ቀጥታ, ኢራን የአሜሪካ ጦር መርከብን በሚሳዔል መምታቷን ስትገልጽ፤ ዋሽንግተን አስተባበለች

የኢራን ጦር የአሜሪካ ባሕር ኃይል አውዳሚ የጦር መርከብን በሁለት ሚሳዔል በመምታት ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ እንዳይገባ መከልከሉን ገለጸ። አክሲዮስ የተሰኘው የዜና ምንጭ ጋዜጠኛ ያነገጋራቸው አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ግን የጦር መርከቡ በኢራን ሚሳዔሎች ተመትቷል መባሉን አስተባብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የነዳጅ ኢንዱስትሪ ዞን የድሮን ጥቃት ተፈጸመበት

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ቁልፍ የነዳጅ ወደብ በሆነው ፉጃኢራህ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሦስት ሰዎች “መጠነኛ ጉዳት” እንደደረሰባቸው የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    የኢምሬቶች ትልቁ ወደብ እና የነዳጅ ማከማቻ ስፍራ የሆነው ፉጃኢራህ፤ በኢራን ድሮን ጥቃት ከተፈጸመበት በኋላ ከፍተኛ እሳት መከሰቱን ተገልጿል።

    በደረሰው ጥቃት የተጎዱት የሕንድ ዜግነት ያላቸው ሦስት ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ተብሏል። የከተማው የመገናኛ ብዙኃን ቢሮ ያወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው የደረሰው ጉዳት “መጠነኛ” የሚባል ነው።

    ፉጃኢራህ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ዞን መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ከሚገኙ ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻዎች አንዱ ነው። የተኩስ አቁም ስምምነት ከመደረሱ በፊትም በኢራን ጥቃት ተፈጽሞበት ነበር።

    ስፍራው መመታቱ የተሰማው፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መከላከያ ሚኒስትር ከኢራን የተወነጨፉ ሦስት ሚሳዔሎችን ማክሸፉን ከገለጸ በኋላ ነው። አራተኛው ሚሳዔል ባሕር ላይ እንደወደቀ ተገልጿል።

    እስካሁን ድረስ ኢራን ስለ ጥቃቱ አስተያየት አልሰጠችም።

  2. ኢራን መርከቦች በሆርሙዝ በኩል አልፈዋል የሚለው የአሜሪካ ገለጻ “ሙሉ በሙሉ ሐሰት ነው” አለች

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ፤ የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች ስለማለፋቸው የሰጠው ገለጻ “ፍጹም ውሸት” ነው ሲል አጣጣለ።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ፤ ሁለት የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማን የሚያውለበልቡ የንግድ መርከቦች “በተሳካ ሁኔታ በሆርሙዝ ወሽመጥ ማለፋቸውን” ገልጾ ነበር።

    በኢራን መገናኛ ብዙኃን የወጣው የአብዮታዊ ዘቡ መግለጫ ግን “በቅርብ ሰዓታት አንድም የንግድ ወይም ነዳጅ ጫኝ መርከብ” በሆርሙዝ ወሽመጥ አላለፈም ብሏል።

    የአሜሪካን መግለጫ “መሠረተ ቢስ እና ሙሉ በሙሉ ሐሰት” ሲል የጠራው የኢራን አብዮታዊ ዘብ፤ ከባሕር ኃይሉ ትዕዛዝ ውጪ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ “ከፍተኛ አደጋ እንደሚገጥመው” አስጠንቅቋል።

    ቢቢሲ ቬሪፋይ የአሜሪካን ገለጻ እውነተኛነት ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ ነው። የባሕር ጉዞ መከታተያ የሆነው ‘ማሪን ትራፊክ’ ድረ ገጽ ከአሜሪካ ገለጻ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የመርከብ ጉዞ መደረጉን አያሳይም።

    ይሁን እንጂ መርከቦች አቅጣጫ ጠቋሚያቸውን አጥፍተው ጉዞ ሊያደርጉ ስለሚችል ትክክለኛ ቦታቸው ሳይገለጽ አልፈው ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ።

  3. የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከኢራን ሚሳዔል እንደተተኮሰባት አስታወቀች

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መከላከያ ሚኒስቴር ከኢራን የተወነጨፉ ሦስት ሚሳዔሎችን ማክሸፉን እና አራተኛው ባሕር ላይ መውደቁን አስታወቀ።

