አሜሪካ የቬንዙዌላን 65 ቢሊዮን በርሜል የነዳጅ ዘይት ክምችት ለመቆጣጠር ከስምምነት ደረሰች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከቬንዙዌላ ጋር ከ65 ቢሊዮን በርሜል በላይ የነዳጅ ክምችትን ለመቆጣጠር ስምምነት ላይ መድረሷን አስታወቁ።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "ይህ ታሪካዊ ስምምነት የአሜሪካን የነዳጅ ክምችት ከእጥፍ በላይ ከፍ አድርጎታል፤ የነዳጅ አቅርቦታችንን በእጅጉ ያሳድጋል እንዲሁም ለሁሉም አሜሪካውያን የነዳጅ ዋጋን በእጅጉ ይቀንሳል" ሲሉ ጽፈዋል።
የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝም ስምምነቱን የአገራቸውን ምጣኔ ሃብት በማነቃቃት ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸው አወድሰውታል።
ትራምፕ በዚህ ዓመት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ካዋሉ በኋላ በዓለም ላይ ትልቁን የቬንዙዌላን የነዳጅ ክምችት እንደሚጠቀሙ ተናግረው ነበር።
የኢራን ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በአሜሪካ በታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የተነሳም ጫና ሲደረግባቸው ቆይቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የነዳጅ ስምምነቱን "ለአሜሪካም ሆነ ለቬንዙዌላ ሕዝብ ትልቅ ድል" ሲሉ ጠርተውታል።
ሁለቱ አገራት ስላደረጉት ስምምነት የወጡት ዝርዝር መረጃዎች ውስን ናቸው።
"ለቬንዙዌላውያን ይህ ስምምነት ወደ 100 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የግል ኢንቨስትመንት ያመጣል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቁ ሥራዎችን ይደግፋል እንዲሁም የቬንዙዌላ ኢኮኖሚ ዳግም እንዲያንሰራራ ያደርጋል" ሲሉ ሩቢዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው ሩቢዮ እና የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ከቬንዙዌላ አመራር ጋር በመሆን "ከግል የንግድ አጋሮች ጋር በመተባበር" ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ከግል የንግድ አጋሮች ጋር ስለተገባው ስምምነት እንዲሁም በስምምነቱ መሠረት አሜሪካ ስለገባቻቸው ግዴታዎች እና ኃላፊነቶች ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡም፣ ስምምነቱ "የአሜሪካ ግብር ከፋዮችን ምንም ወጪ" እንደማያስወጣ ተናግረዋል።
የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ባወጡት መግለጫ ስምምነቱ "በአገራችን መነቃቃት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ብለዋል።
ስምምነቱ የተረጋገጠ የ65 ቢሊዮን በርሜል ክምችት ያላቸው 17 የነዳጅ ሥፍራዎችን ማልማትን እንዲሁም "ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት እና ለአገሪቷ ከ209 ቢሊዮን ዶላር በላይ ግብር የሚያስገኝ" መሆኑን ሮድሪጌዝ ተናግረዋል።
"እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ኢንዱስትሪያችንን መልሶ ማቋቋምና ማዘመን ብቻ ሳይሆን፣ ለአገራችን የኢኮኖሚ እድገት፣ ለአህጉራችን የኤነርጂ ደኅንነት እና በዓለም አቀፍ ገበያዎች ላይ የበለጠ ሚዛንን ለማስጠበቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ" ብለዋል።
በስምምነቱ መሠረት የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት "በቬንዙዌላ ልምድ ካለው የግል ኩባንያ ጋር" በጋራ በሚኖር ሽርክና 55 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለቢቢሲ የሚዲያ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ፣ ሮድሪጌዝ ኩባንያው በነዳጅ ማውጫ ሥፍራዎች ለ100 ዓመታት ሥራውን እንዲያከናውን ፈቃድ ሰጥተዋል።
ትራምፕ ከዚህ በፊት እምብዛም ስላልተለመደው ስምምነት ጥቂት ዝርዝሮችን ብቻ ሰጥተዋል። ይህም በግልጽ ዩናይትድ ስቴትስ በሌላ ሉዓላዊ አገር ሀብቶች ላይ ቀጥተኛ ቁጥጥር እና አስተዳደር እንዲኖራት ያስችላታል።
ስምምነቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2003 ሳዳም ሁሴን በአሜሪካ መሪነት በተካሄደው ወረራ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የአሜሪካ መራሹ ጦር የሽግግር መንግሥት በኢራቅ የነዳጅ ገቢ ላይ ከነበረው ቁጥጥር የበለጠ ስፋት ያለው ይመስላል።
ነገር ግን የቬንዙዌላ ስምምነት በአገሪቱ ውስጥ ምን ዓይነት ሕጋዊ እና ሕገ መንግሥታዊ ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙት እንደሚችል ግልፅ አይደለም።
በዋሽንግተን እና ካራካስ መካከል የተደረገውን ስምምነት የሚያሳይ ሰነድ እስካሁን ይፋ አልተደረገም።
ፕሬዝዳንት ማዱሮ እና ባለቤታቸው ሲሊያ ፍሎሬስ እአአ ጥር 3፣ 2025 በአሜሪካ ጦር በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ፕሬዚዳንቱ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ትራምፕ አስተዳደራቸው ቬንዙዌላን "አስተማማኝ፣ ትክክለኛ እና ፍትሃዊ ሽግግር" እስኪደረግ ድረስ እንደሚያስተዳድሩ ተናግረዋል። አሜሪካም የአገሪቱን የነዳጅ ሽያጭ ላልተወሰነ ጊዜ እንደምትቆጣጠር ጨምረው ገልጸው ነበር።
ቬንዙዌላ በዓለም ላይ ትልቁ ነው የተባለ 303 ቢሊዮን በርሜል የሚገመት የተረጋገጠ የነዳጅ ክምችት አላት።
ይሁን እንጂ እአአ ከ1990ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ የአገሪቱ የነዳጅ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።
ትራምፕ የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎች የአገሪቱን የነዳጅ ኢንደስትሪ ወደነበረበት ለመመለስ ቢያንስ 100 ቢሊዮን ዶላር እንዲያወጡ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም አገሪቱ ቀደም ሲል "የአሜሪካን ነዳጅ፣ የአሜሪካን ንብረቶች እና የአሜሪካን ነዳጅ መፈለጊያ ቁሳቁሶች በተናጠል በመያዝ እና በመሸጥ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ኪሳራ ላይ ጥላናለች" ካሉ በኋላ የቬንዙዌላ ነዳጅ ይገባናል ብለዋል።















