ቀጥታ , ጥቃት በሩሲያ የጦር መርከብ ላይ፡ ወደ ሰሜን አፍሪካ የደረሰው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት

በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚደረገው ጦርነት ከግዛታቸው አልፎ እስከ ሰሜን አፍሪካ ደርሶ ዩክሬን የሩሲያን የጦር መርከብ በሊቢያ የባሕር ዳርቻ ላይ መትታ ማስመጧን አስታውቃለች። ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ እንደተናገሩት በዩክሬን ድሮን በተፈጸመ ጥቃት እሁድ ዕለት በሊቢያ ወደብ ቆማ የነበረች የሩሲያ የጦር መርከብ ሰምጣለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዩኬ፤ ኤአይ የጡት ካንሰርን አስቀድሞ ለመለየት ይረዳ እንደሆነ ለማረጋገጥ ሰፊ ሙከራ ማካሄድ ጀመረች

    ፕሮፌሰር ፊዮና ጊልበርት
    የምስሉ መግለጫ, ፕሮፌሰር ፊዮና ጊልበርት ኤአይ የጡት ካንንሰር ሕክምናን ያሻሽል እንደሆነ የሚካሄደውን ሙከራ ከሚመሩት ተመራማሪዎች አንዷ ናቸው

    የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) ሠው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የጡት ካንሰርን አስቀድሞ ለመለየት ይረዳ እንደሆነ ለማወቅ በዓለም ሰፊ የተባለውን ሙከራ ማካሄድ ጀመረ።

    ለዚህም በመላ አገሪቱ የሚገኙ ወደ 700 ሺህ የሚጠጉ ሴቶች በሙከራው እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል።

    በሙከራው ኤአይ የጡት ካንሰርን ቀድሞ ለመለየት ይረዳ እንደሆነ እና የሕክምና ባለሙያዎችን ጫና ያቃልል እንደሆነ ለማየት የጡት ካንሰር ምርመራ (ማሞግራም) ውጤቶችን ለማየት ኤአይ ጥቅም ላይ ይውላል።

    ተሳታፊዎችን የመመልመል ሒደቱ በዩኬ ከተመረጡ 30 ጣቢያዎች አንዱ በሆነው በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ተጀምሯል።

    በሙከራው ዕድሜያቸው ከ50 እስከ 71 የሚሆን ሴቶች በየሦስት ዓመቱ መደበኛ የጡት ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ የተጋበዙ ሲሆን፣ በዓመት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይታመናል።

    አሁን ላይ ሁለት የብሔራዊ ጤና እንክብካቤ ባለሙያዎች እያንዳንዱን ማሞግራም በመባል የሚታወቀውን የጡት ካንሰር ምርመራ ወይም ራጅ የሚያዩ ሲሆን፣ በሙከራው አንደኛው ባለሙያ በኤአይ እንዲተካ ይደረጋል።

    ከዚህ ቀደም የተሠሩ በርካታ ትናንሽ ጥናቶች ኤአይ የጡት ካንሰርን ለመለየት እንደሚረዳ ቢያመለክቱም፤ ይህንን ሙከራ የሚያካሂዱት ተመራማሪዎች ጉዳት እንዳያስከትል እርግጠኛ መሆን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

    የጡት ካንሰር በዩኬ የተለመደ የካንሰር ሕመም ሲሆን በየዓመቱ ወደ 59 ሺህ ሴቶች ሕክምና ያደርጋሉ።

    ተያያዥ ዘገባዎች፡

  2. የዛምቢያው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ “መንግሥትን በመገልበጥ” ሙከራ ተከሰሱ

    የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ብሪያን ሙንዱባይል

    ዛምቢያዊው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ብራያን ሙንዱቢሌ ከ12 በላይ ባልደረቦቻቸው ጋር “መንግሥትን በመገልበጥ ሙከራ” ክስ ቀረበባቸው።

    የክስ መዝገቡን የተመለከተው ሮይተርስ እንደዘገበው ግለሰቦቹ የአገር ክህደት ወንጀል በመፈፀም በከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ተመሥርቶባቸዋል።

    ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ለተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩ የነበሩት ሙንዱቢሌ እና የቀድሞው የፓርላማ አባል ማኬቢ ዙሉ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጭበርብሯል ያሉት ምርጫ ከተካደሄ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር።

