ቻይና በአባይ እና በቀይ ባሕር ጉዳይ የግብፅን አቋም ማንጸባረቋ ለኢትዮጵያ ምን ማለት ነው?

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የግብፅ ፕሬዝዳንት አብድልፈታህ አልሲሲ

የፎቶው ባለመብት, @China_Amb_India

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 7 ደቂቃ

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ አገራቸው ከግብፅ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሠረተችበትን 70ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ወደ ካይሮ አቅንተው ነበር።

ማክሰኞ እና ረቡዕ ነሐሴ 26 እና 27/2018 ዓ.ም. የተደረገው የዢ ጉብኝት ሲጠናቀቅ ሁለቱ አገራት ያወጡት የጋራ መግለጫ ጠንካራ አቋሞች የተንጸባረቁበት ሆኖ ታይቷል።

ይህ የጋራ መግለጫ ግብፅ ከኢትዮጵያ የምትወዛገብበትን የአባይ ውሃ ጉዳይ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአዲስ አበባ ዋነኛ አጀንዳ የሆነውን የቀይ ባሕር ጉዳይን አንስቷል።

መግለጫው ላይ ስለ ሁለቱ ጉዳዮች የሰፈሩት ነጥቦች ግብፅ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ያነሳቻቸው ናቸው።

ጉዳዩን ትኩረት የሚስብ ያደረገው፣ ግብፅ በአባይ እና በቀይ ባሕር ላይ የምታራምዳቸው እነዚህ ምልከታዎች የቻይናም አቋም ሆነው በጋራ መግለጫ መውጣታቸው ነው።

"[መግለጫው] ውስጥ የታጨቁት ቃላቶች በሙሉ የግብጽ ቋንቋ ናቸው" ይላሉ የውሃ ሀብት ልማት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና ሀይድሮ ዲፕሎማሲ አማካሪው ፈቅአህመድ ነጋሽ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት ሃይድሮ ዲፕሎማሲ ባለሙያዎች፣ በአሁኑ የጋራ መግለጫ ላይ የሰፈሩት አገላለጾች ከዚህ ቀደም ቻይና በአባይ ጉዳይ ላይ ስትከተል ከነበረው የገለልተኝነት አካሄድ የተለዩ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

በዚህ ዓመት ጥቅምት ላይ አውሮፓ ኅብረት እና ግብፅ በጋራ ያወጡት መግለጫ ላይ ስለ አባይ ውሃ የተንጸባረቀው አቋም ከኢትዮጵያ በኩል ተቃውሞ አስነስቶ ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልፕ ትራምፕም አባይ እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ባደርጓቸው ንግግሮች ለግብፅ ያደለ አቋማቸውን አሳይተዋል።

የአሁኑ መግለጫ ሁለተኛዋ ልዕለ ኃያል አገር ቻይና በአባይ ጉዳይ ላይ ወደ ግብፅ ማዘንበሏን ያሳያል? ይህ አቋም ለኢትዮጵያ ምን ማለት ነው?

የጋራ መግለጫው ምን ይላል?

በግብፅ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት እና የቻይና ይፋዊ የመንግሥት ዜና ወኪል በሆነው 'ዢንዋ' ላይ የወጣው የጋራ መግለጫ የሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ 21 ነጥቦችን የያዘ ነው። በመግለጫው ሦስተኛው ነጥብ ላይ የሰፈረው ሁለቱ አገራት "አንዳቸው የሌላኛቸው መሠረታዊ ጥቅሞች እና ዋና ስጋቶችን" በተመለከተ "የማይናወጥ የጋራ ድጋፍ" እንዳላቸው ይገልጻል።

ቻይና ከዚህ ጋር በተያያዘ ያነሳችው እንደ ግዛቷ አካል የምትቆጥራትን የታይዋንን ጉዳይ ነው። በግብፅ በኩል ደግሞ የአባይ ጉዳይ ተነስቷል።

