በደቡብ ሱዳን አነስተኛ የመንገደኞች አውሮፕላን ተከስክሶ 15 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, ማኅበራዊሚዲያ
በደቡብ ሱዳን በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ አብራሪውን ጨምሮ ሁሉም ተሳፋሪዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተነገረ።
የአገሪቱ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አነስተኛ አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ሁሉም ተሳፋሪዎች እና አብራሪው በአደጋው መሞታቸውን አስታውቋል።
አደጋው ወደደረሰበት ስፍራ የምርመራ ቡድን የተላከ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ እንደሚያሳየው የአደጋው መንስኤ ከባድ የአየር ሁኔታ በተለይም እይታን የሚከለክል ጭጋግ የተሞላበት ደመና ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።
አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ከመዲናዋ ጁባ በስተ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። አውሮፕላኑ የበረራ ግንኙነቱ የተቋረጠው በረራ በጀመረ በ30ኛው ደቂቃ መሆኑ ታውቋል።
በአውሮፕላኑ ውስጥ አብራሪውን ጨምሮ በድምሩ 15 ሰዎች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል የደቡብ ሱዳን ዜጎች 13 ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሁለለቱ ደግሞ ኬንያውያን ናቸው። ሁሉም በአደጋው ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ሴስና 208 ካራቫን የተባለችው ይህች አውሮፕላን 'ሲቲሊንክ አቪየሽን' ንብረት ናት።
ደቡብ ሱዳን ደካማ የሚባል የትራንስፖርት ስርዓት ያላት ሲሆን መልካም የሚባል የበረራ ታሪክም የላትም።
አገሪቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011 ነጻነቷን ካገኘች በኋላ ይህኛው የአውሮፕላን አደጋ ለ55ኛ ጊዜ በደቡብ ሱዳን ምድር የተከሰተ ነው።
አንዳንዶቹ አደጋዎች የሚከሰቱት በአውሮፕላኖቹ እርጅና ወይም በደካማ የቁጥጥር ስርዓት ምክንያት ነው።
ከመጠን በላይ ጭነት፣ መጥፎ የአየር ሁኔታ እና የአብራሪዎች ስህተትም ለአደጋዎቹ ተጨማሪ መንስኤዎች ናቸው።
ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ከጁባ የተነሳ አውሮፕላን በረራ በጀመረ በ3 ደቂቃ ውስጥ ተከስክሶ 20 የነዳጅ ሠራተኞች ሞተዋል።
በአገሪቱ ታሪክ የከፋው የአውሮፕላን አደጋ የደረሰው በ2015 ሲሆን በዚህም በጁባ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ አንድ አንቶኖቭ ተከስክሶ 41 ሰዎች ሞተዋል።















