'እንደ ላባ የቀለለው' የማራቶን ክብረ ወሰንን የሰበሩት አትሌቶች ያደረጉት ጫማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት ኬንያዊው ሴባስቲያን ሳዌ 'የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የማራቶን ክብረ ወሰን ይሰበራል' ማለቱን ተከትሎ ብዙ ሰዎች ያ ጊዜ ምናልባት የለንደን ማራቶን ሊሆን ይችላል ብለው ነበር።
ውጤቱ ግን ከክብረ ወሰንም በላይ ነው። በአንድ ሰዓት ከ59 ደቂቃ እና 30 ሰከንድ የ31 ዓመቱ ኬንያዊ አትሌት ተዓምር የሚባል ታሪክ ጽፏል።
ምንም እንኳን እአአ በ2019 ሌላኛው ኬንያዊ ኢሉይድ ኪፕቾጌ ከ2 ሰዓት በታች ማራቶንን ቢያጠናቅቅም ቁጥጥር በሚደርግበት ውድድር የተካሄደ ስላልነበር በይፋ አልተመዘገበም። ሳዌ ይህንን ታሪክ ሲጽፍ ኢትዮጵያዊው ዮሚፍ ቀጀልቻም የታሪኩ ተጋሪ ሆኗል። ዮሚፍ 1፡59፡40 በመግባት ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በታሪክ ሁለተኛው ፈጣን ሰው ሆኗል።
በሴቶቹ የማራቶን ውድድር ደግሞ ትዕግስት አሰፋ የራሷን ክብረ ወሰን በዘጠኝ ሰከንድ በማሻሻል 2፡15፡41 በመግባት አሸንፋለች።
ከውድድሩ በኋላ የሁሉም ሰው ጥያቄ የነበረው እንዴት ሦስቱም በዚህ ደረጃ ክብረ ወሰን ለመስበር ቻሉ" የሚለው ነበር።
መልሱ ምናልባት ጫማው ሳይሆን እንደማይቀር ብዙዎቹ ያስባሉ።
ሳዌ፣ ዮሚፍ እና ትዕግስት ምን አይነት ጫማ ነበር የተጫሙት?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሦስቱም ሯጮች የተጫሙት አዲዳስ አዲዜሮ አዲዮስ ፕሮ ኢቮ 3 ነው።
ጫማው የተዋወቀው ውድድሩ ከመካሄዱ ከሁለት ቀን በፊት ነበር።
በጣም ተወዳጅ በሆነው ጫማ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ ማሻሻያ ተደርጎበታል። ይህንን ዓይነት ጫማ ለማምረት አዲዳስ ላለፉት ሦስት ዓመታት ከእነዚህ ሦስት አትሌቶች ጋር ሲሠራ ቆይቷል።
ሳዌ በሌላኛው ኬንያዊ ኪፕቱም ተይዞ የነበረውን የ2፡01፡25 ክብረወሰን 2 ደቂቃ በሚጠጋ ጊዜ ለማሻሻል አግዞታል።
ሳዌ ከውድድሩ በኋላ ቀላል እና ምቹ የሆነ ጫማ ስላዘጋጀለት አዲዳስን አመስግኗል።
የአዲዳሱን ፕሮ ኢቮ 3 ጫማ ምን ልዩ ያደርገዋል?
99 ግራም የሚመዝነው ይህ ጫማ ከ100 ኪሎ ግራም በታች የሚመዝን ሆኖ ሲዘጋጅ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ይህ ማለት ከአንድ መካከለኛ አፕል፣ ሙዝ ወይም ከሳሙና ያነሰ ክብደት ነው።
ከቅርብ ኪዜ ወዲህ በጫማ መካከል በሚገጠመው ካርቦን ፕሌት [ሶል] ምክንያት የማራቶን ሰዓት በተደጋጋሚ እየተሻሻለ ነው። ፕሮ ኢቮ 3 ጫማ ግን የመካከለኛው ሶል ሩጫን እንዲያስቀጥል እና አጠቃላይ ክብደትን እንዲቀንስ ተደርጎ የተገጠመውን የካርቦን ቴክኖሎጂ ተጠቅሟል።
የአዲዳስ ምክትል ፕሬዝዳንት ፓትሪክ ናቫ "እያንዳንዱ ጥቃቅን ነገር አስተዋጽዖ አለው። እስከ ናኖግራም ድረስ ወርደን ነው ነገሮችን የምንለካው" ብለዋል።
"በጣም ረጅም ሂደት ነበር፤ ያም ወደ አንድ ጠቃሚ ነገር እንድናመራ አድርጎናል። ያ ነገርም ለውድድር ጫማ ይሆናል ብለን አመን።"
በእርግጥ ጫማው ለመደበኛ ሯጮች ውድ የሚባል ነው። በዚህ ዓመት የተወሰነ ምርት ብቻ ስለሆነ የተዘጋጀው ለማግኘት አስቸጋሪ ነው። በሚቀጥለው ዓመት ለገበያ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን 450 ፓውንድ ወይም 95 ሺህ ብር አካባቢ ዋጋ ተተምኖለታል።
አዲዳስ በዝና ናይክን በልጦታል?
