ቀጥታ, አሜሪካ ስለ ኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዦች መረጃ ለሚሰጣት 10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አቀረበች

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሕይወት ያሉ እና የሞቱ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አዛዦችን በተመለከተ መረጃ ለሚሰጡ ግለሰቦች ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥ አስታወቀ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. “የኢራን መንግሥት ለጦር ሠራዊቱ ደመወዝ መክፈል አልቻለም” ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራን መንግሥት ለአብዛኛው የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ወርሃዊ ደመወዝ መክፈል የማይችል ነው በማለት አስተዳደሩ መዳከሙን አመለከቱ።

    ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ “የከሰረው የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ለአብዛኛው ወታደሮቹ መክፈል ያልቻለ ሆኖ ሳለ ሕዝቡ እየተቃወመ ባልሆነበት ጊዜ እንኳን በከፍተኛ ሁኔታ ዜጎቹን እየገደለ ነው” ሲሉ ከስሰዋል።

    ትራምፕ የኢራን መንግሥት ተቃዋሚዎቹ ላይ የሚፈጽመውን ግድያ “ሰብዓዊ ቀውስ” በማለት ትሩዝ በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

    ኢራን ውስጥ በተቃዋሚዎች ላይ ይፈጸማል ያሉትን ግድያ “ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ስለሆነ አሁኑኑ መቆም ይገባዋል” ብለዋል።

    ከኢራን ጋር ለወራት በተካሄደው ጦርነት ያለመውን ማሳካት ያልቻለው የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ግዙፍ የምጣኔ ሀብት ዕቀባ ዘመቻ በኢራን ላይ መጀመሩን ያስታወቀ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱም “ኢራን ሙሉ ለሙሉ ተፍረክርካለች” ብለዋል።

  2. በኤአይ የተሰሩ ሙዚቃዎች በአውስትራሊያ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ውስጥ እንዳይካተቱ ታገደ

    የሙዚቃ ሰንጠረዥ ሎጎ

    የፎቶው ባለመብት, ARIA

    የምስሉ መግለጫ, ሙዚቃዎች በአውስትራሊያ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ለመካተት "በአብዛኛው በሰው የተሰሩ" መሆን አለባቸው

    ሙሉ በሙሉ ወይም በአብዛኛው በኤአይ የተሰሩ ሙዚቃዎች በአውስትራሊያ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ውስጥ እንዳይካተቱ ታገደ።

    በመሆኑም ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በሙዚቃ ሰንጠረዡ ውስጥ የሚካተቱ ሁሉም ሙዚቃዎች “በአብዛኛው በሰው አቅም የተሰሩ” መሆን ይኖርባቸዋል።

    የአውስትራሊያ የሙዚቃ ማኅበር አዲሱ ደንብ “የሰውን ተፈጥሯዊ ጥበብ ለማሳደግ ይረዳል።” ብሏል።

    ደንቡ የወጣው አውስትራሊያዊው ዲጄ ጆሽ ፋዋዝ፣ የማዶናን ‘ላይክ ኤ ፕሬየር’ የተባለውን ሙዚቃ በኤአይ በድጋሚ ከሰራው በኋላ ውዝግብ መፈጠሩን ተከትሎ ነው።

    የሙዚቃ ሥራው በአገሪቷ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ላይ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር። በራዲዮ ጣቢያዎች ላይም በተደጋጋሚ ሲጫዎት የነበረ ሲሆን በስፖቲፋይ ብቻ ከ48 ሚሊዮን በላይ ጊዜ ተደምጧል።

    ፋዋዝ ከውዝግቡ በኋላ ለኤአይ ክሬዲት ሰጥቷል።

    ሆኖም የሙዚቃ ማኅበሩ “ አውስትራሊያውያን ሙዚቀኞች ትኩረት ለማግኘት በታሪክ በጣም በተጨናነቀው ገበያ ውድድር ላይ ናቸው" በማለት "የሰው ጥበብ ያልታየባቸው በኤአይ የተፈበረኩ ሙዚቃዎችን ስኬት ማስተዋወቅም ሆነ በውጤታቸው መደሰት እንደማይፈልግ” ገልጿል።

    በአዲሱ ደንብ መሠረት ሙዚቃ ለመስራት በኤአይ መደገፍ የሚቻል ቢሆንም ግጥሙ በሰዎች የተጻፈ፣ በድምጻቸው እና በትክክለኛ የሙዚቃ መሣሪያዎች የተሰሩ መሆን አለባቸው።

    አውስትራሊያ እንዲህ ዓይነት እርምጃ የወሰደች የመጀመሪያዋ አገር አይደለችም።

    በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አንድ በኤአይ የተሰራ ሙዚቃ ከስዊድን የሙዚቃ ሰንጠረዥ ላይ እንዲወርድ ተደርጓል።

    ሐምሌ ወር ላይ ደግሞ ዓለም አቀፉ የሙዚቃ ፌደሬሽን፣ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ውስጥ ለመካተት በላቲን አሜሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ ፣ አፍሪካ እና ደቡብ ምሥራቅ እስያ የኤአይ መመሪያዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ አስታውቋል።

    በፌደሬሽኑ መመሪያ መሠረት የተሻሻለው ደንብ የሥርጭት እና የደረጃ ሰንጠረዦችን ሚዛን የማዛባት ስጋት የሚፈጥሩ ሙዚቃዎች መካተት እንደሌለባቸው ይገልጻል።

  3. የዩኬ የድሮን ፋብሪካዎች ‘በማይታወቁ አካላት’ ጥቃት ሊፈፀምባቸው እንደሚችል የቀድሞ የሩሲያ ሚኒስትር ተናገሩ

    ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም እና የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ

    የፎቶው ባለመብት, WPA Pool via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር በርንሃም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በዩክሬን የመጀመሪያውን የውጭ አገር ጉብኝታቸውን አድርገዋል

    ዩናይትድ ኪንግደም ብሪታኒያ ሰራሽ ሚሳዔል ንድፎችን ለዩክሬን ለመስጠት ቃል በመግባቷ በድሮን ማምረቻ ፋብሪካዎቿ ላይ “ በማይታወቁ አካላት” “በከፊል ወታደራዊ” የሆነ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚችል የቀድሞው የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ።