    መከላከያ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ እንዳሰፈረው፤ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ፍንዳታ የተሰማው በከሸፉት ሚሳዔሎች ምክንያት ነው።

    ሚኒስቴሩ ይህንን ያለው፤ የአገሪቱ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ባለሥልጣን ለተወነጨፉ ሚሳዔሎች ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ካስታወቀ በኋላ ነው። ባለሥልጣኑ፤ የአገሪቱ ዜጎች ደኅንነቱ የተጠበቀ ስፍራ ውስጥ እንዲቆዩ አሳስቦ ነበር።

    እስካሁን ኢራን ስለ ጥቃቱ አስተያየት አልሰጠችም። በአሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት የተከፈተባት ኢራን፤ ኤምሬቶችን ጨምሮ የባሕረ ሰላጤው አገራትን በማጥቃት አጸፋ ስትሰጥ ቆይታለች።

    ከአሜሪካ ጋር ከተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ግን ጥቃቶቹ ረግበው ነበር። አሁን ኤምሬቶች ላይ ጥቃት የተፈጸመው አሜሪካ በኢራን በተዘጋው ሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚጓዙ መርከቦችን እንደምታጅብ ካስታወቀች በኋላ ነው።

  4. አሜሪካ በኢራን ኃይሎች እና የሚሳዔል ይዞታዎች ላይ እርምጃ ልትወስድ መሆኑ ተነገረ

    በባሕረ ሰላጤው አካባቢ የተሰማሩት የአሜሪካ ኃይሎች በኢራን ሠራዊት እና ይዞታዎች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ መመሪያ እንደተላለፈላቸው ተዘገበ።

    የአሜሪካ የዜና ድረ ገጽ የሆነው አክሲዮስ አንድ የአገሪቱን ከፍተኛ ባለሥልጣን ጠቅሶ እንደዘገበው በቀጣናው ያሉ የአሜሪካ ኃይሎች በሚወስዱት እርምጃ ዙሪያ የነበረው መመሪያ ተለውጧል።

    ስማቸው ያልተጠቀሰው ባለሥልጣን ተናገሩት እንደተባለው በባሕረ ሰላጤው የተሰማሩት የአሜሪካ ኃይሎች “የኢራንን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ፈጣን ጀልባዎች ወይም የሚሳዔል ማስወንጨፊያ ቦታዎችን” ዒላማ እንዲያደርጉ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል።

    የአሜሪካ ሠራዊት ይህንን እርምጃ እንዲወስድ የታዘዘው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ ተጨባጭ ስጋት ይፈጽማሉ ብለው ባመኗቸው ዒላማዎች ላይ ነው።

    የአሜሪካ ሠራዊት እርምጃ የሚወስድባቸው ዒላማዎችን በተመለከተ አዲስ መመሪያ የወጣው አሜሪካ በሆርሙዝ በኩል ለሚተላለፉ መርከቦችን ከለላ እንደምትሰጥ ካሳወቀች በኋላ ነው።

    በዚህም ሳቢያ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ ሲሆን፣ ኢራን በአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ የሚሳዔል ጥቃት መፈጸሟን ስታስታውቅ አሜሪካ ደግሞ ዜናውን በማስተባበል መርከቦቿ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጻለች።

  5. በሆርሙዝ የሚያልፉ መርከቦችን ማጀብ አደጋ እንዳለው የቀድሞ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ካፒቴን ተናገሩ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚጓዙ መርከቦችን ለማጀብ የሚዘጋጅ ማንኛውም ዕቅድ “ከፍተኛ አደጋ” እንደሚያስከትል የቀድሞ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ካፒቴን ለቢቢሲ ተናገሩ።

    የሦስት የአሜሪካ ጦር መርከቦች አዛዥ የነበሩት ኬቪን ኤየር እንዳስረዱት፤ ዋሽንግተን ልትተገበር ያቀደችው መርከቦችን “ለመምራት እና ለማቀናጀት ወይስ በቀጥታ ወደ ውስጥ ገብቶ የተለመደውን የእጀባ” ተግባር ማስፈጸም የሚለው ግልጽ አይደለም።

    “በእነዚህ ሁለት ነገሮች መካከል ያለው ልዩነት በምሽት እና በቀን መካከል እንዳለው ልዩነት ነው። በቀጥታ እጀባ ማድረግ እጅግ አደገኛ እና አስቸጋሪ መፍትሔ ነው” ብለዋል።

