ሩሲያ እና ዩክሬን ስንት እየከፈሉ ነው የውጭ አገር ዜጎችን ለጦርነት የሚመለምሉት?

ከጀርባው የሚታይ ወታደር እና ራቅ ብሎ የሚወነጨፍ ከባድ መሳሪያ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ሙሉ ወረራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ40 በላይ አገራት የተውጣጡ ቢያንስ 3,589 የውጭ አገር ዜጎች ለሞስኮ ሲዋጉ መገደላቸውን ቢቢሲ ያደረገው ምርመራ አሳይቷል።

ለወታደርነት ከተመለመሉበት መካከል ከሩሲያ ወህኒ ቤት ውስጥ የተመለመሉ፣ በተለያዩ መንገዶች የተገደዱ ወይም የተታለሉ ስደተኞች እንዲሁም በቀረበላቸው ማራኪ ክፍያ የተሳቡ ፈቃደኞች ይገኙበታል። ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ባደረጉት ስምምነት አማካነኝት የተላኩ ወታደሮችን ለሞስኮ ተሰልፈው ተገኝተዋል።

ቢቢሲ ኒውስ ራሺያ እና ሜዲያዞና የተባለ ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን በሩሲያ በኩል የተገደሉ ሰዎችን ዝርዝር እየመዘገቡ ነው። ይህ ዳሰሳ የሚካሄደው እንደ ይፋዊ መግለጫ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች እንዲሁም የመቃብር እና የጦርነት መታሰቢያ ምሥሎች ያሉ በግልጽ የሚገኙ መረጃዎችን በማሰባሰብ ነው።

ኡጋንዳዊው ኤድሰን ካምዌሲግዬ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት አንዱ ነው። ቤተሰቦቹ እንደሚናገሩት ወደ ሩሲያ ሲጓዝ በጥበቃነት እንደሚሠራ ነበር ያሰበው።

የ45 ዓመቱ የኡጋንዳ ዜጋ በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ ኢራቅ እና አፍጋኒስታን ውስጥ በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ነበር። በእነዚህ ጊዜያት ጭምር ግን ውጊያ ላይ ተሳትፎ እንደማያውቅ ባለቤቱ ካሮሊን ሙኩዛ ለጋዜጠኞች ተናግራለች።

በውጭ አገራት ያገኛቸው የነበሩት ሥራዎች እየተቀዛቀዙ ሲመጡ ወደ ኡጋንዳ ተመልሶ በታክሲ አሽከርካሪነት እና በግብርና ሥራ ላይ ለመሰማራት ሞክሯል። የሚያገኘው ገንዘብ ግን ባለቤቱን እና ሁለት ልጆቹን ለማስተዳደር የሚበቃ አልሆነም።

ከዚህ ቀደም ሲሠራ የነበረው ዓይነት የጥበቃ ሥራ ሩሲያ ውስጥ ማግኘቱን ለቤተሰቡ የተናገረው በታኅሣሥ 2016 ዓ.ም. ነበር። በቀጣዩ ወር ጥር ላይ ግን ከጠበቀው የተለየ ነገር እንዳጋጠመው ለባለቤቱ ትናገራለት።

ባለቤቱ ሙኩዛ "ወታደራዊ ሥልጠና እየወሰደ እና በቅርቡ ወደ ግንባር ሊላክ መሆኑን ነግሮኝ እንድጸልይለት ጠየቀኝ" ስትል 'ታዝ' ለተሰኘ የጀርመን ጋዜጣ ተናግራለች።

ካምዌሲግዬ፣ ከአንድ ሳምንት በኋላ በሰሜን ምሥራቅ ዩክሬን በሚገኘው ኩፒያንስክ አቅራቢያ መገደሉን ቢቢሲ ራሺያ ማረጋገጥ ችሏል።

ባለቤቱ አስከሬኑን ወደ አገሩ ለመመለስ አሁንም እየጣረች ነው። የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያሳየው፤ የኡጋንዳ ባለሥልጣነት አስከሬኑ የሚመለስበትን መንገድ ለማመቻቸት ፈቃደኛ አልሆኑም።

እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ ለሩሲያ ሲዋጉ የነበሩ ቢያንስ ሁለት ሌሎች ኡጋንዳውያን መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

 ኤድሰን ካምዌሲግዬ

የፎቶው ባለመብት, Facebook

የምስሉ መግለጫ, ዩጋንዳዊው ኤድሰን ካምዌሲግዬ ለሩሲያ ሲዋጉ ከተገደሉ የውጭ አገር ዜጎች አንዱ ነው

ካምዌሲግዬ፣ ለሩሲያ ጦር ሲዋጉ እንደተገደሉ ቢቢሲ ራሺያ ካረጋገጣቸው 1,285 የውጭ አገር ተዋጊዎች አንዱ ነው። የኩባ፣ የአሜሪካ፣ የቻይና፣ የቪየትናም፣ የፖላንድ፣ የሕንድ፣ የኔፓል፣ የሰርቢያ እና የሌሎች በርካታ አገራት ዜጎችም በተመሳሳይ መልኩ ሞተዋል።

ቢቢሲ ኒውስ ኮሪያም የሳተላይት ምሥሎች እና በሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግ ባለ ወታደራዊ መታሰቢያ ላይ የሚገኙ ፎቶግራፎችን በመጠቀም ባደረገው ምርመራ ተጨማሪ 2,304 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን መለየት ችሏል።

የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች የተገደሉት በነሐሴ 2024 ዩክሬን ሩሲያ ኩርስክ ግዛት ድንገተኛ ጥቃት በከፈተችበት ወቅት በተደረገ ውጊያ ላይ ነው።

በሕይወት የተረፉትን ጨምሮ በአጠቃላይ ለሩሲያ የተዋጉ የውጭ አገር ዜጎች ቁጥር ከዚህ እጅግ እንደሚበልጥ ይታመናል።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)፤ ከ44 አገራት የተውጣጡ በግምት 24,000 ገደማ የውጭ አገር ቅጥረኛ ተዋጊዎች በሩሲያ ጦር ውስጥ እየተዋጉ ነው የሚል እምነት እንዳለው አንድ የጥምረቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ራሺያ ተናግረዋል።

እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ፣ ከእነዚህ ተዋጊዎች ውስጥ አብዛኞቹ ከአፍሪካ አገራት የመጡ ናቸው።

"ምናልባትም በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ውል ፈርመዋል። አንዳንዶቹ ይህንን ያደረጉት በፈቃደኝነት ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ተገድደው ነው" ብለዋል።

በዚህ ዝርዝር ውስጥ፤ ከሩሲያ ጎን በመሆን እየተዋጉ ካሉት የዩክሬን ግዛቶች የመጡ ተዋጊዎችን የማያካትት ሲሆን፣ ለሞስኮ ሲዋጉ የተገደሉ 25 የዩክሬን ዜጎች ተመዝበግዋል። ከእነዚህ ዩክሬናውያን ውስጥ አብዛኞቹ ተመለመሉት ከእስር ቤቶች ነው።

ለሩሲያ ሲዋጉ የተገደሉ ሰዎች መቃብር

የፎቶው ባለመብት, BBC/Mediazona

የምስሉ መግለጫ, በተለይም ከማዕከላዊ እስያ የመጡ የቀድሞ የሶቪየት ሀገራት በርካታ ዜጎች ለሩሲያ ሲዋጉ ተገድለዋል።

ምልመላ ከእስር ቤቶች እና ከውጭ አገራት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሩሲያ የካቲት 2022 ላይ የከፈተችው ሙሉ ወረራ እንደታቀደው በፍጥነት አለመጠናቀቁ፣ የክሬምሊክ መንግሥት የሰው ኃይል እጥረት እንዲያጋጥመው ምክንያት ሆኗል።

በ2022 አጋማሽ የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ እስረኞች የሚዋጉ ከሆነ ከእስር እንደሚለቀቁ የሚገልጽ አማራጭ ቀረበላቸው። መጀመሪያ ላይ ምልመላው የተከናወነው ቫግነር በተባለው የግል ወታደራዊ ኩባንያ ቢሆንም ኋላ ላይ በመከላከያ ሚኒስቴር ሥር ሆኗል።

