ቀጥታ, ዩኬ በእስራኤል ሰፈራዎች ላይ ማዕቀብ በመጣል፣ ሰፋሪዎችን ‘በዘር ማጽዳት’ ከሰሰች

የዩናይትድ ኪንግድም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድ ሚሊባንድ አገራቸው ሕገ ወጥ ከሆነው የምዕራብ ዳርቻ (ዌስት ባንክ) የእስራኤል ሰፈራዎች የሚመጡ ምርቶች ላይ እገዳ መጣሉን እና ተጨማሪ የቅጣት እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታወቁ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. እስራኤል የዩኬን ውሳኔ በመቃወም የአጸፋ እርምጃ ወሰደች

    ዩናይትድ ኪንግድም በዌስት ባንክ የሚካሄዱ ሕገ ወጥ የእስራኤል ሰፈራዎችን በመቃወም ከሰፈራዎቹ በሚወጡ ምርቶች ላይ እገዳ መጣሏን ተከትሎ እስራኤል የአጸፋ እርምጃ በዩኬ ላይ መውሰዷን አስታወቀች።

    የዩናይትድ ኪንደግም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድ ሚሊባንድ በአገራቸው ምክር ቤት ቀርበው ይፋ እንዳደረጉት ከሕገ ወጥ የሰፈራ አካባቢዎች በሚወጡ ምርቶች ላይ እገዳ መጣሉን እና ተጨማሪ የቅጣት እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

    ይህንንም ተከትሎ በሰዓታት ውስጥ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳአር ለዩኬ እርምጃ አጸፋ አራት ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን ይፋ አድርገዋል።

    • በዚህም በኢየሩሳሌም የሚገኘው የብሪታኒያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት እንዲዘጋ
    • በደቡባዊ እስራኤል በሚገኘው የጋዛ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ማዕከል ውስጥ የሚገኙ የብሪታኒያ ተወካዮች ለቀው እንዲወጡ
    • በዌስት ባንክ የፍልስጤም አስተደዳር ኃይሎችን የማሠልጠን የብሪታኒያ ተሳትፎ እንዲቋረጥ
    • 12 የብሪታኒያ እንደራሴዎች እና በፀረ እስአኤል እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉ ሌሎች የብሪታኒያ ዜጎች ወደ እስራኤል እንዳይገቡ የሚከለክል ውሳኔ ተላልፏል።

    የእስአኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጨምረውም “ከእስራኤል በተቃራኒ እርምጃ በሚወስዱ ወይም በወሰዱ” እንዲሁም የዩኬ ዓይነት ውሳኔን በሚያሳልፉ ሌሎች አገራት ላይም አገራቸው የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ገልጸዋል።

    "እኛን ለሚጎዱ ለሁሉም ይህ መልዕክት ግልጽ ነው፤ በእስራኤል ላይ ጎጂ እርምጃ የሚወስድ ማንም ወገን በቀጣናው ያለውን ተጽእኖ እና ተቀባይነት ያጣል” ሲሉ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል።

  2. ዩኬ በእስራኤል ሰፈራዎች ላይ ማዕቀብ በመጣል፣ ሰፋሪዎችን ‘በዘር ማጽዳት’ ከሰሰች

    የዩናይትድ ኪንግድም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድ ሚሊባንድ አገራቸው ሕገወጥ ከሆኑት የምዕራብ ዳርቻ (ዌስት ባንክ) የእስራኤል ሰፈራዎች በሚመጡ ምርቶች ላይ እገዳ መጣሏን እና ተጨማሪ የቅጣት እርምጃዎችን መውሰዷን አስታወቁ።

    ሚሊባንድ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ፓርላማ የታችኛው ምክር ቤት ቀርበው እንደገለጹት ከእስራኤል ወደ አገሪቱ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተጣለውን እገዳ ይፋ በደረጉበት ጊዜ “የብሪታንያ ሕዝብ በመደብሮቻችን ውስጥ [ከእስራኤል] ሰፈራዎች የሚመጡ ምርቶችን በመቀበል ወረራውን እንድንደግፍ አይፈልግም” ብለዋል።

