ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቢቢሲ ላይ ላቀረቡት የስም ማጥፋት ክስ የተጠየቁትን ሰነዶችን እንዲያስረክቡ ታዘዙ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአሜሪካ የፍሎሪዳ ፍርድ ቤት ዳኛ፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢቢሲ ላይ ላቀረቡት የ10 ቢሊዮን ዶላር የስም ማጥፋት ክስ የተጠየቁትን የገንዘብ ሰነዶች እንዲያስረክቡ ትዕዛዝ ሰጡ።

ዳኛዋ ትዕዛዙን የሰጡት በመዝገቡ የመጀመሪያ ችሎት ሲሆን፤ የ2021ዱ የካፒቶል ሂል አመፅ ላይ የተሰራጨ ንግግራቸው የተለያየ ክፍልን ፓናሮማ ዘጋቢ ፊልም ወጥ አስመስሎ በማቅረቡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቢቢሲን ከስሰዋል።

ዳኛ ኤንጀልክ ሊት የቢቢሲ የሕግ ክፍል ያቀረበው የፕሬዝዳንቱ የፋይናንስ ሰነድ ተላልፎ ይሰጠን አቤቱታ ፈቅደዋል።

ማክሰኞ ዕለት የተሰጠው የዳኛዋ ትዕዛዝ ይግባኝ ማለት የሚቻል ነው።

ትዕዛዙ ትራምፕ በቢቢሲ ፓናሮማ የቪዲዮ አርትዖት ምክንያት የገንዘብ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ማስረጃ እንዲያቀርቡ ለማስገደድ የተደረገ ጥረት ከፊል ስኬት ነው።

ዳኛዋ የካፒቶል ሂል አመፅን በሚመለከት በቢቢሲ የቀረቡ የሰነድ አቤቱታዎች ላይ ሁለት የተለያዩ ትዕዛዞችን ሰጥተዋል።

የስም ማጥፋት ክሱ አሁን ላይ ያተኮረው ሁለቱ ወገኖች የውስጣዊ እና ሌሎች ሰነዶችን ለማስረጃነት እንዲውሉ ማቅረብ ላይ ነው።

የቢቢሲ ጠበቆች ኮርፖሬሽኑ 87 ሺህ ገፆች ያሏቸው ሰነዶችን ማቅረቡን ሲናገሩ የትራምፕ ጠበቆች ደግሞ 735 ፆችን ማቅረባቸውን ነቅፈዋል። በትራምፕ ጠበቆች የቀረቡ ሰነዶች "የዜና ዘገባዎች" እና "ከበይነ መረብ የወረዱ" ሌሎች ፅሑፎች ናቸው ብለዋል።

የቢቢሲ የሕግ ባለሙያ ቻርለስ ቶቢን ይህም የማስረጃ አቅርቦቱ "ሙሉ ለሙሉ" የአንድ ወገን መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

የትራምፕ ጠበቃ አሊሀንድሮ ብሪቶ የቢቢሲን የሰነድ ጥየቃ "ጨቋኝ" እና "የሚጠራርግ" ብለውታል።

ቢቢቢ ከካፒቶል ሂል አመፅ ጋር በተያያዘ ትራምፕ ከረዳቶቻቸው ጋር ያደረጓቸውን ንግግሮች የሚያሳዩ ሰነዶችን መጠየቁን እንዲሁም የፌደራል ተቋማት እና የቀድሞ ባለሥልጣናት ምስክር እንዲሆኑ መጥራቱን ተቃውመዋል።

የትራምፕ የሕግ ቡድን ቢቢሲ ማስረጃ በግምት ለመፈለግ እና የቀድሞ ባለሥልጣናትን "ለመተናኮስ" እየሞከመረ ነው ሲሉ ከስሰዋል።

አብዛኛው የትራምፕ ጠበቆች መከራከሪያ ባለፈው ዓመት የቢቢሲ ሊቀ መንበር ሳሚር ሻ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት የላኩት ደብዳቤ ላይ ያተኮረ ነው።

በዚህ ደብዳቤ ሊቀ መንበሩ በፓናሮማ ላይ በቀረበው ክፍል ሳይታወቅ ዶናልድ ትራምፕ በቀጥታ የአመፅ ጥሪ ያቀረቡ በማስመሰሉ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ጠበቃ ብሪቶ ደብዳቤውን በቢቢሲ "እጅ መስጠት" እና "ማመን" ሲሉ ገልፀውታል።

ቢቢሲ ዘጋቢ ፊልሙ በአሜሪካ ባለመሰራጨቱ ሙሉ ክሱ እንዲነሳ ፍላጎቱን ገልጿል። የአሜሪካ ፍርድ ቤት እዚህ አቤቱታ ላይ ገና ውሳኔ አልሰጠም።