ከኦስትሪያ ቤተ መዘክር በ600 የአልማዝ ፈርጦች የተንቆጠቆጠ ሐብል የሰረቁ ሌቦች እየታደኑ ነው

ሐብሉን በመስረቅ የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, LPD Wien

የምስሉ መግለጫ, የቬየና ፖሊስ ከደኅንነት ካሜራ ያገኘውን የተጠርጣሪዎቹን ፎቶ ይፋ አድርጓል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በኦስትሪያ ቪየና ከሚገኝ ቤተ መዘክር ከ600 በላይ የአልማዝ ፈርጦች የተንቆጠቆጠ የአንገት ሐብል የሰረቁ ሁለት ግለሰቦች በፖሊስ እየተፈለጉ ነው።

ግለሰቦቹ በጠራራ ፀሐይ ድርጊቱን የፈፀሙት ሐብሉ ለዕይታ በቀረበበት ሙዚየም ትኬት ገዝተው በመግባት ነው።

ፖሊስ እንደገለፀው ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ሐሙስ ዕለት ከሰዓት የቪየና የጥበብ ሙዚየም በመግባት ሐብሉ የተቀመጠበትን መስታዋት በመስበር በፕላቲኒየም እና በአልማዝ ፈርጥ የተዋበውን ሐብል ወስደው ተሰውረዋል። ይህ ሐብል ከአራት ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ እንዳለው ይታመናል።

ለቀድሞ የግብፅ ንጉሳውያን ቤተሰብ የተሰራው ሐብል በቬይና በተዘጋጀ እና እስከ መስከርም ወር በሚቆየው አውደ ርዕይ የቀረቡ ነበሩ።

ከ200 ካራት በላይ የሆነው የአንገት ሐብሉ እአአ በ1939 የመጀመሪያዋ የግብፅ ንግሥት ናዚል ሳብሪ በልጃቸው ሰርግ ላይ አድርገውት ነበር።

የዚህ ሐብል ስርቆት በአውሮፓ ቤተ መዘክሮች አስደናቂ የጥበብ ሥራዎች ላይ በተደጋጋሚ ከተፈፀሙት የቅርብ ጊዜው ነው።

የቪየና ፖሊስ በደኅንነት ካሜራ ያገኛቸውን የሁለቱን ተጠርጣሪዎች ፎቶ ይፋ ያደረገ ሲሆን ሕዝቡ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።

ፖሊስ በመግለጫው እንዳለው አንደኛው ተጠርጣሪ መሣሪያ ይዞ እንደነበር ይታመናል። ሐብሉን ከያዙ በኋላ በቤተ መዘክሩ ደቡባዊ አቅጣጫ በኩል ማምለጣቸውን ፖሊስ ገልጿል።

ከ600 በላይ የአልማዝ ፈርጦች የተንቆጠቆጠ ሐብል

የፎቶው ባለመብት, Austrian Interior Ministry

የምስሉ መግለጫ, ከ200 ካራት በላይ የሆነው የአንገት ሐብሉ እአአ በ1939 የመጀመሪያዋ የግብፅ ንግሥት ናዚል ሳብሪ በልጃቸው ሰርግ ላይ አድርገውት ነበር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሙዚየም ኦፍ አፕላይድ አርትስ (ኤምኤኬ) ቤተ መዘክር ዋና ዳይሬክተር ሊሊ ሆሌይ ፣ "እጅግ ውድ የሆነው ጌጣጌጥ ስርቆት ከባድ ጉዳት አስከትሎብናል" ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ በመግለጫቸው ቤተ መዘክሩ በተለይ ለአውደ ርዕዩ የደኅንነት ዕቅድ እንዳዘጋጀ ጠቅሰው፣ " የደኅንነት ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል፤ ሁሉም የደኅንነት እርምጃዎች በጥንቃቄ ተዘጋጅተዋል" ብለዋል።

ጨምረውም በመሣሪያ የታገዘው ስርቆት ሲፈፀም የቤተ መዘክሩ ሠራተኞች በተረጋጋ ሁኔታ የተቀመጡ አሰራሮችን እንደተከተሉ እና የተጎዳ አካል አለመኖሩን ገልጸዋል።

ቤተ መዘክሩ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በዋና ዋና ሙዚየሞች ውስጥ ያጋጠሙ ክስተቶችን ተከትሎ የደኅንነት እርምጃዎችን በጥልቀት መገምገሙንም ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

ሐሙስ ዕለት ከጥንታዊው የጌጣጌጥ ዕቃዎች ውስጥ አንዱ ከስፔን ቤተ መዘክር ተሰርቋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይም በጣልያን ሲሲሊ ከሚገኝ ቤተ መዘክር ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው አራት የህዳሴ ዘመን ሥዕሎች ተዘርፈዋል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይም በሚሊዮን ዩሮዎች የሚያወጡ ሦስት ሥዕሎች በዚያው ጣልያን ፓርማ ከተማ ከሚገኝ ቤተ መዘክር ተዘርፈዋል።

እነዚህ ስርቆቶች ያጋጠሙት ባለፈው ሕዳር ወር ጭምብል ያጠለቁ ወንበዴዎች በጠራራ ፀሐይ በፈረንሳይ ፓሪስ በጎብኚዎች በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጎበኘው ሉቭር ሙዚየም 102 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ቅርሳ ቅርሶች ከሰረቁ በኋላ ነው።

በተደጋጋሚ የተፈፀሙ እነዚህ ስርቆቶች በአውሮፓ የባህል ተቋማት ላይ ያለው የደኅንነት ሁኔታ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል።

የአውሮፓ ኅብረት ሕግ አስፈፃሚ ኤጀንሲ -ዩሮፖል በቤተ መዘክሮች የሚፈፀሙ ስርቆቶች በኃይል እና በከባድ ዘዴዎች ታግዘው እየጨመሩ መጥተዋል፤ ይህም "አዳዲስ የወንጀል መረቦች ተሳትፎን ሊያመለክት ይችላል" ብሏል።