ኤል ኒኖ “አንድ ፐርሰንት እንኳ የሚያክል ጫና ሳይፈጥር ነው ያለፈው” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ አፍሪካ ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የተገመተው ኤል ኒኖ “አንድ ፐርሰንት እንኳ የሚያክል ጫና ሳይፈጥር ነው ያለፈው” አሉ።
ከባድ የሆነ አየር ሁኔታን የሚፈጥረው ኤል ኒኖ፣ ከመጠን በላይ የሆነው የውሃ መጠን እንዲኖር ወይም የእርጥበት በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ የሚያደርግ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው። የዘንድሮው የኤል ኒኖ ክስተት በታሪክ ከተመዘገቡት ጠንካራው እንደሚሆን ተገምቷል።
የኤል ኒኖ ተጽዕኖ ከፍተኛ ይሆንበታል በተባለው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ይህ የአየር ሁኔታ ከሚያጋጥማቸው አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች።
በዛሬው የፓርላማ ውሎ ስለዚህ ጉዳይ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ኤል ኒኖ “ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ድርቅ እና ሞት ያስከትላል የሚል ትንበያ ነው የነበረው” ብለዋል። መንግሥትም፣ አስቀድሞ “ሰፊ ዝግጅት” ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ከዝግጅቶቹ መካከል፣ “ቆላማ አካባቢ በፍጥነት የሚደርሱ ምርቶች አዳዲስ ዝርያዎች ማምጣት፣ መኖ በስፋት በማምረት፣ በስፋት ሊመረት የሚችልባቸው አካባቢዎች ደግሞ በደንብ መሥራት” እንደሚገኙበት ዝርዝረዋል።
አክለውም፣ “ኤልኒኖ ያደርሳል የተባለው ጉዳት እንደው ዜሮ ነው ባልላችሁ፣ አንድ ፐርሰንት እንኳ የሚያክል ጫና ሳይፈጥር ነው ያለፈው፤ ይህም በቂ ዝግጅት በማድረጋችን” ሲሉ ተናግረዋል።
የዝናብ እጥረት የሚያስከትል የኤል ኒኖ ክስተት ከተፈጠረ በኋላ “ውሃ በዝቶ ጎርፍ ያስከትላል” የሚል ስጋት መኖሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን ለመከላከል “ባለፉት ወራት የውሃ ማቆያ ቦታዎች እና ጥንቃቄዎች በስፋት” መሠራታቸውን ተናግረዋል።
“ኤልኒኖ በምዕራቡ አካባቢ ቡና፣ ስንዴ፣ ሩዝ የሚመረትባቸው አካባቢ ከፍተኛ ዝናብ ነው ያለው፤ የዝናብ ችግር የለም። ቆላማ አካባቢዎች ደግሞ አንዳንድ የተለዩ ቦታዎች ደግሞ ከፍተኛ የዝናብ እጥረት ነበር። ያንን ጊዜ አልፈነዋል” ብለዋል።
- ተያያዥ ዘገባዎች ፦