    ኢራን አሁንም በርካታ ፀረ መርከብ ባለስቲክ ሚሳዔሎች፣ 1,000 የሚደርሱ ፀረ መርከብ ድሮኖች እና “ሮኬት ሊታጠቁ የሚችሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፈጣን የቅኝት ጀልባዎች” እንዳሏት አንስተዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሆርሙዝ በኩል ማለፍ ያልቻሉ መርከቦችን እንደሚያስወጡ ከተናገሩ በኋላ የአሜሪካ ባሕር ኃይል አውዳሚ መርከቦች እና የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማን ያነገቡ የንግድ መርከቦች ማለፋቸው ተገልጿል።

    ይህ ከመሰማቱ አስቀድሞ የኢራን ጦር የአሜሪካ መርከቦች ወደ ወሽመጡ የሚገቡ ከሆነ ጥቃት እንደሚፈጽም ዝቶ ነበር።

  6. አሜሪካ ሁለት የጦር መርከቦቿ ሆርሙዝን አልፈው ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ እየተንቀሳቀሱ ገለጸች

    አሜሪካ ጦር ሚሳዔል የታጠቁ ሁለት የባሕር ኃይል አውዳሚ የጦር መርከቦቹ ኢራን እገዳ በጣለችበት ሆርሙዝ ወሽመጥ አልፈው በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስታወቀ።

    የአሜሪካን የመካከለኛው ምሥራቅ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የሚመራው ማዕከላዊ ዕዝ እንደገለጸው፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት የተነሳ ማለፊያ ያጡ የንግድ መርከቦችን “እየመሩ ለማውጣት” ላስጀመሩትን ዘመቻ እገዛ እያደረገ ነው።

    ማዕከላዊ ዕዙ፤ የአሜሪካን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ ሁለት የንግድ መርከቦች “በተሳካ ሁኔታ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማለፋቸውንም” ገልጿል። በተሳካ ሁኔታ ወሽመጡን አልፈዋል የተባሉትን መርከቦች ስም ግን አልጠቀሰም።

    ማዕከላዊ ዕዙ አክሎም “የአሜሪካ ኃይሎች የንግድ መርከቦችን ጉዞ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት በንቃት እያገዙ ነው” ብሏል።

    የአሜሪካ ጦር ይህንን ያለው ኢራን ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ለመግባት የሞከረ የአሜሪካ አውዳሚ የጦር መርከብ ላይ ጥቃት ፈጽሜያለሁ ካለች በኋላ ነው።

    ማዕከላዊ ዕዙ ባወጣው መግለጫ ተፈጽሟል የተባለውን ጥቃት አስተባብሏል። አንድም የአሜሪካ መርከብ አልተመታም ያለው ማዕከላዊ ዕዙ፤ የአሜሪካ ኃይሎች ዘመቻውን እየደገፉ እና “በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለን የጉዞ እገዳ እያስፈጸሙ” መሆኑን ገልጿል።

  7. ኢራን በአሜሪካ ጦር መርከብ ላይ ጥቃት ፈጸምኩ ካለች በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ለመግባት የሞከረ የአሜሪካ የጦር መርከብ በሁለት ሚሳዔል መመታቱን ከዘገቡ በኋላ የነዳጅ ዋጋ የጎላ ጭማሪ አሳየ።

    ለዓለም የነዳጅ ንግድ የዋጋ መነሻ የሆነው ብሬንት የአንድ በርሜል የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ዜናው ከተሰማ በኋላ በደቂቃዎች ውስጥ ከአራት ዶላር በላይ ጭማሪ አሳይቶ 114 ዶላር ደርሷል። ይህም በዕለቱ የነዳጅ ዋጋ ላይ ከአምስት በመቶ በላይ ጭማሪን አስከትሏል።

    ኢራን በአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ከገለጸች በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ማስተባበያ ያወጣች ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎም ዋጋው ቅናሽ አሳይቷል።

    ትናንት ምሽት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ መተላለፊያ አጥተው የቆሙ የጭነት መርከቦችን በማጀብ ከአካባቢው የማስወጣት ዕቅዳቸውን አሳውቀው ነበር። ይህንንም ዕቅድ “ሰብአዊነት ማሳያ” ሲሉ ገልጸውታል።

