"ልጄ የተገደለችበት ቀን ሳስታውሰው ውስጤ ይንገበገባል"፡ ፍትሕ የሚጠይቁት ታንዛኒያውያን

የ40 ዓመቷ ኒማ ሙኖ የደረሰባትን ስቃይ መንግሥት እውቅና እንዲሰጠው ትፈልጋለች
የምስሉ መግለጫ, የ40 ዓመቷ ኒማ ሙኖ የደረሰባትን ስቃይ መንግሥት እውቅና እንዲሰጠው ትፈልጋለች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ከአንድ ዓመት በፊት በታንዛኒያ ከምርጫ ሁከት ጋር በተያያዘ የተገደሉ ሰዎች ቤተሰቦች ፍትሕ እንደሚሹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከምርጫው በኋላ በተነሳው ግርግር ቢያንስ 500 ሰዎች ተገድለዋል። የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም የሕክምና ወጪያቸው እንዲሸፈን እየጠየቁ ነው።

እግሩ ላይ በጥይት የተመታው ሜሼክ ሴን "የሆስፒታል ወጪያችንን ከዚህ በኋላ መሸፈን አንችልም" ብሏል።

ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ሐሰን 98% ድምጽ አግኝተው ተመርጠዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ ሌሎችም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት፤ የሳሚያ መንግሥት "የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ" በሚል ሽፋን ተቺዎች ላይ አፈና አድርሷል፤ ዜጎችንም ፍርሃት ውስጥ ከትቷል።

ተቃዋሚዎች የምርጫውን ውጤት "ቀልድ" ሲሉ አጣጥለውታል። የፕሬዝዳንቷ ሁለት ዋነኛ ተቀናቃኞች ከምርጫው ታግደው ነበር።

የዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቱንዱ ሊሱ በአገር መክዳት ተከስሰዋል። ተቃዋሚው የምርጫ ሥርዓቱ መሻሻል እንዳለበት ሲያሳስቡ ነበር።

በቀጣይ ሳምንት ፍርድ ቤት የሚቀርቡት ፖለቲከኛው ከጠበቆቻቸው ጋር እንዳይገናኙ ስለታገዱ የረሃብ አድማ መምታታቸውን ገልጸው ነበር። መንግሥት ክሱን አስተባብሏል።

ጠበቃቸው ዲክሰን ማታታ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ከደንበኛቸው ጋር እንዲገናኙ ስለተፈቀደ ፖለቲከኛው መመገብ ጀምረዋል።

የአምነስቲ ሪፖርት እንደሚያሳየው መንግሥት፤ ተቃዋሚዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ከገዢው ፓርቲ ያፈነገጡ ፖለቲከኞች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ፈጽሟል።

እግሩ ላይ በጥይት የተመታው ሜሼክ ሴን "የሆስፒታል ወጪያችንን ከዚህ በኋላ መሸፈን አንችልም" ብሏል
የምስሉ መግለጫ, እግሩ ላይ በጥይት የተመታው ሜሼክ ሴን "የሆስፒታል ወጪያችንን ከዚህ በኋላ መሸፈን አንችልም" ብሏል
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአምነስቲ የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታ "የፀጥታ ኃይሎች ከልክ ያለፈ ኃይል ከመጠቀማቸው ጋር በተያያዘ አንድም ባለሥልጣን ላይ የወንጀል ምርመራ አልተደረገም፤ የተቀጣም የለም" ይላሉ።

እንዲያውም ከምርጫው በኋላ መንግሥት የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንቀጠለ ይናገራሉ።

"እንደ ሌሎች አምባገነኖች ሁሉ 'ሽብርን መከላከል' የሚለውን እንደ መሣሪያ እየተጠቀሙ ነው" ብለዋል።

የታንዛኒያ መንግሥት ሰብአዊ መብት እንደሚያከብር እና ብዝበዛ እንዳልፈጸመ በተደጋጋሚ አስተባብሏል።

ፕሬዝዳንት ሳሚያ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ገለልተኛ ነው ብለዋል። ለተፈጠረው ሁከት የውጭ ኃይሎችን ተጠያቂ አድርገዋል። ዓላማው እሳቸውን ከሥልጣን ማንሳት መሆኑንም ተናግረዋል።

አምና ቢቢሲ ያረጋገጣቸው ቪድዮዎች ፖሊስ ተቃዋሚዎች ላይ ሲተኩስ ያሳያሉ። አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ተቃዋሚዎችን ለመበተንም ተሞክሯል።

ማዊጃ ሐሚሲ ባለቤቷ ጆርጅ ኪሲቫኒ የተገደለው በምርጫው ቀን እንደሆነ ትናገራለች።

"ባሌን አጥቻለሁ። እኔና አምስት ልጆቼ የሚደግፈን የለም። ቤተሰቤን ብቻዬን አስተዳድራለሁ። ደጋፊ የለንም" ትላለች የ32 ዓመቷ ማዊጃ።

