ቀጥታ, በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ሁለተኛ ሳምንቱን ቢይዝም ጥቃቶች መቀጠላቸው ተገለጸ

እስራኤል ከሊባኖስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ብትደርስም በደቡባዊ ሊባኖስ ሐሙስ ዕለት በፈጸመችው ከባድ ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴተር አስታወቀ። እስራኤል ሐሙስ ዕለት የሄዝቦላህ መሠረተ ልማት ናቸው ባለቻቸው ስፍራዎች በፈጸመችው ድብደባ 23 ሰዎች መጎዳታቸውን እና ከእነዚህም መካከል ስምንቱ ሕጻናት፣ ሰባቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዩኤኢ፣ ኢራን በሆርሙዝ ላይ እምነት ሊጣልባት አይችልም አለች

    አንድ ከፍተኛ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለሥልጣን አርብ ዕለት ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ የምታደርገው ማንኛውም የአንድ ወገን ውሳኔ ላይ እምነት ሊጣል እንደማይችል ለሮይተርስ ተናገሩ።

    ይህም የኢራንን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት አስቸጋሪ አድርጎ ለመቆየቱ እና በሁሉም ወገኖች ዘንድ ያለውን ጥልቅ አለመተማመንን የሚያሳይ ነው ተብሏል።

    ግጭቱ ከተከሰተ ከሁለት ወራት በኋላም ወሳኝ የሆነው የባህር መተላለፊያ አሁንም በኢራን እገዳ ምክንያት በአብዛኛው የተዘጋ ሲሆን የአሜሪካ የባህር ኃይልም ወደ ኢራንን ወደብ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን አግዷል።

    እገዳው 20 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦቶችን ከማስተጓጎሉም በላይ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከፍ አድረጓል። ይህም የኢኮኖሚ መቀዛቀዝን እንዳይስከትል አስግቷል።

    ከሦስት ሳምንታት በፊት በኢራን እና አሜሪካ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ቢደረግም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቴህራን ላይ ሊሰነዘር ስለታቀደው አዲስ ጥቃት ሐሙስ ዕለት ማብራሪያ ተሰጧቸዋል።

    እቅዱ ኢራንን ወደ ድርድር ለመመለስ ያለመ ቢሆንም የነዳጅ ዋጋን በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮታል።

    ኢራን የአየር መከላከያዎቿን በተጠንቀቅ ያቆመች ሲሆን ጥቃት ከተፈጸመ ሰፊ ምላሽ ለመስጠት ዝታለች።

    በቴህራን ዘንድ አሜሪካ አጭር እና ከባድ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላል የሚል ግምገማ መኖሩን ሁለት ከፍተኛ የኢራን ምንጮች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

  2. ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ ዜጎቿ ከኢራን፣ ኢራቅ እና ሊባኖስ በአስቸኳይ እንዲወጡ አሳሰበች

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዜጎቿ ወደ ኢራን፣ ኢራቅ ወይም ሊባኖስ እንዳይጓዙ ከለከለች።

    የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ "በአሁኑ ወቅት በቀጣናው ባለው ሁኔታ የተነሳ” በማለት የጉዞ እገዳው መደረጉን አስታውቋል።

    በእነዚህ አገራት የሚገኙ ዜጎችም በፍጥነት ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እንዲመለሱ አሳስቦ ሚኒስቴሩን በስልክ እንዲያነጋግሩ ጠይቋል።

    ሚኒስቴሩ በመግለጫው ላይ የሚሰጣቸውን መመሪያዎችና ምክሮች “በሙሉ ማክበር” አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።

    እአአ ከ2021 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዜጎቿ ወደ ሊባኖስ እንዳይጓዙ ከልክላ ነበር። እገዳው የተነሳው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነው።

    የካቲት 21 2018 ዓ.ም. አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በመሆን ኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ ግጭቱ ወደ ሊባኖስ እና ኢራቅ ተዛምቷል።

    ሊባኖስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ላይ ቢደርሱም አሁንም በደቡባዊ ሊባኖስ የሚፈጸመው ጥቃት እንደቀጠለ ነው።

    በሆርሙዝ ወሽመጥም ቢሆን የመርከቦች እንቅስቃሴ እንደቆመ ሲሆን ቴህራን ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው የሰላም ውይይት ተቋርጧል።

  3. በለንደን ሁለት አይሁዳውያን ላይ በስለት ጥቃት ያደረሰው ኢሳ ሱሌይማን በግድያ ሙከራ ክስ ተመሰረተበት

    በሰሜን ምዕራብ ለንደን፣ ጎልደርስ ግሪን ሁለት አይሁዳውያን ላይ በስለት ጥቃት ያደረሰው ኢሳ ሱሌይማን በግድያ ሙከራ ወንጀል ክስ ተመሰረተበት።

    የ45 ዓመቱ ግለሰብ የግድያ ሙከራ በማድረግ እና በአደባባይ ስለት ይዞ በመገኘት ወንጀሎች ክሶች እንደተመሰረቱበት ፖሊስ አስታውቋል።

    ረቡዕ ዕለት 5 ሰዓት አካባቢ ጥቃት የደረሰባቸው የ34 ዓመቱ ሽሎይሜ ራንድ እና የ76 ዓመቱን ሞሼ ሺንን ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

    አይሁዳውያን ላይ በስለት ጥቃት ያደረሰው ሱሌይማን ዛሬ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ፖሊስ አስታውቋል።

    ሱሌይማን የተወለደው ሶማሊያ ውስጥ ሲሆን ወደ ዩኬ የመጣው እአአ በ1990ዎቹ በልጅነቱ ነበር።

    ከዚህ ቀደም እአአ በ2020 የጸረ አክራሪነት ፕሮግራም ሱሌይማን ላይ ክትትል ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ከአንድ ዓመት በኋላ መዝገቡ ተዘግቷል።

    ሐሙስ ዕለት ዩኬ ያለው የሽብር ስጋት ደረጃ ከፍ ማለቱን አስታውቃለች።

    የሽብር ስጋት ከፍ ማለቱን ተከትሎ ሕዝቡ "ንቁ እና ጠንቃቃ" እንዲሆን ነገር ግን "እንዳይረበሽ" የዩኬ የደህንነት ሚኒስትር አሳስበዋል።