    አንድሬይ ፌዶሮቭ ለቢቢሲ ኒውስናይት ይህን ያሉት ዩክሬን በአገር ውስጥ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ የጦር መሣሪያ እንድታመርት ያስችላታል የተባለውን ብሪታኒያ ሰራሽ የሚሳዔል ንድፍ ለመስጠት መስማማቷን ዩኬ ካስታወቀች በኋላ ነው።

    በሩሲያ ቴሌቪዥን አስተያየታቸውን በመስጠት የሚታወቁት የክሬሚሊን ደጋፊ ፌዶሮቭ፣ ፕሬዚደንት ፑቲን በዩኬ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

    ጫናው “ከጋዜጠኞች፣ ከሚዲያዎች እና ከሕዝብ አስተያየት” የመጣ እንደሆነም የቀድሞ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

    "ከፊል ወታደራዊ ምላሽ" ምን ማለት እንደሆነም የተጠየቁት ፌዶሮቭ “ ለዩክሬን ድሮን በሚያመርቱ ተቋማት፣ በፋብሪካዎች” ላይ የሚፈፀም እንደሆነ አስረድተዋል።

    እነዚህ ተቋማት ሊጠቁ የሚችሉትም በሩሲያ ሳይሆን በሌሎች “ባልታወቁ አካላት” እንደሆነም ገልጸዋል። የቀድሞ ሚኒስትሩ የሰጡት አስተያየት የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሰኞ ዕለት ከተናገሩት ጋር የሚገናኝ ነው።

    ፔስኮቭ ዩኬ ለዩክሬን ሚሳኤል ለመስጠት መወሰኗ “ሰላም ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ሒደት የሚያደናቅፍ ነው” ሲሉ ከስሰዋል።

    ጨምረውም የሩሲያ ጦር የሚሳኤል ማምረቻዎችን ለማውድም መገኛቸውን ለመለየት መረጃ እየሰበሰበ እንደሆነ ተናግረዋል።

    የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም በበኩላቸው “እሳቱን ማነው የጀመረው? ጥያቄው ይህ ነው። አይደለም እንዴ?” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    በርንሃም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሰኞ ዕለት በዩክሬን የመጀመሪያውን የውጭ አገር ጉብኝታቸውን አድርገዋል። በዚህ ጉብኝታቸውም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የተጠናከረውን የሩሲያ ጥቃት ምክንያት በማድረግ አገራቸው ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ አረጋግጠዋል።

  4. አሜሪካ በኢራን ላይ ማዕቀብ ብትጥልም ቻይና ጥቅሟን እንደምታስከብር አስታወቀች

    የኢራን እና የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን እና የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች

    ቻይና ያላትን የምጣኔ ሀብት ጥቅሞችን አሜሪካ በኢራን ላይ ከጀመረችው የኢኮኖሚ ዘመቻ እንደምትከላከል አስታወቀች።

    አሜሪካ ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ባላቸው ተቋማት፣ ባንኮች እና አገራት ላይ ማዕቀቦችን በመጣል እንደምትቀጣ ማስታወቋን ተከትሎ ነው ቻይና አቋማን የገለጸችው።

    "ቻይና የአንድ ወገን እና ሕገወጥ ማዕቀቦችን እንደምትቃወም በተደጋጋሚ አስታውቃለች. . . ስለዚህም ቻይና እየተካሄደ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለች ጥቅሟን እና መብቷን ለማስከበር አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ትወስዳለች” ሲሉ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ ሊን ጂያን ጨምረውም ቻይና ከኢራን ጋር ያላት ትብብር በዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ ሥር የሚካሄድ በመሆኑ ጣልቃ ገብነትን ፈጽሞ እንደማትቀበለው ገልጸዋል።

    ቻይና ከአሜሪካ ጋር ለወራት በዘለቀ ጦርነት እና በአስርት ዓመታት ፍጥጫ ውስጥ የምትኘው ኢራን ትልቋ የንግድ አጋር ናት።

    የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት “እስካሁን ከታዩት የከፋ” ያሉትን ምጣኔ ሀብታዊ ጫና በኢራን ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የያዙትን ዕቅድ ሰኞ ዕለት ይፋ አድርገዋል።

    ከዚህም ጋር ተያይዞ የኢራንን የነዳጅ ምርቶች ትልቋ ገዢ የሆነችው ቻይና እንዲሁም ባንኮቿ እና ተቋማቷ ከኢራን ጋር ባላቸው የንግድ ግንኙነት የተነሳ በአሜሪካ ማዕቀብ ሊጣልባቸው ይችላል።

    የአሜሪካው ባለሥልጣን የአሜሪካንን ማስጠንቀቂያ በመጣስ ከኢራን ጋር የንግድ እና የገንዘብ ልውውጥ የሚያደርጉ ወገኖች ከዶላር ግብይት ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ ምጣኔ ሀብታዊ መነጠል እንደሚገጥማቸው አስጠንቅቀዋል።

  5. ኢራን ለአሜሪካ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ “ሙሉ በሙሉ ዝግጁ” መሆኗን አስታወቀች

    በቴህራን መንገድ ላይ የሚራመዱ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

    አሜሪካ በኢራን ላይ “ኢኮኖሚክ ዲ-ዴይ” ስትል የጠራቸውን እርምጃ መውሰድ እንደጀመረች ካስታወቀች በኋላ፣ ኢራን ይህን ሰፊ ማዕቀብ ለመመከት የሚያስችል የሁለት ዓመት ዕቅድ ማዘጋጀቷን ገለጸች።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሰንት [የገንዘብ ሚኒስትር] ትናንት በሰጡት መግለጫ፣ “እስካሁን ከተወሰዱት ትልቁ የሆነው የፋይናንስ ጥቃት” ኢራን ላይ እንደሚተገበር ተናግረው ነበር።

