ተመድ እስራኤል የሊባኖስን አምባ መቆጣጠሯን በተመለከተ አስቸኳይ ውይይት አካሄደ
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እስራኤል የሊባኖስን ጥንታዊ አምባ - ቢውፎርትን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን በተመለከተ ትናንት አስቸኳይ ውይይት አካሄደ።
በተመድ የሩሲያ አምባሳደር ቫስሊ ነቤንዝ “እስራኤል እና ሊባኖስ በአሜሪካ አሸማጋይነት የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል ሊባኖስ ላይ ጥቃት እንድትፈጽም ከለላ ሰጥቷል” ብለዋል። ሊባኖስ የጋዛ ሰርጥ እጣ ፈንታ እንደሚጠብቃትም አክለዋል።
በተመድ የፈረንሳይ ልዑክ ጀሮም ቦንፎን ውይይቱ እንዲካሄድ አገራቸው ጥሪ ማቅረቧን ጠቅሰው “እስራኤል ራሷን የመለካከል መብት ቢኖራትም ሊባኖስ ላይ የምታደርሰው ጥቃት ምክንያታዊ አይደለም” ብለው ንግግር አድርገዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን እንደተጎዱ እና እንደተፈናቀሉ የፈረንሳዩ ተወካይ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ተወካይ ማይክል ጄ ዋልዝ በበኩላቸው፤ድርድርን ጨምሮ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
“ሕጋዊው የሊባኖስ መንግሥት በቴህራን ከሚደገፈው አሸባሪ አገሪቱን ነጻ ለማውጣት ተነሳሽነት አሳይቷል” ብለዋል።
የሊባኖስ ተዋካይ አሕመድ አራፋ ደግሞ መንግሥታቸው ነገሮችን ለመቆጣጠር ቢሞክርም “እስራኤል እንደ ሁልጊዜው ቀጣናዊውን ሁኔታ እየተጠቀመችበት ነው” ብለዋል።
እስራኤል ሐኪሞችን፣ ሆስፒታሎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ትምህርት ቤቶችን እና የፀጥታ ተቋማትን ዒላማ በማድረግ “ስልታዊ የውድመት ዘመቻ” መክፈቷንም ጠቅሰዋል።
በተመድ የእስራኤል ልዑክ ዳኒ ዳኖን “አንድ ቀን ተነስተን ሊባኖስ ለመግባት አልወሰንም። አማራጭ አጥተን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኢራን ሄዝቦላህን በእጅ አዙር መጠቀም መቀጠሏን ጠቅሰው፤ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደረስም “ሄዝቦላህ ሚሳዔል እና ድሮን መተኮስ” እንዳላቆመ ተናግረዋል።