ይህ አሠራር በዋናነት ትኩረት ያደረገው በተለይም ከማዕከላዊ እስያ የመጡ የቀድሞ የሶቪየት አገራት ዜጎችን ነው። ምሳሌ፣ በጦርነቱ ከተገደሉት የኡዝቤኪስታን እና የታጂኪስታን ዜጎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የተመለመሉት ከሩሲያ እስር ቤቶች ነው።

የሩሲያ ባለሥልጣናት 2024 ላይ ደግሞ ውጊያውን ለሚቀላቀሉ ሰዎች የሚቀርበውን ክፍያ በከፍተኛ መጠን ጨምረውታል።

የሚቀርበው ክፍያ እንደ የክልሉ ይለያያል። በአሁኑ ሰዓት ሞስኮ ውስጥ ውል የሚፈርም አዲስ ምልምል 30,000 ዶላር ገደማ ቅድመ ክፍያ እና 3,500 ዶላር ገደማ መርሃዊ ደመወዝ እንደሚቀበል ቃል ይገባለታል።

ውጊያ ላይ የሚሰጥ ጉርሻ ያለ ሲሆን፣ ይህም ምልምሎቹ በመጀመሪያው ዓመት የሚያገኙትን ገቢ ከ72,300 ዶላር በላይ ሊያደርሰው ይችላል።

ሩሲያ ውስጥ አማካዩ የአንድ ሰው ወርሃዊ ገቢ 760 ዶላት ገደማ ነው።

የሩሲያ መንግሥት እንደ ኩባ፣ ኔፓል፣ ሕንድ፣ ሲሪላንካ እና የመን ካሉ ራቅ ያሉ አገራት የሚያደርገውን ምልመላ ያጠናከረው በዚህ መልኩ ነው።

የተወሰኑት ሠራዊቱን እንደሚቀላቀሉ ያውቁ ነበር። ሌሎች ደግሞ ሩሲያ ውስጥ እንደሚማሩ ወይም በግንባታ እና በጥበቃ ሥራ ላይ እንደሚሰማሩ ነበር ያሰቡት። ሩሲያ ከደረሱ በኋላ ግን ወደ ወታደራዊ ሥልጠና፣ ከዚያም ወደ ግንባር መላካቸውን ገልጸዋል።

ከደሃ የአፍሪካ አገራት ወታደር ለመመልመል የተደረጉ ጥረቶችም እንደነበሩ ሮይተርስ የዜና ወኪል እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ፌዴሬሽን ያወጧቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

ከሌሎች አገራት ከመጡ ምልምሎች በተለየ፣ ሰሜን ኮሪያውያን አገራቸው ከሩሲያ ጋር በፈረመችው የመከላከያ ስምምነት አማካኝነት ለውጊያ ተልከዋል።

በአጠቃላይ ሲታይ፣ ሩሲያ ከተገደሉባት ወታደሮች ጋር ሲነጻጸር የውጭ አገር ተቀጣሪዎች ብዛት አነስተኛ ነው። በመንግሥታቸው በግልጽ የተላኩትን ሰሜን ኮሪያውያንን ጨምሮ፤ በአጠቃላይ ቢቢሲ ካረጋገጠው 233,033 የሟቾች ቁጥር ውስጥ የውጭ አገራት ዜጋ ድርሻ ከ2 በመቶ በታች ነው።

የውጭ አገር ቅጥር የሩሲያን ዋነኛ የወታደር ምንጭ የሆኑትን የአገሪቱ ዜጎች አይተካም። ነገር ግን የሚሞቱ ሰዎች ብዛት እየጨመረ እና ለምልመላ ፈቃደኛ የሚሆኑ ሩሲያውያን እያነሱ በሄዱ ቁጥር፣ ሞስኮ ወደውጭ ማማተሯ የሚቀር አይመስልም።

የሩሲያ መንግሥት ከመስከረም 2022 ወዲህ የሟቾች ቁጥር መረጃ አውጥቶ አያውቅም። ቢቢሲ ራሺያ ስላገኛቸው መረጃዎችም አስተያየት ሰጥቶ አያውቅም።