    ለዚህ እርምጃ ምላሽ የሰጡት የኢራን የኢኮኖሚ ሚኒስትር አሊ ማዳኒዛዴህ፣ ቴህራን “ለአሜሪካ ማዕቀቦች ሙሉ በሙሉ ዝግጁ” መሆኗን ተናግረዋል። እርምጃው አሜሪካ ላይ ሌላ ሽንፈት እንደሚያመጣም አክለዋል።

    አዲሱን የአሜሪካ እርምጃ ይፋ ያደረጉት ግምጃ ቤት ኃላፊው ቤሰንት፣ ከኢራን ጋር የፋይናንስ ግንኙነት የሚያደርግ የትኛውም አገር እንደሚገለል ተናግረዋል። ከኢራን ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉ ባንኮች እና ተቋማትም ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ ፈቃደኛ ካልሆኑ መገለል እንደሚደርስባቸው ገልጸዋል።

    የግምጃ ቤት ኃላፊው ይህ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እርምጃ ኢራን ላይ “ገመዱን የሚያጠብቅ እንዲሁም በሁሉም የገቢ ምንጭ የሚያግድ” እንደሆነ ተናግረዋል።

    ኢራኑ የኢኮኖሚ ሚኒስትር አሊ ማዳኒዛዴህ ግን “መንግሥት ዝግጁ ነበር፣ ነውም። እነዚህን ክስተቶች ለማስተናገድም የሁለት ዓመት ዕቅድ አለው” ሲሉ ለአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል። ኢራን “እነዚህን ዕቅዶች [ለመተግበር] ለረጅም ጊዜ ስትጠብቅ እንደነበረም” አክለዋል።

    “እኛም የራሳችን መሣሪያዎች አሉን፤ ጨዋታውን እንዴት እንደምንጫወት እናውቃለን” ብለዋል።

    አሜሪካ ኢኮኖሚያዊ እርምጃ የሚመሠረተው በኢራን የንግድ አጋሮች ላይ በመሆኑ፣ ውጤታማ የመሆኑ ጉዳይ ጥያቄ እንደሚነሳበት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

    የኢራን ከፍተኛ ነዳጅ ገዢ የሆነችው ቻይና ከዚህ ቀደም አሜሪካ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች ችላ በማለት ከቴህራን ጋር የንግድ ግንኙነቷን ቀጥላ ነበር።

    በሌላ በኩል ሌላኛዋ የኢራን አጋር የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምረቶች ከአገሪቱ ጋር ያላትን ሁሉንም የፋይናንስ ግንኙነት እንደምታቋርጥ ባለፈው ሳምንት አስታውቃለች።

    አሜሪካ እርምጃዋን ይፋ ካደረገች ከሰዓታት በኋላ ኢራን ከሌሎች አገራት ጋር የንግድ ግንኙነት ይቀጥላል የሚል መተማመን እንዳላት ገልጻለች።

    የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ ማዳኒዛዴህም ቻይናም ሆነች ሩሲያ የአሜሪካን እርምጃ እንደማይቀበሉ እንዲሁም ሌሎች አገራትም ይቃመዋሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

    ቻይና “ሕገ ወጥ የተናጠል ማዕቀብ” ስትል የጠራችውን የአሜሪካን እርምጃ በጽኑ ተቃውማለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ ሊን ጂያንግ፣ ኢኮኖሚያዊ ታክቲኮች ችግሮችን እንደማይፈቱ እና ቤይጂንግ የራሷን ፍላጎት እንደምታስጠብቅ አስታውቀዋል።

  6. አሜሪካ በኢራን ላይ ያጠናከረችው ማዕቀብ የትኞቹ ዘርፎች ላይ ያተኩራል?

    ስኮት ቤሴንት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, በኢራን ላይ የሚጣለውን ማዕቀብ ይፋ ያደረጉት የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት

    ለወራት ከኢራን ጋር ጦርነት ውስጥ የቆየችው አሜሪካ ከወታደራዊ እርምጃዎቿ በተጨማሪ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ ዘመቻ መጀመሯን አስታውቃለች። የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት የኢራን መንግሥትን ለማሽመድመድ አሜሪካ ሁሉንም የገንዘብ ምንጮቹን ትዘጋለች ብለዋል።

    በዚህም በኢራን የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ፣ የበይነ መረብ ሀብት፣ ወርቅ፣ ቴክኖሎጂ እና የመርከብ ዘርፍ ላይ እንዲሁም 60 በሚደርሱ ግለሰቦች እና ተቋማቷ ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል አሜሪካ ገልጻለች።

    ጫናው ኢራን ላይ ብቻ ያነጣጠረ አይደለም። ከአገሪቱ ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው አገራት እና ተቋማት ላይ ሁለተኛ ደረጃ ማዕቀብ ይጣላል። ለኢራን የንግድ ልውውጥ የሚውሉ መርከቦች የሚገኙባቸው አገራት ጭምር ለቅጣት ይዳረጋሉ።

    ኢራን የነዳጅ ምርቷን እና “ወሳኝ የጦር መሳሪያ ክፍሎችን” የምታጓጉዝበት መንግሥታዊው የመርከብ ትራንስፖርት የዕቀባ ዒላማ ከሆኑት መካከል ነው።

    በተጨማሪም አሜሪካ ለኢራን የጦር መሳሪያ ግንባታ ፕሮግራም ግብዓት የሚሆኑ ቁሶችን ለማግኘት ያስችላታል ባለቻቸው የቴክኖሎጂ ምርቶች አቅርቦት ላይ ዕቀባ ይጣላል።

    የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር በኢራን የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ማዕቀብ የሚጣለው የጦር መሣሪያዎችን፣ ወታደሮችን እና የገንዘብ ድጋፎችን በተለያዩ አገራት ለሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ያቀርባል በሚል ክስ ነው።

    ከወታደራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ዕቀባዎች በተጨማሪ አሜሪካ ከኢራን ጋር በተያያዘ የትምህርት እና የሥልጠና ልውውጦች፣ የግል ገንዘብ ዝውውሮችን ማድረግን እንዲሁም በተወሰኑ የስፖርት ውድድሮች መሳተፍን ጭምር እንደምትከለክል አስታውቃለች።

