ለስደተኞች ፈታኝ እየሆነች ባለችው አሜሪካ ስደተኞች በእግር ኳስ አማካኝነት የፈጠሩት ማኅበረሰብ

የፎቶው ባለመብት, Anthony Fiori
የዓለም ዋንጫ ሰዎችን አንድ የማድረግ ኃይል እንዳለው በዚህ ዓመት የፍፃሜ ጨዋታዎች ታይቷል። በኒው ኢንግላንድ የሚገኝ አንድ ሜዳ ደግሞ ከትኩረት ውጪ ሆኖ ጨዋታው ሕይወትን ምን ያህል እንደሚቀይር ዕድሉን እየሰጠ ነው።
በአሜሪካ ፖርትላንድ በኬኔዲ ፓርክ የሚጫወቱ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች እግር ኳስ የጋራ ተወዳጅ ስፖርታቸው ነው።
ይሁን እንጂ የገነቡት ትስስር በአሜሪካ ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ተፈትኗል። የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በሁለተኛ የሥልጣን ዘመኑ ጠንካራ የኢምግሬሽን ፖሊሲን ተግባራዊ እደያረገ ነው።
ዓለም አቀፍ ቋንቋው እግር ኳስ
ለታዳጊው ጆርጅ ሉሶሎ ምንም በማያውቀው አገር እግር ኳስ የሚያውቀው ነገር ሆኖ አገኘው።
አሁን 19 ዓመት የሆነው ጆርጅ በአውሮፓውያኑ 2018 ነበር ከእናቱ ጋር ሆኖ ጥገኝነት ለመጠየቅ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወደ አሜሪካ የመጣው።
"ቋንቋውን ምንም አላውቅም ነበር። ሰዎችንም አላወቅም ነበር" ሲል ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግሯል።
"ገና ልጅ ስለነበርኩ ለእኔ እና ለእናቴ ሁሉም ነገር ከባድ ነበር።"
በቴክሳስ ማቆያ ውስጥ እና በኒው ዮርክ መጠለያ የተወሰነ ጊዜ ከሳለፈ በኋላ ጆርጅ በመጨረሻም በፖርትላንድ ኑሮውን መሥርቷል።
የጥገኝነት ጥያቄው በሂደት ላይ እያለ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ስለ እግር ኳስ ጨዋታዎች ልጥፎችን ተመለከተ።
"በጣም ለእኔ ደስ የሚለው ሜዳ ላይ እንደ እኔ ዓይነት ሰዎች መኖራቸው ነው" ይላል።
"እዚህ መጣሁ፤ ተጫወትኩ፤ በጣም ደስ ይል ነበር።
"እግር ኳስ ሕክምናዬ ነው። ኪንሻሳ [በኮንጎ ዋና ከተማ] ሕፃን እያለሁ ጀምሮ ሁሌም እጫወታለሁ።
"አንተ ከመጣህበት ስፍራ ከመጡ ሠዎች ጋር፤ ተመሳሳይ ችግር ካዩት ጋር ስትጫወት በጣም የደስታ ስሜት አለው።"
በ2021 በኬኔዲ ፓርክ አስፓልት ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የተጀመረው መሰባሰብ ወደ ማኅበረሰብ ደረጃ አድጓል። ከበርካታ አገራት የመጡ ሰዎች የምርጡን ጨዋታ ፍቅራቸውን ይጋራሉ።
ሌላኛው ኮንጓዊ የሆነው ዲጊ ኩሪባንዛ ከአንጎላ ወደ አሜሪካ የመጣ ነው። እግሩን ዓለም አቀፍ ቋንቋ ከሆነው እግር ኳስ አገናኝቷል።
"እያንዳንዱ ሰው አንድ ዓይነት ቋንቋ መናገር አይጠበቅበትም" ይለል የ18 ዓመቱ ወጣት።
"እግርህ ላይ ጠቁም [ወይም] ሌላ የአካል ክፍል ላይ እና ኳሱን ጠይቅ። በጣም ደስ የሚል ነገር ነው።"
የአንድነት ምላሽ

የፎቶው ባለመብት, Anthony Fiori
ባለፈው ዓመት በሜይን ግዛት የስደተኞች ማኅበረሰብ የአሜሪካ የኢምግሬሽን እና ጉምሩክ አስፈፃሚ ባለሥልጣን (አይስ) በወሰደው እርምጃ ድንጋጤ ውስጥ ነበሩ።
ገለልተኛ እና ነፃ የሆነው የፍልሰተኞች ፖሊሲ ተቋም ከጥር 2025 ጀምሮ 400 ሺህ ሰዎች እንደታሰሩ ይገምታል።
በአሜሪካ መንግሥት ዒላማ የሚደረጉት ስደተኞች ለሕብረተሰብ እና ብሔራዊ ደኅንነት ላይ አደጋ የሚደቅኑ ናቸው ይላል።
የኢምግሬሽን እና ጉምሩክ ተቆጣጣሪውን አካልን የሚመራው የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በሕጋዊ መንገድ አገር ውስጥ ያሉ ሰዎች "ምንም የሚያሰጋቸው ነገር የለም" ይላል።
ይሁን እንጂ የመብት ተሟጋቾች በእርምጃው ለማኅበረሰቡ ምንም ስጋት የማያሳድሩ ንፁህ ሰዎች እንደታሰሩ ይሞግታሉ።
በኬነዲ ፓርክም የሆነው ይህ ነው።
"የኢምግሬሽን ተቆጣጣሪዎች በሳደሩት ስጋት ምክንያት ተጫዋቾች እና ቤተሰቦቻቸው ከቤታቸው ለመውጣት በጣም ፈርተው ነበር" ይላል ጨዋታዎቹን የሚያዘጋጀው አንተኒ ፊዮሪ።
"በዚህ ምክንያት ተማሪዎች የሁለት ሳምንታት ትምህርት አምልጧቸዋል።
"የኢምግሬሽን ተቆጣጣሪው ከባድ ፍርሃት ፈጥሯል። እዚህ ማኅበረሰብ ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሱ ነበር።"
ይሁን እንጂ የእግር ኳሱ ማኅበረሰብ በፀጥታ አልተመለከተውም። በቁጥጥር ስር ላለመዋል ቤታቸው ለሆኑት ሰዎች ከ70 በላይ የአስቤዛ አቅርቦቶችን አመቻችቷል።
በኬነዲ ፓርክ በጨዋታዎች ተሳታፊ የሆነው ጆዌል አንድሬ እና ቤተሰቦቹ እንዲለቀቁ ዘመቻ መርቷል።

