ጀርመን የአሜሪካ ወታደሮችን መውጣት "የሚጠበቅ" እንደሆነ ስትናገር ኔቶ ማብራሪያ መጠየቁን አስታወቀ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር አሜሪካ 5000 ወታደሮቿን ለማስወጣት መወሰኗን አገራቸው "የምትጠብቀው" እንደነበር ሲናገሩ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) በበኩሉ ከዋሺንግተን ማብራሪያ መጠየቁን ተናገረ።

ቦሪስ ፒስቶሪየስ ለዲፒኤ የዜና ወኪል እንደተናገሩት "የአሜሪካ ወታደሮች በአውሮፓ መገኘት በተለይ ደግሞ በጀርመን እንዲሁም በአሜሪካ ፍላጎት መሠረት ነው" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኔቶ ቃል አቀባይ አሊሰን ሃርት ጥምረቱ "የውሳኔውን ዝርዝር ጉዳዮች ለመረዳት ከአሜሪካ ጋር እየተነጋገሩ" መሆኑን አስታውቀዋል።

ዋሺንግተን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ፤ አሜሪካ በኢራን ተደራዳሪዎች "ተዋርዳለች" በማለት ዶናልድ ትራምፕን ከተቹ በኋላ ነው።

በአሁን ሰዓት በጀርመን የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ብዛት 36,000 ሲሆን ይህም በአውሮፓ ካለው ጦር ሁሉ ከፍተኛ ቁጥር የያዘ ነው።

አሜሪካ በጣሊያን 12,000 እንዲሁ በዩናይትድ ኪንግደም 10,000 ወታደሮች አሏት።

ቅዳሜ ምሽት አገራቸው በጀርመን የሚገኙ ወታደሮቿን ቁጥር ለመቀነስ ስለመወሰኗ የተጠየቁት ፕሬዚዳንት ትራምፕ "ከዚህም በላይ እንቀንሳለን፤ ከ5000 በላይ እንቀንሳለን" በማለት ተጨማሪ ዝርዝር ሳይሰጡ ምላሽ ሰጥተዋል።

ትራምፕ ጦራቸውን ከስፔን እና ከጣሊያን ስለማስወጣትም ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ዋሺንግተን በሮማኒያ የሚገኙ ወታደሮች ቁጥርን መቀነሷ ይታወቃል።

ይህ ውሳኔ የመጣው የአሜሪካ ጦር ያለው ትኩረት ከአውሮፓ በማንሳት ወደ ኢንዶ ፓሲፊክ በማዞሩ ነው።

የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን 32 አባል አገራት ይህ የአሜሪካ ውሳኔ ድርጅቱን ያዳክመዋል ሲሉ ሰግተዋል።

የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ ቅዳሜ ዕለት "በትራንስአትላንቲክ ማኅበረሰብ ላይ ትልቁ ስጋት የውጭ ጠላቶቹ ሳይሆኑ ቀጣይነት ያለው የኅብረታችን መፍረስ ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሁላችንም ይህንን አስከፊ አካሄድ ለመቀልበስ የበኩላችንን ማድረግ አለብን" ሲሉ ተናግረዋል።

ሁለት ሪፐብሊካን ሕግ አውጪዎች በበኩላቸው "የአሜሪካ ጦር ከጀርመን እንዲወጣ በመወሰኑ በጣም ስጋት እንደገባቸው" ተናግረዋል።

ሴናተር ሮጀር ዊከር እና ማይክ ሮጀርስ "ከአህጉሪቱ ጦርን ጠቅልሎ ከማስወጣት ይልቅ፣ የማይበገር መከላከያ በአውሮፓ ማየት የአሜሪካ ፍላጎት ነው" ብለዋል።

ፒስቶሪየስ ቅዳሜ ዐዕለት በነበራቸው ቃለ ምልልስ አውሮፓ ለራሷ ደህንነት ትልቁን ኃላፊነት መሸከም አለባት ብለዋል። አክለውም በርሊን ከአጋሮቿ ጋር በመሆን በቅርበት እንደምትሰራ ተናግረዋል።

