
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት ኮፕ31 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የተገኙ የዓለም አገራት በነዳጅ እና በፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶቸቻውን ማጥበብ ባለመቻላቸው፣ አየር ንብረት ለውጥን መከላከል የሚያስችል አዲስ ትልቅ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቀሩ።
በቱርክ የተካሄደው ድርድር አርብ ዕለት እንዲጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፣ የጋራ መግባባት ለማግኘት ሲባል እስከ እሁድ ምሽት ድረስ ቀጥሏል።
በዚህ የተነሳም ጉባኤው ረጅም ጊዜ የወሰደው የተመድ የአየር ንብረት ኮንፈረንስ ሆኗል።
ይሁን እንጂ በድርድሩ መጨረሻ በቀረበው ረቂቅ ሰነድ ላይ የቅሪተ አካል ነዳጅ (ፎሲል ፊውል) በቀጥታ አለመጠቀሱ የአውሮፓ ኅብረት፣ የፓስፊክ ደሴት አገራት እና
ሌሎችንም አስቆጥቷል።
እንደ ነዳጅ፣ ከሰል እና የተፈጥሮ ጋዝ ያሉ የኃይል አማራጮች የወል መጠሪያ የሆው 'ፎሲል ፊዩል'፣ የዓለም ሙቀት መጨመር ዋነኛ መንስኤ ነው።
በርካታ ደሃ አገራት በበኩላቸው፣ እየጨመረ ከመጣው
የዓለም ሙቀት ተፅዕኖ ጋር ራሳቸውን ማላመድ የሚያስችላቸውን ገንዘብ ከበለጸጉ አገራት ስለሚያገኙበት መንገድ በግልፅ ቃል ባለመገባቱ
ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
በዓመታዊው የኮፕ ጉባኤ ይህ ዓይነቱ የዋነኛ ፖለቲካዊ
ስምምነት አለመሳካት ለመጨረሻ ጊዜ የታየው በአውሮፓውያኑ 2009 ኮፐንሃገን ላይ ነበር።
ከሥልጣን ከመውረዳቸው በፊት ለመጨረሻ ጊዜ በተሳተፉበት
በዚህ የኮፕ ጉባኤ ላይ የተገኙት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ስምምነት ላይ ባለመደረሱ “እጅግ ማዘናቸውን” ገልጸዋል።
ጉቴሬዝ “ኃያል የፎሲል ፊውል የጥቅም ፍላጎት”
አላቸው ያሏቸውን አካላት ተችተዋል።
“በሁሉም ስፍራ የሚገኙ ሕዝቦች ዋጋ በሚከፍሉበት
በዚህ ወቅት፣ የግዙፍ የትንባሆ ኩባንያዎችን ስልት በመኮረጅ ሳይንሱን በማዛባት፣ ፖሊሲዎችን በማዘግየት፣ እርምጃዎችን በማገድ ትልቅ
ትርፍ እያካበቱ ነው” ብለዋል።
ከቱርክ ጋር በመሆን ጉባኤውን ያዘጋጀችው አውስትራሊያ
ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ በበኩቸላው፣ ኮንፈረንሱ ያለ ስምምነት ለመበተኑ ተጠያቂ ያደረጉት “አስቸጋሪ ጂኦፖለቲካዊ ጊዜ”
መኖሩን ነው።
ላይ ታች ሲሉ የከረሙት የተሳታፊ አገራት ልዑካን
ከሁለት ሳምንታት ድርድር በኋላ፣ አለመግባባቱን ለመፍታት ያስችላል የተባለ አዲስ ረቂቅ ስምምነት እሁድ ጠዋት ቀርቦላቸው ነበር።
ነገር ግን በዚህ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ውስጥ
‘ፎሲል ፊውል’ የሚለው ቃል አንድም ቦታ አልተጠቀሰም።
የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝን
በተመለከተ የተጠቀሰው ብቸኛው ቀጥተኛ ያልሆነ አገላለጽ፣ በአውሮፓውያኑ 2023 በተካሄደው ኮፕ28 ስብሰባ ወቅት አገራት ከፎሲል ፊውል ተጠቃሚነት “ለመሸጋገር” ስምምነት መፈጸማቸውን የሚያስታውስ አንቀጽ ነው።
የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ የሆኑት አየርላንዳዊው
ሚኒስትር ዳራግ ኦብራየን፣ ኅብረቱ ይህንን አካሄድ “በጽኑ” እንደሚቃወም አሳውቀዋል።
“የተላለፉት ውሳኔዎች የአየር ንብረት ለውጥን
ለመከላከል ከሚያስፈልገው የቁርጠኝነት ደረጃ ጭራሽ የሚቀራረቡ አይደሉም” ሲሉ ተናግረዋል።
ባለፈው ሰኞ ዕለት በቀረበው የመጀመሪያው ረቂቅ
ላይ ‘ፎሲል ፊውል’ ወይም ‘ፎሲል ፊውልስ’ የሚለውን ቃል ስድስት ጊዜ ተጠቅሶ የነበረ ሲሆን፣ ነዳጅ አምራች አገራት ግን ተቃውመውታል።
የሳዑዲ አረቢያ ልዑክ መሐመድ አዩብ የአረብ
አገራት “በቅን ልቦና መሳተፋቸውን እንደቀጠሉ” አንስተው፣ ነገር ግን አረብ አገራቱ በታሪክ ውስጥ የነበራቸው የበካይ ጋዝ ልቀት
ድርሻ አነስተኛ መሆኑን በመጥቀስ ተከራክረዋል።
ሩሲያ በበኩሏ ሀገራት እንደ የድንጋይ ከሰል፣
ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ካሉ የኃይል አማራጮች ተጠቃሚነት በፍጥነት የሚወጡ “የነዳጅ ድኅነት” ይከሰታል ስትል ሞግታለች።