በበርሊን የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን በተሰበሰቡበት ጥቃት የፈጸመው ተጠርጣሪ መገደሉ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በበርሊን የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን በተሰባሰቡበት ክብረ በዓል ላይ "እስላማዊ የሽብር ጥቃት" አድርሷል ተብሎ የተጠረጠረ ግለሰብን ተኩሶ መግደሉን ፖሊስ አስታወቀ።
ተጠርጣሪው የ21 ዓመት ወጣት የሊባኖስ ዝርያ ያለው ጀርመናዊ አብዱል ባላውት እንደሚባል ፖሊስ ይፋ ያደረገ ሲሆን በምዕራብ በርሊን ስፓናዱ በተገኙበት ወቅት ቢላ ይዞ ወደ እነርሱ መሮጡን ተናግረዋል።
ፖሊስ ግለሰቡ ቅዳሜ ምሽት በቲየርጋርተን መናፈሻ ስፍራ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ያሽከረክረው የነበረውን ነጭ መኪና በፍጥነት በመንዳት ቢያንስ 29 ሰዎች ካቆሰለ እና አንዲት ሴት ከገደለ በኋላ ሲፈልገው ነበር።
የበርሊን ፖሊስ አክሎም መኪናው በርካታ ሰዎች ወደ ተሰበሰቡበት ዘልቆ ከገባ በኋላ በርካቶች በስለት በመወጋት ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የጀርመን አገር ውስጥ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዶብሪንድት እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልለስ ማስረጃዎች የሚጠቁሙት "እስላማዊ የሽብር ጥቃት" መሆኑን ነው ብለዋል።
ዶብሪንድት "ቀደም ሲል ከፍተኛ ወንጀሎችን፣ አክራሪነትን እና ከእስላማዊ ቡድኖች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ትኩረትን ወደ ራሱ ስቦ ከነበረው ተጠርጣሪ ወንጀለኛን እያደንን ነው" ብለው ነበር።
የበርሊን አቃቤ ሕግ ቢሮ ባወጣው መግለጫ ደግሞ ስለ ባላውት የወንጀል ታሪክ ተጨማሪ ዝርዝሮችን ይፋ አድርጓል።
እንደ አውሮፓውያኑ በግንቦት 2025 አቃቤ ሕግ በቱርክ በኩል ወደ ሊባኖስ እንደተጓዘ እና በሶሪያ ውስጥ ያለውን የእስላማዊ መንግሥት ቡድን (አይኤስ) ለመቀላቀል አስቦ እንደነበር ተናግሯል። በሊባኖስ እያለ የአይኤስ አባላት እንደሆኑ ከሚያምናቸው በርካታ ግለሰቦች ጋር መገናኘቱ ተነግሯል።
እአአ በሐምሌ 2025 በሊባኖስ ተይዞ የሃይማኖትና የጎሳ ግጭትን በማነሳሳት ለሦስት ወራት እስራት ተፈርዶበታል።
ከዚያም በኅዳር ወር 2025 ወደ ጀርመን ተመልሶ በበርሊን ብራንደንበርግ አየር ማረፊያ ተይዞ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት በእስር ቤት ቆይቷል።
በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ላይ "አገርን አደጋ ላይ የሚጥል ከባድ የአመፅ ድርጊት በማዘጋጀት" በሚል ለአንድ ዓመት ከ10 ወር እስራት ተፈርዶበታል። ውሳኔው ለስድስት ወራት እንዲዘገይ ሆኖ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲቆይ ተደረጓል።
ቀደም ሲል እአአ በ2022 ጥቃት በማድረስ እና ዝርፊያ በመፈጸም እና በ2020 ደግሞ የጆሮ ማዳመጫ ያደረገ ግለሰብን በመዝረፍ ጥፋተኛ ሆኖ ተፈርዶበታል።

የፎቶው ባለመብት, Polizei Berlin
ዶብሪንድት ጥቃቱን ተከትሎ የጀርመን ስጋት ደረጃ ከፍ እንደሚል፣ ሌሎች አገራትም ስለ ጥቃቱ ገለጻ እየተደረገላቸው መሆኑን እና ለዋና ዋና ክስተቶች የደህንነት እርምጃዎቻቸውን እንዲገመግሙ መክረዋል።
እሁድ ዕለት የጀርመን ቻንስለር ፍሬድሪክ መርዝ ጥቃቱ የተፈፀመበትን ቦታ ቲየርጋርተን መናፈሻን ጎብኝተዋል።
በኋላም ተጎጂዎች ለማሰብ በተዘጋጀ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር "የመኖር ነፃነትን ለመጠበቅ" ቃል ገብተዋል።
"እነዚህ ጽንፈኞች በኅብረተሰባችን ውስጥ ቦታ የላቸውም" ሲሉ ጀርመን "የሽብርተኝነት መርዝ" በኅብረተሰቧ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር አትፈቅድም ብለዋል።