"ጀርመን ትክክለኛው መንገድ ላይ ነች" ያሉት መከላከያ ሚኒስትሩ አገራቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመከላከያ ወጪዋን በከፍተኛ ቁጠር ማሳደጓን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም ትራምፕ ጀርመን ለጦር ሠራዊቷ የምትመድበው በጀት ኔቶ ካስቀመጠው እና ከአገራዊ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) 2 በመቶ መሆን አለበት ከሚለው መመሪያ በታች በመሆኑ "ቸልተኛ" ሲሉ ተችተዋት ነበር። ይህ ግን በመርዝ አስተዳደር በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል።

ጀርመን በሚቀጥለው ዓመት፣ እአአ በ2027 አጠቃላይ አገራዊ ምርቷ 3̏.1 በመቶ እንደሚደርስ በመገመት 105.8 ቢሊዮን ዩሮ ለመከላከያ ለማውጣት ውሳኔ አሳልፋለች።

የኔቶ ጥምረት ቃል አቀባይዋ ሃርት ቅዳሜ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ አሜሪካ ጦሯን ከጀርመን ለማስወጣት መወሰኗ "አውሮፓ መከላከያዋ ላይ የበለጠ ሃብቷን እንድታፈስ አጽንኦት የሚሰጥ እንዲሁም ለጋራ ደህንነታችን የጋራ ኃላፊነት እንዳለብን የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

"አባላት ባለፈው ዓመት በሄግ በተካሄደው ጉባዔ ወቅት የመከላከያ ወጪያቸው ላይ የአጠቃላይ ምርታቸው 5 በመቶ ለመመደብ በመስማማታቸው ለውጦች ማየት ጀምረናል" ብለዋል።

የጀርመኑ መራሄ መንግሥት መርዝ አሜሪካን የሚተቸውን ንግግራቸውን ያሰሙት ሰኞ ዕለት ማርስበርግ ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ለተማሪዎች ባደረጉት ንግግር ወቅት ነው።

መርዝ "አሜሪካ ምንም ስትራቴጂ እንደሌላት ግልጽ ነው" ሲሉ ለተማሪዎቹ ተናግረዋል።

"ኢራናውያኑ ድርድር ላይ እጅግ የተካኑ መሆናቸው ወይም ድርድር አለማድረግ ላይ በጣም ጎበዝ መሆናቸው ግልጽ ነው። አሜሪካውያን ወደ ኢዝላማባድ እንዲጓዙ እና ያለ ውጤት በድጋሚ እንዲመለሱ አድርገዋል" ብለዋል።

"መላ አገሪቱ" በኢራን አመራር "እየተዋረደ" ነው ሲሉም አክለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በምላሹ የመርዝ ሃሳብ "ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ቢኖራት ችግር የለውም ማለት ነው" ካሉ በኋላ "ስለምን እንደሚያወራ አያውቅም" ብለዋቸዋል።

"በምጣኔ ሃብቱም ሆነ በሌሎች መስኮች ጀርመን ደካማ ብትሆን አይደንቅም" ሲሉ በልጥፋቸው ላይ መርዝን እና አመራራቸውን ወርፈዋል።

ከዚህ በኋላ አሜሪካ ጦሯን ከጀርመን ለማስወጣት ወስናለች።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሺን ፓርኔል በሰጡት መግለጫ ውሳኔው የተላለፈው በመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት መሆኑን ተናግረዋል።

"ይህ ውሳኔ በአውሮፓ ውስጥ የመምሪያውን የኃይል አቀማመጥ በጥልቀት በመገምገም የቲያትር መስፈርቶችን እና በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው" ብለዋል።

ወታደሮቹ መቼ ጀርመንን ለቅቀው እንደሚወጡ ሲያስረዱም "ከስድስት ወራት እስከ 12 ወራት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ተጠቃልለው ይወጣሉ ብለን እንጠብቃለን" ሲሉ ተናግረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ለረዥም ጊዜ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ጥምረትን (ኔቶ) በመተቸት ይታወቃሉ። አባል አገራቱ የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ለማስከፈት በሚደረግ ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ እምቢተኛ በመሆናቸው በተደጋጋሚ ተችተዋቸዋል።