በማለዳ ከባድ ሙቀት በሚፈትነው እና በርካቶች በሙቀት በሚሞቱባት ስፍራ መኖር

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ማለዳ 12፡00 ሰዓት ላይ በሕንድ ባንዳ የምትወጣው ፀሐይ ገና ማለዳ መሆኑን ዘንግታዋለች።

ጨረሩ የበጋ ቀትር ያህል አናት የሚበሳ ነው። ጥላም ገና ቁርስ እንኳን ሳይበላ ያጥራል።

ግንቦት ላይ በሕንዷ ኡታር ፕራዲሽ ግዛት የምትገኘው ወረዳ ለቀናት በአገሪቷ እጅግ ሞቃታማዋ ሥፍራ ሆና መጀመሪያ ላይ ተቀምጣለች።

የሙቀቷ መጠን ከአንድ ሳምንት ለሚበልጥ ጊዜ ከ47 እስከ 48 ዲግሪ ሴልሽየስ (ከ116 እስከ 118 ፋራናይት) ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም በአካባቢው ታይቶ የማይታወቅ ነው።

የሚገርመው ነዋሪዎች ይህንን ለመቋቋም የሚያደርጉት ጥረት ነው።

ባንዳ ከ2 ሚሊዮን የሚበልጡ ነዋሪዎች አሏት። አብዛኞቹ በእርሻ፣ በግንባታ፣ በትራንስፖርት እና ሌሎች ከቤት ውጭ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ናቸው።

በዚህም ምክንያት የአየሩን ሁኔታ ከመላመድ ውጭ በቤት ውስጥ ለማሳለፍ ምርጫ የላቸውም።

ሕይወታቸውንም ሆነ የቀን ውሏቸውን በዚሁ መሠረት አስተካክለዋል።

ከወረዳው መቀመጫ 30 ኪሎ ሜትር በምትገኘው አታራ የሚገኘው የአትክልት ገበያ በርካታ ከተሞች ገና ከእንቅልፋቸው ሳይነቁ ነው የሚከፈተው።

አርሶ አደሮች ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ሎሚ፣ ብርቱካን ሌላም ሌላም ይዘው በሌሊት ነው የሚደርሱት። ሁሉም ሙቀቱ ከማየሉ በፊት የያዙትን በፍጥነት ሸጠው ወደ ቤታቸው መመለስ ነው የሚፈልጉት።

"ተመልከቱ ፀሐይዋን፣ አሁን ገና ከማለዳው 12፡15 ነው። ሙቀቱ ግን ከቀትር በኋላ ከ8፡00 እስከ 9፡00 ሰዓት ያለውን ነው የሚመስለው" ይላል ሒማንሹ የተባለው ነጋዴ።

ሙቀቱ ገበያው የሚቆይበትን ሰዓት ስለሚያሳጥረው የሚያገኘውን ገቢ ቀንሶበታል።

"አንድ ሳጥን ቲማቲም ዛሬ ወይም ነገ መሸጥ አለበት፤ በዚህ ሙቀት ከዚህ በላይ መቆየት አይችልም" ሲል ያለበትን ሁኔታ ይገልጻል።

ሆኖም የያዘውን ሳይሸጥ ገና ረፋድ ላይ ገበያው ይበተናል።

በባንዳ ሌሎች ክንውኖችም በሰዓት የተገደቡ ናቸው።

ፖላንዳዊው ጋዜጠኛ ርይስዛርድ ካፑሲብስኪ አካባቢውን ዞር ዞር ብሎ እንደተመለከተው ልክ በአፍሪካ እንዳሉ ሌሎች ሞቃታማ ሥፍራዎች ሰዎች ጥላ በመፈለግ እና በማረፍ ነው ጊዜያቸውን የሚጨርሱት።

ግንበኛው ፓፑ ሸርማን ከጠዋቱ 1፡00 እስከ እኩለ ቀን ድረስ ይሠራል። ከዚያም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት እስከ ምሽት 1፡00 ሰዓት ሥራውን ይቀጥላል። በመካከል ያሉትን ሰዓቶች የሚያሳልፈው ከባዱ ሙቀት እስከሚያልፍ በመጠበቅ ነው።