ቤተሰቧን አትክልት በመሸጥ ታስተዳድራለች። መንግሥት እንዲረዳቸውም ትማጸናለች።

እግሩን በጥይት የተመታው ሜሼክ የሦስት ልጆች አባት ነው።

አምስት ጊዜ ቀዶ ሕክምና ተደርጎለታል። ከዚህ በኋላ የሚያስፈልጉትን ቀዶ ሕክምናዎች ለመሸፈን ግን ገንዘብ የለውም።

"ማድረግ የምንችለውን አድርገናል፤ ከዚህ በላይ መሄድ አንችልም" ይላል የ33 ዓመቱ ሜሼክ።

"መንግሥት የተጎዳውን ሰዎች መርዳት አለበት። አንዳንዶቻችን አሁንም ታማሚ ነን" ሲልም ይናገራል።

ከምርጫው ግርግር በኋላ ሆስፒታሎች የተጎዱ ሰዎችን ለማከም አለመፍቀዳቸውን ያስታውሳል።

ቤተሰቡ የአካባቢውን ባለሥልጣናት እርዳታ ቢጠይቅም መንግሥት በነውጡ ለተጎዱ ሰዎች ገንዘብ አለመመደቡ ተነግሯቸዋል።

ቢቢሲ ይህንን በገለልተኛ ወገን አላጣራም።

ለፕሬዝዳንቷ የተሰጠው ይፋዊ መረጃ 518 ሰዎች መገደላቸውን ያሳያል። አምነስቲ እንደሚለው ግን የሪፖርቱ ዝርዝር ይፋ ሳይደረግ "በምሥጢር" ተይዟል።

ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ሐሰን 98% ድምጽ አግኝተው ተመርጠዋል
የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ሐሰን 98% ድምጽ አግኝተው ተመርጠዋል

"የፀጥታ ኃይሎች በነውጡ ወቅት ምን አድርገዋል የሚለውን አዲስ የተቋቋመው ኮሚሽን መፈተሽ አለበት" ሲሉ የአምነስቲ ባለሙያ ይናገራሉ።

ከአውሮፓውያኑ መስከረም 3 እስከ 17 ድረስ አምነስቲ ያነጋገራቸው 17 ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች የደረሰውን ጥቃት አብራርተዋል።

አንዳንዶቹ ባለፈው ሐምሌ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ከተጠራ በኋላ ዒላማ ሆነዋል። የተቃውሞ ሰልፍ የተጠራው ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲደረግ እና ፍትሕ እንዲሰፍን ነበር።

መንግሥት የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይካሄድ አግዷል።

አንድ የ26 ዓመት ታንዛኒያዊ ለአምነስቲ እንደገለጸው፤ ሐምሌ ላይ ዳሬ ሰላም ውስጥ ታስሮ ለ47 ቀናት ክስ ሳይቀርብበት ቆይቷል።

መርማሪዎቹ ዐይኑን ሸፍነው፣ ማን ተቃውሞውን በገንዘብ እንደሚደግፍ ሲጠይቁት እንደነበር እና ሊገድሉት እንደዛቱበትም ተናግሯል።

"በመጀመሪያው ቀን ምግብ አልሰጡኝም። ውሃ ስጠይቅ ዐይኔን በጨርቅ ሸፍነው ፊቴ ላይ ሸኑብኝ። 'ድምጽ ለማሰማት አፋችሁን የምትከፍቱ ሰዎች ዋጋችሁ ይሄ ነው' አሉኝ።"

በሁለተኛው ቀን ጎጎኒ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው እንደደበደቡት ይናገራል። እግሩ እስከሚዝል ድረስ ደብድበውት እንዲቆም ያስገድዱትም ነበር።

አምነስቲ "የማሰቃየት ድርጊቶች፣ የዘፈቀደ እስራት፣ በግዳጅ መሰወር እና አፈና" መፈጸሙን ገልጿል።

የታንዛኒያ መንግሥት ለአምነስቲም ሆነ ለቢቢሲ ምላሽ አልሰጠም።

የ40 ዓመቷ ኒማ ሙኖ የደረሰባትን ስቃይ መንግሥት እውቅና እንዲሰጠው ትፈልጋለች። የ18 ዓመት ልጇ ማሪያ ቻሚን ያጣችው እናት ፍትሕ እንዲሰፍንም ትጠይቃለች።

አሩሻ ውስጥ ልጇ የስልክ ካርድ ልትገዛ ወጥታ በተተኮሰባት ጥይት ተገድላለች።

ኒማ አሁን ላይ ከቤት ለመውጣት አቅም እንዳጣች ትናገራለች።

"ያንን ቀን እስከ ሕይወቴ መጨረሻ አልረሳውም። ሳስታውሰው ውስጤ ይንገበገባል።"

በቪክቶሪያ ሐይቅ አቅራቢያ የሚኖረው ጁማ ናሲቡ የ25 ዓመቱን የወንድሙን ልጅ ከምርጫው ግርግር ወዲህ አላየውም።

ጁማ ፊልም ለማየት ሲኒማ ቤት ከሄደ በኋላ አልተመለሰም። በሆስፒታሎች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ቢፈለግም አልተገኘም።

አጎቱ ኋላ ላይ እንደሰማው ከታሰሩ ወይም ከተገደሉ ሰዎች አንዱ ሊሆን ይችላል።

"እስከዛሬም የሚያመኝ አስከሬኑን አለማግኘታችን ነው" ይላል አጎቱ።