    በተጨማሪም “ሁሉን አቀፍ የማዕቀብ ሥርዓት” እንደሚዘረጋ ገልጸው፣ በውስጡም “ተገቢ የሃይማኖት ልዩ ፈቃዶች” እንደሚካተቱ ተናግረዋል።

    ሕገ ወጥ ሰፈራዎችን የሚያመቻቹ ወይም የሚደግፉ ግለሰቦችን በመለየት “የዩኬ የማዕቀብ ቅጣት ተግባራዊ ይደረግባቸዋል” ብለዋል።

    መንግሥታቸው በምዕራብ ዳርቻ አካባቢዎች የዘር ማጽዳት እየተፈጸመ እንደሆነ እንደሚስማማ ገልጸው፣ “ሰፋሪ ሽብርተኞች” ፍልስጤማውያንን ከመሬታቸው እያፈናቀሉ መሆኑን ተናግረዋል። እንዲሁም “በአብዛኛው የእስራኤል መንግሥት ይህንን ድርጊት እንዳላየ ያልፈዋል” ብለዋል።

    ጨምረውም መንግሥታቸው የእስራኤል የምዕራብ ዳርቻ ወረራ “ሕገ-ወጥ” ነው የሚል አቋም እንዳለውም ተናግረዋል።

    “የብሪታንያ መንግሥት ይፋዊ አቋም እስራኤል ቁጥጥሯን በማጠናከር፣ ቋሚ የሉዓላዊነት ግዛት ለማስፋፋት ያላት ፍላጎት እና በሕገ ወጥ ሰፈራዎች አማካይነት በምታራምደው የመስፋፋት አጀንዳ ምክንያት ወረራው ሕገወጥ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

    በተጨማሪም በብሪታንያ ውስጥ ሕገወጥ የምዕራብ ዳርቻ ሰፈራዎችን ማስተዋወቅ እንደሚከለከል አስታውቀዋል።

    ሚኒስትሩ እንዳሉት ይህ ይፋ የተደረገው “ማዕቀብ ዒላማ የሚያደርገው እስራኤልን ሳይሆን፣ ሕገወጥ ሰፈራዎችን እና የሰፈራ መስፋፋትን ነው።”

    ሚሊባንድ በተጨማሪ በፍልስጤም ማኅበረሰቦች ላይ ጥቃትን የደገፉ ወይም ያነሳሱ “ጽንፈኛ ሰፋሪዎች” ላይ አዳዲስ ቅጣቶች እየተጣሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

    “እንዲሁም ነባሩን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች አሠራርን በማጠናከር የሰፈራዎችን መስፋፋት በተለይም ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የታቀደውን የሰፈር ልማት ለመከላከል እና ለመግታት ፈጣን እርምጃ ይፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

  3. በዓለም ከፍተኛው ተከፋይ የሆኑት መሪ 1 ሚሊዮን ዶላር ደመወዝ ሊጨመርላቸው ነው

    የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሌሎችም ሚኒስትሮች ደመወዝ ሊጨመርላቸው እንደሆነ ተገለጸ።

    የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ሎውረንስ ዎንግ በዓለም ከፍተኛው ክፍያ የሚሰጣቸው መሪ ናቸው። ደመወዛቸው በዓመት በ1.1 ሚሊዮን ዶላር እንደሚጨምርም ተገልጿል።

    የሚደረግላቸውን የደመወዝ ጭማሪ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ለእርዳታ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የሚኒስትሮችን ደመወዝ መጨመር ያስፈለገው ችሎታ ያላቸው ባለሥልጣናትን ወደ ኃላፊነት ለመሳብ ነው።

