ሕንዳዊው አክቲቪስት የአገሪቱ ትምህርት ሚኒስትር እንዲነሱ የጀመረውን የረሃብ አድማ ከ26 ቀናት በኋላ አቆመ

ሕንዳዊው አክቲቪስት ሶናም ዋንግቹክ ሆስፒታል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Sonam Wangchuk / X

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሕንዳዊው አክቲቪስት ሶናም ዋንግቹክ የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ እንዲደረግ የጠየቁ ወጣቶችን ተቃውሞ በመደገፍ የጀመረውን የረሃብ አድማ ከ26 ቀናት በኋላ አቆመ።

"ሶናም ሰር" በመባል የሚታወቀው ዋንግቹክ፣ "በተለያዩ ጉዳዮች ረዥም ሰዓት የፈጀ ድርድር ከተደረገ በኋላ" እንዲሁም "በአገሪቱ ሊኖር የሚችል ግጭትን" ለመቀልበስ በሚል የረሃብ አድማውን ማቆሙን በኤክስ ገጹ አስታውቋል።

የ59 ዓመቱ ዋንግቹክ የረሃብ አድማውን የጀመረው የኮክሮች ጃንታ ፓርቲ (ሲጄፒ) አባላት የሕንድ ትምህርት ሚኒስትር ዳርሜንድራ ፕራዳን ከሥልጣን እንዲወርዱ ያቀረቡትን ጥያቄ በመደገፍ ነው።

አክቲቪስቱ ቀደም ሲል 11 ኪሎ ግራም ቢቀንስም "አሁንም በሕይወት አለሁ" ብሎ ነበር።

አክቲቪስቱ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት በዴልሂ እየተካሄደ ከነበረ የተቃውሞ ሠልፍ ላይ በኃይል እንዲወጣ ተደርጎ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

በሕንድ ሰፊ እውቅና ያለው ዋንግቹክ፣ የረሃብ አድማውን ያቆመው መንግሥት በጃንታ ማንታር በሚገኙ ተቃዋሚ ሠልፈኞች ላይ ምንም ዓይነት ሕጋዊ እርምጃ እንደማይወስድ ቃል ከገባ በኋላ መሆኑን የሕንዱ ኤንዲቲቪ ድረገጽ ዘግቧል።

የሕንድ ጤና ሚኒስትር እና ምክትላቸው ዋንግቹክ በሆስፒታል ሳለ ጎብኝተውታል።

የሲጄፒ መስራች አብሂጄት ዲፕኬ ስለ ዋንግቹክ ውሳኔ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ "ሶናም ሰር ከ26 ቀናት በኋላ የረሃብ አድማውን ለማቆም በመወሰኑ በጣም ደስተኞች ነን፤ እረፍት ተሰምቶናል" ብለዋል።

አክለውም "የኮክሮች ጃንታ ፓርቲ በካንታር ማንታር የሚያካሄደው ሰላማዊ ተቃውሞ [የትምህርት ሚኒስትሩ] ዳህርሜንድራ ፕሬዳን እስኪለቅቁ ድረስ ይቀጥላል" ሲሉ ተናግረዋል።

በሕንድ ዋና ከተማ የሚካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ የቀጠለ ሲሆን ሰኞ ዕለት ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመሄድ ያደረጉትን እንቅስቃሴ ለመግታት የጸጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ ፖሊስን ጨምሮ በርካቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ሲጄፒ በአሁን ሰዓት በሕንድ ውስጥ ካሉ የወጣቶች እንቅስቃሴ ስሙ በጉልህ ይነሳል።

እአአ ከ2014 ጀምሮ በሥልጣን ላይ የሚገኙትን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲን እና አስተዳደራቸው ላይ ያለውን ቅሬታ በሰፊው በመግለጽ ይታወቃል።

እንቅስቃሴው የተጀመረው በግንቦት ወር ሲሆን በሕንድ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመግባት የሚሰጠው ፈተና ሾልኮ ከወጣ በኋላ በኦንላይን በሚያሰራጫቸው ስላቅ አከል መልዕክቶች ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል።

ተቃዋሚ ሠልፎቹ ራሳቸውን 'ኮክሮችስ' ብለው የሚጠሩ ሲሆን ባለፈው አንድ ወር የተቃውሞ ሠልፍ እያካሄዱ የተወሰኑ አባሎቻቸውም የረሃብ አድማ እያደረጉ ይገኛሉ።

በግንቦት ወር ወደ ሕክምና ትምህርት ቤቶች ለሚገቡ ተማሪዎች የሚሰጠው ፈተና ሾልኮ ከወጣ በኋላ ተቃዋሚ ሠልፈኞቹ የትምህርት ሚኒስትሩ ዳህርሜንድራ ፕሬዳን ከሥልጣን እንዲወርዱ እየጠየቁ ሲሆን ይገኛሉ።

ሠልፈኞቹ ሚኒስትሩ የሞራል ኃላፊነት ወሰደው ስራቸውን መልቀቅ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።