ቀጥታ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአዲሱ የኢራን እቅድ ደስተኛ አለመሆናቸውን ተናገሩ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ጦርነቱን ለመቋጨት ያቀረበችው አዲስ የሰላም እቅድ እንዳላስደሰታቸው ገለጹ። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው አሜሪካ አካሄዷን የምትቀይር ከሆነ ኢራን ለዲፕሎማሲ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ ውድቅ ያደረጉት የኢራን እቅድ ከኒውክሌር ንግግር በፊት ሆርሙዝ እንዲከፈት የሚጠይቅ መሆኑ ተዘገበ

    ኢራን በፓኪስታን በኩል ያቀረበችው እና ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያልተደሰቱበት አዲሱ የሰላም እቅድ ስለ ኒውክሌር ፕሮግራም የሚደረግ ንግግር በይደር ተይዞ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት እና አሜሪካ የጣለችው የባሕር ጉዞ እገዳ እንዲያበቃ የሚጠይቅ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ።

    የዜና ወኪሉ ስማቸው ያልተጠቀሰ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ፤ ቴህራን የኒውክሌር ድርድሩን ለሌላ ጊዜ ለማቆየት ያቀረበችው እቅድ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚረዳ ትልቅ እርምጃ ነው ብላ ታምናለች ሲል ዘግቧል።

    በአዲሱ እቅድ መሠረት ጦርነቱ የሚቋጨው እስራኤል እና አሜሪካ በድጋሚ ኢራን ላይ ጥቃት እንደማይከፍቱ ዋስትና ሰጥተው እንደሚሆን ዘገባው ጠቅሷል። ኢራን በምላሹ ዘግታው የከረመችውን ወሳኙን የሆርሙዝ ወሽመጥ የምትከፍት ሲሆን አሜሪካም ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ የጣለችውን እገዳ ታነሳለች።

    በመጀመሪያው ደረጃ ንግግር ይህ ከተከናወነ በኋላ በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ ስለሚጣል ገደብ እና ማዕቀቦችን ስለማንሳት ድርድር ይደረጋል። ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለማገድ ብትስማማ እንኳ አሜሪካ ለቴህራን ለሰላማዊ ዓላማ ዩራኒየም የማበልጸግ መብት እውቅና እንድትሰጥ እንደምትጠየቅ የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

    ሮይተርስ ያነጋገራቸው ባለሥልጣን፤ "በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ለስምምነቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንዲቻል ይበልጥ ውስብስብ በሆነው የኒውክሌር ጉዳይ ላይ የሚደረገው ድርድር ወደ መጨረሻው ደረጃ እንዲዛወር ተደርጓል" ብለዋል።

    ኢራን ከዚህ ቀደም ያቀረበችው እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ ውድቅ ያደረጉት ሌላ እቅድም በተመሳሳይ የኒውክሌር ጉዳይ በቅድሚያ ንግግር የሚደረግበት ጉዳይ እንዳይሆን የሚጠይቅ ነበር።

    ቴህራን አዲስ እቅድ ማቅረቧን ካስታወቀች በኋላ አስተያየት የሰጡት ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንዳላስደሰታቸው በመናገር “ልስማማበት የማልችለውን ነገር እየጠየቁ ነው” ብለዋል።

    “ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ። እኔ አልረካሁበትም፤ ስለዚህ የሚፈጠረውን እናያለን” ሲሉም ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት የሚያደርግ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ጦርነቱ ሊቋጭ እንደማይችል በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ኢራን በበኩሏ የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ ዓላም የሚውል መሆኑን በአጽንኦት ገልጻለች።

  2. ኩባ በአሜሪካ የተጣለባትን አዲስ ማዕቀብ “ሕገወጥ” እና “ግፈኛ” ስትል አወገዘች

    የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ አሜሪካ አገራቸው ላይ የጣለቻቸውን ተከታታይ ማዕቀቦች “ሕገወጥ” እና “ግፈኛ” በማለት ተቃወሙ።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኩባ የኤነርጂ፣ የመከላከያ፣ የፋይናንስ ወይም የደኅንነት ዘርፎች ባለሥልጣናትን እንዲሁም "የሰብዓዊ መብት ጥሰት" ወይም ሙስና ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦች ዒላማ ያደረገ ማዕቀብ የሚጥል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ አርብ ዕለት ፈርመዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ማዕቀብ የጣሉት አሜሪካ ወደ ኩባ ነዳጅ እንዳይጓዝ የጣለችውን እገዳ የሚቃወሙ ኩባውያን በዋና ከተማዋ ሀቫና ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰልፍ በወጡበት በዓለም አቀፉ የላብአደሮች ቀን ነው።

    የአሜሪካ እገዳ በመላ አገሪቱ የኃይል መቋረጥ እና የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

    በደሴቷ አገር ላይ የሚከተሉትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የበለጠ እያጠበቁ ያሉት ትራምፕ፤ የአገሪቱን ኮሚዩኒስት መንግሥት የመቀየር ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል።

    ትራምፕ አርብ ዕለት ከኩባ 145 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በፍሎሪዳ ግዛት ባደረጉት ንግግር አሜሪካ የካረቢያን ደሴት አገሯን “እንደምትቆጣጠር” ተናግረዋል። ይህ እርምጃ በቅርቡ ሊፈጸም እንደሚችልም አመልክተዋል።

    "ከኢራን ስንመለስ ከታላላቅ መርከቦቻችን አንዱን፤ ምናልባትም በዓለም ትልቁ የሆነውን ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ እንዲሄድ እናደርጋለን፤ ከባሕር ዳርቻው 100 ያርድ ርቀት ላይ ሲቆም 'በጣም እናመሰግናለን፣ እጅ ሰጥተናል' ይላሉ" ሲሉ ተደምጠዋል።

    የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ እንዲህ አይነት “የተናጠል አስገዳጅ እርምጃዎች” የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር እንደሚጥስ ገልጸዋል።

    ይህ ዓይነት እርምጃዎች “በኩባ ሕዝብ ላይ የጅምላ ቅጣት ለመጣል” ያለሙ እንደሆኑ ጠቅሰዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ የተካሄዱ ሰልፎች ቪዲዮዎችን አጋርተውም “ሕዝባችን ሸብረክ አይልም” ብለዋል።