    በምርጫው ፕሬዝደንት ሃካይንዴ ሂቺሌማ በድጋሚ ያሸነፉ ሲሆን፣ ምርጫው ተጭበርብሯል መባሉን ውድቅ አድርገዋል።

    ሙንዱቢሌ፣ ዙሉ እና 12ቱ ግለሰቦችም ከሚያዝያ እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት ውስጥ መንግሥትን ለመገልበጥ ሴራ ሲጠነስሱ እንደነበር የክስ መዝገባቸው ያስረዳል።

    መዝገቡ ሙንዱቢሌ እና አንድ ነጋዴ መንግሥትን ለመጣል በሚደረገው ሙከራ አምስት ሰዎች ወደ ሩሲያ ሄደው ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ በገንዘብ ደግፈዋል ሲልም ጠቅሷል።

    የተከሳሾች ጠበቃ ሳክዊባ ሲኮታ በበኩላቸው ክሱን “ምንም ትርጉም የማይሰጥ” ብለውታል።

    ሙንዱቢሌም ቀደም ብሎ ጥፋተኛ እንዳልሆኑ እና ክሶቹ ፖለቲካዊ እንደሆኑ ገልጸዋል።

    በዛምቢያ ነሐሴ ላይ የተካሄደው ምርጫ ውዝግቦችን ያስከተለ ሲሆን፣ ተንታኞች እና ታዛቢዎች ከባድ የአጀራር ግድፈቶች የታዩበት እና በማዕድን የበለፀገችውን አፍሪካዊት አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውቅና ያጎደፈ ብለውታል።

    ተያያዥ ዘገባዎች፡

  3. የእስራኤል ጥቃቶች ጋዛን ወደ “መርዛማ ምድረ በዳነት ለውጧታል” - ኦክስፋም

    በጋዛ ፍርስራሽ ላይ የቆመ ታዳጊ

    እስራኤል የፈፀመቻቸው ጥቃቶች ጋዛን ወደ “መርዛማ ምድረ በዳነት እንደለወጧት” እና ከ99 በመቶ በላይ የሚሆነው የፍልስጤማውያን ግዛት እንደተበከለ የኦክስፋም ሪፖርት አመለከተ።

    ግብረ ሰናይ ድርጅቱ እንዳለው በጋዛ የተከማቹት ከባባድ ብረቶች፣ የፈንጂ ቅሪቶች፣ የሕንፃ ፍርስራሾች፣ መርዛማ ኬሚካሎች እንዲሁም ሥነ ሕይወታዊ የአየር፣ የውሃ እና የአፈር ብክለቶች አሁን እና በመጪዎቹ አስርት ዓመታት ለፍልስጤማውያን ስጋት ናቸው።

    የኦክስፋም ኢንተርናሽናል ዋና ዳይሬክተር አሚትባህ ብሃር፣ “አባቢያዊ የጦር ወንጀልን” በጋዛ እየተካሄደ ያለው “የዘር ማጥፋት” አካል በማድረግ የእስራኤልን መንግሥት ከስሰዋል።

    “የደረሰው ውድመት እና ብክለት ለሰዎች ደኅንነት እና ኅልውና ወሳኝ የሆነውን አካባቢያዊ ሁኔታ በመሠረታዊነት አበላሽቶታል” ብለዋል።

    የእስራኤል መንግሥት በሪፖርቱ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠየቅም ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም።

    ሆኖም በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እየታየ ባለው መዝገብ የቀረበበትን የዘር ማጥፋት ወንጀል “መሠረተ ቢስ እና የተዛባ” ሲል ውድቅ አድርጎታል።

    ኦክስፋም እና ተቀማጭነቱን በዩኬ ያደረገው ‘ኮንፍሊክት ኤንድ ኢንቫይሮንመንታል ኦቭዘርቫቶሪ’ ለሦስት ዓመት የዘለቀው የጋዛ ጦርነት ያደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ድምዳሜ ላይ የደረሰው የሳተላይት ምሥሎችን፣ የርቀት ዳሰሳን፣ የቦታ ትንተናዎችን እና ሌሎች ምንጮችን በመጠቀም ነው።

