በኢትዮጵያ ለኤል ኒኖ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? ምን ያህልስ አሳሳቢ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህ ቀደም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከመጠን ያለፈ ዝናብ እንዲሁም ዝናብ በወቅቱ አለመጣሉ ጉዳት አስከትለዋል።
ዘንድሮም የኤል ኒኖ ተቃራኒ ውጤቶቸ የሆኑት አነስተኛ ዝናብ እና ከልክ ያለፈ ዝናብ ማኅበረሰቡ ላይ የጋረጡትን አደጋ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።
ዓለም አቀፉ የሜትሮሎጂ ተቋም ባወጣው ትንበያ በተለይ በኢትዮጵያ፣ በአብዛኛው ኤርትራ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኡጋንዳ፣ በጂቡቲ፣ በሱዳን እንዲሁም በምዕራባዊ እና ባሕር ዳርቻ የኬንያ ክፍሎች ከመደበኛው ያነሰ የዝናብ መጠን ይጠበቃል።
ወቅቱ 50 በመቶ ገደማ ዓመታዊ የቀጣናው ዝናብ የሚገኝበት እንደመሆኑ የዝናብ እጥረት ጫናው በግብርና፣ በውሃ አቅርቦት፣ በውሃ አቅርቦት፣ በምግብ ደኅንነት እና በሕብረተሰብ ጤና ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
የዘንድሮው ኤል ኒኖ በአውሮፓውያኑ 1997 እና በ2023 ከተከሰተው ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስትቲዩት ከሰኔ 2018 ዓ.ም. እስከ መስከረም 2019 ዓ.ም. ባወጣው ትንበያ፤ ዋነኛ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሰሜን ምሥራቅ እና የምሥራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ "መደበኛ እና ከመደበኛ በታች ያመዘነ" እንዲሁም በመካከለኛው እና በሰሜን ምዕራብ "መደበኛ እና ከመደበኛ በታች" ዝናብ ይኖራል።
በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ክረምት ከመደበኛው "ቀደም ብሎ" እንደሚገባም ያመለክታል።
በክረምቱ መግቢያ በሰኔ ወር እና በመውጫው የመስከረም ወር የዝናብ ሥርጭት "የተዛባ እና ደረቅ ሰሞናት የሚዘወተርበት" እንደሚሆን ይጠበቃል።
አልፎ አልፎ የሚኖር የከባድ ዝናብ ክስተት "ቅፅበታዊ ጎርፍ" ሊያስከትል እንደሚችልም ያመለክታል።
በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ሥር ያለው 'ክላይሜት ፕሪዲክሽን ኤንድ አፕልኬሽንስ ሴንተር' እንደሚለው፤ ከመደበኛው በታች የሆነ ዝናብ በማዕከላዊ፣ ሰሜን ምሥራቅ እና ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ሊከሰት ይችላል።
በተቃራኒው በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዝናብ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።
በአብዛኛው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች ከመደበኛው ከፍ ያለ ሙቀት እንደሚኖርም ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ያወጣው ሪፖርት፤ ሁለት የኤል ኒኖ ገጽታዎችን ያሳያል።
በአንድ አከባቢ ድርቅ እና የውሃ እጥረት ሲያስከትል በሌላ አካባቢ ደግሞ የጎርፍ መጥለቅለቅ እንደሚከሰት ያትታል።
በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ ያለውን የውሃ እጥረት በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ከተከሰተው ጎርፍ ጋር ማነጻጸር ይቻላል።
ወደ ኋላ ብንመለስ ከአውሮፓውያኑ 2023 እስከ 2024 ድረስ ኤል ኒኖ የተራዘመ ዝናብ አልባ ወቅት እና የከፋ ጎርፍ አስከትሏል።
ኤል ኒኖ የሚከሰተው በምሥራቅ እና መካከለኛው ፓስፊክ ውቅያኖስ በሚፈጠር የባሕር ወለል ሙቀት እና የንፋስ ሁኔታ ለውጥ ነው።
ከ0.5 ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ የሆነ ሙቀት ሲከሰት የምድር ወገብ አካባቢ የሚፈጠሩ የአየር ሁኔታዎችን ይለውጣል።
የንፋስን አቅጣጫ የማስቀየር፣ እርጥበት አዘል የአየር ሁኔታን የመለወጥም አቅም አለው።
ኦቻ-ኢትዮጵያ እንደሚለው በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ወንዞች እና የውሃ ጉድጓዶች እንዲሁም አዝመራም ለመድረቁ ምክንያት ነው።
በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ኃይለኛ ዝናብ እና ቅጽበታዊ ጎርፍ ቤትን ያጥለቀልቃል፤ ከብቶች ይወስዳል።
ዝናብ ከመጠን በላይ ወይም በታች ሲሆን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ያስቸግራል፤ ከብቶች ይሞታሉ፤ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመፈናቀል ይገደዳሉ፤ አዝመራ ይደርቃል፤ የምግብ ዋስትናም አደጋ ላይ ይወድቃል።
ቀጣዩ ኤል ኒኖ "ጠንካራ" ሊሆን እንደሚችል ትንበያዎች ያሳያሉ። በመላው ዓለም ጫና እንደሚያሳድርም ስጋት አለ።