  4. የብራዚል ኮንግረስ የቦልሶናሮን የእስር ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ የሚያስችል ዕቅድ አጸደቀ

    የብራዚል ኮንግረስ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጃየር ቦልሶናሮ ባለፈው ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ የመፈንቅለ መንግሥት አሲረው ነበር በሚል የተላለፈባቸውን የእስር ቅጣትን በእጅጉ የሚቀንስ ረቂቅ ሕግ ውድቅ አደረገ።

    ቦልሶናሮ በ2022 ምርጫ ከሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ከተሸነፉ በኋላ በሥልጣን ለመቆየት ባደረጉት ሙከራ 27 ዓመታት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

    የቦልሶናሮን እስር ዘመን ከሁለት ዓመት ትንሽ ከፍ ያለ ለማድረግ የቀረበውን ሃሳብ ሉላ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው ሽረውት ነበር። ሕግ አውጪዎች ሐሙስ ዕለት የእስር ቅጣቱ እንዴት ይሰላል የሚለውን የፕሬዝዳንቱን ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል።

    ሕጉ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ክርክር ሊደረግበት ይችላል።

    የ71 ዓመቱ ቦልሶናሮ በመጋቢት ወር በጤና እክል ምክንያት ለጊዜው በቤታቸው እንዲታሰሩ ተፈቅዶላቸዋል።

    ከ2019 እስከ 2022 በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት የቀድሞው የጦር ካፒቴን፣ ሉላን እና በምክትል ፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩትን ጄራልዶ አልክሚንን ለመግደል ዕቅድ ነበራቸው በሚል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

    የአገሪቱ የጦር ኃይል ከፍተኛ አመራሮች ድጋፍ ሳይደረግላቸው በመቅረቱ ሴራው ባለመሳካቱ ሉላ በጥር 2023 ቃለ መሃላ ፈጸመዋል።

    የሉላ ሃሳብ ውድቅ ከተደረገ በኋላ በርካታ የሕግ አውጪዎች 'ነፃነት' እያሉ መፈክር ያሰሙ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ለመሆን ፍላጎት ያለውን የቀድሞ መሪው የበኩር ልጅ ፍላቪዮ ቦልሶናሮን ስም ደጋግመው ጠርተዋል።

    ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑ የኮንግረሱ አባላት የቀድሞውን ፕሬዚዳንትን የእስር ጊዜ ለመቀነስ የቀረበውን ዕቅድ በመደገፍ ድምጽ ሰጥተዋል።

  5. ኢራን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በሚኖራት ድርድር ፓኪስታን ይፋዊ አደራዳሪ ሆና እንደምትቀጥል አስታወቀች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት የሰላም ውይይት ፓኪስታን ይፋዊ አደራዳሪ መሆኗን አስታወቁ።

    በርካታ አገራት ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን የሰላም ንግግር ለማመቻቸት መሞከራቸውን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ “ፓኪስታን ይፋዊ አደራዳሪያችን ናት” ብለዋል።

    “ንግግሩን ለመቀጠል ውሳኔ ላይ የሚደረስ ከሆነ በግልጽ እናሳውቃለን” ሲሉ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራጋቺ ወደ ሩሲያ ያደረጉትን ጉዞ በመጠቀስ “ኢራን እና ሩሲያ በፖለቲካ፣ ደህንነት እና ምጣኔ ሃብት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነት አላቸው። አሁን ባለው ሁኔታም ኢራን ለተለያዩ አገራት አቋሟን ግልጽ አድርጋለች” ብለዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው ከአሜሪካ የምታደርገው የሰላም ንግግር ሳይካሄድ ከቀረ በኋላ ወደ ኢዝላማባድ፣ ሙስካት እና ሞስኮ በማቅናት ከአገራቱ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ቃል አቀባዩ ከቻይና እና ሩሲያ ጋር ያላትን አገራቸው ያላትን የዲፕሎማሲ ትብብር በማስታወስ “የአንዳንድ የቀጣናው አገራት ተንኮል የተሞላበት ተግባር” በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውድቅ መደረጉን ተናግረዋል።

  6. አሜሪካ የኮንጎ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ ላይ ማዕቀቦችን ጣለች

    አሜሪካ የቀድሞው የኮንጎ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ አማፂያንን ይደግፋሉ በሚል ማዕቀብ ጣለች። ጆሴፍ ካቢላ የተከሰሱት ኤም23 እና ኤኤፍሲ የተባሉ አማፂያን ቡድኖችን በመደገፍ ነው።

    ዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞው የኮንጎ ፕሬዘዳንት ኤኤፍሲ (AFC) ለተባለው አማፂ ቡድን የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ፣ ከኮንጎ ጦር እንዲከዱ ያበረታታሉ፣ አማፂያኑ ድንበር ተሻግረው የመንግሥት ወታደሮች ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ ይደግፋሉ ስትል ወንጅላቸዋለች።

    ባለሥልጣናት የጆሴፍ ካቢላ ዓለማ ኪንሻሳን እንዳትረጋጋ ማድረግ ነው ያሉ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች የፖለቲካ ተጽዕኖ እንዲያገኙ ይጥራሉ በማለት ይከስሷቸዋል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ይፋ ባደረገው ማዕቀብ ውስጥ ካቢላ በአሜሪካ ያላቸው ንብረት ላይ እገዳ ተጥሏል።

    በማዕቀቡ ላይ የአሜሪካ ዜጎችና ኩባንያዎች አብረዋቸው ምንም ዓይነት ሥራ እንዳይሰሩ ክልከላ ተቀምጧል።

    ባንኮች እና የውጭ አጋሮች ከካቢላ ጋር በተዘዋዋሪ የሚያደርጉት ግንኙነትን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ይህንን ጥሶ የተገኘ ከባድ ቅጣቶች እንደሚጠብቀውም አስጠንቅቀዋል።

    ማዕቀቡ የተጣለው ለመቅጣት ብቻ ሳይሆን የባህሪ ለውጥ እንደሚያመጡ ለማስገደድ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ዋሽንግተን ግጭትን በማባባስ የተከሰሱትን የቀድሞ መሪ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ለመጣል ፈቃደኛ መሆኗን ያሳያል።