"ስምንት የሥራ ሰዓቶች ማጠናቀቅ ይኖርብሃል። በተከታታይ የፀሐዩን ግለት ጠብቀህ ሠራህም፣ እያረፍክ እንደገና ጀመርክም ክፍያው ግን ተመሳሳይ ነው" ይላል። በመሃል የሚወስደው እረፍት ከራስ ምታት እና ከሙቀት ህመም ቢያድነውም የሥራ ሰዓቱን በቀን ከ12 እስከ 13 ሰዓት አድርሶበታል።

"ይህን ካላደረኩ የማገኘው በሙሉ ለመድኃኒት የሚጠፋ ነው የሚሆነው" ሲልም እረፍት ማድረጉ ብቸኛው አማራጩ እንደሆነ ገልጿል።

ባለፈው ሳምንት በባንዳ ከእኩለ ቀን በኋላ ያለው የሙቀት መጠን 46 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሶ ነበር።

ሙቀቱ ባየለበት በዚያ ወቅት ሦስት ሴቶች ድልድይ ላይ አረፍ ብለው ተጠልለው ይታያሉ።

ከእነዚህ ሴቶች አንደኛዋ ሻንቲ ዴቪ ወደ ሥራ ለመምጣት እና ለመመለስ በጥቅሉ 12 ኪሎ ሜትር ትጓዛለች። ምሳዋ ዳቦ እና ሽንኩርት፣ ጨው እና ኩከምበር ነው። "ሌላ አትክልት ካመጣህ ምሳ ሰዓት ሳይደርስ ይበላሻል" ትላለች።

"ድሃ ሰዎች ስለሙቀቱ የማሰብ ቅንጦት የላቸውም" ስትልም አለመሥራት እንደማትችል ትገልጻለች።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት አሸዋ እና የከርሰ ምድር ውሃ ለማውጣት የሚደረግ ቁፋሮ አካባቢውን የማቀዝቀዝ አቅም እያዳከመው ሲሆን፣ የውሃ እጥረት እና ከፍተኛ ሙቀት አንዳቸው በአንዳቸው ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ከችግሩ ለመውጣት አዳጋች አድርጎታል።

ሙቀቱ በምጣኔ ሃብት ላይ ያሳደረው ተፅዕኖም በሁሉም አካባቢ የሚታይ ነው።

አሽከርካሪዎች ከሰዓት በኋላ እንዳይሠሩ አድርጓቸዋል፤ ሱቆች ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት ተከፍተው እኩለ ቀን ላይ ተዘግተው እስከ አመሻሽ ይቆያሉ።

ሙሉ ከተማው ከባድ በሆኑት ሰዓታት በቤት ውስጥ ያሳልፋል፤ መነቃቃት የሚጀምረው ምሽት ላይ ነው።

መንግሥት የሙቀቱን ሁኔታ በተመለከተ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።

በአካባቢው የሚገኙ ሆስፒታሎች በሙቀት ምክንያት የሚታመሙ ሰዎችን እያስተናገዱ ነው።

"ሙቀቱ ካየለበት ጊዜ ጀምሮ በቀን ከ15 እስከ 20 የሚደርሱ ህሙማንን እየተቀበልን ነው፤ አብዛኞቹ ሕፃናት እና አረጋውያን ናቸው" ይላሉ በአካባቢው የሚገኘው የሴቶች ሆስፒታል ኃላፊ ኬ ኩማር።

"የተለመደው የህመማቸው ምልክቶች ትውከት፣ ተቅማጥ እና ትኩሳት ናቸው" ብለዋል።

በእርግጥ በባንዳ ያለው ሁኔታ በጠቅላላ በአገሪቷ ያለው ሁኔታ ማሳያ ነው።

በመላ አገሪቷ የሙቀት መጠን እየጨመረ ነው። በሌሎች ቦታዎች ያለው ሁኔታ አስከፊ ባይሆንም ሙቀት እና ወበቅ በሰዎች ሰውነት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል።

ኡታር ፕራዲሽን ጨምሮ ሰሜናዊ ሕንድን የሚሸፍነው አካባቢ አደገኛ የሆነ ወበቃማ ሙቀት ከሚያስከትሉ በዓለማችን ካሉ ሞቃታማ አካባቢዎች አንዱ እየሆነ መምጣቱን አጥኚዎች ይናገራሉ።

ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት፣ መስኖ፣ ከቤት ውጭ ባሉ ሥራዎች ላይ የተሰማራ ሰፊ ሕዝብ ተደማምረው የየዕለት ሥራን ማከናዎን አደገኛ እንዲሆን አድርገውታል።

በተጋለጠ እና ከቤት ውጭ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ የተሰማራ ሰፊ ሕዝብ ያላት እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤቶች ማቀዝቀዣ የሌላቸው ኡታር ፕራዲሽ ግዛት በተለየ ተጋላጭ መሆኗን አንድ በአየር ንብርት ላይ የሚሠራ የጥናት ተቋም ገልጿል።

ተመራማሪዎች የግዛቱ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና የልማት ምርጫዎች ተደማምረው ችግሩን አባብሰውታል ብሏል።

ባንዳ የምትገኘው ከዓለማችን በጣም ሞቃታማ አካባቢዎች ጋር በሚገናኝ ከምድር ወገብ በላይ ነው።

ወንዞች ጭል ጭል ነው የሚሉት። በዚህም ሙቀትን መጥጠው የሚያስቀሩ እና አንፀባርቀው የሚመልሱ አሸዋና ድንጋይ ተጋልጠዋል። ድንጋዮች አትክልቶችን ተክተዋል።

የደን ሽፋን ከሚመከረው በታች ዝቅተኛ ነው።

በባንዳ የግብርና እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጥናት አንድ ስድስተኛ የሚሆነው የወረዳዋ ደን ከአውሮፓውያኑ 1991 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት ውስጥ መጥፋታቸውን ገልጿል። ምክንያቱ የማዕድን ቁፋሮ እና የግብርና መስፋፋት እንደሆነም ጥናቱ ጠቅሷል።

በእነዚህ ምክንያቶች ባንዳ ለከፍተኛ ሙቀት የመጋለጥ ዕድሏን ጨምሮታል።

በዩኒቨርሲቲው የሚቲዮሮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ዲንሽ ሳህ እንዳሉት ወረዳዋ ከ48 እስከ 49 ዲግሪ ሴልሽየስ የሚደርስ ሙቀት ተከስቶባታል።

እንደ አውሮፓውያኑ 2024፤ 49 ዲግሪ ሴልሽየስ የደረሰው በሁለት ተከታታይ ቀናት ብቻ ነበር።

አሁን ላይ የተከሰተውን የበጋ ሙቀት ያልተለመደ የሚያደርገውም ዘለግ ላለ ጊዜ መቆየቱ ነው።

"ለስምንት ወይም ለዘጠኝ ቀናት ከ47 እስከ 48 ዲግሪ ሴልሽየስ የሚደርሰው ሙቀት ያለምንም ጋብታ ቀጥሏል፤ ይህ ነው አዲሱ ነገር" ብለዋል።

በአካባቢው በግብርና ሥራ የሚተዳደሩት ፕሪም ሲንህ እንደሚሉትም በክልሉ ያለው ሙቀት አዲስ አይደለም። ለአዝዕርትም ወሳኝ እንደሆነ ይገልጻሉ።

የሚያሳስባቸው ጉዳይ ግን ሙቀቱ እያየለ መምጣቱ ነው። ለዚህም የደን መመናመን፣ የማዕድን ቁፋሮ፣ ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል ምንጮች አጠቃቀም መጨመር እና የአየር ብክለት መስፋፋትን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።

"ይህ በተለይ የድሃውን ሕይወት አክብዶታል" ብለዋል።

ሙቀቱ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላም ይዘልቃል።

"ከዚህ በኋላ ጠዋት እና ምሽት የማይኖሩ ዓይነት ስሜት ነው ያለው" ብላለች ሳህ።

ጠዋት 1፡00 ሰዓት ወይም 2፡00 ሰዓት ሙቀቱ ቀትር ነው የሚመስለው። በምሽት ሙቀቱ 30 ዲግሪ ሴልሽየስ ይደርሳል።

ከባንዳ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር የምትርቀው አችሃራውድ መንደር ከሙቀቱ ይልቅ ውሃ ለማግኘት የሚደረገው ትግል ያይላል።