  7. አሜሪካ በኢራን የምታካሂደው ጦርነት ያለው ድጋፍ መቀነሱን የሕዝብ አስተያየት አሳየ

    የአሜሪካ ወታደራዊ ሄሊኮፕተሮች

    የፎቶው ባለመብት, @CENTCOM

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሕዝብ ዘንድ ያላቸው "ተቀባይነት ባሽቆለቆለበት" በዚህ ጊዜ አሜሪካ በኢራን ላይ ለምታካሂደው ጦርነት የሚሰጠው የሕዝብ ድጋፍ መቀነሱን የሕዝብ አስተያየት መለኪያ አመለከተ።

    ባለፈው የካቲት ወር የጀመረው የኢራን ጦርነት የነበረው የሕዝብ ድጋፍ መቀነሱን ያመለከተው የሕዝብ አስተያየት መለኪያ ውጤት እንደሚያሳየው፣ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ፓርቲ ሪፐብሊካን አባላትም ለጦርነቱ የሚሰጡት ድጋፍ ቀዝቅዟል።

    መጋቢት ላይ አሜሪካ በኢራን ላይ እየወሰደችው ላለችው ወታደራዊ እርምጃ ድጋፍ የሚሰጡ አሜሪካውያን ብዛት 37 በመቶ ነበር። ይህ የድጋፍ መጠን በነሐሴ መጀመሪያ ወደ 34 በመቶ ወረደ ሲሆን አሁን ደግሞ በድጋሚ ቀንሶ 31 በመቶ መድረሱን መረጃው አመልክቷል።

    በተጨማሪም በመጋቢት መጀመሪያ 77 በመቶ የነበረው ለጦርነቱ አዎንታዊ ምልከታ ያላቸው የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች ብዛት ወደ 69 በመቶ ወርዷል።

    ለወራት የዘለቀው የኢራን ጦርነት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ድጋፍ ላይ ተጽእኖ በማሳደር ተቀባይነታቸውን እየሸረሸረው መሆኑን የሕዝብ አስተያየት መለኪያው አሳይቷል።

    ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ በሮይተርስ/አይፒኤስኦኤስ በተሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት የተሳተፉ 33 በመቶ መላሾች፣ ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት እያከናወኑት ያለውን ተግባር ደግፈዋል። ይህም በፕሬዝዳንቱ ሁለተኛው ዙር የሥልጣን ዘመን የተመዘገበ እጅግ ዝቅተኛው ተቀባይነት ምጣኔ ነው።

  8. አሜሪካ ስለ ኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዦች መረጃ ለሚሰጣት 10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አቀረበች

    አህመድ ቫሂድ

    የፎቶው ባለመብት, FARS

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አዛዥ አህመድ ቫሂድን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናት በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሕይወት ያሉ እና የሞቱ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አዛዦችን በተመለከተ መረጃ ለሚሰጡ ግለሰቦች ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥ አስታወቀ።

    ከኢራን ጋር ለወራት በዘለቀ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው አሜሪካ በተለይ አራት የአብዮታዊ ዘቡ አዛዦችን በተመለከተ ጥቆማ ለሚሰጡ እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት እንደምትሰጥ አስታውቃለች።

    በተለይ ትኩረት የተደረገባቸው የአብዮታዊ ዘቡ አባላት አሜሪካንን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን በመምራታቸው መሆናቸውን በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ስር የሚገኘው ጉዳዩን የሚከታተል ክፍል በኤክስ ገጹ አመልክቷል።

    “እነዚህ ግለሰቦች የአሜሪካ ወታደሮችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ እና ወሳኝ የአሜሪካ መሠረተ ልማቶች ላይ የበይነ መረብ ጥቃት እንዲያደርሱ የአብዮታዊ ዘቡን ክፍሎች መርተዋል እንዲሁም አዝዘዋል” ሲል ከሷቸዋል።

    በዚህም በተለይ ትኩረት የተደረገባቸው የአብዮታዊ ዘቡ አዛዥ አህመድ ቫሂዲ፣ የኢራን ጦር ኃይሎች ዕዝ የሆነው ኻታም አል አንቢያ አዛዥ አሊ አብዶላሂ፣ የአብዮታዊ ዘቡ የበይነ መረብ ክፍል አዛዥ ሃሚድሬዛ ላሽጋሪያን ይፈለጋሉ ከተባሉት የኢራን ባለሥልጣናት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።

    በተጨማሪም በዝርዝሩ ውስጥ የቀድሞው የአብዮታዊ ዘቡ የአየር ምድብ አዛዥ ሳኢድ አግጃኒ እና የቀድሞው የዘቡ የመረጃ ክፍል አዛዥ ማጂድ ኻዴሚ ይገኙበታል። እነዚህ ሁለት የአብዮታዊ ዘቡ የቀድሞ ከፍተኛ አዛዦች በቅርቡ ተካሄደው ጦርነት ወቅት በተፈጸሙ ጥቃቶች ተገድለዋል።

  9. ከጋዛ የተነሱ ካይቶች መገኘታቸውን ተከትሎ እስራኤል “ኃይል የተሞላበት” እርምጃ እንደምትወስድ አስጠነቀቀች

    ፍልስጤማዊ ሕጻን እሁድ ዕለት ጋዛ ከተማ የተፈናቃይ ካምፕ ውስጥ ካይት ይዞ ፎቶ ተነስቷል

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፍልስጤማዊ ሕጻን እሁድ ዕለት ጋዛ ከተማ የተፈናቃይ ካምፕ ውስጥ ካይት ይዞ ፎቶ ተነስቷል

    እስራኤል፣ ሐማስ ከጋዛ ግዛት በኩል ካይት፣ ድሮን እና ፊኛዎችን ሊልክ ይችላል በሚል ጋዛ ውስጥ የምትፈጽመውን ጥቃት እንደምታጠናክር አስጠነቀቀች።

    ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጋዛ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ የእስራኤል መንደር ውስጥ ፈንጂ ያልያዙ በራሪ ካይቶች መገኘታቸውን የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ ዛሬ ሰኞ በሰጡት መግለጫ "ይህንን ክስተት ለማስቆም ኃይል የተሞላባቸው እርምጃዎች ይወሰዳሉ” ብለዋል።