  3. እስራኤል ደቡባዊ ሊባኖስ ወስጥ በፈጸመችው ጥቃት 13 ሰዎች ተገደሉ

    እስራኤል ደቡባዊ ሊባኖስ ወስጥ በፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች አራት ሴቶች እና አንድ ሕጻን ልጅን ጨምሮ 13 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    የእስራኤል ጦር ጥቃት በፈጸመበት ናባቴህ አውራጃ በተፈጸመው ድብደባ ከተገደሉት ስምንት ሰዎች ውስጥ ሁለት ሴቶች እና አንድ ሕጻን እንደሚገኙበት ተገልጿል።

    ሁለት ሴቶችን ጨምሮ አራት ሰዎች የተገደሉት ደግሞ ሲዶን አውራጃ ውስጥ ሲሆን አንድ ሰው አኢን ባል በተባለው ስፍራ አንድ ሰው ተገድሏል። በአጠቃላይ 32 ሰዎች ተጎድተዋል።

    የሊባኖስ ተኩስ አቁም ለሦስት ሳምንታት ቢራዘምም በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል የሚደረገው ውጊያ ቀጥሏል። ሄዝቦላህ ዛሬ ቅዳሜ ሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    የእስራኤል ጦር አንድ ሐሙስ ዕለት ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ በተደረገ ውጊያ አንድ ወታደሩ መገደሉን ገልጿል። ከመጋቢት ወዲህ የተገደሉ የእስራኤል ወታደሮች ብዛት 17 ደርሷል።

    የመጀመሪያው የ10 ቀናት ተኩስ አቁም ይፋ የሆነው የእስራኤል እና ሊባኖስ አምባሳደሮች ዋሽንግተን ውስጥ ካደረጉት ንግግር በኋላ ነበር።

    ምንም አይነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሌላቸው ሁለቱ አገራት ከአውሮፓውያኑ 1993 ወዲህ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ንግግር ሲያደርጉ የዋሽንግተኑ የመጀመሪያው ነው።

    ሁለቱ አገራት ለሁለተኛ ጊዜ ከተገናኙ በኋላ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ተኩስ አቁሙ ለሦስት ሳምንት መራዘሙን አስታውቀዋል። ትራምፕ፤ “ራሷን ከሄዝቦላህ እንድትጠብቅ” ከሊባኖስ ጋር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

    በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ውስጥ ባይሳተፍም እስራኤል ስምምነቱን የምታከብር ከሆነ ቡድኑም ለተኩስ አቁሙ እንደሚገዛ ጠቁሞ ነበር።

  4. ኢራን ለእስራኤል የደኅንነት ተቋማት ሰልለዋል ያለቻቸውን ሁለት ሰዎች በሞት ቀጣች

    ኢራን ለእስራኤል ሲሰልሉ ነበር ያለቻቸውን ሁለት ሰዎች በዛሬው ዕለት በሞት ቀጣች።

    በሞት ከተቀጡት መካከል አንዱ በማዕከላዊ ኢስፋሃን በሚገኘው ናታንዝ የኒውክሌር ተቋም አካባቢ የደህንነት መረጃዎች ሲሰበስብ ነበር መባሉን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የመገናኛ ብዙኃኑ ዘገባ እንደሚያመለክተው ያግሆብ ካሪምፖር እና ናስር ባካርዛዴህ የተባሉት ኢራናውያን የደኅንነት መረጃዎችን በማቀበል ከእስራኤል የስለላ ተቋም ጋር በመተባበራቸው በስቅላት ተቀጥተዋል።

    ካሪምፖር ወሳኝ የደኅንነት መረጃ ለሞሳድ ባልደረባ ማቀበሉ ሲገለጽ፣ ባካርዛዴህ ደግሞ ስለ መንግሥት እና የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም በናታንዝ ስለሚገኘው የኒውክሌር ተቋም መረጃዎችን ሲሰበስብ ነበር የሚል ክስ ቀርቦበታል።

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ቴህራን ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በተያያዘ ወንጀል 21 ሰዎችን በሞት መቅጣቷን እና ከ4,000 በላይ ማሰሯን ረቡዕ ዕለት አስታውቋል።

    የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኃላፊ ባወጡት መግለጫ ከተገደሉት መካከል ዘጠኙ በጥር ወር በተካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ ጋር በተያያዘ የተቃዋሚ ድርጅቶች አባል ናቸው በሚል ሲወነጀሉ፣ ሁለቱ ደግሞ በአገር ክህደት ተስሰው መገደላቸውን ገልጸዋል።

  5. አሜሪካ ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ከ8.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ሽያጭ አጸደቀች

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለእስራኤል፣ ኳታር፣ ኩዌት እና ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ 8.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ሽያጭ ስምምነትን ማጽደቁን ሮይተርስ ዘገበ።

    የሽያጭ ስምምነቱ መጽደቁ የተሰማው ከኢራን ጋር እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሁለት ወር ከሞላው በኋላ ነው።

    እስራኤል እና አሜሪካ ቴህራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ከዘጠኝ ሳምነት በኋላ የተኩስ አቁም ተደርሷል።

    ምንም እንኳን የተኩስ አቁሙ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ቢደረስም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል መግባቢያ ላይ ግን መድረስ አልተቻለም።

    አሜሪካ ቴህራንን ወደ ድርድር ለማምጣት በሚል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ እንቅስቃሴን አግዳለች።

    ኢራን በበኩሏ በወሽመጡ ላይ የሚደረግን የመርከቦች እንቅስቃሴ በማገዷ የነዳጅ ዘይት፣ የአፈር ማዳበሪያ እንዲሁም መድሃኒቶች እና ሌሎች የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ንረት አጋጥሟል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የትራምፕ አስተዳደር በሁለቱ አገራት መካከል በተደረሰው የተኩስ አቁም ምክንያት ጦርነቱ መቋረጡን አስታውቋል።

    ትራምፕ አርብ ዕለት በፍሎሪዳ ባደረጉት ንግግር ተቺዎቻቸው አሜሪካ ከኢራን ጋር ያካሄደችውን ጦርነት አላሸነፈችም ብለው መናገራቸውን በመጥቀስ ይህ “ክህደት” ነው ብለዋል።

