ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩኬ ከአራት ዓመት በኋላ የሽብር ጥቃት ስጋት ከፍ እንዲል አደረገች
በዩናይትድ ኪንግደም የሽብር ስጋት ከፍ ማለቱን ተከትሎ ሕዘቡ "ንቁ እና ጠንቃቃ" እንዲሆን ነገር ግን "እንዳይረበሽ" የዩኬ የደህንነት ሚኒስትር አሳሰቡ።
በዩኬ ያለው የሽብር ስጋት ደረጃ ከፍ ያለው ረቡዕ ዕለት በምዕራብ ለንደን ጎልደርስ ግሪን ሁለት አይሁዳውያን በስለት ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ነው።
ዩኬ ሐሙስ ዕለት የስጋት ደረጃውን ከፍ ያደረገችው ከአራት ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን ከ"ከፍተኛ" ወደ "ከባድ" ከፍ እንዲል መደረጉ ተገልጿል።
የደህንነት ሚኒስትሩ ዳን ጃቭሪስ የስጋት ደረጃውን ከፍ ማድረግ ያስፈለገው "በጥቃቱ የተነሳ ብቻ ሳይሆን" "ሰፊ ከእስላማዊ እና የቀኝ ክንፍ አክራሪዎች ዛቻ መጨመር" ጋር ተያይዞ ነው ብለዋል።
የሜትሮፖሊታን ፖሊስ የሽብር ጥቃት ሲል የፈረጀው ረቡዕ ዕለት የተፈጸመው የስለት ጥቃት በዩኬ የሚገኙ የአይሁድ ማኅበረሰብን ዒላማ ካደረጉ ተከታታይ ጥቃቶች መካከል የቅርብ ጊዜው ነው።
"ከባድ" የሆነው የስጋት ደረጃ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ የሽብር ጥቃት የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል።
ጃርቪስ የስለላ ተቋማቱ፣ ፖሊስና መንግሥት "የሕዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ሌት ተቀን እየሠሩ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሻባና ማህሙድ እንዳሉት የስጋት ደረጃ መጨመር "በተለይም በአይሁድ ማኅበረሰባችን መካከል ብዙ መከራ ለደረሰባቸው አሳሳቢ ጉዳይ ይሆናል" ብለዋል።
ነገር ግን መንግሥት "ማኅበረሰቡን ከፀረ አይሁድ እንቅስቃሴ ለማላቀቅ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋለን" ሲሉ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል አይሁዶች በሚበዙባቸው ስፍራዎች ለሚኖር የፖሊስ እና የደህንነት አካላት ስምሪት የበጀት ጭማሪ ስለመጠየቁ የተገለጸ ነገር የለም።
"የአደጋው መጠን እየጨመረ በሄደ ቁጥር፣ ሁሉም ሰው የዕለት ተዕለት ኑሮውን ሲያከናውን ንቁ እንዲሆን እና ማንኛውንም ስጋት ለፖሊስ እንዲያሳውቅ አሳስባለሁ" ሲሉ ማህሙድ አክለዋል።
የሜት የፀረ-ሽብርተኝነት ክፍል ኃላፊ የስጋት ደረጃው ከፍ ካለ በኋላ ለጋዜጠኞች ዩኬ "ቀስ በቀስ እየጨመረ የሄደ የሽብር ስጋት" እንዳጋጠማት ተናግረዋል።
ረዳት ኮሚሽነር ላውረንስ ቴይለር ደግሞ "በተለያዩ ርዕዮተ ዓለሞች ላይ የምንሰራው እየጨመረ ሲሄድ በዚህ መካከል በዩኬ የሚገኙ አይሁዶች እና እስራኤላውያን እንዲሁም ተቋማቶቻቸው ያለባቸው ስጋት መጨመሩን አይተናል" ብለዋል።
"እንዲሁም ከመንግሥት ጋር በተያያዙ አካላት ላይ የሚደርሱ አካላዊ ስጋቶችን ጨምሮ፣ ለአገራችን ቅርብ በሆነ ግን ተገማች ያልሆነ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ላይ እየሰራን ነው።"
ቴይለር እንዳሉት ፖሊስ "በመላ አገሪቱ የሚከናወኑትን ሁሉንም ክስተቶች" ይመረምራል።
ረቡዕ ዐዕለት ሁለት አይሁዳውያን ላይ በስለት ጥቃት ያደረሰው የ45 ዓመቱ ኢሳ ሱሌይማን የ34 ዓመቱን ሽሎይሜ ራንድ እና የ76 ዓመቱን ሞሼ ሺንን ለመግደል በመሞከር ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ፖሊስ ተጠርጣሪው ማክሰኞ ዕለት በደቡብ ምሥራቅ ለንደን በተከሰተ ወንጀል ውስጥ ተሳትፎ ሊሆን እንደሚችል ያምናል።
የረቡዕ ጥቃት የተፈጸመው በቅርብ ወራት ውስጥ በዩኬ የአይሁድ ማኅበረሰብ ላይ ያነጣጠሩ በርካታ ክስተቶች ካጋጠሙ በኋላ ነው።
በጥቅምት ወር በማንቸስተር በሚገኝ አንድ ምኩራብ በመኪና እና በስለት በተፈጸመ ጥቃት ሁለት አይሁዳውያን ሲገደሉ ሦስት ደግሞ ከባድ ጉዳት አጋጥሟቸዋል።