መግለጫው፣ "የቻይና ወገን፣ ናይል ወንዝ የግብፅ ዋነኛ የሕይወት መስመር በመሆኑ ያለውን ወሳኝ ጠቀሜታ እንደሚረዳ ያረጋግጣል" ይላል። "ግብፅ የውሃ እና የምግብ ዋስትናዋን እንዲሁም የልማት ጥቅሞቿን የማስጠበቅ ሕጋዊ መብት" እንዳላትም ቻይና በዚህ መግለጫ እውቅና ሰጥታለች።

በተጨማሪም ሁለቱም ወገኖች "ሁሉም የናይል ተፋሰስ አገራት ጉዳት ያለመፍጠር ግዴታን [መወጣትን] ጨምሮ ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲያከብሩ" ጥሪ አቅርበዋል።

ግብፅ ደግሞ በምላሹ "ለአንዲት ቻይና መርህ" ቁርጠኛ እንደሆነች እንዲሁም ታይዋን የቻይና "የማትነጠል የግዛት አካል" ስለመሆኗ ዕውቅና እንደምትሰጥ አስታውቃለች።

የቀይ ባሕር ጉዳይ በተነሳበት የመግለጫው ክፍል ላይ ደግሞ፣ ፕሬዝዳንት ዢ እና የግብፅ ፕሬዝዳንት አልሲሲ በአፍሪካ ቀንድ "መረጋጋትን የማጠናከር" ተግባር የቀጣናውን አገራትን "ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበርን እንደሚጠይቅ" አስፍረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali

የምስሉ መግለጫ, የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጥር ላይ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት የባሕር በር ጉዳይን ያነሱ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ደግሞ "ታይዋን የማትነጠል የቻይና ግዛት አካል" መሆኗን አረጋግጣለች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አክለውም፣ "የቀይ ባሕር አስተዳደር እና ፀጥታ ዋና ኃላፊነት የባሕር ዳርቻው [ተጎራባች] አገራት እንደሆነ እና [አገራቱ] ፍላጎታቸው ሙሉ በሙሉ መከበር እንዳለበት" በአጽንኦት አንስተዋል። "የባሕር ጉዞ እና የዓለም አቀፍ ንግድ ነፃነትን ለማረጋገጥ" በእነዚህ አገራት መካከል ያለው ቀጣናዊ ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

በቤይጂንግ እና ካይሮ የጋራ መግለጫ ላይ የሰፈረው 'የቀይ ባሕር ደኅነት የሚመለከተው የውሃ አካሉን የሚጎራበቱ አገራትን ብቻ ነው' የሚል አቋም ግብፅ ከዚህ ቀደም ከኤርትራ እና ጂቡቲ ጋር በመሆን ያንጸባረቀችው አቋም ነው።

ግብፅ ከአገራት ጋር ባወጣቻቸው በእነዚህ መግለጫዎች ከቀይ ባሕር ፍላጎት ጋር በተገናኘ የጠቀሰችው አገር የለም። ይሁን እንጂ ይህ አቋም እየተንጸባረቀ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቱን በይፋ እያራመደ ባለበት ወቅት ነው።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ባለፈው ጥር ላይ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ከተገናኙ በኋላ በወጣው መግለጫ ላይ የባሕር በር ጉዳይ ተነስቶ ነበር።

በዚህ መግለጫ ላይ ቻይና ከባሕር በር ጋር በተያያዘ የተጠቀመችው አገላለጽ ጥቅል ሊባል የሚችል ነው። እንደ የባሕር በር ማግኘት ያሉ የሎጂስቲክስ ጉዳዮች "የሚመለከታቸውን አገራትን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት" እንዲሁም "የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር እና ዓለም አቀፍ ሕግን. . . በማክበር ላይ መመሥረት" እንዳለባቸው ገልጻለች።

ኢትዮጵያ በበኩሏ "ታይዋን የማትነጠል የቻይና ግዛት አካል" እንደሆነች በመግለጽ፤ ለ"አንድ ቻይና" መርኅ ያላትን ቁርጠኝት በዚሁ የጋራ መግለጫ ማረጋገጧ ይታወሳል።