  6. ትራምፕ የኮንግረስ ቀነ ገደብ መድረሱን ተከትሎ የኢራን ጦርነት “ተቋርጧል” አሉ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተግራዊ እየሆነ ባለው የተኩስ አቁም ምክንያት አሜሪካ ኢራን ላይ የምትፈጽመው ጥቃት “በመቋረጡ” ኮንግረስ ጦርነቱን ለማጽደቅ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ እንደማያስፈልጋቸው ተናገሩ።

    በአሜሪካ ሕግ መሠረት ፕሬዝዳንቱ ወታደራዊ እርምጃ መጀመራቸውን ለሕግ አውጪዎች ባሳወቁ በ60 ቀናት ውስጥ ኮንግረስ ጦርነቱን ሊያጸድቀው ይገባል፤ ካልሆነ ውጊያ ማቆም ይኖርባቸዋል።

    ነገር ግን ትራምፕ ለኮንግረስ መሪዎች በጻፉት ደብዳቤ፤ ባለፈው ወር ከኢራን ጋር ተኩስ አቁም ለማድረግ ስለ ተስማሙ የማጸደቂያ ቀነ ገደቡ መቁጠር አቁሟል ብለዋል። ስለዚህ የኮንግረስን ፈቃድ ግዴታ የሚያደርገውን ‘ዋር ፓወርስ አክት’ ለተሰኘው ሕግ መገዛት እንደማይገባቸው ተከራክረዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን እስካሁን ድረስ ዘላቂ የሰላም ስምምነት ላይ አልደረሱም። ድርድራቸው ቆሞ የነበረ ሲሆን አርብ ዕለት ግን ኢራን በፓኪስታን በኩል አዲስ የሰላም እቅድ አቅርባለች።

    ትራምፕ ለኮንግረስ መሪዎች ደብዳቤ የጻፉት ኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዳቸውን ለምክር ቤቱ ባሳወቁ በ60ኛው ቀን አርብ ዕለት ነው። ከመጋቢት 29/2016 ዓ.ም. “አንስቶ በአሜሪካ ኃይሎች እና በኢራን መካከል ምንም ዓይነት የተኩስ ልውውጥ አልተደረገም" ሲሉ በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።

    “የካቲት 21/2018 ዓ.ም. የጀመረው ግጭት ተቋርጧል" ብለዋል።

    ኢራን አዲስ ዕቅድ ማቅረቧ ከተሰማ በኋላ ትራምፕ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ “"አሁን ከኢራን ጋር ንግግር ነበረን፤ ምን እንደሚፈጠር እናያለን። ነገር ግን ደስተኛ አይደለሁም ማለት እችላለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

    ስምምነት ላይ መድረስ አስቸጋሪ የሆነበት አንዱ ምክንያት በጦርነቱ በርካታ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮቻቸው የተገደሉባቸው የኢራን አመራሮች "በጣም ግራ መጋባታቸው” እንደሆነ ገልጸዋል።

  7. የቱርክ ፖሊስ የወዛደሮች ቀንን ለማክበር አደባባይ የወጡ ከ500 በላይ ሰዎችን አሰረ

    የቱርክ ፖሊስ ዓለም አቀፍ የወዛደሮች ቀንን በማስመልከት በኢስታንቡል አደባባይ የወጡ ሠልፈኞች ላይ አስለቃሽ ጋዝ በመተኮስ ከ500 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነገረ።

    በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ከዚህ ቀደም ጸረ መንግሥት ሰልፎች ወደ ተካሄዱበት የታክሲም አደባባይ ለማምራት የሞከሩ ናቸው ተብሏል።

    በአደባባዩ እአአ ከ2013 ጀምሮ ምንም ዓይነት ሠልፍ ማካሄድ የተከለከለ ሲሆን ሌሊቱን በፖሊስ ዝግ ተደርጓል።

    ቱርክ በየዓመቱ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወዛደሮች ቀንን በማስመልከት ግዙፍ ሠልፎችን ታካሄዳለች።

    ሠልፎቹ የሚዘጋጁት በአገሪቱ ሠራተኞች እና የንግድ ማኅበራት አስተባባሪነት ነው።

    በሠልፉ ላይ የተገኙት የሲኤችዲ ጠበቆች ቡድን ከ500 በላይ ሰዎች ታስረዋል ሲሉ ተናግረዋል። በአንካራ እንዲሁ በርካታ ሰዎች በታንዶጋን አደባባይ ተገኝተዋል።

    ከአርብ ማለዳ ጀምሮ ሠልፎች በሚካሄዱባቸው አደባባዮች ከፍተኛ የጸጥታ አባላት ስምሪት ተስተውሏል።

    የንግድ ማኅበራት በበርካታ የአገሪቱ ከተሞች ሠልፎችን ያዘጋጁ ሲሆን ፕሬዝዳንት ኤርዶዋንም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በኤክስ ገጻቸው አስተላልፈዋል።

  8. ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአዲሱ የኢራን እቅድ ደስተኛ አለመሆናቸውን ተናገሩ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ጦርነቱን ለመቋጨት ያቀረበችው አዲስ የሰላም እቅድ እንዳላስደሰታቸው ገለጹ። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው አሜሪካ አካሄዷን የምትቀይር ከሆነ ኢራን ለዲፕሎማሲ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

    የኢራን ዜና ወኪል ‘ኢርና’ ቴህራን በፓኪስታን በኩል አዲስ የድርድር እቅድ ለአሜሪካ ማቅረቧን ትናንት አስታውቆ ነበር። እቅዱ ስለያዛቸው ዝርዝር ጉዳዮች ግን በዘገባው አልተጠቀሰም።

    የፓኪስታን ባለሥልጣናት በበኩላቸው የኢራንን አዲስ እቅድ ለአሜሪካ ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

    አዲስ እቅድ መቅረቡ በተሰማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለጋዜጠኞች አስተያየት የሰጡት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ “ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ። እኔ አልረካሁበትም፤ ስለዚህ የሚፈጠረውን እናያለን” ማለታቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።