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዮት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምነው ተሾመ እንደሚናገሩት፤ ከሰኔ እስከ መስከረም ያለው የክረምት ወቅት "ለአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢ ዋነኛ የዝናብ ወቅት" ነው።
ከዓመታዊ የዝናብ መጠን እስከ 85 በመቶ የሚደርሰው የዝናብ መጠን እና ሥርጭት የሚስተዋልበት መሆኑን ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በአብዛኛው የኦሮሚያ አካባቢ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ እና በሲዳማ ክልል ዞኖች እንዲሁም በምሥራቅ የአገሪቱ አካባቢም ዋነኛ የዝናብ ወቅት ነው።
ክረምት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት አካባቢዎች "መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ሥርጭት" እንደሚኖር ይናገራሉ።
በጋምቤላ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች የክረምት ዝናብ ቀደም ብሎ ጀምሯል።
ደቡብ እና ምሥራቅ የትግራይ ዞኖች፣ የሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች እንዲሁም የአፋር ክልል ዞኖች እና መካከለኛው የአገሪቱ አካባቢዎች "ብዙ ቦታዎችን የሚሸፍን መደበኛ የሆነ የዝናብ መጠን እና ሥርጭት" ሲኖራቸው፤ በጥቂት ቦታዎች "ከመደበኛ በታች የሆነ የዝናብ መጠን እና ሥርጭት" ይጠበቃል።
ከቀጣዩ ነሐሴ ጀምሮ ኤል ኒኖ ይበልጥ እየተጠናከረ እና እየተስፋፋ በሚሄድበት ወቅት፤ የደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን እና ሥርጭት እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ዶ/ር አሳምነው ይናገራሉ።
ሰኔ ከገባ አንስቶ በተለይ በምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የሆነ ከባድ ዝናብ እየተስተዋለ ይገኛል። ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሲደጋገም ደግሞ በቀላሉ ወደ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊቀየር ይችላል።
"በተለይም በኦሞ ጊቤ ተፋሰሶች እና በአባይ ተፋሰሶች ቅጽበታዊ ጎርፍ የመከሰት ዕድል አለ" ይላሉ።
ኤል ኒኖ እየተጠናከረ ሲሄድ በተለይ በደቡብ እና ምሥራቅ ትግራይ ዞኖች፣ በሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች እንዲሁም በምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል የክረምት ዝናብ ቀደም ብሎ ሊወጣ ይችላል።
የክረምት ዝናብ ቀደም ከወጣ ደግሞ "ደረቅ ሰሞናት" እንደሚፈጠሩ ይናገራሉ።
ኤል ኒኖ በአንዳንድ አገራት የሙቀት ወጀብ ቢያስከትልም፤ በኢትዮጵያ በቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ላይ የተወሰኑ ለውጦች ብቻ እንደሚስተዋል ያክላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ እንደሚለው፤ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት "በተባባሰ ኤል ኒኖ" ምክንያት ለፍተኛ ጎርፍ፣ በሽታ፣ የሙቀት ወጀብ እና ድርቅ ተጋልጠዋል።
በተለይም ከዚህ ቀደም ጎርፍ፣ ድርቅ እና የሰብአዊ ድጋፍ ቅነሳ ካስከተለው ጉዳት በማገገም ላይ ያሉ አገራት የበለጠ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ያመለክታል።
በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝናብ ወንዞች እንዲሞሉ ሲያደርግ፤ በሶማሊያ፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳ እና በሌሎችም የቀጣናው አገራትም ስጋቱ አንዣብቧል።
"ችግሩ ከፍተኛ ደረጃ ሳይደርስ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲረባበሩ" ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል።
የኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ የአስቸኳይ ጊዜ ምክትል ፕሬዝዳንት ቦብ ኪቸን "ሰዎች ሁሉንም ነገር ካጡ በኋላ አንዳች ነገር ከማድረግ ይልቅ" የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ መውሰድን ይመክራሉ።
ችግሩ የአፍሪካ ቀንድ ብቻ አይደለም። ባንግላዲሽ፣ ፓኪስታን፣ አፍጋኒስታን እና ሌሎችም የእስያ አገራትም ተጋላጭ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ተቋም (ፋኦ) ያወጣው ሪፖርት፤ ኤል ኒኖ "በመላው ዓለም ግብርና ላይ አደጋ መደቀኑን" ጠቅሷል።
በሳሃል፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ በማዕከላዊ አሜሪካ እና በካሪቢያን የሚገኙ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች በቀጣይ ወራት ለድርቅ ይጋለጣሉ።
ከ2015 እስከ 2016 ድረስ፣ በ23 አገራት 60 ሚሊዮን ሰዎች በኤል ኒኖ ምክንያት ሲጎዱ፤ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሰብአዊ ቀውስ ደርሷል።