የፎቶው ባለመብት, Anthony Fiori
ከአራት ወራት በኋላ ስኬታማ ሆኑ። ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ የሥነ ልቦና ጠባሳው አብሮት አለ።
"ምግቡ የማይረባ ጣቢያ ውስጥ ነበሩ። አንዳንዶቹ ክፍሎች በረዶ ነበሩ" ይላሉ ጉዳዩን የያዙት ጠበቃ ታድ ፖምራሉ ለቢቢሲ።
"ጆዌል በሜን የእግር ኳስ ፈርጥ ነው፣ ብሩህ ልጅ ነው። ለወደፊቱ ብዙ ተስፋ አለው።
"ነገር ግን እንደበፊቱ እንደማይሆን መናገር ይቻላል።
"በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚያልፍ ማንኛውም ሰው እንደወትሮው መሆን አይችልም። ማማከር፣ እምነት፣ ጓደኞች፣ ቤተሰቦች ያስፈልጋቸዋል።"
የጆዌል ቤተሰቦች የመጀመሪያ የጥገኝነት ማመልከቻ በአሜሪካ ውድቅ ተደርጓል።
ቤተሰቡ በካናዳ እና በአሜሪካ መካከል በአንደኛው አገር ብቻ ጥገኝነት መጠየቅ የሚፈቅድ ስምምነት እንዳለ ባለማወቅ ጥገኝነት ለመጠየቅ ወደ ካናዳ አቅንቷል።
ይህም በአሜሪካ የኢምግሬሽን ተቆጣጣሪዎች እንዲያዙ አድርጓል። አሁን በአሜሪካ ፌደራል ፍርድ ቤት የጥገኝነት ማመልከቻቸውን ይግባኝ ብለዋል።
በዓለም መድረክ ለመጫወት ማለም

የፎቶው ባለመብት, George Lusolo/BBC
ይህ በእንዲህ እንዳለ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች በአሜሪካ ኳስ ሲጫወቱ መታየታቸው ቅቡልነት እንዲያገኙ ሊረዳን ይችላል ይላሉ።
"አንዳንድ ሰዎች ስደተኞችን የሚያዩት መሄጇ ቦታ የሌላቸው እና አገራቸው መጥተው ምንም የማያደርጉ ሰዎች አድርገው ነው የሚቆጥሯቸው" ይላል ዲጂ።
"ስንጫወት እየተጓዙ የሚመለከቱን በርካታ አሜሪካዊያን አሉ፤ እያወሩ፣ እየተደሰቱ እና ጥሩ ጊዜ እያሳለፉ ያሉ ስደተኞችን ይመለከታሉ።
"በአእምሯቸው ላይ ካለው የስደተኞች ሥዕል የተለየ ነው።"
የአንተኒ ቤተሰብ በሜን ግዛት ዘጠኝ ትውልዶች ወደ ኋላ ይሄዳል። በኬነዲ ፓርክ የተፈጠረው ማኅበረሰብ የሚሰጠውን ጥቅም ለማየት ግልፅ እንደሆነ ያምናል።
"በባህል በጣም የተለያዩ ሰዎች፣ የተለያዩ ዜጎች፣ የተለያዩ ትውልዶች የሚገናኙበት ስፍራ ማግኘት እና ጓደኛ መሆን መቻላቸው በጣም ልዩ ነው። በተለይ ደግሞ ብዝኃነት በሌለው እንደ ሜን ባለ ግዛት" ይላል።
ስደተኞቹ የአሜሪካ ህልምን ተስፋ እንዳደረጉት ባይሆንም፤ የዓለም ዋንጫ በአሜሪካ መሰናዳቱ አንዳንዶች ትልቅ ህልም እንዲያልሙ አድርጓቸዋል።
"ከእኔ ሁለት ግዛቶች ባሻገር [የዓለም ዋንጫ] ጨዋታ መካሄዱ ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አይቼ አላውቅም" ይላል ዲጂ።
"የዚያ አካል የመሆን ከፍተኛ ምኞት ውስጤ እየተጠናከረ ነው።
"እናም ይህ ከህልሞቼ አንዱ ነው፤ በዓለም መድረክ መታየት።"
ጆርጅም አገሩን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ወክሎ እግር ኳስ ተጨዋች የመሆን ህልም አለው።
አናብርቶቹ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ በዓለም ዋንጫ 32ቱ ውስጥ መግባታቸው በውድድሩ ወቅት በኬነዲ ፓርክ ሰፊ ደስታን ፈጥሯል።
ምክንያቱም በፊፋ ዓለም ዋንጫም ሆነ በፓርኩ ጨዋታ እግር ኳስ ከየትኛውም አገር ብትመጡ አንድ ነው።