    በባሕረ ሰላጤው አካባቢ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ 20 በመቶ የዓለም ነዳጅ አቅርቦትን የሚያጓጉዙ በርካታ መርከቦች ከነጭነታቸው መንቀሳቀስ ሳይችሉ ባሉበት እየተጉላሉ ይገኛሉ።

    ይህ የአሜሪካ መርከቦች በባሕረ ሰላጤው በኩል እንዲያልፉ የማድረግ ዕቅድ ሌላ ዙር ግጭትን የሚቀሰቅስ ከሆነ በአሁኑ ወቅት በተወሰነ መጠን እያለፈ ያለውን የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦትን በማስቆም የዓለም የነዳጅ ዋጋ የበለጠ እንዲነር ያደርጋል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

  8. የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የነበረ ነዳጅ ጫኝ መርከቧ መመታቱን አስታወቀች

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ‘አድኖክ’ ከተባለው የመንግሥት የነዳጅ ኩባንያ ጋር ግንኙነት ያለው ነዳጅ ጫኝ መርከቧ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ሲጓዝ ጥቃት እንደተፈጸመበት ገለጸች።

    የኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በጥቃቱ የተጎዳ ሰው የለም።

    ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “በኢራን አብዮታዊ ዘብ” ተፈጽሟል ያለውን ይህንን ጥቃት “የባሕር ውንብድና” ሲል አውግዞታል።

    የኢራን ጦር “ንግድ መርከቦችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት እየፈጸመ እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለኢኮኖሚ ማስገደጃነት ወይም ለዛቻ መሣሪያነት” እየተጠቀመ ነው ሲልም ወቅሷል።

    ይህ አይነቱ ጥቃት “በቀጣናው መረጋጋት፣ በሕዝቦቹ እና በዓለም አቀፍ የኤነርጂ ደኅንነት ላይ ቀጥተኛ ስጋት የሚጋርጥ ነው" ሲልም ተቃውሟል።

    ድርጊቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔን “በግልጽ የጣሰ” እንደሆነ የገለጸችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ ኢራን ጥቃት መፈጸም እንድታቆም ጠይቃለች።

    "ሁሉንም ጠበኛ ድርጊቶች በአስቸኳይ ለማቆም እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ለመክፈት ያላትን ቁርጠኝነት እንድታረጋግጥም" ጥሪ አቅርባለች።

  9. ኢራን ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ሊገባ የነበረን የአሜሪካ የጦር መርከብን በሚሳዔል መምታቷን ገለጸች

    የኢራን ጦር ወደ ሆርሙዝ ሊገባ የነበረ የአሜሪካ ባሕር ኃይል አውዳሚ የጦር መርከብን በሁለት ሚሳዔል በመምታት ወደ ወሽመጡ እንዳይገባ መከልከሉን ገለጸ።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱን ጦር የሕዝብ ግንኙነት ጠቅሰው ባወጡት ዘገባ፤ "ከእስላማዊ ሪፐብሊክ ባሕር ኃይል በተሰጠው ጠንካራ እና ፈጣን ትዕዛዝ የአሜሪካ እና የጽዮናዊው ጠላት አውዳሚ መርከቦች ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ እንዳይገቡ ተከልክለዋል" ብለዋል።

    ከፊል ይፋዊ የዜና ወኪል የሆነው ፋርስ፤ የኢራን ባሕር ኃይል ጦር ሠፈር መገኛ በሆነው ጃስክ ወደብ አቅራቢያ አንድ የጦር መርከብ በሁለት ሚሳዔሎች መመታቱን ዘግቧል።

    የጦር መርከቡ በወሽመጡ ደቡባዊ መግቢያ በኩል ሲቀዝፍ የነበረው “የባሕር ላይ ትራፊክ እና የመርከብ ጉዞ ደኅነትን በመጣስ” እንደሆነ ዘገባው ጠቅሷል።

    እንደ ፋርስ ዘገባ ከሆነ የአሜሪካው የጦር መርከብ “ለማፈግፈግ እና ከአካባቢው ለመሸሽ ተገድዷል።”

    አክሲዮስ የተሰኘው የዜና ምንጭ ጋዜጠኛ ያነገጋራቸው አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ግን የጦር መርከቡ በኢራን ሚሳዔሎች ተመትቷል መባሉን አስተባብለዋል።