አሁን ላይ ግጭት እና የኑሮ ውድነት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረውን ጫና አባብሰዋል።
የፋኦ የተፈጥሮ ሃብት ኃላፊ ዮርግ አልቫር ቤልትራን ስለ ዘንድሮው ኤል ኒኖ ኢገልጹ "ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ኤል ኒኖዎች አይደለም" ይላሉ።
"ዓለማችን አሁን የበለጠ ሞቃለች። ለግጭት እና የምግብ እጥረት ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦች እንዲሁም ውስን የመቋቋም ብቃት ያላቸው የበለጠ ለቀውስ ይዳረጋሉ" ይላሉ።
ፋኦ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በ22 ተጋላጭ አገሮች፣ 8.8 ሚሊዮን ሰዎችን ለመደገፍ 202 ሚሊዮን ዶላር አዘጋጅተዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ግጭት የሚፈትናቸው እና የድርቅ ተጋላጭነት ያላቸው አገራት የገፈቱ ዋነኛ ቀማሽ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተለይም ዝናብ ላይ ብቻ የተንተራሰ ግብርና የተስፋፋባቸው አገራት በቀላሉ ይጎዳሉ።
ከ80 በመቶ በላይ የድርቅ ጉዳት የሚከሰተው አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ላይ እንደሆነ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ሪሊፍ ዌብ ባወጣው ሪፖርት፤ የግጭት ስጋት ባጠላበት እና ገና ከእርስ በርስ ጦርነት እያገገመች ባለችው ትግራይ፣ የፋኖ ታጣቂዎች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ውጊያ በቀጠሉበት የአማራ ክልል እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከመንግሥት ኃይሎች ጋር በሚዋጋበት በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው ሰብአዊ ቀውስ ሊባባስ እንደሚችል ያትታል።
በክረምት የዝናብ ወቅት ሰብል በሚዘራባቸው የትግራይ እና አማራ አካባቢዎች እንዲሁም አርብቶ አደር በሆኑ እንደ አፋር ባሉ ክልሎች የሚፈጠረውን ጫናም ያስረዳል።
ፋኦ እንደሚለው፤ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ለተከታታይ ዓመታት ያደረሰው ጫና ላይ ግጭት እና የሰዎች መፈናቀል ታክለው ስጋቱን አባብሰዋል።
ድርቅ "ከሴኔጋል፣ ደቡብ ሞሪታንያ፣ ኮት ዴቯር፣ ጋና፣ ቶጎ፣ ቤኒን እና ናይጄሪያ አንስቶ እስከ ኢትዮጵያ እና ሱዳን" ሊሻገር እንደሚችል ይጠቁማል።
ድርቅ የሚቋቋም ዘር መምረጥ፣ ለከብቶች መኖ ማከማቸት እንዲሁም ውሃ ማጠራቀምን የመሰሉ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን ይመክራል።
በታዳጊ አገራት የክትባት ሥርጭትን ለማስፋፋት የሚሠራው ዓለም አቀፍ ጥምረት 'ጋቪ ዘ ቫክሲን አሊያንስ' እንደሚለው፤ በመጪዎቹ ወራት የሚከሰት ከልክ ያለፈ ሙቀት፣ ድርቅ እና ጎርፍ "አሁንም ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች" የበለጠ ያሰጋል።
የዘንድሮው ኤል ኒኖ ከ2023 እስከ 2024 ከነበረውም በላይ "የከፋ" ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።
ከዚህ ቀደም የተከሰተው ኤል ኒኖ በ10 ሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የምግብ፣ የውሃ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የጤና አገልግሎት እና የግብርና ድጋፍ እጥረት ማስከተሉን ይጠቅሳል።
የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት የፈጠረው የነዳጅ እና የማዳበሪያ እጥረት እንዲሁም የምግብ ዋጋ ንረትም የችግሩ ሌላ ገጽታ ነው።
በሌላ በኩል የዓለም አቀፍ የእርዳታ ማዕቀፎች ገንዘብ መቀነስ ወይም መቋረጥ ሰብአዊ ድጋፍን ፈታኝ ያደርገዋል።
ዋነኛ ተጋላጭ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው።
ከባድ የአየር ሁኔታ በሚያስከትለው "ሱፐር ኤል ኒኖ" (የላቀ ኤል ኒኖ) ምክንያት በአፍሪካ ከ10 እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የምጣኔ ሃብት ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የአፍሪካ ልማት ባንክ ገልጿል።
'በሱፐር ኤል ኒኖ' የሚጎዱ አገራት በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርታቸው ላይ ቅናሽ እንደሚያስከትልም አስታውቋል። የአገራቱ ብድር የመክፈል አቅም ላይ ጫና በመፍጠር በዜጎቻቸው የመሠረታዊ ፍላጎት አቅርቦት ላይ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ባንኩ ጨምሮም አሳሳቢው የአየር ሁኔታ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት "የዜጎች መፈናቀል እና ስደትን ያስከትላል፣ የመሠረታዊ ምግብ ምርቶች ዋጋ ይወደዳል፣ በውሃ እና በግጦሽ መሬት ችግር ምክንያት ግጮቶች ሊባባሱ ይችላሉ" ሲል አሳስቧል።