    ሪፖርቱ በእስራኤል ከባድ ጥቃቶች ጥቅም ላይ የዋሉ ጥይቶች እንዲሁም የሕንፃ እና የመሠረተ ልማት ፍርስራሾች በአካባቢ ላይ ያሳደሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ በዝርዝር አሳይቷል።

    የካቲት ወር ላይም የተባበሩት መንግሥታት ልዮ ሪፖርት በሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ ከ200 ሺህ ቶን በላይ ፈንጅዎች በጋዛ ላይ እንደዘነቡ አመልክቷል።

    ይህም በጃፓኗ ሄሮሽማ ላይ ከተጣሉት 13 የኒውክሌር ዓይነት ቦምቦች አጠቃላይ ኃይል ጋር የሚስተካከል ነው ብሏል።

    ባለፈው ዓመትም የተመድ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም በእስራኤል ጦር ዘመቻ የፈራረሱ ቤቶች እና መሠረተ ልማቶች ከ61 ሚሊዮን ቶን በላይ ፍርስራሽ መፍጠራቸውን አስታውቆ ነበር። ከዚህ ውስጥ 15 በመቶ የሚሆነው በካይ እና አደገኛ ቁሶችን የያዘ ነው ብሏል።

    • ተያያዥ ዘገባዎች፡
  4. በሰሜን አፍሪካ ወደ ሊቢያ የባሕር ዳርቻ የደረሰው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት

    በሊቢያ የባሕር ዳርቻ የተመታውን የሩሲያ መርከብ የሚያሳዩ ምሥሎች
    የምስሉ መግለጫ, በሊቢያ የባሕር ዳርቻ የተመታውን የሩሲያ መርከብ የሚያሳዩ ምሥሎች

    በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚደረገው ጦርነት ከግዛታቸው አልፎ እስከ ሰሜን አፍሪካ ደርሶ ዩክሬን የሩሲያን የጦር መርከብ በሊቢያ የባሕር ዳርቻ ላይ መትታ ማስመጧን አስታውቃለች።

    ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ እንደተናገሩት በዩክሬን ድሮን በተፈጸመ ጥቃት እሁድ ዕለት በሊቢያ ወደብ ቆማ የነበረች የሩሲያ የጦር መርከብ ሰምጣለች።

    ምሥራቃዊ ሊቢያን የሚቆጣጠረው መንግሥት እንዳለው፣ መርከቧ ወደ ሩሲያ ከመመለሷ በፊት ነዳጅ እና አቅርቦት ለመሙላት በቤንጋዚ የባሕር ኃይል ጣቢያ በመቆመችበት ማለዳ ነበር ፍንዳታ የተከሰተው።

    ዜሌንስኪ ጨምረው እንደተናገሩት ዒላማ የሆነው ሩሲያ የጦር መሣሪያ ለማጓጓዝ የምትጠቀምበት የጭነት መርከብ እንደሆነ አመልክተዋል።

    ከጥቃቱ በኋላ የሩሲያ መንግሥት ክስተቱ “በቀጣናው የተባበሰ ውጥረት” እንደሚፈጥር አስጠንቅቋል፣ ሆኖም በሊቢያ የባሕር ዳርቻ ስለተፈጸሙት ጥቃቶች በቀጥታ አስተያየት አልሰጠም።

    ሩሲያ እና ዩክሬን አንዳቸው በሌላኛቸው ግዛት ውስጥ የሚፈጽሙት ጥቃት እየተጠናከረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ዩክሬን የሩሲያ ንብረቶችን በሌሎች የዓለም ክፍሎች ላይ እየተከታተለች እያጠቃች ነው።

    ባለፉት ሁለት ቀናት ቅዳሜ እና እሁድ አንዲት የሩሲያ የጭነት መርከብ በምሥራቃዊው የፊንላንድ እንዲሁም በሰሜን አፍሪካ ሊቢያውስጥ ደግሞ የሩሲያ ባሕር ኃይል መርከብ በዩክሬን ዒላማ መደረጋቸው እየተነገረ ነው።

    የፊንላንድ መከላከያ ኃይሎች ከጥቃቱ ጀርባ ዩክሬን ልትኖር እንደምትችል ገልጸዋል። ኪየቭ ግን እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠችም።

    የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ “በባልቲክ ክልል የሽብር እንቅስቃሴ መስፋፋት” “አደገኛ አዝማሚያ” ሲሆን “በእርግጥ በክልሉ ውስጥ ውጥረት እንዲባባስ እያደረገ ነው” ብለዋል።

    በሊቢያ ስለተፈጸሙት ጥቃቶች ሲጠየቁ፣ ፔስኮቭ መረጃው በሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር እንደሚነገር ገልጸው፣ “ስለ ጉዳዩ ዜሌንስኪ የተናገረውን ተከታትለናል” ብለዋል።

    ፔስኮቭ በሊቢያ በሩሲያ መርከቦች ላይ ስለተፈጸሙት ጥቃቶች በቀጥታ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው፣ ዝርዝሩ በመከላከያ ሚኒስቴሩ እንደሚቀርብ ገልጸዋል።

  5. በቤልጂየም ከብሔራዊ የበጀት ቅነሳ ጋር በተያያዘ አድማ በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎች ተሰረዙ

    የብራስልስ አውሮፕላን ማረፊያ

    የቤልጂየም መንግሥት ለሕዝብ አገልግሎቶች የሚመድበውን በጀት ለመቀነስ የያዘውን እቅድ በመቃወም ሠራተኞች በመቱት አድማ በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎች ተሰረዙ።

    በዚህም በመዲናዋ ብራስልስ በሚገኘው ዛቭንትም እንዲሁም እንደ ራይንኤር ያሉ ርካሽ አየር መንገዶች በሚገለገሉበት ቻርልሪይስ አየር ማረፊያዎች ሁሉም በረራዎች ቆመዋል።

    ከዚህም በተጨማሪ የባቡር አገልግሎቶች የተቋረጡ ሲሆን የሕዝብ ትራንስፖርት ፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች የሕዝብ አገልግሎቶች መስተጓጎል አጋጥሟቸዋል።

    ተቃውሞው የተቀሰቀሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ባርት ደ ዌቨር፣ ብሔራዊ የበጀት ጉድለትን ለመሙላት መንግሥት ጤናን ጨምሮ ለሕዝብ አገልግሎቶች የሚመድበውን በጀት ለመቀነስ የያዘውን እቅድ ተከትሎ ነው።

    ተቃዋሚዎቹ እቅዱ የኑሮ ውድነትን እንደሚያስከትል እና ማኅበራዊ ጥቅማ ጥቅሞችን እንደሚያሳጣ ገልጸዋል።

    በዚህም ምክንያት በአገሪቱ ያሉ የሠራተኛ ማኅበራት የጠሩትን አድማ ተከትሎ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ሥራ በማቆማቸው ከብራስልስ የሚነሱ እና የሚያርፉ በረራዎች ሙሉ በሙሉ የቆሙ ሲሆን ከ50 ሺህ በላይ መንገደኞች እቅድ ተስተጓጉሏል።

    ዛሬ ምሽት እና ነገም ሌሎች ጉዞዎች ሊስተጓጎሉ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የቤልጂየም የሠራተኛ ፌዴሬሽን መሪ የሆኑት በርት ኢንግሌር መንግሥት “ የማኅበራዊ አገልግሎት ጥበቃ ሥርዓትን ከማፍረስ የተሻለ አማራጭ ነበረው።” ሲሉ የመንግሥትን እቅድ ኮንነዋል።

    “ትክክለኛ የሆነ የንብረት ታክስ ፣ ተመጣጣኝ የሆነ ግብር እና የግብር ጉድለትን ማስወገድ ይችል ነበር” ብለዋል።

  6. ኢራን የተጣሉባት ማዕቀቦች ከተነሱ ሆርሙዝ እንደሚከፈት አስታወቀች

    እስማኢል ባጋይ
    የምስሉ መግለጫ, የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኢል ባጋይ

    አሜሪካ ከዚህ በፊት የተገባውን ስምምነት ካከበረች እና በኢራን ላይ የጣለችውን የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ገደብን ካነሳች በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ሰላም እንደሚሆን ኢራን ገለጸች።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኢል ባጋይ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ “አሜሪካ የገባችውን ቃል ኪዳን ከፈጸመች የሆርሙዝ ወሽመጥ እና የቀጣናው ደኅንነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይመለሳል” ብለዋል።