    የጋዛ ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ ፈንጂ የጫኑ ፊኛዎች (ባሉን) ወደ እስራኤል ተልከው ነበር። ፈንጂው ጫካ እና እርሻ ውስጥ እሳት አስነስቷል።

    ሐማስ አሁን ወደ እስራኤል ገብተዋል የተባሉት ካይቶች የእርሱ አለመሆናቸውን በመግለጽ አስተባብሏል። በጋዛ “ፍርስራሾች ውስጥ ንጹህ ልጅነታቸውን የሚፈልጉ ሕፃናት” የሚጫወቱቸባው እንደሆኑም ጠቅሷል።

    በተጨማሪም ቡድኑ እስራኤል ባለፈው ጥቅምት ላይ የተፈረመውን ተኩስ አቁም በመጣስ የምትፈጽመውን የአየር ጥቃት ለመቀጠል የእነዚህ ካይቶች ጉዳይ “በምክንያትነት” እየተጠቀመች ነው ሲል ከስሷል።

    ባለፈው ሳምንት አርብ እና ቅዳሜ ላይ ከጋዛ ድንበር 800 ሜትር ርቀት ላይ ባለው ‘ኪቡዝ ናሃል ኦዝ’ የተባለ መንደር ውስጥ አራት ካይቶች ተገኝተዋል። ከዚያ በፊትም በደቡባዊ እስራኤል ሌሎች ስፍራዎችም ተጨማሪ ካይቶች መገኘታቸውን የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    መገናኛ ብዙኃኑ የጠቀሷቸው ወታደራዊ ምንጮች፣ ወደ እስራኤል ከገቡት ካይቶች ጀርባ የሐማስ እጅ እንዳለ እና በራሪዎቹን የላከውም እስራኤል ምን ዓይነት ምላሽ እንደምትሰጥ ለመፈተን እንደሆነ ያምናሉ።

    እነዚህ ካይቶች ላይ ግን ምንም አጠራጣሪ ቁስ አለመገኘቱን እና ስጋት እንደማይጋርጡ ወታደራዊ ምንጮቹ ገልጸዋል።

    ይሁንና የመከላከያ ሚኒስትሩ ኢዝራኤል ካትዝ፣ “ምንም ትዕግስት” እንደማይኖር ተናግረዋል። “ባሉን የሚታየው እንደ ካይት ነው፤ ካይት ደግሞ እንደ ድሮን፤ ፈንጂ ኖረውም አልኖረውም” ብለዋል።

    ሐማስ በበኩሉ ከእስራኤል በኩል የሚሰማው “ውንጀላ እና ዛቻ አደገኛ” እንደሆነ አስጠንቅቋል። ካይቶቹ “ከተፈናቃይ ካምፕ የመጡ የሕጻናት መጫወቻ” እንደሆኑም ገልጿል።

  10. በናይጄሪያ ካናቢስ ሲሸጡ የነበሩ “የ101 ዓመት” አዛውንት በቁጥጥር ስር ዋሉ

    በቁጥጥር ስር የዋሉት አዛውንት

    የፎቶው ባለመብት, NDLEA

    የናይጄሪያ ባለሥልጣናት ዕድሜያቸው 101 ዓመት እንደሆኑ የገለጿቸውን አዛውንት ሴት፣ ካናቢስ በመሸጥ ወንጀል ጠርጥረው በቁጥጥር ስር ማዋላቸው መነጋገሪያ ሆነ።

    ቅመ አያት እንደሆኑ የተገለጹት ኤስተር ኦጉንማቦ ቅዳሜ ዕለት በናይጄሪያ ደቡብ ምዕራባዊ ክፍል በሚገኘው ኦጉን ግዛት እንደተያዙ የአገሪቱ የአደንዛዥ ዕፅ ቁጥጥር ተቋም አስታውቋል።

    የተቋሙ የመገናኛ ብዙኃን ዳይሬክተር ፌሚ ባባፌሚ እንደሚናገሩት፣ አዛውንቷ “ለአካባቢው ነዋሪዎች ሊሸጡት እንደነበር የገለጹት 90 ግራም የሚመዝኑ ትናንሽ የካናቢስ ጥቅሎች” ተገኝቶባቸዋል።

    ተጠርጣሪዋ አደንዛዥ ዕፅ ወደመሸጥ የተሰማሩት ሱቃቸው በእሳት ከተቃጠለ በኋላ መሆኑን ለመርማሪዎች እንደተናገሩ ተቋሙ አስታውቋል። አዛውንቷ ኋላ ላይ በዋስትና ተለቅቀዋል።

    አዛውንቷ በየአራት ቀኑ ዕፅ የሚቀርብላቸው ሌጎስ ከተማ ውስጥ በምትኖረው ልጃቸው ነው የሚል ጥርጣሬ መኖሩን የመገናኛ ብዙኃን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

    ተጠርጣሪዋ ካናቢሱን በአነስተኛ መጠን በመጠቅለል ለሚኖሩበት አካባቢ ማኅበረሰብ ሲሸጡ ነበር የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

    አዛውንቷ ዕድሜያቸው በመግፋቱ በዋስትና እንዲወጡ እና የምክር አገልግሎት እንዲሰጣቸው በአደንዛዥ ዕፅ ቁጥጥር ተቋሙ ዋና ኃላፊ መወሰኑ ተገልጿል። በዋስትና ቢወጡም በወንጀል ድርጊት ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ።

    ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የአዛውንቷ ልጅም በቁጥጥር ስር ውላለች።

    አዛውንቷ መያዛቸው የተሰማው፣ ተቆጣጣሪ ተቋሙ በናይጄሪያ የባሕር መስመሮች ላይ ባደረገው ቁጥጥር ከፍተኛ መጠን ያለው አደንዛዥ ዕፅ መያዙ በተገለጸበት ወቅት ነው።

    ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት አክዋ ኢቦም ግዛት ውስጥ በእንጨት ጀልባ ወደ ካሜሩን ሲጓጓዝ የነበረ ከ42 ኪሎ ግራም በላይ ዕፅ እንዲሁም ሦስት ሰዎች ተይዘዋል።