    ቢቢሲ ከካቢላ የኮሙኒኬሽን ቡድን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

    እአአ በ2025 መስከረም ወር የአገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በአገር ክህደት፣ በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል፣ እንዲሁም ግድያ፣ የወሲብ ጥቃት፣ ማሰቃየት እና ማመጽን ጨምሮ በተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ጥፋተኛ ናቸው በሚል ሞት ፈርዶባቸዋል።

    ካቢላ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ቢናገሩም ችሎት ፊት ቀርበው ግን ራሳቸውን አልተከላከሉም።

    የቀድሞው ፕሬዚዳንት ክሱን "በዘፈቀደ" የተመሰረተ ያሉ ሲሆን ችሎቱን ደግሞ "ለጭቆና መሣሪያ ሆኗል" በማለት ውድቅ አድርገውታል።

    ጆሴፍ ካቢላ አሁን የት እንዳሉ አይታወቅም።

    የ55 ዓመቱ ካቢላ እአአ በ2001 በጥይት የተገደሉትን አባታቸው ላውረን ካቢላን በመተካት ለ18 ዓመታት አገሪቱን አስተዳድረዋል።

    ካቢላ እአአ በ2019 ለፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ ያስረከቡ ቢሆንም በኋላ ግን በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት እአአ በ2023 በፈቃዳቸው አገሪቱን ለቅቀው ተሰድደዋል።

  7. ትራምፕ የንጉሥ ቻርልስን ጉብኝት ተከትሎ በውስኪ ላይ የጣሉትን ታሪፍ ሊያነሱ ነው

    ዶናልድ ትራምፕ የንጉሥ ቻርልስን እና የንግሥት ካሚላን የአሜሪካ ጉብኝት ተከትሎ በውስኪ ምርቶች ላይ ጥለውት የነበረውን ሁሉንም ታሪፎች እና ገደቦች እንደሚያነሱ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስኮትላንድ በኬንታኪ ውስኪ እና ቦርቦን ማምረት ላይ የተጣለባትን ገደብ እንደሚያነሱም አስታውቀዋል።

    የዩኬ መንግሥት ይህ ለሁሉም የውስኪ ምርቶች፣ የአየርላንድ ውስኪን ጨምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን አረጋግጧል።

    የኢንዱስትሪ ተወካዮች "በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና በተፈጠርበት በዚህ ወቅት ይህ እፎይታን የሚሰጥ ነው” ብለዋል።

    ትራምፕ እንዳሉት የንጉሡ ጉብኝት "ብዙም ሳልጠየቅ ማንም ሰው ማድረግ የማይችለውን እንዳደርግ ገፍቶኛል" ብለዋል።

    ንጉሡ እና ንግሥቲቷ በዋሺንግተን ዲሲ፣ ቨርጂኒያ እና ኒው ዮርክ የአራት ቀናት ጉብኝት አድርገው ወደ ቤርሙዳ አምርተዋል።

    የትራምፐን ውሳኔ ተከትሎ የበርኪንግሃም ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ ንጉሡ ለትራምፕ "ልባዊ ምስጋናቸውን" ማቅረባቸውን እንዲሁም "ለፕሬዝዳንቱ አሳቢነት ጽዋቸውን ያነሳሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

    የስኮትላንድ ሚኒስትር ጆን ስዊኒ ውሳኔው "ለስኮትላንድ ታላቅ ዜና" ካሉ በኋላ ንጉሡ ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና አመስግነዋል።

    ስዊኒ አክለውም "ከስኮትላንድ ኢኮኖሚ በየወሩ በሚሊዮን የሚቆጠር ፓውንድ እየከሰረ ነበር" ብለዋል።

  8. እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ

    እስራኤል ከሊባኖስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ብትደርስም በደቡባዊ ሊባኖስ ሐሙስ ዕለት በፈጸመችው ከባድ ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴተር አስታወቀ።

    ሁለተኛ ሳምንቱን በያዘው የተኩስ አቁም አሁንም እስራኤል ጥቃቶችን መፈጸሟን ቀጥላለች።

    እስራኤል ሐሙስ ዕለት የሄዝቦላህ መሠረተ ልማት ናቸው ባለቻቸው ስፍራዎች በፈጸመችው ድብደባ 23 ሰዎች መጎዳታቸውን እና ከእነዚህም መካከል ስምንቱ ሕጻናት፣ ሰባቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

    ሄዝቦላህ በበኩሉ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ የእስራኤል ጦር አባላት ላይ በድሮን ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል በዋሺንግተን ንግግር ከተደረገ በኋላ እአአ ከሚያዚያ 16 ጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረሰ ቢሆንም ግጭቶች ቀጥለዋል።

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ኦወን “ምንም እንኳ የተኩስ አቁም ቢደረስም” እስራኤል ስምምነቱን በመጣስ “ጥቃት መፈጸሟን እንደቀጠለች” ነው በማለት የተቹ ሲሆን፣ በሚደርሱ የአየር ድብደባዎች የመኖሪያ ቤቶች እና የአምልኮ ስፍራዎች እየወደሙ ነው ሲሉ ከስሰዋል።

    "እስራኤል ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና ስምምነቶችን እንድታከብር እና በሲቪሎች፣ በሕክምና ባለሙያዎች፣ በሲቪል መከላከያ እና በሰብአዊ ድርጅቶች ላይ ማነጣጠሯን እንድታቆም ጫና መደረግ አለበት" ብለዋል።

    እስራኤለ በበኩሏ ጥቃቶቹን የምትፈጽመው ሄዝቦላህ ለሚተኩሳቸው ድሮን እና ሮኬቶች ምላሽ ለመስጠት መሆንን በመግለጽ ትከራከራለች።

    በተኩስ አቁም ስምምነቱ ሄዝቦላህ ያልተካተተ ቢሆንም እስራኤል የምታከብር ከሆነ ለስምምነቱ እነደሚገዛ አስታውቆ ነበር።

    የተኩስ አቁሙ በቤይሩት ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚካሄደውን ጥቃት በአብዛኛው ቢያቆምም፣ በደቡባዊ ሊባኖስ ግን የሚካሄደው ድብደባ እንደቀጠለ ነው።