    የኢራን ጦር ይህንን ያለው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ጦር በወሳኙ የባሕር ወሽመጥ ላይ ማለፊያ አጥተው የቆዩ መርከቦች ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ እገዛ እንደሚያደርግ ከተናገሩ ከሰዓታት በኋላ ነው።

    “ፕሮጀክት ፍሪደም” በተባለው በዚህ ዘመቻ ላይ 15 ሺህ ወታደሮች፣ ሚሳዔል ተሸካሚ አውዳሚ መርከቦች እና ከ100 በላይ ተዋጊ አውሮፕላኖች እንደሚሳተፉም ተገልጿል።

    ይህንን ተከትሎም ኢራን "ለአሜሪካ ዛቻዎች ምላሽ ለመስጠት" ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።

  10. የዩኬ ባሕር ትራንስፖርት ባለሥልጣናት በሆርሙዝ ወሽመጥ አደገኛ ስጋት መኖሩን አስጠነቀቁ

    የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማቋረጥ የሚሞክሩ መርከቦች “በቀጣናው እየተካሄዱ በሚገኙ ወታደራዊ ዘመቻዎች” ምከንያት “አደገኛ የደህንነት ስጋት” እንደሚገጥማቸው የዩኬ የባሕር ትራንስፖርት እና ንግድ ሥራዎች ማዕከል አስጠነቀቀ።

    የባሕር ትራንስፖርት ባለሥልጣኑ መርከቦች “የፈንጂዎችን አደጋ ወይም ለመጓዝ ባሰቡበት መስመር የሚኖር ሌላ የአደጋ ስጋትን” ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

    በወሽመጡ ውስጥ ማለፍ ወይም በጉዞ መለያ ስፍራው መጓዝ በጣም አደገኛ መሆኑን ባለሥልጣኑ ጨምሮ ገልጿል።

    ምክንያቱም ያልተገኙ እና እንዲወገዱ ያልተደረጉ ፈንጂዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ወይም ደህንነቱ ያልተጠበቀ መስመር ሊሆን እደሚችል አስጠንቅቋል።

    የጉዞ መለያ መስመር ማለት በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችን በሚመለከት እአአ በ1968 የተደረሰ ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው።

  11. ኢራን 'ለአሜሪካ ዛቻዎች ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ገለጸች

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከ"ሰኞ ጠዋት" ጀምሮ መርከቦችን ማስወጣት እንደሚጀምር መግለጻቸውን አስመልክቶ ኢራን ምላሽ ሰጥታለች።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወሽመጡ ዙሪያ "ለአሜሪካ ዛቻዎች ምላሽ ለመስጠት" ዝግጁ መሆኗን አስታውቋል።

    ሜህር የዜና ወኪል ባጋራው መግለጫ ቃል አቀባዩ ኢስማኤል ባጋይ ኢራን የባህር ወሽመጡ "ጠባቂ እና ተከላካይ” ሆና ትቀጥላለች ብለዋል። "መርከቦች እና የመርከብ ኩባንያዎች ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ ከኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ባለስልጣናት ጋር መተባበርን እንደሚጠይቅ በሚገባ ያውቃሉ" ሲሉ አክለዋል።

    የሕግ የበላይነትን የሚከተሉ አገሮች የአሜሪካን "ሕገወጥ እርምጃዎች" የሚከተሉበት ምንም ምክንያት እንደሌለም ተናግረዋል።

    ቀደም ሲል የኢራን ማዕከላዊ ዕዝ ኃላፊ "በተለይም ጠበኛው የአሜሪካ ጦርን” ጨምሮ ወደ ባህር ወሽመጡ ለመቅረብ ወይም ለመግባት የሚሞክርን "ማንኛውም የውጭ የጦር ኃይል" እንደሚያጠቃ ተናግረዋል።

  12. ባለፈው ወር በአሜሪካ ጦር የተያዘችው የኢራን መርከብ አባላት ለቴህራን ሊሰጡ ነው

    ባለፈው ወር በአሜሪካ ቁጥጥር ስር የዋለችው የኢራን መርከብ ሃያ ሁለት ሠራተኞች ለፓኪስታን ተላልፈው መሰጠታቸው ተገለጸ።

    የፓኪስታን መንግሥት "ዛሬ ለኢራን ባለሥልጣናት ይተላለፋሉ” ሲል አስታውቋል።

    የአሜሪካ ወታደሮች ባለፈው ወር ቱስካ በተሰኘው መርከብ የተቆጣጠሯት ሞተሯን ከመቱ በኋላ ነበር። ኢራን ድርጊቱን "የባህር ላይ ውንብድና" ስትል የጠራችው ሲሆን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደግሞ መርከቡ "የባህር ኃይላችንን እገዳች ለማለፍ ቢሙክሩም አልተሳካላቸውም" ብለዋል።