  11. በኦሮሚያ ክልል የደገም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በታጣቂዎች ተገደሉ

    የደገም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ተፈራ ደሴ

    የፎቶው ባለመብት, Paartii Badhaadhinaa Damee Dagam

    በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ ታጣቂዎች ትናንት እሁድ ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም. በፈጸሙት ጥቃት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ተፈራ ደሴ መገደላቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

    በጥቃቱ በወረዳው የምትገኘው አኖ ቀሬ ቀበሌ ሊቀ መንበር አስፋወሰን ኃይሌን ጨምሮ ሌሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተገልጿል።

    የዞኑ የፀጥታ መዋቅር ምንጮች ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ እንደተናገሩት፣ ዋና አስተዳዳሪው የተገደሉት እሁድ ከሰዓት በኋላ ሲሆን ጥቃት የተፈጸመው በደገም ወረዳ አኖ ቀሬ ቀበሌ ውስጥ ነው።

    በዕለቱ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ እንደነበር ምንጮቹ አስረድተዋል። የቀበሌ ሊቀ መንበሩን ጨምሮ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሕክምና እያገኙ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

    ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጮች፣ በመንግሥት ባለሥልጣናቱ ላይ ለተከፈተው ጥቃት ተጠያቂ ያደረጉት በክልሉ የሚንቀሳቀሱትን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) ታጣቂዎችን ነው። ታጣቂ ቡድኑ እስካሁን ስለ ጥቃቱ መረጃ ያለው ነገር የለም።

    የደገም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የአቶ ተፈራን መገደል በተመለከተ ከክልሉ መንግሥትም ይሁን ከሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር የተሰጠ አስተያየት የለም። ቢቢሲ ከዞኑ ዋና አስተዳደሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

    በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ባለልጣናትን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

    በየካቲት 2017 ዓ.ም. ሱሉልታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አበበ ወርቁ በታጣቂዎች መገደላቸው ይታወሳል።

    መንግሥት በሽብር ቡድንነት የፈረጀው እና 'ሸኔ' ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በወቅቱ በወጣው መግለጫው ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል።

    በዚያው ዓመት ታኅሣሥ ላይ ደግሞ የዞኑ የውሃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስዩም አበራ፣ የዞኑ አደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን እጄታ እና የዞኑ የፋይናንስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ግዛው ተገድለዋል።

    ጥቅምት ላይ በተመሳሳይ የወጫሌ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት ንጉሤ ኮሩን ጨምሮ ከ45 በላይ ሰዎች የሚሆኑ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግረው ነበር።

  12. የፓኪስታኑ ጦር አዛዥ ወደ ቴህራን ከማምራታቸው በፊት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ተነጋገሩ

    የፓኪስታኑ ጦር አዛዥ አሲም ሙኒር

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የፓኪስታኑ ጦር አዛዥ አሲም ሙኒር

    የፓኪስታኑ ጦር አዛዥ አሲም ሙኒር ሰኞ ዕለት ወደ ቴህራን ከማምራታቸው በፊት ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጋር መነጋገራቸውን ሦስት የሮይተርስ ምንጮች ተናገሩ።

    የጦር አዛዡ ከትራምፕ ጋር የተነጋገሩት አሜሪካ ጠንካራ የምጣኔ ሃብት ማዕቀብ ቴህራን ላይ ለመጣል እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት ነው።

    ዋይት ሐውስ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ተጠይቆ ወዲያውኑ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል።

    ሙኒር እና ትራምፕ በምን ጉዳዮች እንደተወያዩ ግልጽ አይደለም።

    ፓኪስታን እና ኳታር ቴህራን እና ዋሺንግተንን በማደራደር ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።

    በተያያዘ ዜና የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ማክሰኞ ዕለት የኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር ቡሳይዲ ወደ ቴህራን እንደሚመጡ ተናግረዋል።

    ባጋይ ጨምረውም ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ ገልጸዋል።

    ቃል አቀባዩ የኦማኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት በሁለትዮች ጉዳይ እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ከመናገር ውጪ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    አክለውም ሁለቱ አገራት የሆርሙዝ ወሽመጥን በሚመለከት የሚያደርጉት ውይይት “የቀጣናውን ሰላም እና ደኅንነት ያጠናክራል” ብለዋል።

    ቃል አቀባዩ የኦማኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት ከፓኪስታኑ ጦር አዛዥ ጉብኝት ጋር ምንም የሚያይዛቸው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

  13. ማራዶና “በእግዜር እጅ” ግብ ያስቆጠረባት ኳስ ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሸጠች

    ኳሱ እአአ በ2022 በ2.37 ሚሊዮን ዶላር ተሸጦ ነበር

    የፎቶው ባለመብት, PA Media

    የምስሉ መግለጫ, ኳሱ እአአ በ2022 በ2.37 ሚሊዮን ዶላር ተሸጦ ነበር

    ዲያጎ ማራዶና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1986ቱ የዓለም ዋንጫ በእጁ ግብ ያስቆጠረባት ኳስ በጨረታ 3.3 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠች።

    ከጨዋታው በኋላ ማራዶና ለጋዜጠኞች “በጥቂቱ በማራዶና ጭንቅላት እና በጥቂቱ በእግዜር እጅ” ግብ ማስቆጠሩን ተናግሮ ነበር።

    ማራዶና በዚያው የዓለም ዋንጫ ላይ ከበረኛው ውጪ አምስት የእንግሊዝ ተጫዋቾችን አልፎ “የክፍለ ዘመኑ ግብ” የተባለለትን ጎል አስቆጥሯል።

    ቅዳሜ ዕለት በዩናይትድ ስቴትስ ለጨረታ የቀረበው ኳስ 10 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል ተብሎ ቢጠበቅም በ3.3 ሚሊዮን ዶላር ተሸጧል።

    አጫራቹ ማይክ ፕሮቬንዛሌ ከጨረታው በፊት ለሮይተርስ የዜና ወኪል “ይህ ልዩ የሆነ ዕቃ ነው። እስካሁን ከተገኙት እጅግ አስፈላጊ የእግር ኳስ ዕቃዎች አንዱ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

