በአማራ ክልል ገዳም ላይ "በተጣለ ድሮን" ሁለት ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አረጋገጠች

በጥቃቱ የተገደሉት ሁለት ሴት መነኮሳት መሆናቸውን አንድ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል

የፎቶው ባለመብት, EOTC TV/youtube

የምስሉ መግለጫ, በድሮን ጥቃቱ የተገደሉት ሁለት ሴት መነኮሳት መሆናቸውን አንድ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኝ ገዳም ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሁለት መነኮሳት መገደላቸውን እና 13 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው በዞኑ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት አረጋገጠ።

የተፈጸመውን ጥቃት "ዘግናኝ እና አሰቃቂ ድርጊት" ሲል የገለጸው የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት፤ "የሚመለከተው አካል" ይህ ዓይነቱ ክስተት እንዳይደገም "በትኩረት እንዲያስብበት" ጠይቋል።

በደቡብ ወሎ ዞን፣ ቦረና ወረዳ በሚገኘው 'ግዮን አባይ ገዳመ አስቄጥስ ቅድስት አርሴማ፣ አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ቂርቆስ የአባቶችና የእናቶች አንድነት ገዳም' ጥቃቱ የደረሰው ረቡዕ ሐምሌ 15/2018 ዓ. ም. እንደሆነ አንድ የሀረገ ስብከቱ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሴት መነኮሳት መኖሪያ በሆነው ገዳሙ ላይ ጥቃት የደረሰው ረፋድ አራት ሰዓት ገደማ እንደነበር ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የቤተ ክርስቲያኗ ምንጭ ሐሙስ ዕለት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ትናንት አርብ ሐምሌ 17 ባወጣው መግለጫ የድሮን ጥቃቱ መድረሱን አረጋግጧል።

ቢቢሲ ስለ ክስተቱ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ እና የመንግሥት ኮምንኬሽን አገልግሎት መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።

ሦስት ዓመት በሞላው የአማራ ክልል ግጭት ከፋኖ ኃይሎች ጋር በሚደረጉ ውጊያዎች የድሮን ጥቃቶች በተደጋጋሚ ተፈጽመዋል።

አሁን ጥቃት የተፈጸመበት "ቀጣና ለዓመታት ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱበት" መሆኑን ለቢቢሲ የገለጹት ምንጭ፤ ገዳሙ በሚገኝበት አከባቢ ግን "አለመኖራቸውን" ተናግረዋል።

ዛሬ ቅዳሜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት የፌስቡክ ገጽ የወጣው የሀገረ ስብከቱ መግለጫ እንደሚያስረዳው፤ ጥቃቱ የደረሰው "መናንያን መነኮሳት በአገልግሎት ላይ" በነበሩበት ሰዓት ነው።

በዚህ ጥቃት "ሁለት እናቶች" እንደተገደሉ እንዲሁም 13 ሰዎች ከባድ እና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ሀገረ ስብከቱ አስታውቋል።

"ከጠዋቱ 4፡00 ገደማ በገዳሙ ላይ በተጣለ ድሮን ሁለት እናቶች ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ አንዲት እናት በደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጽኑ ሕሙማን ክፍል እየተረዱ [ይገኛሉ]" ብሏል።

በተጨማሪም "12 መናንያን መነኮሳያት እናቶች ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በቦረና ሰላም ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው" መሆኑን ገልጿል።

"ወዲያውኑ" ሕይወታቸው ያለፈው ሁለት ሰዎች፤ እዚያው ገዳሙ ውስጥ ቀብራቸው መፈጸሙን የሀገረ ስብከቱ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል። "እዛው ገዳሙ አንድ ላይ ነው የተቀበሩት። ሰዎች ተገኝተው ቀብረዋቸዋል" ብለዋል።

ድሮን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በጽኑ በመጎዳታቸው ከፍ ላለ ሕክምና ወደ ደሴ ከተማ የተላኩት መነኩሴ ቀዶ ሕክምና እንደተደረገላቸው ሐሙስ ዕለት ተናግረው ነበር።

በሰዎች ሕይወት እና አካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ፤ በገዳሙ የሚገኙ "መኖሪያ ቤቶች"፣ መነኮሳቱ "የሰበሰቡት የዓመት መቁነን (ቀለብ)" እንዲሁም "የገዳማቱ የዕለት መገልገያ ንዋዬ ቅድሳት" "ከጥቅም ውጪ" እንደሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጭ፤ በጥቃቱ ምክንያት ሌሎች መነኮሳት "እንዳይበተኑ" የማረጋጋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ "ላለመደገሙ ምን ዋስትና አለ" የሚል ስጋት እንደተፈጠረባቸው አንስተዋል።

የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከትም በመግለጫው "ከምናኔ ሕይወት በስተቀር ሌላ አመለካከት በማይታይባቸው" የገዳሙ "መነኮሳያት ላይ የደረሰውን አስከፊ ድርጊት በጽኑ" አውግዟል።

"እንዲህ ዓይነቱ ዘግናኝ እና አሰቃቂ ድርጊት በቤተ ክርስቲያንና በአማኞቿ ላይ እንዳይደገም የሚመለከተው አካል በትኩረት እንዲያሰብብበት" የጠየቀው አገረ ስብከቱ፤ በክስተቱ "የተሰማውን መራር ሐዘን" ገልጿል።