    ከዚህ ቀደም የሲንጋፖር መንግሥት ለባለሥልጣናት ከፍተኛ ደመወዝ መስጠት ሙስናን እንደሚያስወግድ አስታውቋል።

    የደመወዝ ጭማሪው ትችት ገጥሞታል። በተለይም ከሥራ ደኅንነት እና ከኑሮ ውድነት አንጻር ትችቶች እየተሰሙ ነው።

    የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር የደመወዝ ጭማሪ ሳይደረግላቸውም በፊት በዓለም ላይ ከፍተኛ ክፍያ የሚያገኙ የፖለቲካ መሪ ናቸው።

    አሁን ላይ ዓመታዊ ደመወዛቸው 2.2 ሚሊዮን የሲንጋፖር ዶላር ሲሆን በተደረገላቸው ጭማሪ ደመወዛቸው 60% በመቶ አድጎ 3.6 ሚሊዮን የሲንጋፖር ዶላር (2.8 ሚሊዮን ዶላር) ደርሷል።

    ከሲንጋፖር ቀጥሎ ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፈለው ለሆንግ ኮንግ ዋና መሪ ጆን ሊ ነው። ደመወዛቸው 719,000 ዶላር ይደርሳል። በሦስተኛ ደረጃ የስዊትዘርላንድ ፕሬዝዳንት ጋይ ፓርሚሊን ሲሆኑ 606,000 ዶላር ያገኛሉ።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዓመታዊ ደመወዝ 400,000፣ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ ቡርንሀም ደመወዝ ደግሞ 230,000 ዶላር ነው።

  4. የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች ሳዑዲ ውስጥ 73 ሰዎች መጎዳታቸው ተገለጸ

    በየመን የሚገኘው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራ ጥምር ጦር፣ በኢራን የሚደገፈው የየመን ታጣቂ ቡድን ሁቲ ተዋጊዎች በሳዑዲ ላይ በፈጸሙት ጥቃቶች ቢያንስ 73 ሰዎች መጎዳታቸውን አስታወቀ።

    ጥቃቶቹ መቼ እንደተፈጸሙ በግልጽ ባይነገርም የጥምረቱ ጦር ለእነዚህ የሁቲ ታጣቂዎች ጥቃቶች ጠንካራ ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጿል።

    በየመን በርካታ ሕዝብ የሚኖርባቸውን አካባቢዎችን እንዲሁም የአገሪቱን ሰሜናዊ አብዛኛውን ከፍል የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች፣ ሐምሌ ወር በሳዑዲ ላይ የባሕር ላይ እንቅስቃሴ እገዳ መጣላቸውን ካስታወቁ በኋላ ጥቃቶችን ሲፈጽሙባት ቆይተዋል፤ በቀይ ባሕር ላይ የሚንቀሳቀሱ መርከቦቿንም ዒላማ አድርገዋል።

    በየመን በሳዑዲ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ቱርኪ አል ማሊኪ በቅርቡ የተባባሰውን ግጭት “አደገኛ” ሲሉ ገልጸው፣ ሁቲዎቹ በዓለም ትልቋ የነዳጅ ላኪ እና በኦፔክ ውስጥ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆነችውን የሳዑዲ አረቢያን ሲቪል እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን ዒላማ እንዳደረጉ ገልጸዋል።

    ሁቲዎቹ በሳዑዲ ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች ጂዛን እና ናጅራንን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ያሉ ዒላማዎችን ማጥቃታቸው ተዘግቧል።

    ፋይናንሻል ታይምስ እንደዘገበው፣ በጂዛን የሚገኙ የአራምኮ የነዳጅ ተቋማት በአዲስ ጥቃት ዒላማ የተደረጉ ሲሆን፣ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ እየተገመገመ ነው። አራምኮ በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።