  9. የኢራኑ ጠቅላይ መሪ የአገራቸውን የኒውክሌር አቅም ለመከላከል ቃል ገቡ

    የኢራኑ ጠቅላይ መሪ የእስላማዊ ሪፐብሊኩን የኒውክሌር እና የሚሳዔል አቅም ለመከላከል ቃል ገቡ። ሞጅታባ ኻሜኒ ሐሙስ ዕለት በጽሑፍ በሰጡት መግለጫ አሜሪካ በፐርዢያ ባሕረ ሰላጤ ቦታ እንደሌላት በመግለጽ፣ መገኘት የሚገባት “ከውሃዎቿ በታች ነው” ብለዋል።

    ኻሜኒ በሰጡት መገለጫ ላይ የኢራን የኒውክሌር እና የባሌስቲክ ሚሳዔል ፕሮግራም ለንግግር እንደማይቀርብ አመልክተዋል።

    በቴሌቭዥን በተነበበው የጠቅላይ መሪው መግለጫ አያቶላህ ሞጅታባ ኻሜኒ የአሜሪካን ግዙፍ ወታደራዊ ኃይል ዕቅድ አለመሳካቱን በመግለጽ ጦርነቱ በቀጣናው ታሪክ ውስጥ “አዲስ ምዕራፍ“ ከፍቷል ብለዋል።

    ሞጅታባ ኻሜኒ ኢራን ወሽመጡን መቆጣጠሯ ባሕረ ሰላጤውን የበለጠ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል። መግለጫው አክሎም ቴህራን በወሽመጡ ላይ የሚኖራት “ሕጋዊ አመራር እና አዲስ አስተዳደር” የቀጣናውን ዜጎች በሙሉ ተጠቃሚ ያደርጋል ሲል ገልጿል

    ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸውን መገደል ተከትሎ የጠቅላይ መሪነቱን ሥልጣን ከተረከቡ ጀምሮ ለሕዝብ ታይተው አያውቁም።

    ጠቅላይ መሪው መግለጫውን የሰጡት የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ የሚደርሰው ጫና በበረታበት፣ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ቴህራን ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች ላይ የጣለው እገዳ በቀጠለበት ወቅት ነው።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን ተከትሎ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቧል። ሐሙስ ዕለት የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ በበርሜል 126 ዶላር ተሸጧል።

    ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ወደቦች ላይ የጣሉትን እገዳ እንደሚቀጥሉ የገለጹ ሲሆን አጋሮቻቸው ጥምረት በመፍጠር የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲያስከፍቱ ግፊት እያደረጉ ነው ተብሏል።

    ኻሜኒ በመግለጫቸው ላይ አሜሪካን “ታላቋ ሴጣን” በማለት የጠሯት ሲሆን በፐርዢያ ባህረ ሰላጤ ምንም ጉዳይ የላትም ብለዋል።

    የኢራን የበላይ መሪ "መሣሪያዎቻችን እና ቴክኖሎጂዎቻችን እንደ አገር የማንነታችን አካል ናቸው እና ምንም ቢሆን እንጠብቃቸዋለን" ሲሉ ተናግረዋል።

    “ሁሉም የኢራን አቅሞች ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪ፣ የኒውክሌር እና ሚሳዔል ፕሮግራሞች” በ90 ሚሊዮን የኢራን ሕዝብ የሚታዩት እንደ ውድ ብሔራዊ ሃብቶች መሆኑን ጠቅላይ መሪው ተናግረዋል።

    አክለውም “ልክ ውሃችንን፣ ግዛታችንን እና አየር ክልላችንን እንደምንከላከለው እንጠብቀዋለን” ብለዋል።

    በሺህ ኪሎ ሜትሮች አቋርጠው መጥተዋል ያሏቸውን የውጭ ኃይሎች “በስግብግብነት እና በክፋት” ይንቀሳቀሳሉ ሲሉ ወንጅለው፣ በአካባቢው “ምንም ቦታ የላቸውም። ከውሃው በታች ካልሆነ በስተቀር" ብለዋል።

    ኻሜኒ በዚህ መግለጫቸው ላይ ኢራን ወሽመጡን መቆጣጠሯን እንደምትቀጥል አመልክተዋል።

    ኢራን በወሽመጡ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን 2 ሚሊዮን ዶላር እንደምታስከፍል ትናግራለች።

    እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በቴህራን ላይ የጀመሩት ጦርነት ሁለት ወር አልፎታል።

  10. አሜሪካ ዳግም ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ የከፋ እርምጃ እንደምትወስድ ኢራን አስጠነቀቀች

    ኢራን ዋሽንግተን ዳግም ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከጀመረች “ረዥም እና የከፋ ጉዳት የሚያስከትል” የአጸፋ እርምጃ እንደምትሰጥ አስጠነቀቀች።

    ቴህራን አሜሪካ የተወሰነ ቢሆንም እንኳ ጥቃት ዳግም መፈጸም ከጀመረች “ረዥም እና የከፋ ጉዳት የሚያስከትል” ጥቃት በቀጣናው ባሏት የጦር ሠፈሮች ላይ እንደሚፈጽሙ የአብዮታዊ ዘቡ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

    “በቀጣናው ጦር ሠፈሮቻችሁ ላይ የሆነውን አይታችኋል። በጦር መርከቦቻችሁ ላይ ተመሳሳይ ነገር እናያለን” ሲሉ የአየር ኃይል አዛዡ ማጂድ ሞሳቪ መናገራቸው የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በኢራን ላይ ጦርነት መጀመራቸውን ተከትሎ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የተነሳ የዓለም የነዳጅ አቅርቦት ተስተጓጉሏል።

    አሜሪካ አገራት ጥምረት ፈጥረው የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲያስከፍቱ ግፊት እያደረገች መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።

    ቴህራን ረቡዕ ዕለት አሜሪካ መርከቦቿ ላይ የጣለችነው እገዳ የምትቀጥል ከሆነ “ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ወታደራዊ እርምጃ" እንደምትወስድ አስጠንቅቃ ነበር።

    ይህ የቴህራን ማስጠንቀቂያ በቀጣናው ዳግም የአሜሪካ እና የእስራኤል ድብደባ ይቀጥላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

  11. አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ለማስከፈት ዓለም አቀፍ ድጋፍ ትፈልጋለች ተባለ