በእያንዳንዱ ቀን ሴቶች ውሃ ለማግኘት ሙቀቱ ሳይበግራቸው ረዣዥም ሰልፎች ላይ ቆመው ይውላሉ።

የ18 ዓመቷ ክራንቲ ቪሽዋካርማ ውሃ ለመቅዳት አራት ወይም አምስት ሰዓታትን ታጠፋለች። በቤት ውስጥ መብራት ሲጠፋ ትንሽ ቀዝቃዛ አየር የሚያገኙት በአቅራቢያው ካለ የኒም ዛፍ ሥር በመጠለል ነው።

"በቤት ውስጥ ማቀዝቀዣ የለኝም" የምትለው ወጣቷ ዛፉ ይህንን ሚና ይወጣልናል ትላለች።

ወደ 40 ዓመት የሚጠጋቸው ቹኑባዲ የተባሉ አዛውንትም "ምን እንኳ የአየር ማቀዝቀዣው ቢሠራም፤ የሚያመጣው ደረቅ እና ሞቃታማ አየር ነው" ብለዋል።

"በ80 ዓመት ዕድሜዬ እንዲህ ዓይነት ሙቀት አይቼ አላውቅም። በዕድሜ የገፉ ሰዎች በሙቀቱ ምክንያት እየሞቱ ነው። እኔም ይህንን መቋቋም እችል እንደሆን አላውቅም" ይላሉ ስጋታቸውን ሲገልጹ።

ከመንደሩ ባሻገር እንስሳትም በራሳቸው መንገድ ሙቀቱን ለመቋቋም ሲታገሉ ይታያሉ። እኩለ ቀን ላይ በርካታ ጎሾች በቡድን በትንንሽ ኩሬዎች ላይ ይቆማሉ።

የ60 ዓመቱ የቀድሞው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር እና አሁን ላይ ጎሾችን የሚያረባው ራምሽዋር ያዳቭ፣ ለሙቀቱ ለክረምት የሚዘወተሩ ወፍራም ልብሶችን ይለብሳል፤ ጭንቅላቱም ላይ ስካርፍ ይጠመጥማል።

"ወፍራም ልብሶችን የምንለብሰው የፀሐይዋ ሙቀት ወደ ሰውነታችን በቀጥታ እንዳይደርስ ስለሚረዳን ነው፤ ወፍራም ልብሶች ከፀሐይ እና ከሞቃታማ ንፋስ ይጠብቀናል። ያልበናል ግን ከህመም ይታደገናል" ሲልም ምክንያቱን ያስረዳል።

በባንዳ እንደሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ሁሉ ያዳቭ ሙቀቱን ተለማምዶታል። ሆኖም መላመድ እና እፎይታ ማግኘት የተለያዩ ነገሮች ናቸው።

አርብ ዕለት በምዕራባዊ ክፍል የአቧራ ማዕበል እና ዝናብ ተከስቷል። ሙቀቱም ከ8 እስከ 9 ዲግሪ ያህል ወርዷል። ወረዳዋ በድጋሚ ትንፋሽ አግኝታለች።

ይህ ግን ጊዜያዊ ነው። የባንዳ ነዋሪዎች በማለዳ ሥራ ጀምረው ከዕኩለ ቀን በፊት ወደ ቤታቸው መግባታቸውን አሊያም ባሉበት ቦታ ጥላዎችን መፈለግ ተለማምደውታል።

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በርክሌይ በፒዩሽ ናራንጋ እና አሺክ ጋድጊል በጥናታቸው፣ በኡታር ፕራዲሽ ግዛት በአምስት ቀናት ውስጥ ብቻ በሙቀት ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ8 ሺህ እንደሚበልጥ ገምተዋል። ይህም በሌሎች ግዛቶች ከተከሰተው የሚበልጥ ነው።

ከፍተኛው ሙቀት በአረጋውያን፣ ከቤት ውጭ ሥራ በሚሠሩ ሰዎች እና ማቀዝቀዣ በሌላቸው ቤቶች በሚኖሩ ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።

ተመራማሪዎች የአካባቢው ሙቀት ለረዥም ጊዜ በተከታታይ እየጨመረ መምጣቱ አሳስቧቸዋል።