በሕንድ የእህቱን መሞት ለማሳየት አስከሬኗን ወደ ባንክ ይዞ የመጣው ግለሰብ ቁጣን ቀሰቀሰ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሽ የሚችል ዝርዝሮችን ይዟል

በምሥራቅ ሕንድ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ እህቱ ከሞተች በኋላ በባንክ ውስጥ የነበራትን ገንዘብ ለማውጣት ባለመቻሉ መሞቷን ለማሳየት አስከሬኗን እንዲያመጣ መገደዱን ተናገረ።

የ52 ዓመቱ ጂቱ ሙንዳ ወደ ባንክ የእህቱን አስከሬን ተሸክሞ ሲሄድ የሚያሳየው ቪዲዮ በስፋት ከተጋራ በኋላ ቁጣን ቀስቅሷል።

ግለሰቡ በተደጋጋሚ እህቱ በባንክ ውስጥ ያላትን የቁጠባ ገንዘብ ለማውጣት ቢሞክርም መሞቷን የሚያሳይ ማስረጃ ካላመጣ እንደማይቻል ስለተነገረው ይህንን ለማድረግ መገደዱን ተናግሯል።

ፖሊስ የእህቱን አስከሬን ወደ ባንክ ለማምጣት ከተቀበረችበት ቆፍሮ ማውጣቱን አስታውቋል። ባንኩ ግን ግለሰቡ ይህንን እንዲያደርግ አለመጠየቁን በመግለጽ ግለሰቡን የተጠየቀው ሕጋዊ ሰነድ ብቻ መሆኑን አብራርተዋል።

ባንኩ አክሎም ይህ ሊሆን የቻለው የባንክ አሰራርን በሚገባ ካለመረዳት ነው በማለት አሁንም ቢሆን ገንዘቡ ለሕጋዊ ወራሽ ብቻ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

በሕንድ ኬዮንጃሃር አውራጃ የሚኖረው ጂቱ ሙንዳ አስከሬኑን ተሸክሞ ወደ ባንክ የሄደው ሰኞ ዕለት ነበር።

ግለሰቡ የእህቱን አስከሬን ተሸክሞ ሲሄድ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ተቀርጾ በስፋት ከተጋራ በኋላ በመላ አገሪቱ ቁጣ የቀሰቀሰ ሲሆን የአካባቢው አስተዳደር እና ባንኩ ግለሰቡን በሚገባ ማስረዳት ባለመቻላቸው ትችት ተሰንዝሮባቸዋል።

የኦዲሻ ገቢዎች ሚኒስትር ሱሬሽ ፑጃሪ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው በቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

የኬዮንጃር አስተዳዳሪ በበኩላቸው የሰዎችን መብት እና ክብር መከላከል ቅድሚያ የሚሰጡት መሆኑን በመግለጽ የተሰማቸውን "ትልቅ ስጋት" ተናግረዋል።

ሙንዳ ለቢቢሲ ሂንዲ የ56 ዓመቷ እህቱ ካላራ የሞተችው በዚህ ዓመት ጥር ወር አካባቢ መሆኑን ገልጾ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ገንዘቧን ከባንክ ለማውጣት መቸገሩን አስረድቷል።

በቀን ሠራተኝነት ትሰራ ነበር ያለው ሙንዳ፣ ባልተቤቷ እና ልጇ ከሞቱ በኋላ ወደ ቤተሰቦቿ ቤት መምጣቷን አብራርቷል።

ከመሞቷ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ያሏትን ከብቶች ሸጣ 19,300 ሩፒ (203 ዶላር) በባንክ ማስቀመጧን ጨምሮ አስረድቷል።

ሙንዳ ከእህቱ ሞት በኋላ የባንኩን ቅርንጫፍ በተደጋጋሚ እየተመላለሰ ቢያነጋግርም ገንዘቧን ሊሰጡት እንዳልቻሉ አስረድቷል።

"የባንኩ ሥራ አስኪያጅ ሊሰማኝ ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር እና በተደጋጋሚ ማስረጃ እንዳቀርብ ሲጠይቀኝ ተስፋ ቆረጥኩ" ብሏል።