    አሜሪካ ሌሎች አገራት ዓለም አቀፍ ጥምረት እንዲመሠርቱ እና የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲያስከፈቱ እንደምትፈልግ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    የዜና ወኪሉ የተመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰነድ የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበት ወሽመጥን ዳግም ለመርከቦች ክፍት እንዲሆን ለማድረግ አገራት ዓለም አቀፍ ጥምረት እንዲመሰርቱ ግፊት እያደረገች መሆኑን ያሳያል።

    ሁለት ወር ባለፈው በኢራን ጦርነት ምክንያት የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከአራት ኣመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ጭማሪ አሳይቷል።

    ጦርነቱን ለማስቆም የተደረጉ ንግግሮች ውጤት ባለማስገኘታቸው አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች መርከቦች እንዳይገቡ እገዳ ጥላለች።

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሐሙስ ዕለት ኢራን ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንድትመለስ ለማድረግ የሚያስችል ወታደራዊ ዕቅድ ላይ ለፕሬዚዳንቱ ገለጻ እንደሚደረግ አክሲዮስ ዘግቧል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ “አጭር እና ከባድ” የሆነ የጥቃት እቅድ ለፕሬዚዳንቱ እንደሚያቀርብ የተገለጸ ሲሆን በዚህ ጥቃት ምናልባት የኢራን መሠረተ ልማቶች ዒላማ ሊደረጉ እንደሚችሉ አክሲዮስ በስም ያልጠቃሳቸውን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።

    ዋይት ሐውስ እና ማዕከላዊ ዐዕዙ ሮይተርስ ላቀረበው ጥያቄ ምላሸ አልሰጡም።

  12. እስራኤል እርዳታ ይዘው ወደ ጋዛ ሲጓዙ የነበሩ መርከቦችን ጠልፋ፤ 175 አክቲቪስቶችን አሰረች

    ለጋዛ እርዳታ ጭነው ሲጓዙ የነበሩ 22 ጀልባዎች በግሪኳ ክሪት ደሴት አቅራቢያ ዓለም አቀፍ ውሃ ላይ ሳሉ በእስራኤል ኃይሎች መጠለፋቸውን የፍልስጤም ደጋፊ አክቲቪስቶች አስታወቁ።

    የመርከቦቹን የቡድን ጉዞ ያቀናጀው ‘ግሎባል ሱሙድ ፍሎቲላ’ የተባለው ተቋም የእስራኤልን እርምጃ “የባሕር ላይ ውንብድና” ሲል ተቃውሞታል።

    መርከቦቹ ላይ የነበሩት ሰዎች በእስራኤል ባሕር ኃይል ከተዘጋው ጋዛ 965 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መያዛቸውን ተቋሙ ገልጿል።

    የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ከ20 በሚበልጡ ጀልባዎች ውስጥ የነበሩ 175 አክቲቪስቶችን መያዙን እና ወደ እስራኤል እየተወሰዱ መሆኑን አስታውቋል። የጀልባዎቹን ጉዞም “የሕዝብ ግንኙነት ትርኢት” ሲል አጣጥሎታል።

    እስራኤል ጋዛ ላይ የጣለችውን እገዳ የመስበር እቅድ በመያዝ ከሁለት ሳምንት በፊት የሕብረት ጉዞ የጀመሩት ከስፔን፣ ፈረንሳይ እና ጣልያን የተወጣጡ 58 መርከቦች ናቸው።

    የ‘ግሎባል ሱሙድ ፍሎቲላ’ መረጃ እንደሚያሳየው ቀሪዎቹ 36 ጀልባዎች በደቡብ ምዕራባዊ የክሪት ባሕር ዳርቻ አቅራቢያ እየቀዘፉ ነበር።

    የቡድኑ አባላት ከነበሩት መርከቦች ውስጥ ቢያንስ 22 ያህሉ “ሙሉ በሙሉ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት በሆነ መልኩ በእስራኤል ኃይሎች መወረራቸውን” ተቋሙ ገልጿል።

    የእስራኤል ባሕር ኃይል “መርከቦችን እንደጠለፈ፣ የአደጋ ጊዜ ቻናሎችን ጨምሮ የኮሚዩኒኬሽን መስመራቸውን እንደጠለፈ እና ሲቪል ሰዎችን በኃይል አፍኖ እንደወሰደ” በመግለጫው ጠቅሷል።

    “ይሄ የባሕር ላይ ውንብድና ነው። በክሪት አቅራቢያ ክፍት ውሃ ላይ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ እስራኤል ከራሷ ድንበር ሩቅ የሆነ ስፍራ ላይ ያለ ምንም ተጠያቂነት፣ ያለ ምንም መዘዝ እንደምትንቀሳቀስ ያመለክታል” ብሏል።

    የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች በበኩላቸው የባሕር ኃይሉ ለመርከቦቹ ማስጠንቀቂያ እንደሰጠ እና ትዕዛዙን ያልተቀበሉትን እንደያዘ ገልጸዋል። እስራኤል እርምጃዋ ዓለም አቀፍ ሕግን ያከበረ እንደሆነ ትናገራለች።

  13. የነዳጅ ዋጋ ከአራት ዓመት ወዲህ ባልታየ መጠን ጨመረ

    አሜሪካ እና ኢራን ከሁለት ወር በፊት የገቡበት ጦርነት የመቋጨት አዝማሚያ እያሳየ አለመሆኑን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ከአውሮፓውያኑ 2022 ወዲህ ባልታየ መጠን ጨመረ።

    የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋው በሰባት ፐርሰንት ገደማ ጨምሮ በበርሜል ከ126 ዶላር በላይ ተሽጧል። አሁን የተመዘገበው የነዳጅ ዋጋ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከከፈተች ወዲህ የታየ ከፍተኛ ጭማሪ ሆኗል።

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር ያለ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ባለበት መቆሙን ተከትሎ የኤነርጂ ዋጋ በዚህ ሳምንት ጨምሯል።

    በእስያ ገበያ ላይ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል 126.32 ዶላር የተሸጠ ሲሆን የአውሮፓ ገበያ ሲከፈት ግን የብሬንት ዋጋ ወደ 122 ዶላር ተመልሷል።

    ቤንዚን እና ናፍጣ የሚገኝበት ድፍድፍ ነዳጅ ከኢራን ጦርነት ጀመር ወዲህ ያሳየው ጭማሪ የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