    ቃል አቀባዩ ኢራን የምትፈልገው “ሕገወጥ ማዕቀቦች እንዲነሱ እና የባሕር እንቅስቃሴ እገዳው እንዲቆም ነው" ሲሉ የአገራቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

    ለዚህም ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ አሜሪካ እና ኢራን ፓኪስታን ኢስላማባድ ውስጥ በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ያገኘው ስምምነት ተግባራዊ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

    ባፋይ አክለውም “አሜሪካ የገባችውን ቃል ከፈጸመች፣ የሆርሙዝ ወሽመጥ እና የመላው ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ደኅንነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይመለሳል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

    ቃል አቀባዩ የሆርሙዝ ወሽመጥ በሁለት ሰዓታት ውስጥ መልሶ ሊከፈት የሚችል መሆኑን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ኢራን “በጣም ፈጣን እርምጃ ልትወስድ ትችላለች” በማለት መልስ ሰጥተዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በተጨማሪም፣ “የእስላማዊት ሪፐብሊክ ኢራን በራሷ ፈቃድ እና ነጻነት ላይ ተመርኩዛ አገራዊ ዕጣ ፈንታዋን ትወስናለች፤ ስለ ኢራን ውሳኔዎች ከኢራን ውጪ በሌላ ቦታ አይወሰኑም” ብለዋል።

  7. ኢራን ውስጥ በተመረዘ አልኮል ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ታመሙ

    አልኮል መጠጥ በቡትሌ

    ኢራን ውስጥ መርዛማ አልኮል የጠጡ አራት ሰዎች ሲሞቱ ከ120 በላይ ሰዎች ደግሞ ከባድ የጤና ችግር እንዳጋጠማቸው ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    ኔይሻቡር የተባለችው ከተማ የሕክምና ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ ባለፉት ሁለት ቀናት በሜታኖል አልኮል መመረዝ ምክንያት ነው የሰዎቹ ሕይወት ያለፈው እና ጉዳት የደረሰው።

    የኢራን መንግሥት የዜና ኤጀንሲ ኢርና እንደዘገበው፣ በኔይሻቡር የሕክምና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ሚላድ ታቅዲሲ ሄይዳሪያን እንዳሉት፣ አስከ እሁድ ምሽት 4፡00 ሰዓት ድረስ የሟቾች ቁጥር አራት ደርሷል።

    መርዛማው አልኮል በሰዎቹ አንጎል ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ በአልኮል መመረዝ ምክንያት የተጎዱት ሁሉም ወንዶች እንደሆኑም ተገልጿል።

    የኔይሻቡር ዐቃቤ ሕግም፣ “እስካሁን በከተማው ውስጥ በአልኮል መመረዝ ከተጎዱ ሰዎች ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሦስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል” ብለዋል።

    ኢራን ውስጥ አልኮል ማምረት እና መጠጣት ለሙስሊሞች የተከለከለ ሲሆን፣ ለሌሎች ቡድኖችም ከበዓላት ጋር በተያያዘ ሁኔታ ብቻ አልኮል ማዘጋጀት እና መጠጣት ይፈቀዳል።

  8. ትራምፕ ኢራን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከተኮሰችው የበለጠ ድሮን እና ሚሳዔል ባለፈው ሳምንት አስወንጭፋለች አሉ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ኢራን “ባለፈው ሳምንት በአንድ ዓመት ውስጥ በየትኛውም ጊዜ ካስወነጨፈችው በላይ ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን” ብትተኩስም፣ ምንም ጉዳት አልደረሰም ሲሉ እሁድ ዕለት ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ዴሞክራቶች በሁለቱም የኮንግረስ ምክር ቤቶች አብላጫ ድምፅ ያሸነፉበትን የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በኢራን እየተካሄደ ካለው ጦርነት መባባስ ጋር አያይዘው አንስተውታል።

    ፕሬዝዳንቱ ጥቅምት 24/2019 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫን በተመለከተ “ሁለት ነገሮችን ተንብየው” እንደነበረ ጠቅሰዋል።

