ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ ፀረ አውዳሚ መርከብ የሆነ ሚሳዔል አሜሪካ ላይ መጠቀሟን ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, centcom
ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ “በአሜሪካ መርከቦች ላይ ፀረ አውዳሚ መርከብ ሚሳዔል” ጥቅም ላይ ማዋሏን የአገሪቱ ጠቅላይ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊ ሞህሴን ረዛኢ ተናገሩ።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ በአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ የባለስቲክ ሚሳዔል ጥቃት መፈጸሙን አስታውቆ ነበር። ይህ ጥቃት የተፈጸመው የአሜሪካ ጦር የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን በመምታቱ እና በአገሪቱ ላይ የባሕር እገዳ በመጣሉ እንደሆነ ተገልጿል።
የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊው በኢራን ቴሌቪዥን ጣቢያ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “ከ48 ሰዓታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የኢራን ፀረ-አውዳሚ መርከብ ሚሳኤልን በአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ ሞክረናል። ይህ ሚሳዔል ለአሜሪካውያኑ ሲኦል ፈጥሮባቸዋል፤ ሸሽተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ለዚህ የኢራን ገለጻ በቀጥታ ምላሽ አልሰጠም። ይሁን እንጂ ዕዙ ትናንት እሁድ በኤክስ ገጹ ባጋራው ልጥፍ፣ በሁለት መርከቦቹ ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት በተዘዋዋሪ ጠቅሷል።
“ለኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሚተላለፈው መልዕክት ግልጽ ይሁን፤ ሁለት መርከቦቻችን ላይ ተኩስ ከከፈታችሁ፣ እጅግ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንጥልባችኋለን፤ ሦስት መርከቦቻችሁንም እናወድማለን” ብሎ ነበር።
ማዕከላዊ ዕዙ አክሎም “የአሜሪካ ኃይሎችን ለመከላከል አናመነታም፤ አስፈላጊም ከሆነ የተወሰነውን እና ተጋላጭ የሆነውን የኢራን የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ስብስብ ሙሉ በሙሉ እናወድማለን” በማለትም አስጠንቅቋል።
አሜሪካ ቅዳሜ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኙ ሦስት ኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን መምታቷን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባሕር ኃይል ቅዳሜ ዕለት አስታውቆ ነበር።
ኢራንም በምላሹ ባልተፈቀደ የሆርሙዙ መተለላፊያ በኩል ሲጓዙ ነበር እንዲሁም በሌሎች ስፍራዎች ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸው መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገልጿለች።
ቃለ መጠይቅ የሰጡት የኢራን የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊው ረዛኢ ለመርከብ ጉዞ የተከለከለ የባህር ቀጠና ስለማቋቋም ተናግረዋል። “በሚቀጥሉት ቀናት ከአሜሪካ የከበባ መስመር እስከ መጫኛ ወደቦች ያለውን ርቀት የሚያካትት አዲስ ለመርከብ ጉዞ የተከለከለ ቀጠና ይፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
እንደ ዋና ጸሐፊው ገለጻ ሆርሙዝ የትኛውም አቅጣጫዎች “የሚንቀሳቀስ እና ወደ ባህረ ሰላጤው ለመጓዝ ያሰበ የትኛውም መርከብ በኢራን የማዕቀብ ዝርዝር” ውስጥ ይካተታል።