    ረቡዕ ዕለት አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ የጣለችውን እገዳ ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋት እስከቀጠች ድረስ ለማራዘም መዘጋጀቷ ከተዘገበ በኋላም የነዳጅ ዋጋ በስድስት በመቶ ጨምሮ ታይቷል።

  14. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ላይ ሊወሰድ ስለሚችል ወታደራዊ እርምጃ ገለጻ ሊደረግላቸው መሆኑ ተዘገበ

    የአሜሪካ ወታደራዊ አዛዦች ኢራን ውስጥ ሊፈጸሙ የሚችሉ “አጭር እና ኃይለኛ” ተከታታይ ጥቃቶችን የተመለከተ እቅድ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሊያቀርቡ መሆኑን የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ዘገበ።

    አክሲዮስ ለጉዳዮ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ እንደሚያመልክተው፤ የአሜሪካን መካከለኛው ምሥራቅ ዘመቻዎች የሚመራው ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ በሆኑት አድሚራል ብራድ ኩፐር የሚቀርበው እቅድ የኢራን መሠረተ ልማቶችን ማጥቃትን ሊያካትት ይችላል።

    የትራምፕ አስተዳደር ኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድን እያጤነ ያለው ጥቃት መፈጸም ከቴህራን ጋር የሚደረገው ድርድርን ከገባበት ቅርቃር ያስወጣል በሚል ተስፋ መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል።

    ኢራን ጥቃት ከተፈጸመባት ድርድሩ ላይ የኒውክሌር ጉዳይን በተመለከተ መለሳለስ ልታሳይ ትችላለች ተብሎ ተገምቷል።

    በዘገባው መሠረት ለትራምፕ ይቀርባል ሌላኛው እቅድ በኢራን የተዘጋውን ሆርሙዝ ለንግድ መርከቦች ክፍት ለማድረግ ሲባል የወሽመጡን የተወሰነ ክፍል መቆጣጠርን የሚመለከት ነው።

    ይህ አይነቱ እርምጃ እግረኛ ወታደሮችን ማሰማራትን ሊያካትት እንደሚችል አክሲዮስ አንድ ምንጭን ጠቅሶ ዘግቧል።

    በከፍተኛ መጠን የበለጸገውን የኢራን የዩራኒየም ክምችት ለመቆጣጠር በሠራዊቱ ልዩ ኃይል ዘመቻ የማካሄድ እቅድም ለፕሬዝዳንቱ ሊቀርብ ይችላል ተብሏል። ይህ አይነቱ እቅድ ከዚህ ቀደምም ተነስቶ ነበር።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት የተከፈተባት ኢራን ወሳኙን የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ ዘግታለች። በወሽመጡ ለማለፍ የሚሞክሩ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም መዛቷንም ቀጥላለች።

    ይህ የኢራን እርምጃ የዓለም የኤነርጂ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል ያደረሰ ሲሆን አሜሪካ ደግሞ በምላሹ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ እገዳ ጥላለች።

    እንደ አክሲዮስ ዘገባ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራን ወደቦች ላይ የጣሉትን የጉዞ እገዳ እንደ ትልቅ መደራደሪያ ይመለከቱታል። ይሁን እንጂ ኢራን በዚሁ አቋሟ የምትቀጥል ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድን ሊያጤኑት እንደሚችሉ ጠቅሷል።

    በተጨማሪም ኢራን የአሜሪካ እገዳ የሚቀጥል ከሆነ በአጸፋው በቀጣናው የሚገኙ አሜሪካ ኃይሎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች የሚል ግምት መኖሩን የዜና ምንጩ ዘግቧል።

  15. የጀርመን መራሄ መንግሥት አሜሪካን ከተቹ ከቀናት በኋላ ትራምፕ በአገሪቱ የሰፈሩ ወታደሮችን ለመቀነስ እያሰቡ መሆኑ ተናገሩ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጀርመን ውስጥ የሰፈሩትን በሺህዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮች ቁጥር ለመቀነስ “ጥናት እየተደረገ” መሆኑን አስታወቁ።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት፤ የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ፤ አሜሪካ በኢራን ተደራዳሪዎች “ተዋርዳለች” በማለት የዋሽንግተንን አካሄድ ከተቹ ከቀናት በኋላ ነው።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “ጀርመን ውስጥ ያሉ ወታደሮች ላይ ሊደረግ የሚችል ቅነሳን በተመለከተ በመጪው አጭር ጊዜ ውስጥ ምን አይነት ውሳኔ መተላለፍ እንዳለበት እያጠኑ እና እየገመገሙ” መሆኑን ገልጸዋል።

    አሜሪካ ጀርመን ውስጥ ከፍተኛ የሠራዊት አባላትን ያሰፈረች ሲሆን፣ እስከ ታህሳሥ ባለው ጊዜ ውስጥ በመላ አገሪቱ በሚገኙ ጦር ሰፈሮች 36,000 ወታደሮች እንደነበሯት መረጃዎች ያመለክታሉ።

    የጀርመኑ መራሄ መንግሥት መርዝ አሜሪካን የሚተቸውን ንግግራቸውን ያሰሙት ሰኞ ዕለት ማርስበርግ ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ለተማሪዎች ባደረጉት ንግግር ነው። “አሜሪካ ምንም ስትራቴጂ እንደሌላት ግልጽ ነው” ሲሉ ለተማሪዎቹ ተናግረዋል።

    “ኢራናውያኑ ድርድር ላይ እጅግ የተካኑ መሆናቸው ወይም ድርድር አለማድረግ ላይ በጣም ጎበዝ መሆናቸው ግልጽ ነው። አሜሪካውያን ወደ ኢስላማባድ እንዲጓዙ እና ያለ ውጤት በድጋሚ እንዲመለሱ አድርገዋል” ብለዋል። “መላ አገሪቱ” በኢራን አመራር “እየተዋረደ” መሆኑንም አክለዋል።

    ትራምፕ በማግሥቱ ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ፤ የጀርመኑ መሪ “ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ቢኖራት ችግር የለበትም”፤ እንዲሁም “ስለ ምን እንደሚናገር አያውቅም” ሲሉ ተችተዋል።

    “ጀርመን በኢኮኖሚ እና በሌሎች ጉዳዮች ደካማ መሆኗ አያስገርምም” ሲሉ ጽፈዋል።

    ረቡዕ ዕለት ከትራምፕ ጋር ስላላቸው ግንኙነት የተጠየቁት መርዝ፣ “በእኔ እና በአሜሪካው ፕሬዝዳንት መካከል ያለው ግላዊ ግንኙነት እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ ጥሩ ላይ ነው” ብለዋል።