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ (ግራ)፣ የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ (መሃል) እና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን (ቀኝ) ረቡዕ ዕለት በተካሄደው የኅብረቱ እና የግብፅ ጉባኤ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Council of the European Union

የምስሉ መግለጫ, የአውሮፓ ኅብረት ጥቅምት ላይ ከካይሮ ጋር በጋራ ባወጣው መግለጫ፣ "የግብጽን የውሃ ደኅንነትን" እንደሚደግፍ እና ይህ አቋሙ "የኢትዮጵያን ግድብንም እንደሚያካትት" አስታውቋል

የመግለጫው ቃላቶች ምን ያመለክታሉ?

ሀይድሮ ዲፕሎማሲ አማካሪው ፈቅአህመድ፣ ግብፅ "በተለይ ከኃያላን አገራት ጋር ስምምነት ስታደርግ ናይልን እና ናይል ላይ አለኝ የምትለውን የውሃ ድርሻ ሰንጥራ ማስገባቷ የማይቀር ነው" ይላሉ።

በጥቅምት 2018 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ከተካሄደው የአውሮፓ ኅብረት እና ግብፅ ጉባኤ በኋላ የወጣው መግለጫም አባይ ላይ ተቀራራቢ አቋም ያንጸባረቀ ነበር። ኅብረቱ "የኢትዮጵያ ግድብን በተመለከተ ጭምር" ለግብፅ "የውሃ ደኅንነት ድጋፉን" እንደሚሰጥ አስታውቆ ነበር።

"ምንም ጉዳት አለማድረስ" የሚል ገለጻ ጭምር የተካተተበት ይህ መግለጫ በወቅቱ በብራሰልስ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።

ኤምባሲው የአውሮፓ ኅብረት ከግብፅ ጋር ያወጣው መግለጫ ካይሮ በአባይ ወንዝ ላይ የምታነሳውን "የቅኝ ግዛት እና የብቸኛ ተቆጣጣሪነት መብት የሚያስተጋባ [ነው]" በሚል ትችት ቀርቦበታል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው "ይህ የተለመደ መሪዎች ሲገናኙ የሚያወጡት የጋራ መግለጫ ነው" ይላሉ። ይሁን እንጂ "[መግለጫው] ላይ የተጻፉት ነገሮች፤ በተደጋጋሚ በግብፅ ወገን የሚጠቀሱ ቃላቶች መርሆች" መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

በመግለጫው ላይ ለሰፈሩት ቃላት ትኩረት የሚሰጡት ኢንጂነር ጌዲዮን፣ "ጉዳት አለማድረስ" የሚለው አገላለጽን አይቀበሉትም። "'ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ' ከሚለው ጉልህን አውጥቶ ሙሉ በሙሉ ጉዳት ያለማድረስ የሚለው መርህ በየትኛውም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም፣ መርሆች ላይም ቢሆን የለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህንን ሀሳብ የሚጋሩት ሀይድሮ ዲፕሎማሲ አማካሪው ፈቅአህመድም "ምንም ጉዳት አለማድረስ የሚል ዓለም አቀፍ ሕግ የለም። ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ጥንቃቄ ማድረግ ነው" ሲሉ ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል። ፈቅአህመድ፣ "አባይ የግብፅ የሕይወት መስመር" መሆኑን የሚገልጹት እንዲሁም ውሃ ላይ ያለ ጥቅምን "የማስጠበቅ ሕጋዊ መብት" የሚሉት አገላለጾች "የግብፅ ቋንቋዎች ናቸው" ይላሉ።

ይህ የቻይና አቋም ነባር ወይስ አዲስ?

