ሩሲያ በኢትዮጵያ እና ኤርትራን መካከል 'ታማኝ' አደራዳሪ መሆን ትችላለች? ለምንስ ማደራደር ፈለገች?

ዐቢይ፣ ፑቲን እና ኢሳያስ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ሞስኮ የሚገኙት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች "ፍላጎት ካሳዩ" ለማደራደር ዝግጁ መሆኗን ሩሲያ አስታውቃለች።

ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ በሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች በመስከረም ወር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ሙሉ በሙሉ ካቋረጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ መድረክ የሚታደሙበት ነው።

ከጉባዔው አስቀድሞ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረጉት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌ ላቭሮቭ፤ ሁለቱን አገራት የማደራደር ሚናን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሩሲያ ኢትዮጵያን እና ኤርትራን በማሸማገል ሚናዋ ምን ሊሆን ይችላል? የትኞቹ የድርድር ነጥቦች ሊነሱ ይችላሉ? ውጤታማስ ሊሆን ይችላል? በሚሉት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የፖለቲካ እና ደኅንነት ተንታኞችን ምልከታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የሚኖር ድርድር ውስጥ ቁልፍ ከሚሆኑ ነጥቦች መካከል የባሕር በር ጉዳይ በዋናነት ይነሳል።

ሴርጌ ላቭሮቭ ከጋዜጠኞች ከቀረበላቸው ጥያቄ መካከል ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ለምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ሩሲያ ምን ዓይነት ምላሽ ትሰጣለች? የሚለው ይገኝበታል።

እሳቸውም የሁለቱን አገራት ጉዳይ በተመለከተ "እንደተረዳሁት እየተነጋገርን ያለነው ባሕር በር ስለማግኘት ነው። ሁለቱ አገራት በአሁኑ ወቅት የተቋረጠውን ግንኙነታቸውን እንዲያድሱ ፍላጎት አለን" ሲሉ መልሰዋል።

የቀይ ባሕር ጥያቄ

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዲሁም ተመራማሪ ዶ/ር ሙከረም ሚፍታህ፤ በሩሲያ በኩል የባሕር በር ጥያቄ በኩል ያላት አቋም "ያለ ምንም ጥርጥር የሁሉቱን አገሮች ጥቅም ወይም ጥያቄ ችግር ውስጥ በሚከት መንገድ ምላሽ የሚሰጥ እንደማይሆን" ይናገራሉ።

ሁለቱንም "የሚያስከፋ" በሆነ መንገድ ለባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንደማትሰጥም ይገልጻሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ እንደሚሉት፤ ሩሲያ ሁለቱን አገራት ለማስታረቅ የፈለገችበት ዋና ምክንያት "በቀይ ባሕር ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ስለፈለገች" ነው።

የሩሲያ የቀይ ባሕር ድርሻ ከሌሎች የምዕራብ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ሩሲያ "አስታራቂ" መሆን እንደማትችልም ባለሙያው ያስረዳሉ።

ለዚህም ምክንያት ያሉት ሩሲያ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ የበለጠ ወዳጅ መሆኗን ነው። ኢትዮጵያም ከሩሲያ ይልቅ ምዕራባውያን እንዲያስታርቋት እንደምትፈልግ ያምናሉ።

የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ዲፕሎማት እና ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያ አቶ ባይሳ ዋቅወያ በበኩላቸው ሩሲያ ሁለቱ አገራት "ችግር ውስጥ እንዳይገቡ በማደራደር ትክክለኛዋ አካል ነች" ይላሉ።

"ከሩሲያ መንግሥት ይልቅ ከኤርትራ ሕዝብ እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንዲሁም ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከኤርትራ መንግሥት ጋር የሚቀራረብ የለም" ይላሉ።

ሩሲያ ለምን ማደራደር ፈለገች?