    የሳዑዲ ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በሁቲዎች የተፈጸሙት ጥቃቶች "በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት" ማድረሳቸውን እና ጥቃቶቹ ባስነሱት የእሳት ቃጠሎም "በበርካታ ስፍራዎች ላይ ሥራዎች እንዲቋረጡ" ምክንያት ሆኗል ብሏል።

    የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁቲዎች የፈጸሙትን እና "በይ ባሕር ላይ የንግድ መርከቦችን ዒላማ በማድረግ" የቀጠሉትን ጥቃቶች አውግዟል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ተገቢውን የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎችን ተግባራዊ በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል።

  5. ትራምፕ የካናዳውን አውሮፕላን አምራች የአሜሪካ ገበያ ለማቆም ዛቱ

    የካናዳው አውሮፕላን አምራች ቦምባርዲየር ተቋሙን ወደ አሜሪካ ካላዘዋወረ በስተቀር በአሜሪካ ምርቶቹን መሸጥ እንደማይችል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስጠነቀቁ።

    “ከዚህ በኋላ ቦምባርዲየር በአሜሪካ አይሸጥም። ገበያችንን ከፈለጉ እዚህ መጥተው ማምረት ይችላሉ። አሜሪካ ላይ መንጠልጠል አቁሙ” ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ጽፈዋል።

    በአሜሪካ እና ካናዳ መካከል ያለው የንግድ ጦርነት እየተባባሰ መጥቷል።

    ትራምፕ አውሮፕላን አምራቹን እንደሚያግዱ የገለጹት ካናዳ በዋሽንግተን ለተጣለባት ታሪፍ የአጸፋ ታሪፍ ለመጣል ሰዓታት ሲቀራት ነው።

    ካናዳ በአሜሪካ ምርቶች ላይ 20 በሊዮን ዶላር የሚያወጣ ታሪፍ ለመጣል አቅዳለች።

    አውሮፕላን አምራቹ ባወጣው መግለጫ በሺህዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ሠራተኞች እንደቀጠረ አስታውቋል። ከአሜሪካ ተቋማት ጋር ላለው ትስስር ዋጋ እንደሚሰጥም ጠቅሷል።

    ትራምፕ አውሮፕላን አምራቹን በምን መንገድ ከአሜሪካ ገበያ እንደሚያግዱ ግልጽ አይደለም።

    መቀመጫው በካናዳ ሞንትሪያል ቢሆንም በአሜሪካ ካንዛስ ግዛት ፋብሪካ አለው።

    በዚህ ፋብሪካ 3,500 አሜሪካውያን ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፤ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ያመርታል።

    በቴክሳስ፣ አሪዞና፣ ፍሎሪዳ፣ ኮነትኬት፣ ኤልኖይስ፣ ዳላዌር፣ ካሊፎርንያ፣ ዲሲ እና ኒው ጀርሲም ይሠራል።

    ቢቢሲ ከካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ቢሮ ምላሽ ጠይቋል።

  6. ኢራን የአሜሪካን የጦር መርከቦች ዒላማ የማድረግ አቅም እንዳላት ገለጸች

    ኢራን የአሜሪካን የጦር መርከቦች ዒላማ የማድረግ አቅም እንዳላት የአገሪቱ ተጠባባቂ መከላከያ ሚኒስትር ማጅድ ኢብንኢረዛ አስታወቁ።

    ባለፉት ጥቂት ቀናት በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ ሁለት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የኢራን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

    ኢራን በጦር መርከቦቹ ላይ ጥቃት ያደረሰችው ፀረ መርከብ አውዳሚ ሚሳዔል በመጠቀም መሆኑን አስታውቃለች።

    የኢራን ሉዓላዊ ብሔራዊ ፀጥታ ምክር ቤት ጸሐፊ ሞሼን ረዚይ እንዳሉት ባለፉት 48 ሰዓታት የኢራን ጦር “ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ የጦር መርኮች ላይ የኢራን ፀረ መርከብ ሚሳዔል ሞክራለች”።