    “አንደኛ፣ ዴሞክራቶች ካሸነፉ የአክሲዮን ገበያው በከፍተኛ ሁኔታ ይወድቃል የሚል ነበር፤ ይህም ተከስቷል። ሁለተኛው ደግሞ እስከ ዛሬ ድረስ 81,000 ተቃዋሚዎችን የገደለችው እስላማዊቷ የኢራን ሪፐብሊክ ጥቃቷን ይበልጥ ታጠናክራለች የሚል ሲሆን ይህም ሆኗል” በማለት ጽፈዋል።

    በጦርነቱ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን መጨመሩ፣ በአሜሪካውያን ስለ ኢኮኖሚው አካሄድ እንዲሰጉ አድርጓል።

    ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስን ጨምሮ ከፍተኛ የሪፐብሊካን አመራሮች ፓርቲያቸው በምርጫው የተሸነፈበት አንደኛው ምክንያት ከኢራን ጦርነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልጸዋል።

    ትራምፕ በበኩላቸው እሁድ ዕለት ባሰፈሩት ፅሑፍ፣ መራጮች የድምፃቸውን ትርጉም “አልተረዱም” ያሉ ሲሆን፣ ምርጫውንም “እጅግ ‘ያልተለመደ’” ሲሉ ገልጸውታል።

    “የኢራን መሪዎች ዴሞክራቶችን የሚመለከቷቸው እንደ ደካማ፣ ውጤታማ ያልሆኑ እና አገር አጥፊ ነው፤ ነገር ግን ይህ እንዲሆን አልፈቅድም! ዴሞክራቶችም ሆኑ ኢራን የነዳጅ ዋጋ በተቻለ መጠን ለረጅም ጊዜ ከፍ ብሎ እንዲቆይ እጅጉን ተፋልመዋል፤ ከምርጫው በሏላ ግን የነዳጅ ዋጋ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ቀንሷል” ብለዋል።

    አክለውም “መራጮች ድምፅ ከመስጠታቸው በፊት ይህንን አለመረዳታቸው በጣም ያሳዝናል፤ ነገር ግን አጠቃላይ ምርጫው እጅግ ‘ያልተለመደ’ ነበር” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

    • ተያያዥ ዘገባዎች
  9. ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤ 'ኮፕ 31' ያለ ስምምነት ተበተነ

    ሕንጻዎች ከሚገኙበት ከተማ አንድ ስፍራ ላይ ወደላይ የሚወጣ ጭስ

    የተባበሩት መንግሥታት ኮፕ31 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የተገኙ የዓለም አገራት በነዳጅ እና በፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶቸቻውን ማጥበብ ባለመቻላቸው፣ አየር ንብረት ለውጥን መከላከል የሚያስችል አዲስ ትልቅ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቀሩ።

    በቱርክ የተካሄደው ድርድር አርብ ዕለት እንዲጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፣ የጋራ መግባባት ለማግኘት ሲባል እስከ እሁድ ምሽት ድረስ ቀጥሏል። በዚህ የተነሳም ጉባኤው ረጅም ጊዜ የወሰደው የተመድ የአየር ንብረት ኮንፈረንስ ሆኗል።

    ይሁን እንጂ በድርድሩ መጨረሻ በቀረበው ረቂቅ ሰነድ ላይ የቅሪተ አካል ነዳጅ (ፎሲል ፊውል) በቀጥታ አለመጠቀሱ የአውሮፓ ኅብረት፣ የፓስፊክ ደሴት አገራት እና ሌሎችንም አስቆጥቷል።

    እንደ ነዳጅ፣ ከሰል እና የተፈጥሮ ጋዝ ያሉ የኃይል አማራጮች የወል መጠሪያ የሆው 'ፎሲል ፊዩል'፣ የዓለም ሙቀት መጨመር ዋነኛ መንስኤ ነው።

    በርካታ ደሃ አገራት በበኩላቸው፣ እየጨመረ ከመጣው የዓለም ሙቀት ተፅዕኖ ጋር ራሳቸውን ማላመድ የሚያስችላቸውን ገንዘብ ከበለጸጉ አገራት ስለሚያገኙበት መንገድ በግልፅ ቃል ባለመገባቱ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

