በዩኬ የሃይማኖት ቡድን ውስጥ ዘመናዊ ባርነት እና ወሲባዊ ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ ዘጠኝ ሰዎች ታሰሩ

አምቡላንስ

የፎቶው ባለመብት, ቼሻህ ፖሊስ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዩናይትድ ኪንግደም ቼሸር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሺዓ እስልምና አባል ነን በሚሉ አማኞች ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ምክንያት በተካደሄ በሰፊ ዘመቻ ሰዎች መያዛቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

በሃይማኖቱ ተከታዮች ውስጥ በሚደረግ ጾታዊ ጥቃት፣ የግዳጅ ጋብቻ እና ዘመናዊ ባርነት ተንሰራፍቷል በሚል የዩናይትድ ኪንግደም ፖሊስ ባደረገው ከፍተኛ ዘመቻ ዘጠኝ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል። ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ በሦስት ቦታዎች ከ500 በላይ የጸጥታ አካላት ተሰማርተዋል።

ሃይማኖታዊ ቡድኑ አሃማዲ የሰላም እና የብርሃን ሃይማኖት ይባላል። ይህ ሃይማኖታዊ እሳቤ ከአውሮፓውያኑ 2000 መጀመሪያ አካባቢ በሺያ ሙስሊም ተከታይ አባላት ዘንድ የተጀመረ ነው። ነገር ግን የሺዓ ሙስሊም እምነት አራማጆች አዲሱን ሃይማኖት አይቀበሉትም።

በእነዚህ ራሳቸውን የሺዓ ሙስሊም አካል አድርገው በሚቆጥሩት የአሃመዲ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ጥቆማዎች መሰጠት የጀመሩት ከ2023 ጀምሮ መሆኑን በዩናይትድ ኪንግደም የቼሸር ፖሊስ ገልጿል። ፖሊስ እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት የሃይማኖቱ ተከታዮች ክሬው በሚባል አካባቢ 150 አባላት አላቸው።

ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, ቼሻህ ፖሊስ

ፖሊስ ካሰራቸው ዘጠኝ ሰዎች መካከል ስድስቱ ወንዶች ሲሆኑ ሦስቱ ሴቶች ናቸው። የአሜሪካ፣ የሜክሲኮ፣ የጣሊያን፣ ስፔን እና የብሪታኒያ ዜጎች ይገኙበታል።

ፓሊስ ተጠርጣሪዎቹን ቢይዝም ምርመራ የሚያደርገው ግን ሃይማኖቱ ላይ አለመሆኑን ገልጿል። ከምርመራው ጋር ባይያዝም የማኅበረሰብ መስተጋብርን በመተላለፍ 13 ሌሎች ሰዎችም ታስረዋል።

የሃይማኖቱ ተከታዮች ቼሸር ውስጥ በርካታ ንብረቶችን አፍርተዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ ክሶች ቀርበውባቸዋል። የ30 ዓመቱ ሜክሲኳዊ በግዳጅ ጋብቻ፣ ጾታዊ ጥቃት እና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠርጥሯል።

የ44 ዓመቷ ጣሊያናዊት ደግሞ በጾታዊ ጥቃት እና ዘመናዊ ባርነትን በመፈጸም ተጠርጥራ ተይዛለች። በአጠቃላይ ዘጠኙ ተጠርጣሪዎች ከስድስት የተለያዩ አገራት የተሰባሰቡ ናቸው።

አንዱ ተጠርጣሪ የግብጽ ዜግነት ያለው ሲሆን፣ ጾታዊ ጥቃትን በመፈጸም እና ዘመናዊ ባርነትን በመተግበር ተከሷል።

ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ የአየርላንድ እና የስዊድን ፖሊሶችን አሳትፏል።

አሃመዲ የሰላም እና የብርሃን ሃይማኖት (አርፖል) የተመሰረተው በዚህ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ሲሆን ተከታዮቹ ራሳቸውን የሺዓ እስልምና አካል አድርገው ይቆጥራሉ።

ነገር ግን ዋናዎቹ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች አሃመዲዎች በአመለካከት የተራራቁ እንደሆኑ ይገልጻሉ። አሃመዲ ሃይማኖት እስያ ውስጥ የተመሰረተ ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደምም በርካታ ተከታዮች ያሉት የሃይማኖት ዘርፍ ነው።

ፖሊስ በሁሉም ክሶች ተገቢ ፍትህ እንዲሰጥ በጥብቅ እንደሚሰራ አስታውቋል። በሌላ በኩል የሃይማኖት ቡድኑ አባላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።

በፖሊስ ዘመቻ የተደናገጡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, ቼሻህ ፖሊስ

በአካባቢው ባልተለመደ መልኩ የፖሊስ ዘመቻ መደረጉን ተከትሎ በነዋሪዎች ዘንድ መደናገጥ ተፈጥሯል። ነገር ግን ፖሊስ "ሕዝቡ ላይ የሚደርስ ምንም ዓይነት ጫና የለም። ፍላጎታችን ፍትህ ማስፈን ነው። ለዚህ ደግሞ ማረጋገጫ መስጠት እንችላለን። ለዚህም ተጨማሪ ቅኝቶች እየተደረጉ ነው" ብሏል።

በአካባቢው ፖሊስ በስፋት እና ለረጅም ጊዜ እንደሚሰማራ ተገልጿል። ይህም የሚሆነው ለተጀመሩት ክሶች የማጠናከሪያ መረጃ ፍለጋ እና የአካባቢውን ነዋሪ ለማረጋጋት ነው።

የአካባቢው የሠራተኛ ፓርቲ የፓርላማ አባል የሆኑት ኮኖር ናይስሚዝ፣ የፖሊስ ዘመቻው የአካባቢውን ነዋሪ እንደሚያስጨንቅ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

"ነዋሪዎች ምን ሊሰማቸው እንደሚችል እና እንደሚደናገጡ መረዳት ይቻላል" ያሉት የፓርላማ አባሉ፣ "ይህ ፖሊስ ለነዋሪው ደኅንነት ሲባል የሚያካሂደው ከባድ ዘመቻ ነው" ብለዋል።