    የመርከቡ ሠራተኞች ወደ አገራቸው መመለሳቸው “በዩናይትድ ስቴትስ የተወሰደ የመተማመን ግንባታ እርምጃ" እንደሆነ ፓኪስታን ገልጻለች።

    መርከቧ "አስፈላጊው ጥገና ከተደረገለት በኋላ ወደ መጀመሪያዎቹ ባለቤቶቿ ለመመለስ ወደ ፓኪስታን የውሃ አካል ትመለሳለች” ሲል አክሏል።

    "እነዚህ ተመላሾች በኢራን እና በአሜሪካ ድጋፍ ጋር በመተባበር እየተቀናጁ ነው። መርከበኞቹን ለመመለስ ኢራን እና አሜሪካ ትብብር ማድረጋቸውን የፓኪስታን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

    "ፓኪስታን እንዲህ ዓይነት መተማመንን የሚገነቡ እርምጃዎችን ትደግፋለች። ለቀጣናው ሰላም እና ደህንነት የሚደረጉ ቀጣይነት ያላቸውን የድርድር እና የዲፕሎማሲ ጥረቶችን ማድረጓንም ትቀጥላለች" ብሏል።

  13. የኢራን ጦር አሜሪካ ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ የምትገባ ከሆነ ጥቃት እንደሚፈጽም አስጠነቀቀ

    የኢራን ጦር የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገባ ከሆነ ጥቃት እንደሚፈጽም አስጠነቀቀ።

    ዶናልድ ትራምፕ በወሽመጡ መንቀሳቀሻ አጥተው የቆሙ መርከቦችን እየመሩ ለማስወጣት መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል።

    የኢራን ማዕከላዊ ዕዝ ያወጣው መግለጫ “ማንኛውም የውጭ ጦር ኃይል” ወደ ወሽመጡ ለመግባትም ሆነ ለመቅረብ ቢሞክር “በተለይ የጠብ አጫሪዋ የአሜሪካ ጦር” ጥቃት እንፈጽማለን ብሏል።

    ሜጀር ጄነራል አሊ አብዶላሂ ኢራን “በተደጋጋሚ” ወሽመጡ በጦሯ “ቁጥጥር ስር መሆኑን” እና ለማለፍ የሚፈልግ “በሁሉም ሁኔታዎች ስር” ከቴህራን ጋር መተባባር እንደሚያስለፈልገው መናገራቸውን አስታውሰዋል።

    የጦሩ መግለጫ በኢራን መገናኛ ብዙኃን በሆነው ኢሪብ ተጋርቷል።

    እሁድ ዕለት ትራምፕ መርከቦቻቸው በሆርሙዝ ወሽመጥ የቆሙባቸውን አገራት እንደሚያግዙ ተናግረዋል። ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወታደሮቹ እና የጦር አውሮፕላኖቹን ዝግጁ ማድረጉን አስታውቋል።

    ትራምፕ “ለኢራን፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለዩናይትድ ስቴትስ ደህንነት ሲባል ለአገራት መርከቦቻቸውን እየመራን እገዳ ከተጣለበት የውሃው አካል እንደምናስወጣላቸው ነግረናቸዋል። ስለዚህ በነጻነት ወደሚቀጥለው ጉዳይቸው መሄድ ይችላሉ” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ ቆመው ያሉት እና አሜሪካ ድጋፍ ልታደርግላቸው መሆኑን የነገረቻቸው የየትኞቹ አገራት መርከቦች እንደሆኑ አላሰወቁም።

  14. 20,000 የመርከብ ሠራተኞች እና 2,000 መርከቦች መንቀሳቀሻ አጥተው ቆመዋል

    ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ የቆሙ መርከቦችን “እየመራች” ልታስወጣ መሆኑን ከመናገራቸው ቀደም ብሎ የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት በለንደን በካሄዱት ስብሰባ ኢራን በዓለም አቀፍ የመርከብ ጭነት ላይ የምታደርሰውን መስተጓጎል "በጥብቅ አውግዘዋል።”