በ2019 ኪፕቾጌ ናይክ አልፋፍላይስ ለብሶ ከ2 ሰዓት በታች ማራቶንን ሲያጠናቅቅ ያለምንም ጥርጥር ናይክ የገበያው መሪ ሆኖ ነበር።
በተመሳሳይ በ2023 ኪፕቱም በቺካጎ ማራቶን ናይክ አልፋፍሌ 3ኤስን አድርጎ ክብረ ወሰን ሲሰብር በድጋሜ የናይክ ዝና ናኝቶ ነበር።
ነገር ግን እንደ ውድድሩ ሁሉ ገበያው ላይም በተመሳሳይ መገፋፋት እና ቦታ መቀያየር አለ።
አሁን በተመዘገበው ውጤት ያለጥርጥር አዲዳስ ገበያው ይደራለታል። የዓለማችን ፈጣን ወንድ እና ሴት ሯጮች ያደረጉት የአዲዳስን ምርት ነው።
ነገር ግን ሩጫ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተወዳጅ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ የስፖርት ልብስ ማምረት ውድድሩ በሁለቱ ኩባንያዎች ብቻ ተወስኖ አይቀርም።
እሁድ ዕለት በተደረገው የለንደን ማራቶን እንደ አሲክስ፣ ሳኡኮኒ፣ ሆካ፣ ብሩክስ፣ እና ኒው ባላንስ የመሳሰሉ ኩባንያዎችን ጫማ ያደረጉ ሯጮችም የውድድሩ ተሳታፊዎች ነበሩ።
"እንደማስበው ሁላችንም የስፖርት ሰዎች ነን። በመሆኑም ሁልጊዜም የውድድር መንፈስ አለ" ብለዋል የአዲዳሱ ናቫ።
"በዋናነት ግን አትሌቶቹ በምርጥ አቋማቸው ላይ እንዲሆኑ እንፈልጋለን። በመሆኑም ከገበያው እኩል የሚያነሳሳን ነገር የአትሌቶቹ ውጤታማ መሆን ነው"
ደረጃቸው ከፍ ባሉ ጫማዎች ላይ ያለው መመሪያ ምንድን ነው?
የውድድሩ የበላይ አካል በስፖርት ልብሶች ላይ የሚጨመረውን ቴክኖሎጅ እያስቀጠለ ነው። በ2022 የዓለም አትሌቲክስ በዚህ ዙሪያ ያለውን መመሪያ አሻሽሏል።
18 ገጽ በሚሸፍነው መመሪያው እንዳስታወቀው ጫማዎች ለሁሉም አትሌቶች የመቅረብ ዕድል ከሌላቸው በስተቀር የተወሰኑ አትሌቶች ብቻ እንዳያደርጓቸው ከልክሏል።
መመሪያው እንደሚለው የጫማው ከፍታ [እስከተረከዝ ያለው] ከ40 ሚሊ ሜትር መብለጥ የለበትም። ከአንድ በላይ ካርቦን ፕላት [ሶል] ከተገጠመለት ክብረ ወሰኑ ይሰረዛል ይላል።
አዳዲስ ነገሮችን ለመጨመር የተቆጣጣሪ አካላት አዳዲስ ዕድሎችን እየተመለከቱ ነው። ነገር ግን ገደቡ እስከምን እንደሆነ አምራቾች አያውቁትም።
የአዲዳሱ ናቫ "ያስተካከልናቸው የተወሰኑ ነገሮች አሉ" ብለዋል።
"ሴባስስቲያን ከዚህም በላይ ፈጥኖ መሮጥ እንደሚችል ተናግሯል። ስለዚህ ያልታየን ነገር ማፈላለግ ደስ ይላል፤ ምክንያቱም ምን ልታገኝ እንደምትችል አታውቅም"
ስለዚህ ሳዌንን ለድል ያበቃው ጫማው ነው?
ባለፉት 20 ዓመታት የስፖርት ሳይንስ የውድድር ጫማዎችን በቴክኖሎጅ ከማዘመን ጋር ተያይዞ ከፍተኛ መሻሻል ታይቶበታል።
የሳዌን ጉዳይን በተመለከተ የስፖርት የምግብ መለያ ከሆነው ማውርቴን የተወጣጣ የምርምር ቡድን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ስድስት የተለያዩ ጉዞዎችን በማድረግ ከሴባስቲያን ጋር 32 ቀናትን አሳልፏል።
ቡድኑ በሃይድሮጄልስ ክህሎት ያካበተ ሲሆን ሳዌ ምንም ሳይጨናነቅ በአንድ ሰዓት ውስጥ ከ90 እስከ 120 ካርቦሃይድሬት እንዲያቀልጥ ሲያሰሩት ቆይተዋል። በእነዚህ ቀናት በሳዌ ላይ የተለያዩ እገዛዎችን አድርጓል።
የግላይኮጅን መጠን ከፍ ሲል ሰውነታችን ከተከማቸ ስብ ይልቅ ካርቦሃይድሬትን በማስቀደም እንደ ተቀማጭ የኃይል ምንጭ እንዲጠቀም ያደርጋል።
እንደዚህ አይነት አነጋጋሪ ክብረ ወሰኖች ሲሰበሩ ከአበረታች መድሃኒት ጋር የተያያዙ ጥርጣሬዎች የወሬ ማዕከል ይሆናሉ።
በ2024 የችካጎ ማራቶንን በ2፡09፡56 በሆነ ሰዓት የዓለም ክብረ ወሰንን በመስበር ኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች ባለፈው ዓመት በአበረታች መድሃኒት ምክንያት ለ3 ዓመት ታግዳለች።
ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት አዲዳስ እና ሴባስትያን ሳዌ የአትሌቲክስ ተቆጣጣሪ ቡድን የአበረታች መድሃኒት ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ባለፈው ዓመት ከተደረገው የበርሊን ማራቶን በፊት የሴባስቲያን ሳዌ የአበረታች መድሃኒት ምርመራ እንዲያደርግ አዲዳስ 50 ሺህ ዶላር ከፍሏል።















