አሜሪካ 'ሰላዮችን አጥቅቷል' ለተባለው በሽታ ተጎጂዎች ሦስት ሚሊዮን ዶላር ከፈለች

የበሽታው ምልክቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በኩባ ዋና ከተማ ሃቫና በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞች ላይ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የበሽታው ምልክቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በኩባ ዋና ከተማ ሃቫና በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞች ላይ ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ መንግሥት በሰላዮች፣ ዲፕሎማቶች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ በታየው 'ሃቫና ሲንድረም' ተብሎ የሚጠራ ምስጢራዊ የነርቭ ሕመም ለተጎዱ ሰዎች ሦስት ሚሊዮን ዶላር ገደማ ካሳ ከፈለ።

ስለዚህ በሽታ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው ከአስር ዓመት በፊት በኩባ ዋና ከተማ ከሚሠሩ የሲአይኤ መኮንኖች ነበር። የአሜሪካ መንግሥት ከዚህ በሽታ ጋር በተያያዘ ክፍያ ሲፈጽም የአሁኑ የመጀመሪያው ነው።

ከኩባ በኋላ ቻይናን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የአሜሪካ መንግሥት ሠተራኞች "ያልተለመዱ የጤና ክስተቶች" አጋጥሟቸዋል።

ታማሚዎቹ፤ ዝቅ ያለ ሹክሹክታ፣ ሲጢጥ የሚል አይነት ድምፅ እንዲሁም "የሚቆረጥ ብረት" አይነት ድምጾች እንደሚሰሟቸው ተናግረዋል። ሌሎች ደግሞ በራስ ቅላቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲሁም የማዞር እና የማቅለሽለሽ ምልክቶችን ገልጸዋል።

በኩባ ዋና ከተማ ሃቫና የተሰየመውን ይህ በሽታ የተመለከተ ሕግ በአውሮፓውያኑ 2021 ወጥቷል።

የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት በ'ሃቫና ሕግ' አማካኝነት "ለተጎዱ ሠራተኞች የሚቀርበው እንክብካቤ" ቅድሚያ ተሰጥቶት እንደቀሚጥል ካሳውን ይፋ ባደረገበት ወቅት ገልጿል።

ሃቫና ሲንድረም ምንድነው? ተጠያቂውስ ማነው? የሚለው ጉዳይ ለረጅም ጊዜ የተለያዩ መላ ምቶች ሲሰጡበት ቆይቷል።

አንዳንዶች ሕመሙ በ'ማይክሮዌቭ' የተነሳ እንደመጣ ይከራከራሉ። የተለያዩ አገራት ኃይሎች ከአገር ውጪ የሚገኙ የአሜሪካ ሠራተኞችን እና ቤተሰቦቻቸውን ለማጥቃት አንዳች አይነት የድምፅ መሣሪያ ተጠቅመዋል የሚለው መላምት በስፋት ተሰራጭቷል።

ኤሪካ ስቲዝ የተባለች የቀድሞ የሲአይኤ ሠራተኛ 2022 ላይ ለሲቢኤስ ኒውስ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ፤ "አዕምሮዬ ተሰብሯል" ብላ ነበር።

"ይህ የደረሰብን አገራችንን በማገልገላችን ነው። እንክብካቤ ሊደረግልን ይገባል" ብላለች።

ብዙዎቹ የአሜሪካ የስለላ ተቋማት እና መሥሪያ ቤቶች ባለፈው ዓመት ላይ የውጭ አካል የአሜሪካ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸውን ለመጉዳት ሲል "አዲስ የጦር መሣሪያ ወይም ፕሮቶታይፕ መሣሪያ" ተጠቅሟል የሚለው መላምት "የመሆን ዕድሉ እጅግ ዝቅተኛ" ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

አነስተኛ ቁጥር ያለው የአሜሪካ የስለላ ማኅበረሰብ ግን መላምቱን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አላደረጉትም።

የአሜሪካ ብሔራዊ የስለላ ምክር ቤት ባወጣው ሪፖርት፤ የትኛውም ተቋም ወይም መሥሪያ ቤት የአሜሪካ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው "ያሳለፉትን ወይም የደረሰባቸውን ስቃይ ጥያቄ ውስጥ አልከተተውም" ብሏል።

እንደ የስለላ ማኅበረሰቡ፤ ሠራተኞቹ "እውነተኛ፣ አንዳንድ ጊዜ ህመም የሚፈጥር እና የአዕምሮ ጉዳት የሚያስከትል፣ አካላዊ ምልክቶች ያሉት" ያልተለመደ የጤና ክስተት አጋጥሟቸዋል ብሎ ያምናል። ሠራተኞቹ የደረሰባቸውን "በታማኝነት እና በቅንነት" መግለጻቸውን እንደሚያምንም ጠቅሷል።

ሃቫና ሲንድረም ምንድነው?

ስለ ሃቫና ሲንድረም ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የተሰማው በአውሮፓውያኑ በ2016 በኩባ የሚገኙ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች እንደታመሙ እና ሌሊት ላይ ጆሮ የሚበሳ ድምፅ እንደሚሰሙ በገለጹበት ወቅት ነበር።

ከዋሽንግተን እስከ ቻይና የሚገኙ ሠራተኞችም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል።

የውጭ ኃይል የአሜሪካ ሠራተኞችን በአንድ ሚስጢራዊ የድምፅ መሣሪያ አጥቅቷል የሚለው መላ ምት የመጣው እነዚህን ዘገባዎች ተከትሎ ነው።

2017 ላይ በሃቫና የሚገኙ የአሜሪካ መንግሥት ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው ማዞር፣ ማቅለሽለሽ እና ትኩረት ማጣት እንዳጋጠማቸው ከገለጹ በኋላ የአሜሪካ መንግሥት ከግማሽ በላይ የሆኑትን የሃቫና ኤምባሲ ሠራተኞች ከኩባ አስወጥቷል።

የካናዳ መንግሥትም በኩባ በሚገኙ የኤምባሲው ሠራተኞች ላይ ተመሳሳይ ምልክቶች በማጋጠማቸው 2019 ላይ ሃቫና ውስጥ ያሉ ሠራተኞቹን በብዛት ቀንሷል።

የሃቫና ሲንድረም ጉዳይ መሰማት የጀመረው ከአስር ዓመት በፊት ቢሆንም፤ አንዳንዶች ህመሙ በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ጭምር እንደነበረ ይናገራሉ።