    የ1986ቱን የዓለም ዋንጫ የዳኙት ቱኒዚያዊው አሊ ቢን ናስር ኳሱን ከጨዋታው በኋላ በመውሰድ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ጠብቀው አቆይተውታል።

    እአአ በ2023 በጨዋታው ላይ ጥቅም ላይ የዋለ ብቸኛው ኳስ መሆኑን በፊርማቸው ያረጋገጡ ሲሆን ገለልተኛ አጣሪዎችም እውነት መሆኑን መስክረዋል።

    ቢን ናስር እአአ በ2022 ኳሱን 2.37 ሚሊዮን ዶላር ሸጠውታል።

    እአአ በ2023 አዲሱ የኳሱ ባለቤት ለጨረታ ቢያቀርበውም የታሰበለትን ያህል ዋጋ ባለማውጣቱ ሳይሸጥ ቀርቷል።

    በዚሁ ጨዋታ ላይ ማራዶና የለበሰው ቲ ሸርት እአአ በ2022 በ7.1 ሚሊዮን ፓውንድ ተሸጧል።

  14. በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ

    ድሮን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ ታግቶ የቆመ ነዳጅ ጫኝ መርከብን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መግደሉን የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ጥቃቱ የተፈጸመው በሶማሊያ ኑጋል ክልል፣ ጎዶብጂራን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ መሆኑን ተናግረዋል።

    የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት መርከቧ ኤምቪ ሉቱፍ (MV Lutuf) የምትባል ሲሆን ከቀናት በፊት በባሕር ላይ ወንበዴዎች ታግታ ወደ አካባቢው መምጣቷን ተናግረዋል።

    የካሜሮንን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልበው ይህች መርከብ መዳረሻዋ ቱርክ ነበር ተብሏል።

    ቢቢሲ የመርከቧን መዳረሻም ሆነ ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።

    መርከቧ ከዚህ ቀደም ጋርማል የሚባል አካባቢ ቆማ የነበረ ሲሆን በአካባቢው በተፈጸመ የድሮን ጥቃት አራት ሰዎች ሞተዋል።

    የድሮን ድብደባውን ማን እንደፈጸመው በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። የሶማሊያ መንግሥትም ጥቃቱን አላወገዘም።

    የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም የተፈጸመውን ጥቃት አውግዘው የተገደሉት የባሕር ላይ ወንበዴዎች አይደሉም ብለው ነበር።

    የአካባቢው ባለሥልጣናት የድሮን ጥቃቱን የፈጸመችው ቱርክ ልትሆን ትችላለች ቢሉም የቱርክ ባለሥልጣናት ግን ለቢቢሲ ምንም መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል።

    አብዲፋታህ ዩሱፍ የተባለ የዐይን እማኝ ማንነታቸው የማይለይ ስምንት በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎችን መመልከቱን ተናግሯል።

    “ስምንት በጥቃቱ የተቃጠሉ አስከሬኖች አይቻለሁ።” ብሏል።

    የጎዶብጂራን ከንቲባ የሆኑት ኬነን ኦማር ለመበስበስ የተቃረበ አስከሬን ቆይቶ በመገኘቱ የሟቾች ቁጥር ዘጠኝ ደርሷል ብለዋል።

    የሟቾቹ አስከሬን ሰኞ ይቀበራል ተብሎ ይጠበቃል።

    የፑንትላንድ የመረጃ ምክትል ሚኒስትር ቢሌ ቀቦውሳዴ ከክስተቱ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች በመጣራት ላይ ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ቀደም ሲል ከባሕር ላይ ዘረፋ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች እንደገና እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ የውጭ አካላት እየሞከሩ ሊሆን እንደሚችል የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች እንደሚያመለክቱም ገልጸዋል።

    የፑንትላንድ ባለሥልጣናት መርከቦቻቸው በባሕር ላይ ዘራፊዎች ሊያዙ ወይም ሊታገቱ የሚችሉ የመርከብ ባለቤቶች፣ ኦፕሬተሮች፣ የዋስትና ሰጪ ድርጅቶች እና ሌሎች አካላት ከዘራፊ ቡድኖች ጋር በቀጥታ ድርድር እንዳያደርጉ ወይም የማስለቀቂያ ክፍያ እንዳይፈጽሙ አሳስበዋል። እንዲህ ዓይነት ክፍያዎች የወንጀል ቡድኖች ተግባራቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸውን ግብዓትና ማበረታቻ ሊሰጧቸው እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

  15. ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የኤም- 23 አማፂያን በሰላም ንግግር ማዕቀፎች ላይ ተስማሙ

    የኤም 23 አማፂያን በጎማ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኤም 23 አማፂያን በጎማ

    የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት እና በሩዋንዳ የሚደገፈው የኤም 23 አማፂ ቡድን የሰላም ድርድር ፍኖተ ካርታ ላይ ከስምምነት ደረሱ።

    በስዊትዘርላንድ ለአምስት ቀናት የተወያዩት ሁለቱ ወገኖች በጋራ ባወጡት መግለጫ “ሁሉን አቀፍ ሰላም ለማምጣት እና ግጭት ለመፍታት የሚያስችል ድርድር ለማድረግ” እንዲሁም የተኩስ አቁሙን ስምምነቱን አፈጻጸም ለመከታተል የሚያስችል አካል ለማቋቋም ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።

    ፍኖተ ካርታው በ2025 በአሜሪካ አስተባባሪነት በተፈረመው የሰላም ማዕቀፍ ሥር ለሚደረጉ ውይይቶች የጊዜ ሰሌዳ ያስቀምጣል።

    ነገር ግን በኤም 23 ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች፣ የታሳሪዎች አለመፈታት እና የፖለቲካ ማሻሻያዎች የሚደረጉበትን ጊዜ ጨምሮ በርከት ያሉ ጉዳዮች አሁንም በቡድኖቹ መካከል ላለመግባባት ምክንያት ናቸው።

    በድርድሩ ላይ ኤም 23፣ የዲሞክራቲክ ኮንጎ መንግሥት፣ ኳታር፣ አሜሪካ፣ የቶጎ ሪፐብሊክ፣ የአፍሪካ ኅብረት እና አስተናጋጇ ስዊትዘርላንድ ተሳትፈዋል።