    ስብሰባው ዓለም አቀፉ የባህር ኃይል ድርጅት (የመርከብ ጭነትን የሚቆጣጠረው ልዩ የተባበሩት መንግሥታት ተቋም) ያቀረበውን ውሳኔ አጽድቋል። ኢራን የመርከብ ሠራተኞችን ደህንነት "አደጋ ላይ በመጣል ከባድ ስጋትን እና ለባህር አካባቢ አደጋን ፈጥራለች" ሲል ገልጿል።

    ከድምጽ አሰጣጡ በኋላ የተቋሙ ኃላፊ አርሴኒዮ ዶሚንጌዝ የመርከበኞች እርዳታ ላይ ትኩረት እንዲደረግ አሳስበዋል።

    "በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በምንሠራበት መንገድ ዙሪያ ያለኝን ብስጭት መግለጽ እፈልጋለሁ" ብለዋል።

    "እነዚህ ውይይቶች እና ሂደቶች ለዘጠኝ ሳምንታት መንቀሳቀሻ አጥተው የቆዩትን 20,000 የመርከብ ሠራተኞችን እና 2,000 መርከቦችን እንዴት እንደሚረዱ አላየሁም" ሲሉ አስረድተዋል።

  15. የትራምፕን ‘ፕሮጀክት ፍሪደም’ ለመደገፍ 15 ሺህ ወታደሮች እና 100 የጦር አውሮፕላኖች ይሳተፋሉ

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) የትራምፕን ፕሮጀክት ፍሪደም እንዴት አድርጎ እንደሚያስፈጽም ይፋ አድርጓል።

    “የዩኤስ ማዕከላዊ ዕዝ ጦር በሆርሙዝ ወሽመጥ የንግድ መርከቦች ያለ ችግር እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል ፕሮጀክት ፍሪደምን ሚያዚያ 26 ድጋፍ ይሰጣል” ሲል እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል።

    ይህ ድጋፍ 15,000 ወታደሮችን፣ ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ ሚሳዔል አውዳሚዎችን እና 100 አውሮፕላኖቸን የሚያካትት ነው።

    ሴንትኮም “በባሕሩ ላይ የሚካሄደው የዓለም አንድ አራተኛ ነዳጅ ንግድ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ እና የማዳበሪያ ምርት በወሽመጡ ላይ ነው የሚጓጓዘው” ብሏል።

    የሴንቲኮም አዛዥ የሆኑት አዳም ብራድ ኩፐር “የባሕር ላይ እገዳችን ባለበት የመከላከል ተልዕኮ ያለው ድጋፋችን ለቀጣናው ደህንነት እና ለዓለም ምጣኔ ሃብት ወሳኝ ነው“ ብለዋል።

    ሴንትኮም አዛዥ አድም ብራድ ኩፐር አክለውም “ለዚህ የመከላከያ ተልእኮ የምናደርገው ድጋፍ ለክልላዊ ደህንነት እና ለአለም ኢኮኖሚ አስፈላጊ ነው ።

  16. ትራምፕ አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ የቆሙ መርከቦችን “እየመራች” ልታስወጣ መሆኑን ተናገሩ

    እሁድ ዕለት ትራምፕ መርከቦቻቸው በሆርሙዝ ወሽመጥ የቆሙባቸውን አገራት እንደሚያግዙ ተናገሩ።

    “ለኢራን፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለዩናይትድ ስቴትስ ደህንነት ሲባል ለአገራት መርከቦቻቸውን እየመራን እገዳ ከተጣለበት የውሃው አካል እንደምናስወጣላቸው ነግረናቸዋል። ስለዚህ በነጻነት ወደሚቀጥለው ጉዳይቸው መሄድ ይችላሉ” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ ቆመው ያሉት እና አሜሪካ ድጋፍ ልታደርግላቸው መሆኑን የነገረቻቸው የየትኞቹ አገራት መርከቦች እንደሆኑ አላሰወቁም።

    ትራምፕ “ፕሮጀክት ፍሪደም” (የነጻነት ፕሮጀክት) ሲሉ የጠሩት ይህ መርከቦችን ከወሽመጡ የማስወጣት ሂደት ሰኞ ዕለት እንደሚጀመር ተናግረዋል።