"የእህቴን አስከሬን ያመጣሁት መሞቷን ለማሳየት ነው።"

በሕንድ በስፋት የተጋራው የሙንዳ ቪዲዮ በማዳበሪያ የተጠቀለለውን አስከሬን ተሸክሞ ወደ ባንክ ሲሄድ እና መግቢያ በሩ ላይ ሲያስቀምጥ ያሳያል። ቪዲዮውን የቀረጸው ማን እንደሆን አይታወቅም።

ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ቁጣን ከቀሰቀሰ በኋላ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ያለውን ገንዘብ ቤተሰቡ ከባንክ ለማውጣት የሚገጥማቸውን ውጣ ውረድ በመግለጽ ኮንነዋል።

ሌሎች ደግሞ የገጠሩ ማኅበረሰብ የባንክ አሰራርን ባለማወቅ ስለሚገጥመው ሰፊ ተግዳሮት በማንሳት ተወያይተዋል።

በሕንድ አንድ የባንክ አካውንት ያለው ግለሰብ ወራሹን ሳያሳውቅ ከሞተ ቤተሰቡ ወይንም ወራሽ ነኝ የሚሉ ግሰለቦች የሞት ምስክር ወረቀት፣ የወራሽነት ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

እንዲህ ዓይነት ሂደቶች ከከተማ ርቀው በሚገኙ የገጠር አካባቢዎች ረዥም ቀናትን ይወስዳሉ።

የሙንዳ ቪዲዮ ከታየ እና ቁጣን ከቀሰቀሰ በኋላ እህቱ ገንዘቧን ያስቀመጠችበት ባንክ፣ ኢንዲያን ኦቨርሲስ፣ የሟች አስከሬንን ማምጣት አልጠየቅንም ሲል አስተባብሏል።

ሙንዳ ማድረግ ያለበትን ቢነገረውም ያንን አልተከተለም ያለው ባንኩ፣ ግለሰቡ መጀመርያ ሲመጣ "ጠጥቶ ነበር" በማለት በመቀጠልም መረበሹን አስታውቋል።

በኋላ ላይ የእህቱን አስከሬን ተሸክሞ ወደ ባንኩ መምጣቱን በመግለጽ ሁኔታው "የሚረብሽ" እንደነበር አስረድቷል።

የቅርንጫፉ ሥራ አስኪኣጅ ሹሻንት ኩማር ሴቲ ለቢቢሲ ሂንዲ፣ ሙንዳ መጀመርያ እህቱ ፓራላይዝ መሆኗን እና ወደ ባንክ መምጣት አንደማትችል ተናግሮ ነበር ብለዋል።

የባንኩ ሠራተኞች ወደ ቤቷ በመሄድ ሊረዷት ሃሳብ ቢያቀርቡም እርሱ ግን ሞታለች ማለቱን አስረድተዋል።

ሥራ አስከያጁ አክለውም ግለሰቡ ላላፉት ሁለት ወራት ወደ ባንኩ አለመምጣቱን በመግለጽ ገንዘቡን የሚጠይቁ ሌሎች ወራሾች መጥተዋል ብለዋል።

ባንኩ አሁንም ወራሽ መሆናቸውን እና ግለሰቧ መሞቷን የሚያሳይ ሕጋዊ ሰነድ መጠየቁን ጨምረው አስረድተዋል።

ፖሊስ እና የአካባቢው አስተዳደሮች ሙንዳን ካነጋገሩት በኋላ የእህቱን አስከሬን መልሶ እንዲቀብር በማድረግ ጥያቄው እንደሚስተናገድለት አስረድተውታል።

ባለሥልጣናት ለግለሰቡ 30,000 ሩፒ በድጋፍ መልከ አበርክተውለታል። ረቡዕ ዕለት እህቱ መሞቷን የሚገልጽ ምስክር ወረቀት እና ሕጋዊ ወራሽነቱን የሚያሳይ ሰነድ የተሰጠው ሲሆን ባንኩም ገንዘቡ ለሟች ሕጋዊ ወራሽ ቤተሰቦች መተላለፉን ተናግሯል።