    ትራምፕ ጀርመን ውስጥ የሚገኙ ወታደሮችን ቁጥር እንደሚቀንሱ ስለመጠቆማቸው እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፉት ሁለት ወራት 23 አባላት ካሉት እና “የወረቀት ላይ ነብር” ሲሉ ካጣጣሉት ኔቶ አሜሪካን እንደሚያስወጡ ሲዝቱ ቆይተዋል።

  16. አሜሪካ በኢራን ጦርነት እስካሁን 25 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቷን አስታወቀች

    ከሁለት ወር በፊት ኢራን ላይ የተከፈተው ጦርነት እስካሁን አሜሪካን 25 ቢሊዮን ዶላር እንዳስወጣት የዋሽንግተን መከላከያ መስሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊ ተናገሩ።

    አሜሪካ በኢራን ጦርነት ምን ያህል ገንዘብ ወጪ እንዳደረገች በይፋ ሲገለጽ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    የአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር ፒት ሄግሴት ከኢራን ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በቃለ መሃላ ስር ሆነው በሰጡት ስድስት ሰዓት በቆየ የምክር ቤት ማብራሪያ ላይ ከዴሞክራቲክ ሕግ አውጪዎች ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።

    መከላከያ ሚንስትሩ ትናንት ረቡዕ በተወካዮች ምክር ቤት የጦር አገልግሎት ኮሚቴ ፊት የቀረቡት ከአሜሪካ ጦር የጋራ ጦር አዛዦች ኃላፊ ጄነራል ዳን ኬን እና ከመከላከያ መስሪያ ቤቱ የፋይናንስ ዋና ኃላፊ ጁሌስ ኸርትስ ጋር በመሆን ነው።

    ሄግሴት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር “የተጋፈጥነው ትልቁ ጠላት” የዴሞክራቶች እና የተወሰኑ ሪፐብሊካኖችን “የሽንፈት ቃላቶች ነው” ብለዋል።

    የኮሚቴው አባል የሆኑ ዴሞክራት ሕግ አውጪዎች ከኢራን ጋር በሚደረገው ጦርነት የፌደራል መንግሥቱ ገንዘብ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝበትን መንገድ ተችተዋል።

    ከመከላከያ መስሪያ ቤቱ የፋይናንስ ዋና ኃላፊ ኸርትስ ባደረጉት ንግግር እስካሁን ለጦርነቱ 25 ቢሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።

    ኸርትስ እንደገለጹት አብዛኛው ገንዘብ የወጣው ለተተኳሽ እና መሣሪያዎችን ለመተካት ነው። የወጪው ሙሉ ዝርዝር ከጊዜ በኋላ እንደሚቀርብ ለሕግ አውጪዎች ተናግረዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን የሰላም ንግግር ለማድረግ ተኩስ አቁም ላይ ቢደርሱም ጦርነቱ በይፋ አልተቋጨም።

    በምክር ቤቱ ውሎ ዋነኛ መነጋገሪያ ከሆኑ ነጥቦች አንዱ ገንዘብ ነው። ዋይት ሀውስ የአሜሪካ የመከላከያ በጀት በ1.5 ትሪሊዮን ዶላር እንዲጨምር ለኮንግረስ ጥያቄ አቅርቧል።

    ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የአሜሪካ ወታደራዊ ወጪ በዚህ ደረጃ ከፍ ሲል ይህ የመጀመሪያው ነው።

    መከላከያ ሚንስትሩ ሄግሴት የበጀት ጥያቄው “ጊዜው የሚጠይቀውን አጣዳፊነት ያሳያል” ሲሉ ለኮሚቴው ተናግረዋል።

    ጄነራል ኬን በበኩላቸው 1.5 ትሪሊዮን ዶላር አሜሪካ በፍጥነት የሚያድግ ቴክኖሎጂ መታጠቅ እንድትችል የሚያግዝ “ለወደፊት ደኅንነት የሚውል ታሪካዊ ቅድመ ክፍያ” ነው ብለዋል።

    የኮሚቴው አባላት የሆኑ ዴሞክራቶች የአሜሪካ ጦር ኢራን ላይ የሚያካሂደውን ዘመቻ ብዙውን ጊዜ የሚገልጹት ያለ ኮንግረስ ፈቃድ እንደተከፈተ “የምርጫ ጦርነት” ነው።

    የካሊፎርኒያው ዴሞክራቲክ ተወካይ ጆን ጋራሜንዲ፤ “ጦርነቱን በተመለከተ ከመጀመሪያው ዕለት አንስቶ የአሜሪካ ሕዝብን ስትዋሹ ነበር” ሲሉ ባለሥልጣናቱን ወቅሰዋል።

    ትራምፕ በሌላ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት “አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል” ሲሉም ለሄግሴት ተናግረዋል።

    የምክር ቤት አባሉን አስተያየት “ግድ የለሽ” ሲሉ የጠሩት ሄግሴት በበኩላቸው፤ ትራምፕ “አጣብቂኝ” ውስጥ ናቸው መባሉን አስተባብለዋል። “ለትራምፕ ያለህ ጥላቻ አውሮሃል” ሲሉም የምክር ቤት አባሉን ተናግረዋል።

    የኮሚቴው አባል የሆኑ አብዛኞቹ ሪፐብሊካኖች ከመከላከያ መስሪያ ቤቱ ጎን ቆመዋል። የኮንግረስ አባሉ ካርሎስ ጊሜኔዝ ኢራን የህልውና ስጋት ናት ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

  17. የዚምቧብዌ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ልጅ ከደቡብ አፍሪካ ሊባረር ነው

    የዚምባብዌ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ የመጨረሻ ልጅ በአስቸኳይ ከደቡብ አፍሪካ እንዲባረር የጆሃንስበርግ ፍርድ ቤት ወሰነ።

    ቤላርማይን ሙጋቤ በዚህ ወር መጀመርያ ላይ በመኖሪያ ቤቱ የ23 ዓመት ወጣት ላይ በመተኮሱ የተከሰሰ ሲሆን ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።

