በአልጄሪያ በእሳት አደጋ ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ቃጠሎ የሚያስነሱ ግለሰቦች በሞት እንዲቀጡ አዘዙ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
በአልጄሪያ ቢያንስ የ12 ሰዎችን የገደለ የደን እሳት መነሳቱን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አብደልማጅድ ተቡን ቃጠሎ የሚያስነሱ ሰዎች ላይ ይጣል የነበረው የሞት ቅጣት ዳግም ተግባራዊ እንዲሆን እንደሚፈልጉ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ፣ እሳት የሚያስነሱ ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት እንዲጣል የሚያደርግ ድንጋጌ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ውስጥ እንዲካተት ለአገሪቱ ፍትሕ ሚኒስቴር ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
የአልጄሪያ የወንጀል ሕግ በተወሰኑ ጥፋቶች ላይ የሞት ቅጣት እንደሚጣል ቢደነግግም፣ ከአውሮፓውያኑ 1993 ወዲህ ይህ ዓይነቱ ቅጣት ተፈጻሚ ሆኖ አያውቅም።
በቅርብ ቀናት ውስጥ በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ ክፍል ከ100 በላይ የደን እሳት ቃጠሎ ክስተቶች ተመዝግበዋል። አብዛኞቹ የእሳት አደጋዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ፕሬዝዳንት ተቡን እሳት እየተነሳ ያለው ሆነ ተብሎ የመሆን ዕድል እንዳለ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።
አልጄሪያው መሪ በተለይ ከእሳት አደጋዎቹ ከፍተኛነት አንጻር ጉዳዩ ላይ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ፣ ደን ባለባቸው አከባቢዎች ሆነ ብሎ እሳት በማስነሳት ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሰው ላይ የሞት ፍርድ የሚጥል የሕግ ማሻሻያ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ እንዲደረግ እሁድ ዕለት የጊዜ ገደብ አስቀምጠዋል።
አሁን ባለው ሕግ መሠረት፣ ሆነ ብሎ የደን ቃጠሎ ማስነሳት እስከ 30 ዓመት በሚደርስ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ ፍርዱ እስከ የዕድሜ ልክ ከፍ ይላል።
ባለፈው ሳምንት የተነሳው የሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ የእሳት አደጋ፣ መጠነ ሰፊ ውድመት አድርሷል። በርካቶች ጉዳት እንዲደርስባቸው እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉም ምክንያት ሆኗል።
ቃጠሎዎቹ የተነሱት፣ በተለይ በአልጄሪያ እና በቱኒዚያ ጉዳት ያደረሰ ከፍተኛ ሙቀት ሰሜን አፍሪካ ውስጥ በተከሰተበት ወቅት ነው።
የአልጄሪያ ባለሥልጣናት እሁድ ከሰዓት ጭምር የተወሰኑ የእሳት አደጋዎችን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነበር። ከዚህያ በፊት በነበሩት 24 ሰዓታት ውስጥ ከተከሰቱት 19 ቃጠሎዎች መካከል 18ቱ መጥፋታቸውን የአልጄሪያ ፕሬስ አገልግሎት ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ተቡን በእሳት አደጋው የተጎዱ ቤተሰቦች የካሳ ክፍያ እንዲሰጣቸው እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸው ቤቶች እንዲታደሱ እና ወሳኝ አገልግሎቶች እንዲጀምሩ አዝዘዋል።
በደን ቃጠሎው የደረሰውን ጉዳት እና ኪሳራ መጠንን ለማወቅ ምርመራ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
አልጄሪያ በበጋ ወራት ተደጋጋሚ የደን ቃጠሎ የሚያጋጥማት ቢሆንም፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ የተከሰቱ የእሳት አደጋዎች ክብደት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ተባብሷል።















