ኢራን የአሜሪካን የጦር መርከቦች ዒላማ የማድረግ አቅም እንዳላት ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, US Navy via Reuters
ኢራን የአሜሪካን የጦር መርከቦች ዒላማ የማድረግ አቅም እንዳላት የአገሪቱ ተጠባባቂ መከላከያ ሚኒስትር ማጅድ ኢብንኢረዛ አስታወቁ።
ባለፉት ጥቂት ቀናት በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ ሁለት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የኢራን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ኢራን በጦር መርከቦቹ ላይ ጥቃት ያደረሰችው ፀረ መርከብ አውዳሚ ሚሳዔል በመጠቀም መሆኑን አስታውቃለች።
የኢራን ሉዓላዊ ብሔራዊ ፀጥታ ምክር ቤት ጸሐፊ ሞሼን ረዚይ እንዳሉት ባለፉት 48 ሰዓታት የኢራን ጦር “ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ የጦር መርኮች ላይ የኢራን ፀረ መርከብ ሚሳዔል ሞክራለች”።
“ይህ ሚሳዔል ለአሜሪካውያን ገሀነም ሆኖባቸው ሸሽተዋል” ብለዋል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ለኢራን ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም።
ሆኖም ትናንት ባወጣው ጽሑፍ “ለአብዮታዊ ዘቡ የሚተላለፈው መልዕክት ግልጽ ነው። ሁለት መርከቦቻችን ላይ ከተሶሳችሁ፣ ሦስት መርከቦቻችሁን እናወድማለን በምጣኔ ሃብትም የላቀ ዋጋ እናስከፍላችኋለን” ብሏል።
ማዕከላዊ ዕዙ “የአሜሪካ ጦር ከመከላከል ወደኋላ አንልም። አስፈላጊ ከሆነ የኢራንን ውስን እና ስሱ የነዳጅ ታንከር እናወድማለን” ሲልም አክሏል።





