በቀጣይ ሳምንት ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ትራምፕ ተናገሩ
ከኢራን ጋር የተኩስ አቁም ለማራዘም እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት በቀጣይ ሳምንት ስምምነት ላይ እንደሚደረስ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኤቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናገሩ።
“አሁን ላይ ነገሮች በጣም ጥሩ ናቸው። ውስን ችግር ነበር፤ ነገር ግን እንዳያችሁት በፍጥነት ፈትቼዋለሁ” ሲሉ በስልክ በሰጡት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።
ትራምፕ ችግር ብለው የጠቀሱት እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታደርሰው ጥቃት ኢራንን ማስቆጣቱን ነው።
ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት ማድረስ እንዲያቆም ከአሜሪካ የቀረበለትን ሐሳብ መቀበሉን ሊባኖስ አስታውቃለች። እስራኤልም በሊባኖስ መዲና ቤሩት ጥቃት ላለመፈጸም መስማማቷም ተገልጿል።
ትራምፕ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ከሄዝቦላህ ተወካዮች ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰው “ተኩስ ለማቆም ተስማምተዋል” ብለዋል።
ትራምፕ “ሄዝቦላህን አትተኩሱ ብያቸዋለሁ። ቢቢ [ኔታንያሁ] እንዳይተኩስም ነግሬዋለሁ። ሁለቱም ተኩስ አቁመዋል” ሲሉም አክለዋል።
በቀጣይ ሳምንት የሆርሙዝ ወሽመጥ ይከፈታል ብለው እንደሚያምኑም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።