እስራኤል የዩኬን ውሳኔ በመቃወም የአጸፋ እርምጃ ወሰደች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዩናይትድ ኪንግድም በዌስት ባንክ የሚካሄዱ ሕገ ወጥ የእስራኤል ሰፈራዎችን በመቃወም ከሰፈራዎቹ በሚወጡ ምርቶች ላይ እገዳ መጣሏን ተከትሎ እስራኤል የአጸፋ እርምጃ በዩኬ ላይ መውሰዷን አስታወቀች።
የዩናይትድ ኪንደግም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድ ሚሊባንድ በአገራቸው ምክር ቤት ቀርበው ይፋ እንዳደረጉት ከሕገ ወጥ የሰፈራ አካባቢዎች በሚወጡ ምርቶች ላይ እገዳ መጣሉን እና ተጨማሪ የቅጣት እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ በሰዓታት ውስጥ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳአር ለዩኬ እርምጃ አጸፋ አራት ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን ይፋ አድርገዋል።
- በዚህም በኢየሩሳሌም የሚገኘው የብሪታኒያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት እንዲዘጋ
- በደቡባዊ እስራኤል በሚገኘው የጋዛ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ማዕከል ውስጥ የሚገኙ የብሪታኒያ ተወካዮች ለቀው እንዲወጡ
- በዌስት ባንክ የፍልስጤም አስተደዳር ኃይሎችን የማሠልጠን የብሪታኒያ ተሳትፎ እንዲቋረጥ
- 12 የብሪታኒያ እንደራሴዎች እና በፀረ እስአኤል እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉ ሌሎች የብሪታኒያ ዜጎች ወደ እስራኤል እንዳይገቡ የሚከለክል ውሳኔ ተላልፏል።
የእስአኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጨምረውም “ከእስራኤል በተቃራኒ እርምጃ በሚወስዱ ወይም በወሰዱ” እንዲሁም የዩኬ ዓይነት ውሳኔን በሚያሳልፉ ሌሎች አገራት ላይም አገራቸው የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ገልጸዋል።
"እኛን ለሚጎዱ ለሁሉም ይህ መልዕክት ግልጽ ነው፤ በእስራኤል ላይ ጎጂ እርምጃ የሚወስድ ማንም ወገን በቀጣናው ያለውን ተጽእኖ እና ተቀባይነት ያጣል” ሲሉ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል።