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ፤ አሁን ላይ በሁለቱ አገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አለመኖሩን ጠቅሰው "ይህ ሁኔታ ከዚህ ቀደም አንድ አገር እንደነበሩ ሁሉ፣ ለረዥም ጊዜ በጎረቤትነት አብረው ለኖሩ ሁለት አገራት መልካም አይደለም" ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አገራቸው "ከረዥም ዓመታት በፊትም" የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት ማድረጓን አስታውሰዋል።

ዶ/ር ሙከረም እንደሚሉት፤ ሩሲያ በሁለቱም አገሮች ዘንድ "አንጻራዊ የሆነ ጠንካራ ቅቡልንት እንዳላት" ታስባለች።

ላቭሮቭ ያንን መሠረት አድርገው፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት እንዳይሻክር ወይም "ወደ ግጭት እንዳይሄድ" ማድረግ ይሻሉ።

በተለይም የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛቶች መግባታቸውን ተከትሎ ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

ኢትዮጵያ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ወታደሮቹ ከግዛቷ እንዲወጡ ጠይቃለች።

ኤርትራት በምላሹ ለምክር ቤቱ በጻፈችው ደብዳቤ ኢትዮጵያ ወረራ ለመፈጸም ሽፋን እንደፈለገች ከስሳለች።

ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ያቋረጠችው ከኤርትራ ጋር ብቻ አይደለም። በኢትዮጵያ ታጣቂዎችን በመደገፍ ከከሰሰቻት ግብፅ ጋርም ዲፕሎማሲያዊ ቁርሾ ውስጥ ገብታለች። ኤርትራ እና ግብፅ ክሶቹን አስተባብለዋል።

አሁን ላይ የህወሓት ኃይሎች ከፌደራል መንግሥቱ እና አጋሮቹ (የትግራይ የሰላም ኃይሎች) ጋር ግጭት ውስጥ ቢገቡም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ይፋዊ ውጊያ አለመኖሩን ዶ/ር ሙከረም ይጠቅሳሉ።

ላቭሮቭ ያቀረቡት ሐሳብ "ልዩነቶቻቸውን መፍታት ባይችሉም፣ ይሄ ልዩነት አገርሽቶ፣ ሁለቱ አገራት ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንዳይገቡ በማገድ ሚና እንደሚኖረው" ያስረዳሉ።

ሩሲያ በድርድር ስኬታማ ልትሆን ትችላለች?

ላቭሮቭ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የሚነሳ "ማንኛውም ችግር መልካም ፈቃድ ላይ ተመሥርቶ" በሚደረስ እና "ፍላጎቶችን በሚያማክል ስምምነት መሠረት ይፈታል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የደኅንነት ተንታኝ፤ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረገድ፣ ምዕራባውያን አገራት ከኤርትራ ይልቅ ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዳላቸው እና ኤርትራ ከምዕራቡ ዓለም ይልቅ ከሩሲያ ጋር ቅርብ እንደሆነች ያምናሉ።

"ኤርትራ ብቻ ሳትሆን የኤርትራ አጋር ግብፅም ሩሲያ የእርቅ ሽማግሌ እንድትሆን እንደምትፈልግ" ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ ግን ወደ ምዕራባውያን አገራት አሸማጋይነት ልታጋድል እንደምትችልም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጦር ጄቶችን ከሩሲያ ሲረከቡ ባደረጉት ንግግር፤ መሣሪያዎቹን ለመረከብ ተይዞ ከነበረው አንድ ዓመት ቀድመው እንዲያኙ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማዘዛቸውን ጠቅሰዋል።

"ፑቲን ኢትዮጵያን ይወዳሉ፣ ኢትዮጵያን ማገዝ ይፈልጋሉ" ሲሉም ተናግረዋል።

አቶ ባይሳ ሩሲያ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ "በጣም ከፍተኛ ፍላጎት" እንዳላት ይገልጻሉ።

"እንደ ሩሲያ ኤርትራን እና ኢትዮጵያን ለማስታረቅ የሚችል ኃይል የለም" ይላሉ።

የሩሲያ መንግሥት "በሁለቱም ላይ ሥልጣን አለው" በማለትም "በእነሱ ላይ ጫና ሊፈጥርባቸው ይችላል" ሲሉ የማደራደር ሚናው ጠንካራ እንደሚሆን ያስረዳሉ።

ሩሲያ ከሁለቱ አገራት ለማን ትቀርባለች?

