ትራምፕ የካናዳ ሰደድ እሳት በግዛቶቼ የአየር ብክለት አስከትሏል ሲሉ አዲስ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዛቱ

ማስክ አድርጋ የምትራመድ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Selcuk Acar/Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከፍተኛ በሆነው ሰደድ እሳት ምክንያት የተከሰተው ጭስ የኒው ዮርክ ከተማን በጭጋግ ሸፍኖታል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በካናዳ በተከሰቱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰደድ እሳቶች የተፈጠረው ጭስ ሰሜን አሜሪካን በመበከሉ በአገሪቷ ላይ አዲስ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዛቱ።

ትራምፕ ይህን ያሉት የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች በሰደድ እሳቱ ላይ ቅሬታ ካቀረቡ እና የኦንታሪዮ አስተዳዳሪ ዳግ ፎርድ አሜሪካ ቅሬታ ከማቅረብ ይልቅ ድጋፍ እንድትልክ ከጠየቁ በኋላ ነው።

ትራምፕ፣ በካናዳ "ግድ የለሽነት" ምክንያት "አሜሪካ በጭስ ፣ በብክለት እና ጤናማ ባልሆነ አየር ተወርራለች" ብለዋል።

እንደ 'ካናዳ ዋይልድላንድ ፋየር ኢንፎርሜሽን ሲስተም' መረጃ ከሆነ እስከ አርብ ዕለት ድረስ በካናዳ 888 ሰደድ እሳቶች የተከሰቱ ሲሆን አብዛኞቹ ከቁጥጥር ውጭ ሆነዋል።

ከ190 በላይ የሚሆኑት ሰደድ እሳቶች ኦንታሪዮን እየለበለቡ ነው፤ የተወሰኑትም ከቁጥጥር ወጥተዋል።

እንደ ተቋሙ ከሆነ ወደ 3 ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋ የካናዳ መሬት በሰደድ እሳቱ ወድሟል።

አደጋውን ተከትሎም ከሚኒሶታ እና ሚቺጋን እስከ ፔንሲልቫኒያ፣ ኦሃዮ እና ኒው ዮርክ ድረስ የአሜሪካ ግዛቶች በወፍራም ጭስ ተሸፍነዋል።

በአብዛኞቹ አካባቢዎችም ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን በርካታ ከቤት ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተሰርዘዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ተመራማሪዎች እንደሚሉት እየጨመሩ ለመጡት ከባድ ሰደድ እሳቶች ምክንያቱ ዋነኛው የአየር ንብረት ለውጥ ነው።

የአየር ንብረት ለውጡ ሞቃታማና ደረቅ ሁኔታዎችን ስለሚፈጥር ሰደድ እሳቶች በቀላሉ እንዲዛመቱ ያደርጋል ብለዋል። የተወሰኑ አደጋዎች በመብረቅ ምክንያት እንደሚፈጠሩም አስረድተዋል።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ የካናዳውን ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒን ጠርተው አገራቸው ስላሳየችው "ግድ የለሽነት" ማብራሪያ እንደሚጠይቁ ገልጸዋል።

ትራምፕ ጨምረውም "አገሪቷ ደኗን እና ቁጥቋጦዎቿን በተገቢው መንገድ እየጠበቀች አይደለም" ሲሉም ከሰዋል።

የኦንታሪዮ አስተዳዳሪ ፎርድ ግን እሳቱን በአግባቡ አልተቆጣጠረም በሚል የተሰነዘረውን ትችት ውድቅ አድርገውታል።

ከ150 በላይ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እንዲሁም ከ80 በላይ የውሃ አርከፍካፊ አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች እሳቱን በመዋጋት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

መንግሥታቸው ከ2018 ጀምሮ ለሚከሰተው ሰደድ እሳት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንዳደረገ እና እንደ አስፈላጊነቱም በየዓመቱ ለእሳት አደጋ መከላከያ ከሚመደበው በጀት በላይ እንደሚያወጣ አክለዋል።

ካርኒም ቀደም ብለው የአየር ንብረት ለውጥን መዋጋት የሁለቱም አገራት ኃላፊነት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከትራምፕ አስተያየት በኋላም የካርኒ የድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ካቢኔ ሚኒስትር ሁለቱ አገራት እየተነጋገሩ እንደሆነ ገልጸው፣ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ አብሮ የመሥራት ታሪክ እንዳላቸው አስታውሰዋል።

ለዚህም በአውሮፓውያኑ 1982 የእሳት አደጋ መዋጋት ስምምነት መፈራረማቸውን እና በ2025ም በቡድን ሰባት ጉባኤ ላይ ሌላ የመደጋገፍ ስምምነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ሪፐብሊካኖች የሰደድ እሳቱን ጉዳይ ትራምፕ ካናዳን 51ኛ ግዛት ለማድረግ ያቀረቡትን ሃሳብ እንደገና ለማንሳት ተጠቅመውበታል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ካናዳን 51ኛ ግዛታቸው አድርገው እንደሚጠቀልሉ መናገራቸው ካናዳውያንን ክፉኛ ያስቆጣ ሲሆን በርካቶችም ወደ አገሪቷ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲያቆሙ አድርጓል።

ሌሎች ደግሞ ኦንታሪዮን እና ሚቺጋንን የሚያገናኘው እና በካናዳ የገንዘብ ድጋፍ የሚገነባው ጎርዲ ሆዌ ዓለም አቀፍ ድልድይ መከፈቱን እንዳዘገየው ይናገራሉ።

ባለፈው ዓመት ትራምፕ ለአስርተ ዓመታት ከአሜሪካ ጋር ከቀረጥ ነፃ የንግድ ትስስር በነበራት ካናዳ ላይ የንግድ ታሪፍ ከጣሉ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት የነገሰበት ሆኖ ቆይቷል።

አገራቱ በዚህ ላይ ሲደራደሩ ቢቆዩም እስካሁን ሥምምነት ላይ አልደረሱም።