    ትራምፕ ትናንት አርብ በዋይት ሐውስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በእቅዱ ውስጥ ያላስተደሰታቸው ጉዳይ ምን እንደሆነ አላብራሩም።

    የኢራን አመራር “እጅጉን ተከፋፍሏል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “ልስማማበት የማልችለውን ነገር እየጠየቁ ነው” ማለታቸውን ሮይተርስ አስነብቧል።

    ትራምፕ ከቆይታ በኋላ በፍሎሪዳ ተገኝተው ንግግር ባደረጉበት ወቅትም የኢራንን ጉዳይ አንስተዋል። አሜሪካ ከኢራን ጋር የገባችበትን ግጭት በቶሎ ቋጭታ “በተጨማሪ ሦስት ዓመታት ውስጥ ችግር እንዲፈጠር” እንደማትፈቅድ ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት እንደማይፈቅዱ በተደጋጋሚ ገልጸዋል። ኢራን ባለፈው ሳምንት ያቀረበችው የሰላም እቅድ የኒውክሌር ጉዳይ ወደ ጎን ተደርጎ የመጀመሪያው ደረጃ ድርድር ጦርነቱን መቋጨት እና ሆርሙዝን መክፈት ላይ እንዲያተኩር የሚጠይቅ ነበር።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በበኩላቸው አሜሪካ የያዘችውን “የተለጠጠ አካሄድ፣ የዛቻ ንግግር እና ተንኳሽ ድርጊቶች” የምታቆም ከሆነ አገራቸው ለዲፕሎማሲ ዝግጁ መሆኗን እንደተናገሩ ሮይተርስ ዘግቧል።

    ይህም ቢሆን ግን “የኢራን ጦር ኃይሎች አገሪቱን ከማንኛውም ስጋት ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውን” በቴሌግራም ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ገልጸዋል።

  9. የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር የኢራን ጦርነት ባለበት በመቆሙ የኮንግረስን ፈቃድ መጠየቂያ ጊዜ አላለፈም አሉ

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት የትራምፕ አስተዳደር የኢራን ጦርነትን ባለበት በማቆሙ ከኮንግረስ ፈቃድ ለማግኘት የሚያስፈልገው የ60 ቀናት ገደብ አልተጠናቀቀም ሲሉ ተከራከሩ።

    ሄግሴት ይህንን ያሉት ሐሙስ ዕለት በሴኔት አባላት የቀረበላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ ነው። ትራምፕ በይፋ ኮንግረስን ኢራን ላይ ስለሚፈጽሙት ጥቃት ካሳወቁ 60 ቀን የሚሞላው ዛሬ አርብ ነው።

    ኮንግረስ ጦርነት እንዲቀጥል በ60 ቀናት ውስጥ ይሁንታ የማይሰጥ ከሆነ ፕሬዝዳንቱ “የዩናይትድ ስቴትስ ጦርን መጠቀም እንደሚያቋርጡ” በአሜሪካ ሕግ ተደንግጓል።

    አንድ ከፍተኛ የአስተዳደሩ ባለሥልጣን ከኢራን ጋር የሚደረገው ጦርነት የተጀመረው በሚያዚያ ወር ስለሆነ “ተቋርጧል” ሲሉ ተናግረው ነበር።

    አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ከመስማማት በዘለለ የተጀመረው ውይይት ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም።

    ቴህራን ለድርድር የሚሆን አዲስ ነጥቦችን በፓኪስታን በኩል መላኳን የኢራኑ የዜና ወኪል ኢርና ዘግቧል። የዜና ወኪሉ ዝርዝር ጉዳዮችን አልተዘገበም። የፓኪስታን ባለሥልጣናት እቅዱ ለአሜሪካ መሰጠቱን የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ከዘጋች በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨምሮ የነበረ ቢሆንም የኢራን አዲስ የሰላም እቅድ ከተሰማ በኋላ ቅናሽ አሳይቷል።

    ወሽመጡ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ለሁለት ወራት ያህል በመቆየቱ ተጽዕኖው የዓለም ምጣኔ ሃብት ላይ እየታየ ነው።

    ሐሙስ ዕለት ሴናተሮች ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት መከላከያ ሚኒስትሩ “አሁን ያለነው በተኩስ አቁም ውስጥ ነው፤ ይህም በእኛ መረዳት የ60 ቀኑ ሰዓት ለጊዜው ቆሟል ወይም በተኩስ አቁሙ ቆሟል የሚል ነው” ብለዋል።

  10. የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአሜሪካ የጦርነት ወጪ ባለሥልጣናቱ ከገለጹት "አራት እጥፍ" ነው አሉ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣናት ጦርነቱ እስካሁን ድረስ 25 ቢሊዮን ዶላር ስለማስወጣቱ ለምክር ቤት የሰጡትን ማብራሪያ “ውሸት” ሲሉ አጣጣሉ።

    የውጭ ጉዳዩ ሚኒስትሩ ጦርነቱ እስካሁን አሜሪካን “100 ቢሊዮን ዶላር” አስወጥቷታል ብለዋል።

    የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታጎን የፋይናንስ ዋና ኃላፊ ጁሌስ ኸርትስ ከትናንት በስቲያ በአገሪቱ ምክር ቤት ቀርበው ከኢራን ጋር ለሚደረገው ጦርነት እስካሁን 25 ቢሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን ተናግረው ነበር።

    ኸርትስ እንደገለጹት አብዛኛው ገንዘብ የወጣው ለተተኳሽ እና መሣሪያዎችን ለመተካት ነው። የጦርነቱ ወጪ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ መነጋገሪያ ሆኖም ነበር።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ዛሬ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “ፔንታጎን እየዋሸ ነው” ሲሉ ቁጥሩን አጣጥለዋል።

    “[የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር] ኔታንያሁ ቁማር እስካሁን ድረስ አሜሪካን በቀጥታ 100 ቢሊዮን ዶላር አስወጥቷታል፤ ከሚናገሩት አራት እጥፍ” ብለዋል።

    የአሜሪካ መንግሥት ጦርነት ውስጥ መግባቱ የአሜሪካ ታክስ ከፋዮች ላይ ያስከተለው “ቀጥተኛ ያልሆነ ወጪ” ደግሞ “እጅግ ከፍተኛ” መሆኑን ጠቅሰዋል። “የእያንዳንዱ የአሜሪካዊ ወርሃዊ ወጪ ጣሪያ 500 ዶላር ነው፤ በፍጥነትም እየጨመረ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