ዶ/ር ሙከረም የሩሲያ መንግሥት ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጋር በወታደራዊ እና ዲፕሎማሲ ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ያነሳሉ።

ሩሲያ በንግድ ከሁለቱ አገራት ጋር እምብዛም ትስስር ባይኖራትም፤ በድሮን ቴክኖሎጂ፣ በወታደራዊ የደኅንነት መረጃ ልውውጥ ዘርፎች ግንኙነታቸው ጠንካራ ነው።

የግብርናውን ዘርፍ ስንመለከትም ሁለቱም አገራት ወደ ሩሲያ ምርቶች ይልካሉ።

ኤርትራ በሰብአዊ መብት ጥሰት እና በዴሞክራሲ ማጣት በምዕራባውያን የተጣለባትን ማዕቀብ ለመቋቋም ወደ ሩሲያ ትቀርባለች።

ኤርትራ በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያን መንግሥት አቋም በመደገፍም ትታወቃለች።

እነዚህን እውነታዎች የሚጠቅሱት ባለሙያው፤ ሩሲያ "ግልጽ ጦርነት እንዳይነሳ ለማድረግ" አቅሙ እንዳላት ያስረዳሉ።

"ነገር ግን ቁርሾዎችን በመፍታት ወደ ሰላማዊ ግንኙነት ለማምጣት አቅም አላቸው አልልም" ይላሉ።

እንደ ሩሲያ ጠንካራ ጫና የማሳደር አቅም ያላት በሁለቱም አገራት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ባለቤት የሆነችው ቻይና ነች ይላሉ።

"ቻይና እና ሩሲያ አንድ ላይ ቢመጡ የሁለቱን አጋራት ቁርሾ የማጥፋት አቅም አላቸው። እርስ በርስ ከመጠፋፋት እርምጃቸውን እንዲያቅሙ የማድረግ አቅም አላቸው" ሲሉም ያስረዳሉ።

የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራህማን ሰይድ፤ ሩሲያ ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ጋር ጥሩ ግንኙነት ካላቸው ጥቂት አገሮች አንዷ ናት ይላሉ።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሩሲያን እንደ "የረዥም ጊዜ ቁልፍ አጋር" አድርገው ይመለከቱታል።

ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር በብሪክስ ውስጥ ትገኛለች። በሰላማዊ የኒውክሌር ጉዳዮች እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይም አብረው ይሠራሉ።

ሩሲያ በዓለም ላይ ካሉት አምስት ድምጽን በድምጽ የመሻድ ኃይል ካላቸው አገሮች አንዷ መሆኗ "ሁለቱም አገሮች [ሽምግልናውን] ትኩረት እንዲሰጡ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ተናግረዋል።

ሩሲያ በቀይ ባሕር ጉዳይ መሳተፏ ሁለቱም አገራት "ትኩረት እንዲሰጧት" ሊያደርግ እንደሚችልም ይገልጻሉ።

ሩሲያ ለማደራደር ጥያቄ ባቀረበችበት መድረክ ላይ ኢትዮጵያ ከሞስኮ መሣሪያ መረከቧ ሌላው ነጥብ ነው።

አቶ ባይሳ ይህ "ከኢኮኖሚያዊ ዕይታ አንጻር" መታየት እንዳለበት ይናገራሉ።

ኤርትራ በሩሲያ ላይ ያላትን እምነት እንደማያዳክም የሚያምኑት ባለሙያው "ሩሲያ በታሪክ ኤርትራን ፈጽሞ አልጎዳችም" ይላሉ።