    ትራምፕ ይህ መርከቦቸን የማስወጣት ሂደትን ለማደናቀፍ የሚሞክር ካለ “የኃይል እርምጃ” እንደሚወስዱ አስጠንቀቅቀዋል።

    ኢራን ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ በወሽመጡ ላይ የሚደረግ እንቅስቃሴን ሙሉ በሙሉ አግዳለች።

    ዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁ ወደ ኢራን ወደቦች መርከቦች እንዳይገቡ እና እንዳይወጡ እገዳ ጥላለች።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥ የነበሩት እና አሁን የፓርላማ አባል የሆኑት ኢብራሂም አዚዝ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “ማንኛውም የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት” እንደ “የተኩስ አቁም ጥሰት” ይቆጠራል ብለዋል።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ልጥፋቸው ላይ የአሜሪካ ተወካዮች ከኢራን ጋር “በጣም አዎንታዊ” የሆነ ውይይት ማካሄዳቸውን ጠቅሰው “ሁላችንንም በጣም በጎ ወደ ሆነ ነገር ይመራል” ብለዋል።

    አክለውም መርከቦችን ከወሽመጡ የማስወጣት ዘመቻ “የሰብዓዊነት እርምጃ” መሆኑን ተናግረው በአሜሪካ፣ ኢራን እና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ስም የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።

    ትራምፕ በዚህ ልጥፋቸው ላይ ከቴህራን ጋር ያለው ትብብር በምንም መልኩ እንደሚስተናገድ ያሉት ነገር የለም።

    ትራምፕ ". . . የመርከብ እንቅስቃሴው ምንም ጥፋት ያልፈጸሙ ሰዎችን፣ ኩባንያዎችን እና አገራትን ለማስለቀቅ የሚደረግ ብቻ ነው" ሲሉ አብራርተዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በፕሮጀክት ፍሪደም ላይ 15,000 ወታደሮች፣ ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ ሚሳዔል ማምከኛዎች እንዲሁም ከ100 በላይ አውሮፕላኖች እንደሚሳተፉ አስታውቋል።

    በባሕረ ሰላጤው ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወደ 20,000 የሚገመቱ ባህረተኞች መንቀሳቀሻ አትተው መቆማቸው ይገመታል።

    ለመርከቦቹ እና ሠራተኞቻቸው በየጊዜው እየቀነሰ የመጣው አቅርቦት እና የባሕረተኞቹ አካላዊ እና የአእምሮ ጤና አሳሳቢነት እያደገ መጥቷል።

    የዓለም 20 በመቶ የሚሆነው ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚተላለፈው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነው።

  17. ኢራን ላቀረበችው የሰላም ዕቅድ አሜሪካ ምላሽ መስጠቷን ገለጸች

    ኢራን ላቀረበችው የሰላም ዕቅድ ከአሜሪካ ምላሽ ማግኘቷን የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አሜሪካ የሰጠችው ምላሽ በፓኪስታን በኩል እንደደረሳቸው እና እየተመለከቱት መሆኑን መናገራቸውን ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።

    አሜሪካ እስካሁን ድረስ ለቴህራን የሰላም ዕቅድ ምላሽ መስጠቷን በይፋአላሳወቀችም። ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እሁድ ዕለት ለእስራኤሉ ካን ኒውስ ዕቅዱ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን የቴህራን ባለ 14 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ዋሺንግተን ጦሯን ከድንበር አካባቢ እንድታርቅ፣ የኢራን ወደቦች ላይ ያለቸውን እገዳ እንድታነሳ እንዲሁም የትኛውም ግጭት፣ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጨምሮ እንዲቆም የሚጠይቅ ነው ሲሉ ዘግበዋል።

    ዕቅዱ በሁለቱ አገራት መካከል በሰላሳ ቀናት ውስጥ ስምምነት እንዲደረስይጠይቃል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን አክለውም የሰላም ዕቅዱ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች አሁን ያለውን የተኩስ አቁም ከማራዘም ይልቅ “ጦርነቱን በማስቆም” ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ይጠይቃል።

    መገናኛ ብዙኃኑ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይን ጠቅሰው “አሁን ባለው ደረጃ ስለ ኒውክሌር ድርድር የለም” ማለታቸውን ዘግበዋል።

    ኢራን በተደጋጋሚ የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ የሚውል መሆኑን ትናገራለች።

    ነገርግን ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባይኖራትም ዩራኒየምን የጦር መሣሪያ ለማምረት በሚያስችል ደረጃ ያበለጸገች ብቸኛ አገር ናት።