  11. ኢራን ለሁለተኛው ዙር ድርድር አዲስ እቅድ አቀረበች

    ኢራን ሁለት ወር የተሻገረውን ጦርነት ለመቋጨት ለሚደረገው ድርድር በፓኪስታን በኩል አዲስ የስምምነት እቅድ ማቅረቧን የአገሪቱ መንግሥት የዜና ወኪል ‘ኢርና’ ዘገበ።

    ኢራን ለሁለተኛው ዙር ቀጥተኛ ድርድር ያቀረበችው እቅድ ለአሜሪካ እንደደረሰ የፓኪስታን ባለሥልጣናት የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

    የኢራኑ መገናኛ ብዙኃን ባወጣው ዘገባ፤ “የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ሐሙስ ምሽት አዲሱን የድርድር እቅድ ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር አሸማጋይ ለሆነችው ፓኪስታን አቅርባለች” ብሏል። አዲሱ እቅድ ያካተታቸውን ዝርዝር ጉዳዮች በተመለከተ ዘገባው ማብራሪያ አልሰጠም።

    ሲቢኤስ ኒውስ ያነጋገራቸው የፓኪስታን ባለሥልጣናት ኢራን አዲስ እቅድ ማቅረቧን አረጋግጠው፤ የተከለሰው የቴህራን ምላሽ ለአሜሪካ ባለሥልጣናት መድረሱን ገልጸዋል።

    ኢራን ከዚህ በፊት አቅርባው የነበረው የሰላም እቅድ የኒውክሌር ጉዳይ ወደ ጎን እንዲተው እንዲሁም የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ዙር ንግግር ጦርነቱን ማቆም እና የሆርሙዝ ወሽመጥን መክፈት ላይ እንዲያተኩር የሚጠይቅ ነበር።

    ሀሳቡ ያላስደሰታቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እቅዱን ውድቅ አድርገውታል።

    አሁን ኢራን አዲስ እቅድ ማቅረቧን ተከትሎ ሁለቱ አካላት ስምምነት ላይ ሊደርሱ ይችላል የሚል ተስፋ መጫሩን የፓኪስታን ባለሥልጣናት መናገራቸውን ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

  12. ዩኤኢ፣ ኢራን በሆርሙዝ ላይ እምነት ሊጣልባት አይችልም አለች

    አንድ ከፍተኛ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለሥልጣን አርብ ዕለት ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ የምታደርገው ማንኛውም የአንድ ወገን ውሳኔ ላይ እምነት ሊጣል እንደማይችል ለሮይተርስ ተናገሩ።

    ይህም የኢራንን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት አስቸጋሪ አድርጎ ለመቆየቱ እና በሁሉም ወገኖች ዘንድ ያለውን ጥልቅ አለመተማመንን የሚያሳይ ነው ተብሏል።

    ግጭቱ ከተከሰተ ከሁለት ወራት በኋላም ወሳኝ የሆነው የባህር መተላለፊያ አሁንም በኢራን እገዳ ምክንያት በአብዛኛው የተዘጋ ሲሆን የአሜሪካ የባህር ኃይልም ወደ ኢራንን ወደብ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን አግዷል።

    እገዳው 20 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦቶችን ከማስተጓጎሉም በላይ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከፍ አድረጓል። ይህም የኢኮኖሚ መቀዛቀዝን እንዳይስከትል አስግቷል።

    ከሦስት ሳምንታት በፊት በኢራን እና አሜሪካ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ቢደረግም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቴህራን ላይ ሊሰነዘር ስለታቀደው አዲስ ጥቃት ሐሙስ ዕለት ማብራሪያ ተሰጧቸዋል።

    እቅዱ ኢራንን ወደ ድርድር ለመመለስ ያለመ ቢሆንም የነዳጅ ዋጋን በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮታል።

    ኢራን የአየር መከላከያዎቿን በተጠንቀቅ ያቆመች ሲሆን ጥቃት ከተፈጸመ ሰፊ ምላሽ ለመስጠት ዝታለች።

    በቴህራን ዘንድ አሜሪካ አጭር እና ከባድ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላል የሚል ግምገማ መኖሩን ሁለት ከፍተኛ የኢራን ምንጮች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

  13. ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ ዜጎቿ ከኢራን፣ ኢራቅ እና ሊባኖስ በአስቸኳይ እንዲወጡ አሳሰበች

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዜጎቿ ወደ ኢራን፣ ኢራቅ ወይም ሊባኖስ እንዳይጓዙ ከለከለች።

    የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ "በአሁኑ ወቅት በቀጣናው ባለው ሁኔታ የተነሳ” በማለት የጉዞ እገዳው መደረጉን አስታውቋል።

    በእነዚህ አገራት የሚገኙ ዜጎችም በፍጥነት ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እንዲመለሱ አሳስቦ ሚኒስቴሩን በስልክ እንዲያነጋግሩ ጠይቋል።

    ሚኒስቴሩ በመግለጫው ላይ የሚሰጣቸውን መመሪያዎችና ምክሮች “በሙሉ ማክበር” አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።

    እአአ ከ2021 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዜጎቿ ወደ ሊባኖስ እንዳይጓዙ ከልክላ ነበር። እገዳው የተነሳው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነው።

    የካቲት 21 2018 ዓ.ም. አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በመሆን ኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ ግጭቱ ወደ ሊባኖስ እና ኢራቅ ተዛምቷል።

    ሊባኖስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ላይ ቢደርሱም አሁንም በደቡባዊ ሊባኖስ የሚፈጸመው ጥቃት እንደቀጠለ ነው።

    በሆርሙዝ ወሽመጥም ቢሆን የመርከቦች እንቅስቃሴ እንደቆመ ሲሆን ቴህራን ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው የሰላም ውይይት ተቋርጧል።

