናቸው የሚባሉ የዝንጀሮዎችን ባህሪ አጥንተው ነው እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሱት።

ሁለት የዝንጀሮ ዓይነቶች ላይ ጥናት ያደረጉት የዱረም ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ዝንጀሮዎች በምግብ ግጭት ከመነሳቱ በፊት አካላዊ ንክኪ በማድረግ እርስ በርሳቸው መተማመኛ ይሰጣጣሉ ብለዋል።

በጥናቱ ከተገኙ ግኝቶች መካከል አስገራሚው ምንም እንኳን ዝንጀሮዎች በጠበኛነት ታዋቂ ቢሆኑም ጣታቸውን ሌላኛው አፍ ላይ ማድረግን ጨምሮ የቅርብ አካላዊ ንክኪ ያደርጋሉ።

ፕሮፌሰር ዛና ክሌይ "ከአስጨናቂ ሁነት በፊት አንድ ላይ መጥተው እርስ በርሳቸው መተማመኛ ይሰጣጣሉ፤ ይነካካሉ፤ እርስ በርሳቸው ይተቃቀፋሉ" ብለዋል።

ይህን ባህሪያቸውንም ከትልቅ የእግር ኳስ ጨዋት በፊት ከመተቃቀፍ ጋር አመሳስለውታል።

"ከ 'እኔ' ይልቅ 'እኛ' ዓይነት ነው" ብለዋል።

ባለሙያዎቹ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ዛምቢያ የሚኖሩ ሁለት ትላልቅ የዝንጀሮ ዝርያዎችን አጥንተዋል።

ሁለት ዝንጀሮዎች ተቃቅፈው

የፎቶው ባለመብት, Zanna Clay / Lola ya Bonobo Sanctuary

የለውዝ ፍሬዎችን በመጠቀም ተፈጥሯዊ አመጋገብን አመሳስለው ሙከራዎችን ነድፈዋል።

ዝንጀሮዎች ምግብ ከመቅቡ በፊት ለአምስት ደቂቃ ያህል ባህሪያቸው ምን እንደሚመስል ምልከታ ተደርጎባቸዋል።

ተመራማሪዎች መነካካት፣ መተቃቀፍን እና መሳሳምን ጨምሮ አካለዊ ንክኪ ማድረጋቸውን መዝግበዋል።

እርስ በርስ የተነካኩ እና የተቃቀፉ ዝንጀሮዎች የተሻለ ምግብ ማግኘታቸውን እና በሰላም አብረው መመገባቸውን የጥናት ቡድኑ ግኝት ያሳያል።

መቻቻልን የሚያሳዩ ቡድኖች ተራን መቀበልን ጨምሮ ከፍተኛ የመተማመን ንክኪዎችን ያሳዩ ናቸው።

ዶ/ር ጄክ ብሩከር የሰው ልጅ የቅርብ ዝርያ ናቸው ተብለው የሚታመኑት የዝንጀሮዎች ባህሪ "እነርሱ እና እኛ ውጥረትን፣ ውድድርን እና ትብብርን እንዴት እንደምናስተናግድ" አስደናቂ ዕይታ ይሰጣል ብለዋል።

መነካካት ጥንታዊ የተግባቦት መንገድ እና ምንአልባትም ከቋንቋ በፊት የነበረ መግባቢያ እንደሆነ ተናግረዋል።

ተመራማሪዎች አመኔታን ለመገንባት እና ለትብብር መነካካት ቢያንስ ከሰባት ሚሊዮን ዓመት በፊት የነበረ ነው ብለዋል።

ስለዚህም ሰዎች ከአስጨናቂ ሁነት በፊት ለእግር ኳስ ሲነካኩ፣ ከቡድናቸው ጋር ሲተቃቀፉ ወይም ትከሻቸውን ችብ ቸብ ሲደራደጉ ሚሊዮን ዓመታቶችን የተሻገረ የማኅበራዊ መንገድ እየተጠቀሙ ይሆናል።