    “ይህ ሚሳዔል ለአሜሪካውያን ገሀነም ሆኖባቸው ሸሽተዋል” ብለዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ለኢራን ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም።

    ሆኖም ትናንት ባወጣው ጽሑፍ “ለአብዮታዊ ዘቡ የሚተላለፈው መልዕክት ግልጽ ነው። ሁለት መርከቦቻችን ላይ ከተሶሳችሁ፣ ሦስት መርከቦቻችሁን እናወድማለን በምጣኔ ሃብትም የላቀ ዋጋ እናስከፍላችኋለን” ብሏል።

    ማዕከላዊ ዕዙ “የአሜሪካ ጦር ከመከላከል ወደኋላ አንልም። አስፈላጊ ከሆነ የኢራንን ውስን እና ስሱ የነዳጅ ታንከር እናወድማለን” ሲልም አክሏል።

  7. እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ባደረሰችው የአየር ጥቀት ቢያንስ 12 ሰዎች ተገደሉ

    እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በሚገኙ መንደሮች ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ 12 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ሁለት ሕጻናት እና አራት ሴቶችን ጨምሮ 11 ሰዎች የተገደሉት በካፍር ሮማን መንደር መኖሪያ ሕንጻ ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት ነው።

    የእስራኤል ጦር በበኩሉ የሄዝቦላህ መሠረተ ልማት ላይ አነጣጥሮ ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል።

    ከሄዝቦላህ በተጨማሪ “በርካታ አሸባሪዎችን” ዒላማ እንዳደረገ ጦሩ ገልጿል። በይዞታ ሥር በሚገኝ የሊባኖስ አካባቢ ለተፈጸመ የድሮን ጥቃት በምላሹ እነዚህ ቡድኖች መሣሪያ ሲያዘዋውሩ ነበር ብሏል።

    ባለፉት ሦስት ቀናት እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ 27 ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

    የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን “አደገኛው የግጭት መባባስ” በሰኔ ላይ በአሜሪካ አማካኝነት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ያደናቅፋል ብለዋል።

    ሰኔ ላይ በሄዝቦላህ እና እስራኤል መካከል ግጭት የማቆም ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።

    የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል የምታደርሰውን ጥቃት እንድታቆም ጫና እንዲያሳድር አሳስበዋል።

  8. ኢራን ለአሜሪካ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጠች

    ኢራን በአሜሪካ የሚፈጸምባት ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ እሷም አጸፋውን በመመለስ በአሜሪካ ዒላማዎች ላይ እንደምትመልስ ከፍተኛ ባለሥልጣኗ ተናገሩ።

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ እና ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር ዋነኛ ተደራዳሪ የሆኑት ሞሐመድ ባጊር ጋሊባፍ፣ ለአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት አስተያየት በሰጡት ምላሽ ኢራን የሚፈጸሙባትን ጥቃቶች በዝምታ እንደማታልፍ ገልጸዋል።

    "ጉዳዩ ቀላል ነው፤ በዚህ አካባቢ ያለው የዘይት እና የጋዝ ምርት ሰንሰለት ሰፊ፣ በቀላሉ የሚደረስበት እና ለጥቃት የተጋለጠ ነው። በቀጣናው ባሉ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ የነዳጅ እና የጋዝ ኩባንያዎችም እንዲሁ ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው" ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

    "ንብረቶቻችንን ካጠቃችሁ እናንተም ትመታላችሁ። ይህን አስቀድመን አሳይተናል። ከጥቅም ውጪ የሆኑትን የወታደራዊ ጣቢያዎቻችሁን ተመልከቱ" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

    ጋሊባፍ ከመልዕክታቸው ጋር የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ያስተላለፉትን መልዕክት አያይዘዋል።

    የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትሩ ከሁለት ቀናት በፊት በኤክስ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ "ጉዳዩ ቀላል ነው፤ ኢራን በአሜሪካ መርከቦች ላይ ከተኮሰች የእርሷን ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን እናጠፋቸዋለን (እንሰጥማቸዋለን)። ማድረግ ያለባት አንድ ነገር ብቻ ነው፤ በአሜሪካ ባሕር ኃይል ላይ አትተኩስ" ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።

  9. የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ባለቤት ሕይወታቸው አለፈ

    የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን ባለቤት የሆኑት ሀፊድ አሜር ሀሰን፣ እዚያው ታንዛኒያ ዛንዚባር ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተሰጣቸው እያለ ሕይወታቸው አለፈ።

    የአሜርን ሕልፈት ይፋ ያደረጉት የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ዴኦግራቲየስ ንዴጀምቢ እንደገለጹት፣ የፕሬዝዳንቷ ባለቤት የልብ ሕመም አጋጥሟቸው ነበር።

    የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ከፊል ራስ-ገዝ ደሴት በሆነችው ዛንዚባር በምትገኘው ኪዚምካዚ መንደር እየተዘጋጀ መሆኑንም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

    የግብርና ምሁር የሆኑት አሜር ባለቤታቸው ሳሚያ ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ቢሆኑም እርሳቸው ግን ለሕዝብ ዕይታ የቀረበ ሕይወት አልነበራቸውም።

    እምብዛም በአደባባይም ከፕሬዝዳንቷ ጎን አይታዩ የነበሩት አሜር፣ አልፎ አልፎ ብቻ በኦፊሴላዊ ኹነቶች ላይ አብረዋቸው ይገኙ ነበር።

    አሜር ከሳሚያ ጋር ትዳር የመሠረቱት ፕሬዝዳንቷ ወደ ፖለቲካ ከመግባታቸው በፊት በአውሮፓውያኑ 1978 ነው። ሦስት ወንዶች እና አንዲት ሴት ልጅ በድምሩ አራት ልጆችን አሏቸው።

    ሴት ልጃቸው ዋኑ ሀፊድ አሜርም ፖለቲከኛ ስትሆን፣ በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ምክር ቤት ውስጥ የዛንዚባር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነች።

  10. የነዳጅ ዋጋ በሳምንት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ

    አሜሪካ በኢራን ላይ ዳግም ጥቃት በመክፈቷ ያገረሸውን የጥቃት ምልልስ ተከትሎ እየጨመረ የመጣው የነዳጅ ዋጋ ዛሬ ሰኞ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።

    ባለፉት ቀናት አሜሪካ እና ኢራን በፋርስ ባሕረ ሰላጤ በሚተላለፉ ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን፣ ይህም በወሳኙ የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ቁጥርን በከፍተኛ መጠን ቀንሷል።

    ዛሬ ጠዋት በምሥራቅ እስያ በዋለው የነዳጅ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ የአሜሪካ ጥቃት ከመጀመሩ በፊት ከነበረበት ወደ 10 ዶላር ያህል ጭማሪ አሳይቷል።

    የነዳጅ ዋጋ መተመኛ በሆነው ብሬንት የነዳጅ ዓይነት በሰኞ ጠዋት አንድ በርሜል ዋጋው ወደ 97 ዶላር ተጠግቷል።

    በኢራን እና አሜሪካ መካከል እየተካሄደ ያለው አዲሱ የወታደራዊ ግጭት ባለፈው ሳምንት ከመቀስቀሱ ቀደም ብሎ በነበሩት ቀናት በተመሳሳይ አንድ በርሜል ነዳጅ 86 ዶላር ገደማ ነበር።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከፍተው ጦርነቱ በቀጠለበት ባለፉት ስድስት ወራት የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ መጥቷል።