  14. በለንደን ሁለት አይሁዳውያን ላይ በስለት ጥቃት ያደረሰው ኢሳ ሱሌይማን በግድያ ሙከራ ክስ ተመሰረተበት

    በሰሜን ምዕራብ ለንደን፣ ጎልደርስ ግሪን ሁለት አይሁዳውያን ላይ በስለት ጥቃት ያደረሰው ኢሳ ሱሌይማን በግድያ ሙከራ ወንጀል ክስ ተመሰረተበት።

    የ45 ዓመቱ ግለሰብ የግድያ ሙከራ በማድረግ እና በአደባባይ ስለት ይዞ በመገኘት ወንጀሎች ክሶች እንደተመሰረቱበት ፖሊስ አስታውቋል።

    ረቡዕ ዕለት 5 ሰዓት አካባቢ ጥቃት የደረሰባቸው የ34 ዓመቱ ሽሎይሜ ራንድ እና የ76 ዓመቱን ሞሼ ሺንን ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

    አይሁዳውያን ላይ በስለት ጥቃት ያደረሰው ሱሌይማን ዛሬ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ፖሊስ አስታውቋል።

    ሱሌይማን የተወለደው ሶማሊያ ውስጥ ሲሆን ወደ ዩኬ የመጣው እአአ በ1990ዎቹ በልጅነቱ ነበር።

    ከዚህ ቀደም እአአ በ2020 የጸረ አክራሪነት ፕሮግራም ሱሌይማን ላይ ክትትል ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ከአንድ ዓመት በኋላ መዝገቡ ተዘግቷል።

    ሐሙስ ዕለት ዩኬ ያለው የሽብር ስጋት ደረጃ ከፍ ማለቱን አስታውቃለች።

    የሽብር ስጋት ከፍ ማለቱን ተከትሎ ሕዝቡ "ንቁ እና ጠንቃቃ" እንዲሆን ነገር ግን "እንዳይረበሽ" የዩኬ የደህንነት ሚኒስትር አሳስበዋል።

  15. የብራዚል ኮንግረስ የቦልሶናሮን የእስር ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ የሚያስችል ዕቅድ አጸደቀ

    የብራዚል ኮንግረስ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጃየር ቦልሶናሮ ባለፈው ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ የመፈንቅለ መንግሥት አሲረው ነበር በሚል የተላለፈባቸውን የእስር ቅጣትን በእጅጉ የሚቀንስ ረቂቅ ሕግ ውድቅ አደረገ።

    ቦልሶናሮ በ2022 ምርጫ ከሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ከተሸነፉ በኋላ በሥልጣን ለመቆየት ባደረጉት ሙከራ 27 ዓመታት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

    የቦልሶናሮን እስር ዘመን ከሁለት ዓመት ትንሽ ከፍ ያለ ለማድረግ የቀረበውን ሃሳብ ሉላ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው ሽረውት ነበር። ሕግ አውጪዎች ሐሙስ ዕለት የእስር ቅጣቱ እንዴት ይሰላል የሚለውን የፕሬዝዳንቱን ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል።

    ሕጉ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ክርክር ሊደረግበት ይችላል።

    የ71 ዓመቱ ቦልሶናሮ በመጋቢት ወር በጤና እክል ምክንያት ለጊዜው በቤታቸው እንዲታሰሩ ተፈቅዶላቸዋል።

    ከ2019 እስከ 2022 በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት የቀድሞው የጦር ካፒቴን፣ ሉላን እና በምክትል ፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩትን ጄራልዶ አልክሚንን ለመግደል ዕቅድ ነበራቸው በሚል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

    የአገሪቱ የጦር ኃይል ከፍተኛ አመራሮች ድጋፍ ሳይደረግላቸው በመቅረቱ ሴራው ባለመሳካቱ ሉላ በጥር 2023 ቃለ መሃላ ፈጸመዋል።

    የሉላ ሃሳብ ውድቅ ከተደረገ በኋላ በርካታ የሕግ አውጪዎች 'ነፃነት' እያሉ መፈክር ያሰሙ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ለመሆን ፍላጎት ያለውን የቀድሞ መሪው የበኩር ልጅ ፍላቪዮ ቦልሶናሮን ስም ደጋግመው ጠርተዋል።

    ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑ የኮንግረሱ አባላት የቀድሞውን ፕሬዚዳንትን የእስር ጊዜ ለመቀነስ የቀረበውን ዕቅድ በመደገፍ ድምጽ ሰጥተዋል።

  16. ኢራን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በሚኖራት ድርድር ፓኪስታን ይፋዊ አደራዳሪ ሆና እንደምትቀጥል አስታወቀች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት የሰላም ውይይት ፓኪስታን ይፋዊ አደራዳሪ መሆኗን አስታወቁ።

    በርካታ አገራት ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን የሰላም ንግግር ለማመቻቸት መሞከራቸውን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ “ፓኪስታን ይፋዊ አደራዳሪያችን ናት” ብለዋል።

    “ንግግሩን ለመቀጠል ውሳኔ ላይ የሚደረስ ከሆነ በግልጽ እናሳውቃለን” ሲሉ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራጋቺ ወደ ሩሲያ ያደረጉትን ጉዞ በመጠቀስ “ኢራን እና ሩሲያ በፖለቲካ፣ ደህንነት እና ምጣኔ ሃብት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነት አላቸው። አሁን ባለው ሁኔታም ኢራን ለተለያዩ አገራት አቋሟን ግልጽ አድርጋለች” ብለዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው ከአሜሪካ የምታደርገው የሰላም ንግግር ሳይካሄድ ከቀረ በኋላ ወደ ኢዝላማባድ፣ ሙስካት እና ሞስኮ በማቅናት ከአገራቱ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ቃል አቀባዩ ከቻይና እና ሩሲያ ጋር ያላትን አገራቸው ያላትን የዲፕሎማሲ ትብብር በማስታወስ “የአንዳንድ የቀጣናው አገራት ተንኮል የተሞላበት ተግባር” በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውድቅ መደረጉን ተናግረዋል።

  17. አሜሪካ የኮንጎ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ ላይ ማዕቀቦችን ጣለች

    አሜሪካ የቀድሞው የኮንጎ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ አማፂያንን ይደግፋሉ በሚል ማዕቀብ ጣለች። ጆሴፍ ካቢላ የተከሰሱት ኤም23 እና ኤኤፍሲ የተባሉ አማፂያን ቡድኖችን በመደገፍ ነው።

    ዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞው የኮንጎ ፕሬዘዳንት ኤኤፍሲ (AFC) ለተባለው አማፂ ቡድን የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ፣ ከኮንጎ ጦር እንዲከዱ ያበረታታሉ፣ አማፂያኑ ድንበር ተሻግረው የመንግሥት ወታደሮች ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ ይደግፋሉ ስትል ወንጅላቸዋለች።

    ባለሥልጣናት የጆሴፍ ካቢላ ዓለማ ኪንሻሳን እንዳትረጋጋ ማድረግ ነው ያሉ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች የፖለቲካ ተጽዕኖ እንዲያገኙ ይጥራሉ በማለት ይከስሷቸዋል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ይፋ ባደረገው ማዕቀብ ውስጥ ካቢላ በአሜሪካ ያላቸው ንብረት ላይ እገዳ ተጥሏል።

    በማዕቀቡ ላይ የአሜሪካ ዜጎችና ኩባንያዎች አብረዋቸው ምንም ዓይነት ሥራ እንዳይሰሩ ክልከላ ተቀምጧል።

    ባንኮች እና የውጭ አጋሮች ከካቢላ ጋር በተዘዋዋሪ የሚያደርጉት ግንኙነትን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ይህንን ጥሶ የተገኘ ከባድ ቅጣቶች እንደሚጠብቀውም አስጠንቅቀዋል።

    ማዕቀቡ የተጣለው ለመቅጣት ብቻ ሳይሆን የባህሪ ለውጥ እንደሚያመጡ ለማስገደድ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ዋሽንግተን ግጭትን በማባባስ የተከሰሱትን የቀድሞ መሪ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ለመጣል ፈቃደኛ መሆኗን ያሳያል።

    ቢቢሲ ከካቢላ የኮሙኒኬሽን ቡድን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

    እአአ በ2025 መስከረም ወር የአገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በአገር ክህደት፣ በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል፣ እንዲሁም ግድያ፣ የወሲብ ጥቃት፣ ማሰቃየት እና ማመጽን ጨምሮ በተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ጥፋተኛ ናቸው በሚል ሞት ፈርዶባቸዋል።

    ካቢላ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ቢናገሩም ችሎት ፊት ቀርበው ግን ራሳቸውን አልተከላከሉም።

    የቀድሞው ፕሬዚዳንት ክሱን "በዘፈቀደ" የተመሰረተ ያሉ ሲሆን ችሎቱን ደግሞ "ለጭቆና መሣሪያ ሆኗል" በማለት ውድቅ አድርገውታል።

    ጆሴፍ ካቢላ አሁን የት እንዳሉ አይታወቅም።

    የ55 ዓመቱ ካቢላ እአአ በ2001 በጥይት የተገደሉትን አባታቸው ላውረን ካቢላን በመተካት ለ18 ዓመታት አገሪቱን አስተዳድረዋል።

    ካቢላ እአአ በ2019 ለፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ ያስረከቡ ቢሆንም በኋላ ግን በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት እአአ በ2023 በፈቃዳቸው አገሪቱን ለቅቀው ተሰድደዋል።

  18. ትራምፕ የንጉሥ ቻርልስን ጉብኝት ተከትሎ በውስኪ ላይ የጣሉትን ታሪፍ ሊያነሱ ነው

    ዶናልድ ትራምፕ የንጉሥ ቻርልስን እና የንግሥት ካሚላን የአሜሪካ ጉብኝት ተከትሎ በውስኪ ምርቶች ላይ ጥለውት የነበረውን ሁሉንም ታሪፎች እና ገደቦች እንደሚያነሱ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስኮትላንድ በኬንታኪ ውስኪ እና ቦርቦን ማምረት ላይ የተጣለባትን ገደብ እንደሚያነሱም አስታውቀዋል።

    የዩኬ መንግሥት ይህ ለሁሉም የውስኪ ምርቶች፣ የአየርላንድ ውስኪን ጨምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን አረጋግጧል።

    የኢንዱስትሪ ተወካዮች "በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና በተፈጠርበት በዚህ ወቅት ይህ እፎይታን የሚሰጥ ነው” ብለዋል።

    ትራምፕ እንዳሉት የንጉሡ ጉብኝት "ብዙም ሳልጠየቅ ማንም ሰው ማድረግ የማይችለውን እንዳደርግ ገፍቶኛል" ብለዋል።

    ንጉሡ እና ንግሥቲቷ በዋሺንግተን ዲሲ፣ ቨርጂኒያ እና ኒው ዮርክ የአራት ቀናት ጉብኝት አድርገው ወደ ቤርሙዳ አምርተዋል።

    የትራምፐን ውሳኔ ተከትሎ የበርኪንግሃም ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ ንጉሡ ለትራምፕ "ልባዊ ምስጋናቸውን" ማቅረባቸውን እንዲሁም "ለፕሬዝዳንቱ አሳቢነት ጽዋቸውን ያነሳሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

    የስኮትላንድ ሚኒስትር ጆን ስዊኒ ውሳኔው "ለስኮትላንድ ታላቅ ዜና" ካሉ በኋላ ንጉሡ ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና አመስግነዋል።

    ስዊኒ አክለውም "ከስኮትላንድ ኢኮኖሚ በየወሩ በሚሊዮን የሚቆጠር ፓውንድ እየከሰረ ነበር" ብለዋል።

  19. እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ

    እስራኤል ከሊባኖስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ብትደርስም በደቡባዊ ሊባኖስ ሐሙስ ዕለት በፈጸመችው ከባድ ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴተር አስታወቀ።

    ሁለተኛ ሳምንቱን በያዘው የተኩስ አቁም አሁንም እስራኤል ጥቃቶችን መፈጸሟን ቀጥላለች።

    እስራኤል ሐሙስ ዕለት የሄዝቦላህ መሠረተ ልማት ናቸው ባለቻቸው ስፍራዎች በፈጸመችው ድብደባ 23 ሰዎች መጎዳታቸውን እና ከእነዚህም መካከል ስምንቱ ሕጻናት፣ ሰባቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