    የ28 ዓመቱ የሙጋቤ ልጅ መሳሪያ በመደቀን እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለ ሕጋዊ ፈቃድ በመኖር ጥፋተኛ መሆኑ ተገልጿል።

    ፍርድ ቤት በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ 36,000 ዶላር እንዲከፍል ወስኖበታል።

    አብሮት የተከሰሰው የአጎቱ ልጅ ቶቢያስ ማቶንሆድዜ በግድያ ሙከራ፣ በሕገወጥ ስደት፣ የጦር መሣሪያ በመያዝ እና በፍትህ ስርዓቱ ላይ ጣልቃ በመግባት ወንጀሎች የሦስት ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

    ሁለቱም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአስር ቀን በፊት ፖሊስ በጆሃንስበርግ በሚገኘው የሙጋቤ ልጅ ቤት ተጠርቶ ከመጣ በኋላ ነው።

    በቅጥር ግቢው ውስጥ ይሰራ የነበረው ግለሰብ በጥይት ተመትቶ ክፉኛ በመጎዳቱ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

    አቃቤ ሕጎች ለፍርድ ቤቱ ግለሰቡ ላይ የተተኮሰው በቅጥር ግቢው ውስጥ ሦስት ሰዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን አስረድተዋል።

    አክለውም ግለሰቡ ለማምለጥ ሲሞክር ከኋላው ሁለት ጊዜ ተተኩሱበት መመታቱን ገልጸዋል።

    ፖሊስ የመኖሪያ ቤቱ ላይ ብርበራ ያካሄደ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የጦር መሣሪያውን አላገኘም።

  18. በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለው እገዳ እንደሚራዘም ከተሰማ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን እገዳ ለማራዘም ማቀዷ ከተሰማ በኋላ የዓለም ነዳጅ ዘይት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ።

    ማክሰኞ ዕለት 110 ዶላር የተሸጠው አንድ በርሜል ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ረቡዕ 115 ዶላር ገብቷል።

    የነዳጅ ዋጋ የጨመረው ዎል ስትሪት ጆርናል ዶናልድ ትራምፕ የኢራን ምጣኔ ሃብትን ለማዳከም በቴህራን ወደቦች ላይ የተጣለውን እገዳ እንደሚያራዝሙ ለረዳቶቻቸው መናገራቸውን ከዘገበ በኋላ ነው።

    ኢራን የአሜሪካ እገዳ እስካልተነሳ ድረስ በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦች እንደማያልፉ ተናግራለች።

    የካቲት 21 2018 ዓ.ም. እስራኤል እና አሜሪካ ኢራንን መደብደብ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

    ኢራን ለተከፈተባትን ጦርነት ምላሽ ለመስጠት በሚል የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ምርት የሚመላለስበት የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታለች።

  19. ፈረንሳይ ዜጎቿ በፍጥነት ማሊን ለቅቀው እንዲወጡ አሳሰበች

    የማሊ ታጣቂዎች በሳምንቱ መጨረሻ የተቀናጀ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ፈረንሳይ ዜጎቿ “በተቻለ ፍጥነት” አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አሳሰበች።

    ቅዳሜ ዕለት በማሊ ተገንጣይ ቡድኖች እና እስላማዊ ታጣቂዎች በጋራ በመሆን በከፈቱት ጥቃት ዋና ከተማዋ ባማኮን ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ ክፍል ውጊያ ተካሄዷል።

    ፈረንሳይ ረቡዕ በማሊ ያለው ሁኔታ “ፈጽሞ ያልተረጋጋ” መሆኑን በመግለጽ ዜጎቿ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር እንዳይሄዱ መክራለች።

    የማሊ የመከላከያ ሚኒስትር በዋና ከተማዋ ባማኮ አቅራቢያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸው ተገልጿል።

    ሳዲዮ ካማራ የተገደሉት እስላማዊ ታጣቂዎች እና ተገንጣዮች በመላ አገሪቱ በከፈቱት የተቀናጁ የጥቃት ማዕበሎች መሆኑን የበርካታ የዜና አውታሮች ዘገባ አመልክቷል።

    የማሊ ጦር ጄነራል አሲሚ ጎይታ የአገሪቱ ጸጥታ መረጋጋቱን በትናንትናው ዕለት አስታውቀዋል።

    ማክሰⶉ ምሽት የአገሪቱ ጦር በታጣቂዎች ላይ “ከፍተኛ ኪሳራ” ማድረሱን ገልጾ አሁንም ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁሟል።

  20. እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በፈጸመችው ተከታታይ ጥቃት ሦስት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተገደሉ

    እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በፈጸመችው ሁለት ተከታታይ ጥቃት ሦስት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥቃቱን “የጦር ወንጀል” ሲሉ ኮንነውታል።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በመጀመርያው የእስራኤል ጥቃት የተጎዱ ሰዎችን ለማትረፍ የተላኩ ሦስት የአገሪቱ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በሁለተኛው ጥቃት መገደላቸውን አስታውቋል።

    በኋላ ላይ የሞታቸው መንስዔ ሲጣራ በፍርስራሸሶች ውስጥ ተቀብረው ሕይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።

    ሚኒስቴሩ ሁለቱ የተገደሉት ሰዎች ማን እንደሆኑ ይፋ አላደረገም። በጥቃቱ ሁለት የሊባኖስ ጦር ወታደሮች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ታውቋል።

    የእስራኤል ጦር ስለጥቃቱ ጥያቄ ቢቀርብለትም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።

    የሰብዓዊ መብቶች ብድኖች በሕክምና ባለሙያዎች ላይ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ጥቃት ከጦር ወንጀል ጋር ይስተካከላል ብለዋል።

    በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል ዳግም ግጭት የተቀሰቀሰው የኢራን ጦርነትን ተከትሎ ወደ ቴል አቪቭ ሮኬቶችን ማስወንጨፍ በመጀመሩ ነው።

    እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደርሱም፣ በደቡባዊ ሊባኖስ የእግረኛ ጦሯን አሰማርታ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደች ትገኛለች።

    በእስራኤል ጦር በተፈጸሙ ጥቃቶች እስካሁን ድረስ 103 የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ 2500 ሰዎች ተገድለዋል።

    ከሟቾቹ መካከል 270 ሴቶች እና ከ 170 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሕጻናት መሆናቸው ተገልጿል።