ከተጠናቀቀ አንድ ዓመት ሊደፍን የተቃረበው ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአዲስ አበባ እና በካይሮ መካከል የውዝግብ እና የውጥረት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። የግድቡ ግንባታ እና ውሃ ሙሌት ቢጠናቀቅም፣ የውሃ አስተዳደሩ አሁንም በግብፅ ቅሬታ የሚነሳበት ጉዳይ ነው።

የግድቡ ውሃ እየተዳደረ ያለበት መንገድ ሱዳን ላይ "ተጽዕኖ እንደሚያሳድር" የምትናገረው ግብፅ፣ የተራዘመ ድርቅ በሚከሰትበት ጊዜ የሚኖረውን የውሃ አለቃቀቅ በተመለከተ ስምምነት መፈጸም ትሻለች። የአባይ ውሃን በተመለከተ አሳሪ ስምምነት እንዲፈረምም በተደጋጋሚ ትወተውታለች።

እነዚህን ክሶች ውድቅ የምታደርገው ኢትዮጵያ በአንጻሩ፣ ከፍተኛውን የውሃ መጠን በምታዋጣበት አባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብት እንዳላት ትገልጻለች።

ለዓመታት በዘለቀው በዚህ የኢትዮጵያ እና የግብፅ ውዝግብ ውስጥ ቻይና "ገለልተኛ" የሚባል አቋም ይዛ መቆየቷን ሁለቱ የሃይድሮ ፖለቲክስ ባለሙያዎች ያስታውሳሉ። ፈቅአህመድ፣ የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ፀጥታው ምክር ቤት በተነሳበት ወቅት ቻይና ይዛ የነበረውን አቋም በማሳያነት ይጠቅሳሉ።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የግብፅ ፕሬዝዳንት አብድልፈታህ አልሲሲ

የፎቶው ባለመብት, Egyptian Presidency

በ2013 ዓ.ም. መጨረሻ ግድቡን በተመለከተ በፀጥታው ምክር ቤት በተካሄደው ስብሰባ ወቅት ቻይና የአፍሪካ ኅብረት ጉዳዩን እንዲፈታ ድጋፏን በመግለፅ ገለልተኛ አቋም ይዛ ታይታለች።

የቻይናው ተወካይ በወቅቱ በተመድ የቻይና ቋሚ ተወካይ የነበሩት ዣንግ ጁን አገራቸው "ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ያሏቸውን ሕጋዊ ስጋቶች ሙሉ በሙሉ እንደምትረዳ" ተናግረው ነበር።

አክለውም፤ "ቻይና በጋራ ጥረት አማካኝነት የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ፣ የጋራ መተማመንን እና ሁሉን አሸናፊ የሚያደርግ ትብብርን የሚያጎለብት የሦስትዮሽ የልማት ፕሮጀክት ሊሆን ይችላል ብላ ታምናለች" ብለው ነበር።

የወቅቱ የቻይና የፀጥታው ምክር ቤት ንግግር በ2015 ዓ.ም. ሦስቱ አገራት በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ ለተፈራረሙት የመርሆዎች መግለጫ ጭምር አድናቆትን ያቀረበ ነበር።

በዚህ ሳምንቱ የቻይና እና የግብፅ የጋራ መግለጫ ላይ የታየው አገላለጽ ግን በአንጻሩ፣ "የመርህ ስምምነቱ ላይ የተቀመጡ ቃላቶች እና መርሆችን እንደማይከተል" ኢንጂነር ጌዲዮን ይናገራሉ።

ይህ "የአቋም ለውጥ" ለኢትዮጵያ ምን ማለት ነው?

እንደ ፈቅአህመድ ገለጻ እነዚህ አቋሞች በቻይና ዘንድም መታየታቸው "ወደ ግብፅ አዘንብላ ሊሆን እንደሚችል" ያመለክታል። "ቻይና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ትፈልጋለች። ይህንን ግንኙነት ደግሞ 'ግብፅ ታሳልጥልኛለች' የሚል እምነት ሊኖራት ይችላል" በማለት መላ ምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ቻይና በታይዋን ጉዳይ ላይ ድጋፍ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት አካል ሊሆን እንደሚችልም ያነሳሉ። ግብፅ፣ ከ70 ዓመት በፊት ለኮሚዩኒስት ቻይና ዕውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ አረብ አገር በመሆኗ ለከፈለችው ዋጋ "ውለታ እንደመክፈል" የመሆን ዕድል እንዳለውም ጠቅሰዋል።

የሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪው ኢንጂነር ጌዲዮን፣ ይህ ዓይነቱ ወደ ግብፅ "ያጋደለ" መግለጫ ለኢትዮጵያ "አዲስ ነገር አይደለም" ይላሉ። "በሌሎችም አገራት መግለጫዎች፣ ደብዳቤዎች ካለፈውም እንዳየነው ትንሽ ያጋደሉ ነገሮች፣ ወደ ግብፅ ያጋደሉ ነገሮች ተመልክተናል፣ ታዝበናል" ይላሉ።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በአባይ ጉዳይ ላይ ያንጸባረቀውን አቋምም በማሳያነት ይጠቅሳሉ። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጥር ላይ ለግብፁ ፕሬዝዳንት አብድልፈታህ አልሲሲ በጻፉት ደብዳቤ "የትኛውም አገር የናይልን ውድ ሃብት በተናጠል መቆጣጠር እና በሂደቱ ጎረቤቶቹን መበደል የለበትም" ብለው ነበር።

"የናይል ወንዝ ለግብፅ እና ለሕዝቧ ያለውን ጥቅም እንደሚረዱም" ጠቅሰው፣ በውሃው ምክንያት ካይሮ ከአዲስ ጋር የገባችበትን ውዝግብ ለማሸማገል አገራቸው ዝግጁ መሆኗን አስታውቀው ነበር።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali

የአሁኑን የቻይና መግለጫ የሚጠቅሱት ኢንጂነር ጌዲዮን፣ "በዓለም አቀፍ ደረጃ ትላልቅ አገራት የሚወስዱት አቋም ተጽዕኖ ይኖረዋል። በአባይ ወንዝ ተካፋይ አገሮች መካከል በሚደረገው የስምምነት ጥረት ውስጥ ተጽዕኖ አይኖረውም ማለት አይቻልም" ብለዋል።

ይህም ቢሆን ግን "ቻይናም ሆነች አሜሪካም፣ ሌሎችም ትልልቅ አገራት ከአገራችን ጋር ያላቸው ግንኙነትም በቀላሉ የሚታይ አይደለም" ሲሉ በሂደት "ነገሮች እየተስተካከሉ እንደሚሄዱ" እምነታቸውን ገልጸዋል።

የሃይድሮ ፖለቲክስ አማካሪው ፈቅአህመድም በተመሳሳይ፣ "በፊት የአውሮፓ ኅብረትም ገለልተኛ ነበር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ወደ ግብፅ የሚያደላ አንዳንድ መግለጫዎችን ሲያወጣ ታይቷል" ይላሉ።

"እነዚህ አገራት ሀብታም ናቸው፣ ኃያል አገራት ናቸው። በዲፕሎማሲ፣ በዓለም አቀፍ ፖለቲካም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉ ናቸው። የተወሰነ ጫና መፍጠር ይችሉ ይሆናል" በማለት አብራርተዋል።

ነገር ግን ፈቅአህመድም ቻይና የናይል ተፋሰስ አገር ባለመሆኗ "ተዘዋዋሪ ጫና መፍጠር ትችል ይሆናል እንጂ ወሳኝ አካል አይደለችም" የሚል ምልከታ አላቸው። በዚህም ምክንያት "ውሃውን በመጠቀም ረገድ ተጽእኖ ይኖረዋል ግን፤ ወሳኝ ተጽእኖ አይኖረውም" ይላሉ።

"የዲፕሎማሲ ሥራ ጠንክሮ" የሚከናወን ከሆነ ኢትዮጵያ ካላት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና የሕዝብ ብዛት አንጻር "ተፈላጊ" እንደሆነችም ያነሳሉ።

"ቻይናም ሆነች አሜሪካ እንዲሁም አውሮፓ ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች። ምናልባትም በዚህ በምሥራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ተጽእኖ ማሳደር የምትችል አገር ነች" ብለዋል።