    ሄዝቦላህ በበኩሉ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ የእስራኤል ጦር አባላት ላይ በድሮን ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል በዋሺንግተን ንግግር ከተደረገ በኋላ እአአ ከሚያዚያ 16 ጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረሰ ቢሆንም ግጭቶች ቀጥለዋል።

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ኦወን “ምንም እንኳ የተኩስ አቁም ቢደረስም” እስራኤል ስምምነቱን በመጣስ “ጥቃት መፈጸሟን እንደቀጠለች” ነው በማለት የተቹ ሲሆን፣ በሚደርሱ የአየር ድብደባዎች የመኖሪያ ቤቶች እና የአምልኮ ስፍራዎች እየወደሙ ነው ሲሉ ከስሰዋል።

    "እስራኤል ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና ስምምነቶችን እንድታከብር እና በሲቪሎች፣ በሕክምና ባለሙያዎች፣ በሲቪል መከላከያ እና በሰብአዊ ድርጅቶች ላይ ማነጣጠሯን እንድታቆም ጫና መደረግ አለበት" ብለዋል።

    እስራኤለ በበኩሏ ጥቃቶቹን የምትፈጽመው ሄዝቦላህ ለሚተኩሳቸው ድሮን እና ሮኬቶች ምላሽ ለመስጠት መሆንን በመግለጽ ትከራከራለች።

    በተኩስ አቁም ስምምነቱ ሄዝቦላህ ያልተካተተ ቢሆንም እስራኤል የምታከብር ከሆነ ለስምምነቱ እነደሚገዛ አስታውቆ ነበር።

    የተኩስ አቁሙ በቤይሩት ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚካሄደውን ጥቃት በአብዛኛው ቢያቆምም፣ በደቡባዊ ሊባኖስ ግን የሚካሄደው ድብደባ እንደቀጠለ ነው።

  20. የኢራኑ ጠቅላይ መሪ የአገራቸውን የኒውክሌር አቅም ለመከላከል ቃል ገቡ

    የኢራኑ ጠቅላይ መሪ የእስላማዊ ሪፐብሊኩን የኒውክሌር እና የሚሳዔል አቅም ለመከላከል ቃል ገቡ። ሞጅታባ ኻሜኒ ሐሙስ ዕለት በጽሑፍ በሰጡት መግለጫ አሜሪካ በፐርዢያ ባሕረ ሰላጤ ቦታ እንደሌላት በመግለጽ፣ መገኘት የሚገባት “ከውሃዎቿ በታች ነው” ብለዋል።

    ኻሜኒ በሰጡት መገለጫ ላይ የኢራን የኒውክሌር እና የባሌስቲክ ሚሳዔል ፕሮግራም ለንግግር እንደማይቀርብ አመልክተዋል።

    በቴሌቭዥን በተነበበው የጠቅላይ መሪው መግለጫ አያቶላህ ሞጅታባ ኻሜኒ የአሜሪካን ግዙፍ ወታደራዊ ኃይል ዕቅድ አለመሳካቱን በመግለጽ ጦርነቱ በቀጣናው ታሪክ ውስጥ “አዲስ ምዕራፍ“ ከፍቷል ብለዋል።

    ሞጅታባ ኻሜኒ ኢራን ወሽመጡን መቆጣጠሯ ባሕረ ሰላጤውን የበለጠ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል። መግለጫው አክሎም ቴህራን በወሽመጡ ላይ የሚኖራት “ሕጋዊ አመራር እና አዲስ አስተዳደር” የቀጣናውን ዜጎች በሙሉ ተጠቃሚ ያደርጋል ሲል ገልጿል

    ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸውን መገደል ተከትሎ የጠቅላይ መሪነቱን ሥልጣን ከተረከቡ ጀምሮ ለሕዝብ ታይተው አያውቁም።

    ጠቅላይ መሪው መግለጫውን የሰጡት የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ የሚደርሰው ጫና በበረታበት፣ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ቴህራን ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች ላይ የጣለው እገዳ በቀጠለበት ወቅት ነው።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን ተከትሎ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ አሻቅቧል። ሐሙስ ዕለት የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ በበርሜል 126 ዶላር ተሸጧል።

    ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ወደቦች ላይ የጣሉትን እገዳ እንደሚቀጥሉ የገለጹ ሲሆን አጋሮቻቸው ጥምረት በመፍጠር የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲያስከፍቱ ግፊት እያደረጉ ነው ተብሏል።

    ኻሜኒ በመግለጫቸው ላይ አሜሪካን “ታላቋ ሴጣን” በማለት የጠሯት ሲሆን በፐርዢያ ባህረ ሰላጤ ምንም ጉዳይ የላትም ብለዋል።

    የኢራን የበላይ መሪ "መሣሪያዎቻችን እና ቴክኖሎጂዎቻችን እንደ አገር የማንነታችን አካል ናቸው እና ምንም ቢሆን እንጠብቃቸዋለን" ሲሉ ተናግረዋል።

    “ሁሉም የኢራን አቅሞች ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪ፣ የኒውክሌር እና ሚሳዔል ፕሮግራሞች” በ90 ሚሊዮን የኢራን ሕዝብ የሚታዩት እንደ ውድ ብሔራዊ ሃብቶች መሆኑን ጠቅላይ መሪው ተናግረዋል።

    አክለውም “ልክ ውሃችንን፣ ግዛታችንን እና አየር ክልላችንን እንደምንከላከለው እንጠብቀዋለን” ብለዋል።

    በሺህ ኪሎ ሜትሮች አቋርጠው መጥተዋል ያሏቸውን የውጭ ኃይሎች “በስግብግብነት እና በክፋት” ይንቀሳቀሳሉ ሲሉ ወንጅለው፣ በአካባቢው “ምንም ቦታ የላቸውም። ከውሃው በታች ካልሆነ በስተቀር" ብለዋል።

    ኻሜኒ በዚህ መግለጫቸው ላይ ኢራን ወሽመጡን መቆጣጠሯን እንደምትቀጥል አመልክተዋል።

    ኢራን በወሽመጡ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን 2 ሚሊዮን ዶላር እንደምታስከፍል ትናግራለች።

    እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በቴህራን ላይ የጀመሩት ጦርነት ሁለት ወር አልፎታል።