    ለዚህም ምክንያቱ ኢራን የተከፈተባትን ጥቃት ተከትሎ የዓለም 20 በመቶ የነዳጅ ፍጆታ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷ ነው።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ እንደተናገሩት አሜሪካ እና እስራኤል በአገራቸው ላይ "ወረራ ከመክፈታቸው በፊት ሆርሙዝ ሙሉ በሙሉ ክፍት ነበር። አሜሪካ ሕገ ወጥ እና ጨካኝ ጦርነት በመክፈቷ መደበኛው የባሕር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል" ብለዋል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ በሚፈጸመው ጥቃት ምክንያት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ለመቆም የተገደዱ ሲሆን በዚህም ምክንያት የነዳጅ እና ሌሎች ምርቶች ዋጋ ዋጋ በእጅጉ አሻቅቧል።

  11. ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ ፀረ አውዳሚ መርከብ የሆነ ሚሳዔል አሜሪካ ላይ መጠቀሟን ገለጸች

    ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ “በአሜሪካ መርከቦች ላይ ፀረ አውዳሚ መርከብ ሚሳዔል” ጥቅም ላይ ማዋሏን የአገሪቱ ጠቅላይ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊ ሞህሴን ረዛኢ ተናገሩ።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ በአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ የባለስቲክ ሚሳዔል ጥቃት መፈጸሙን አስታውቆ ነበር። ይህ ጥቃት የተፈጸመው የአሜሪካ ጦር የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን በመምታቱ እና በአገሪቱ ላይ የባሕር እገዳ በመጣሉ እንደሆነ ተገልጿል።

    የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊው በኢራን ቴሌቪዥን ጣቢያ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “ከ48 ሰዓታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የኢራን ፀረ-አውዳሚ መርከብ ሚሳኤልን በአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ ሞክረናል። ይህ ሚሳዔል ለአሜሪካውያኑ ሲኦል ፈጥሮባቸዋል፤ ሸሽተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ለዚህ የኢራን ገለጻ በቀጥታ ምላሽ አልሰጠም። ይሁን እንጂ ዕዙ ትናንት እሁድ በኤክስ ገጹ ባጋራው ልጥፍ፣ በሁለት መርከቦቹ ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት በተዘዋዋሪ ጠቅሷል።

    “ለኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሚተላለፈው መልዕክት ግልጽ ይሁን፤ ሁለት መርከቦቻችን ላይ ተኩስ ከከፈታችሁ፣ እጅግ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንጥልባችኋለን፤ ሦስት መርከቦቻችሁንም እናወድማለን” ብሎ ነበር።

    ማዕከላዊ ዕዙ አክሎም “የአሜሪካ ኃይሎችን ለመከላከል አናመነታም፤ አስፈላጊም ከሆነ የተወሰነውን እና ተጋላጭ የሆነውን የኢራን የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ስብስብ ሙሉ በሙሉ እናወድማለን” በማለትም አስጠንቅቋል።

    አሜሪካ ቅዳሜ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኙ ሦስት ኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን መምታቷን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባሕር ኃይል ቅዳሜ ዕለት አስታውቆ ነበር።

    ኢራንም በምላሹ ባልተፈቀደ የሆርሙዙ መተለላፊያ በኩል ሲጓዙ ነበር እንዲሁም በሌሎች ስፍራዎች ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸው መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገልጿለች።

    ቃለ መጠይቅ የሰጡት የኢራን የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊው ረዛኢ ለመርከብ ጉዞ የተከለከለ የባህር ቀጠና ስለማቋቋም ተናግረዋል። “በሚቀጥሉት ቀናት ከአሜሪካ የከበባ መስመር እስከ መጫኛ ወደቦች ያለውን ርቀት የሚያካትት አዲስ ለመርከብ ጉዞ የተከለከለ ቀጠና ይፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

    እንደ ዋና ጸሐፊው ገለጻ ሆርሙዝ የትኛውም አቅጣጫዎች “የሚንቀሳቀስ እና ወደ ባህረ ሰላጤው ለመጓዝ ያሰበ የትኛውም መርከብ በኢራን የማዕቀብ ዝርዝር” ውስጥ ይካተታል።