የሩሲያ መንግሥት ከመስከረም 2022 ወዲህ የሟቾች ቁጥር መረጃ አውጥቶ አያውቅም

የፎቶው ባለመብት, BBC/Mediazona

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ መንግሥት ከመስከረም 2022 ወዲህ የሟቾች ቁጥር መረጃ አውጥቶ አያውቅም

የዩክሬን 'የውጭ ሠራዊት'

ዩክሬንም፤ ሩሲያ በየካቲት 2022 ሙሉ ወረራ ከከፈተች በኋላ በዘረጋችው ብሔራዊ ሥርዓት አማካኝነት የውጭ አገር ዜጎችን ትቀጥራለች።

ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ የዩክሬንን 'ዓለም አቀፍ ሠራዊት' (International Legion) ያቋቋሙት በቀናት ልዩነት ውስጥ ሲሆን፣ በውጭ አገር ለሚገኙ ፈቃደኞችም ጥሪ አቅርበዋል። የውጭ አገር ዜጎች በዚህ ሠራዊት ውስጥ እና በሌሎች የዩክሬን ክፍለ ጦሮች ውስጥ ያገለግላሉ።

በአገሪቱ የጦርነት ጊዜ አዋጅ መሠረት፤ ለሩሲያ የሚዋጉት የውጭ አገር ዜጎች በፈቃዳቸው መልቀቅ የሚችሉት ከስድስት ወር አገልግሎት በኋላ ነው።

ዩክሬን የሠራዊቱን ደመወዝ እንደምትጨምር እና ከውጭ የሚመጡ ተጨማሪ ተዋጊዎችን እንደምትቀጥር ዜሌንስኪ ተናግረዋል። ዩክሬንም በተመሳሳይ ፊቷን ወደ ውጭ ምልመላ ያዞረችው ከአራት ዓመታት በላይ በዘለቀው ጦርነት የተነሳ የሰው ኃይል እጥረት እያጋጠማት በመሆኑ ነው።

ለዩክሬን ሲዋጉ የተገደሉ አጠቃላይ ውጭ ዜጎች ቁጥር ይፋ አይደረግም። የዩክሬንን የምድር ጦር ብቻ የተቀላቀሉ የውጭ ፈቃደኛ ተዋጊዎች ቁጥር ከ8,000 በላይ መሆኑን ምልመላውን የሚያስተባብረው መሥሪያ ቤት ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።

በመላው የዩክሬን ጦር ኃይሎች ቅርንጫፎች ውስጥ የሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች ቁጥር 16,000 እንደሚገመት እና ከ72 አገራት የተወጣጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቅድሚያ ከተቀላቀሉት ፈቃደኞች ውስጥ አብዛኞቹ ከምዕራባውያን እንዲሁም ከቀድሞ ሶቪየት ኅብረት አገራት የመጡ ናቸው። የተወሰኑትም ወታደራዊ ልምድ አላቸው።

ኋላ ላይ ዩክሬን የስፓኒሽ ቋንቋ ምልመላ እና የዕዝ ያቋቋመች ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ወታደሮችም ተቀላቅለዋል።

የተወሰኑት የተቀላቀሉት ዩክሬንን ለመደገፍ መሆኑን ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ የሚያገኙት ገንዘብ አነሳስቷቸዋል። ኮሎምቢያ ውስጥ ለወታደሮች የሚከፈለው ገንዘብ ዩክሬን ከምታቀርበው በብዙ ይበልጣል።

ለዩክሬን የሚዋጉ የውጭ አገር ዜጎች የሚከፈላቸው ከአገሪቱ ወታደሮች እኩል ነው። ውጊያ ላይ የሚያሳልፉ ወታደሮች በወር የሚያገኙት ክፍያ 2,690 ዶላር ገደማ ይደርሳል።

በተጨማሪም በግንባር ቀደምትነት ለሚያሳልፏቸው 30 ቀናት 1,570 ዶላር ይከፈላል።

ይህም ሆኖ ግን ሩሲያም ሆነች ዩክሬን የሚያሰልፏቸው የውጭ አገራት ዜጋ የሆኑ ተዋጊዎች፣ ከአገሮቻቸው ለተወጣጣጡት ሠራዊቶች አነስተኛ ማሟያ ናቸው።