    "ተፈላሚ ወገኖች የዶሃ ማዕቀፍ ስምምነትን ተከትሎ የተጣለባቸውን ግዴታዎችና ኃላፊነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የገጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችል አካል ለማቋቋም ተስማምተዋል።" ሲል መግለጫው አክሏል።

    ግጭቱ በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና በአጎራባች ሩዋንዳ መካከል ካለው ውጥረት ጋር በቅርበት የተያያዘ ነው።

    ሩዋንዳ የፀጥታ ስጋት እንደሆነ የምትቆጥረውን ኤፍዲኤልአር የተባለውን ነፃ አውጪ ኃይል ዲሞክራቲክ ኮንጎ ማፍረስ እንዳልቻለች ገልጻለች።

    ዲሞክራቲክ ኮንጎ ታጣቂ ቡድኑን ኤፍዲኤልአርን እንደማትደግፍ አስተባብላ ሩዋንዳም ኤም-23ን በወታደሮችና በጦር መሳሪያዎች እንደምትደግፍ ትከሳለች።

    በጥር 2025 ኤም23 ጎማን እና ሁለት የአየር ማረፊያዎችን ጨምሮ ሲቆጣጠር ግጭቱ ተባብሶ ነበር።

    በአስርት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።

    ምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊ በሆኑ ኮልታን እና ሌሎች ማዕድኖች የበለፀገች ናት።

  16. አሜሪካ በቴህራን ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን እንደምትጥል ስትገልጽ፣ ኢራን በባሕረ ሰላጤው የሚካሄዱ የነዳጅ ግብይቶችን ለማቋረጥ ዛተች

    የኢራን ባንዲራ

    የፎቶው ባለመብት, AP

    አሜሪካ፣ የኢራንን የንግድ አጋሮች ዒላማ ያደረጉ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ሰኞ ዕለት ለመጣል ስትዘጋጅ፤ "እስካሁን ከተደረጉት ሁሉ እጅግ ከፍተኛው የፋይናንስ ጥቃት" ብላ በጠራችው እርምጃ ኢራንን አስፈራራች።

    ኢራን በበኩሏ “የምጣኔ ሃብት ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ” በባሕረ ሰላጤው የሚካሄዱ የትኛውንም የነዳጅ ግብይቶች እንደምትዘጋ አስጠንቅቃለች።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ሰኞ ዕለት ረፋዱ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    አሜሪካ አሁን ለመጣል እየተዘጋጀች ያለችው የኢኮኖሚ ማዕቀብ እስላማዊ አብዮቱ እአአ በ1979 ከተመሰረተ ወዲህ አጋጥሞት የማያውቅ ነው ተብሏል።

    ቤሴንት በፋይናንሻል ታይምስ ላይ እሁድ ዕለት በታተመላቸው ጽሑፍ ላይ “[ሰኞ] ማለዳ አንድ ወሳኝ የኢኮኖሚ ጥቃት ይጀመራል፤ ይህም በአንድ ተቀናቃኝ ላይ እስካሁን ከተሰነዘሩት ሁሉ እጅግ የከፋው የፋይናንስ ጥቃት ነው።” ብለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ለሳምንታት የተኩስ ልውውጥ ያላደረጉ ቢሆንም ለስድስት ወር የዘለቀውን ጦርነት የሚያስቆም ተጨባጭ የሆነ ንግግር አላደረጉም።

    እሁድ ዕለት የኢራን የደኅንነት ኃላፊ አዲሱን የአሜሪካ የኢኮኖሚ ማዕቀብ የሚደግፉ አገራት በእስላማዊ ሪፐብሊክ ኢራን ላይ ”ጦርነት እንዳወጁ” እንቆጥረዋለን ሲሉ ዝተዋል።

    ሞህሰን ረዛኢ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት “ትራምፕ እርምጃ መውሰድ ከፈለጉ ተመጣጣኝ ምላሽ እንሰጣለን” ሲሉ ዝተዋል።

    ኢራን በፐርዢያ ባሕረ ሰላጤ የሚንቀሳቀሱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ዒላማ እንደምታደርግም ዝተዋል።

    ቤሰንት በፋይናንሻል ታይምስ ላይ በወጣው ጽሑፋቸው ላይ ዝርዝር እርምጃዎችን ሳይሰጡ የኢራን ኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ሥርዓት ላይ በመሳተፍ “የሚያባብሉ” ያሏቸውን “ፈሪ አገራትን” አሜሪካ ዒላማ እንደምታደርጋቸው አስታውቀዋል።

    “ይህን ማስቀጠል የሚያስከትለውን ውጤት ቢያጤኑት መልካም ይሆናል” ሲሉም በፋይናንሻል ታይምስ ላይ ጽፈዋል።

    ኢራን በበኩሏ ከአሜሪካ ሊሰነዘርባት ለሚችል የኢኮኖሚ ማዕቀብ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝታለች።

    የኢራን ከፍተኛ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሞህሰን ረዛኢ፣ እሁድ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “የኢኮኖሚ ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ፣ በሆርሙዝም ሆነ በፋርስ ባህረ ሰላጤ ውስጥ ከየትኛውም ሥፍራ አንድም የነዳጅ ጠብታ ወደ ውጭ አይላክም” ብለዋል።

    “ኢራን፣ የትኛውም አገር በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በሚደረገው የኢኮኖሚ ጦርነት ውስጥ ቢሳተፍ ወይም ድጋፍ ቢሰጥ፣ ድርጊቱን እንደ ጦርነት ተግባር ትቆጥረዋለች” ሲሉም አክለዋል።

    ቤሰንት ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የነዳጅ ምርት ከኢራን የምትገዛውን ቻይና ከአሜሪካ ጋር እንድትተባበር አሳስበው ነበር።

    በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው አሜሪካ በኢራን ጉዳይ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ እንድትከተል ጥሪ በማቅረብ "ማዕቀቦች እና ጫናዎች ችግሩን ለመፍታት አይረዱም።" ብለዋል።