    በዓመታዊው የኮፕ ጉባኤ ይህ ዓይነቱ የዋነኛ ፖለቲካዊ ስምምነት አለመሳካት ለመጨረሻ ጊዜ የታየው በአውሮፓውያኑ 2009 ኮፐንሃገን ላይ ነበር።

    ከሥልጣን ከመውረዳቸው በፊት ለመጨረሻ ጊዜ በተሳተፉበት በዚህ የኮፕ ጉባኤ ላይ የተገኙት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ስምምነት ላይ ባለመደረሱ “እጅግ ማዘናቸውን” ገልጸዋል።

    ጉቴሬዝ “ኃያል የፎሲል ፊውል የጥቅም ፍላጎት” አላቸው ያሏቸውን አካላት ተችተዋል።

    “በሁሉም ስፍራ የሚገኙ ሕዝቦች ዋጋ በሚከፍሉበት በዚህ ወቅት፣ የግዙፍ የትንባሆ ኩባንያዎችን ስልት በመኮረጅ ሳይንሱን በማዛባት፣ ፖሊሲዎችን በማዘግየት፣ እርምጃዎችን በማገድ ትልቅ ትርፍ እያካበቱ ነው” ብለዋል።

    ከቱርክ ጋር በመሆን ጉባኤውን ያዘጋጀችው አውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ በበኩቸላው፣ ኮንፈረንሱ ያለ ስምምነት ለመበተኑ ተጠያቂ ያደረጉት “አስቸጋሪ ጂኦፖለቲካዊ ጊዜ” መኖሩን ነው።

    ላይ ታች ሲሉ የከረሙት የተሳታፊ አገራት ልዑካን ከሁለት ሳምንታት ድርድር በኋላ፣ አለመግባባቱን ለመፍታት ያስችላል የተባለ አዲስ ረቂቅ ስምምነት እሁድ ጠዋት ቀርቦላቸው ነበር።

    ነገር ግን በዚህ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ውስጥ ‘ፎሲል ፊውል’ የሚለው ቃል አንድም ቦታ አልተጠቀሰም።

    የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝን በተመለከተ የተጠቀሰው ብቸኛው ቀጥተኛ ያልሆነ አገላለጽ፣ በአውሮፓውያኑ 2023 በተካሄደው ኮፕ28 ስብሰባ ወቅት አገራት ከፎሲል ፊውል ተጠቃሚነት “ለመሸጋገር” ስምምነት መፈጸማቸውን የሚያስታውስ አንቀጽ ነው።

    የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ የሆኑት አየርላንዳዊው ሚኒስትር ዳራግ ኦብራየን፣ ኅብረቱ ይህንን አካሄድ “በጽኑ” እንደሚቃወም አሳውቀዋል።

    “የተላለፉት ውሳኔዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከሚያስፈልገው የቁርጠኝነት ደረጃ ጭራሽ የሚቀራረቡ አይደሉም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ባለፈው ሰኞ ዕለት በቀረበው የመጀመሪያው ረቂቅ ላይ ‘ፎሲል ፊውል’ ወይም ‘ፎሲል ፊውልስ’ የሚለውን ቃል ስድስት ጊዜ ተጠቅሶ የነበረ ሲሆን፣ ነዳጅ አምራች አገራት ግን ተቃውመውታል።

    የሳዑዲ አረቢያ ልዑክ መሐመድ አዩብ የአረብ አገራት “በቅን ልቦና መሳተፋቸውን እንደቀጠሉ” አንስተው፣ ነገር ግን አረብ አገራቱ በታሪክ ውስጥ የነበራቸው የበካይ ጋዝ ልቀት ድርሻ አነስተኛ መሆኑን በመጥቀስ ተከራክረዋል።

    ሩሲያ በበኩሏ ሀገራት እንደ የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ካሉ የኃይል አማራጮች ተጠቃሚነት በፍጥነት የሚወጡ “የነዳጅ ድኅነት” ይከሰታል ስትል ሞግታለች።

    • ተያያዥ ዘገባዎች
  10. የኅዳር 14 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ዘገባ ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የሰኞ ኅዳር 14 ቀን 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ዘገባችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። አብራችሁን እንድትቆዩ በአክብሮት እንጋብዛለን።