ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጭንቀት እና ምግብ ያላቸው ትስስር ምንድን ነው? ስንጨነቅ አመጋገባችን ይለወጣል?
ጭንቀት ጤና ያቃውሳል። ራስ ምታት፣ የሆድ ሕመም፣ እንቅልፍ ማጣት ያስከትላል። አመጋገብንም ያዛባል።
ስንጨነቅ ቸኮሌት ወይም ፒዛ ያምረናል። ለመሆኑ ጭንቀት አመጋገባችንን የሚለውጠው እንዴት ነው?
ጭንቀት ምንድን ነው?
የሥነ ልቦና ባለሙያ እና በዬል ዩኒቨርስቲ የጭንቀት ጥናት ምርምር ማዕከል የከፈቱት ፕ/ር ራጂታ ሳናሀ እንደሚሉት፤ ጭንቀት ማለት ሰውነት እና አእምሮ ለፈታኝ የሚሰጡት ምላሽ ነው።
"ምንም ማድረግ የምንችለው ነገር እንደሌለ ሲሰማን የሚመጣ ስሜት ነው" ይላሉ።
በአካባቢያችን የሚፈጠር ነገር ወይም አእምሯችን ውስጥ የሚፈጠር የስሜት መዋዠቅ አልያም ደግሞ እንደ ረሃብ እና ጥማት ያለ የሰውነት ለውጥ በአእምሯችን ውስጥ የሚገኘውን ሀይፖታላሙስ (hypothalamus) ላይ ለውጥ ያስከትላል። ይህ ለውጥ ነው ጭንቀት የሚያስከትለው።
ባለሙያዋ እንደሚሉት፤ ይህ የሰውነታችን ክፍል ምላሽ የሚሰጠው እንደ አድረነሊን እና ኮሪስትሮል ያሉ ሆርሞኖች ለውጥ ሲፈጠር እንዲሁም የልብ ምት እና የደም ዝውውር ሲቀየር ነው።
ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ጭንቀትን ሰውነት ራሱን ከአደጋ እንዲከላከል ስለሚያነቃቃ እምብዛም አይጎዳም።
ሆኖም ግን ዘለግ ላለ ጊዜ የሚቆይ ጽኑ ጭንቀት (chronic stress) የጤና ቀውስ ያስከትላል።
ከቤተሰብ፣ ከሥራ፣ ከገንዘብ እና ከሌሎች ነገሮችም ጋር በተያያዘ የሚፈጠር ጭንቀት ወደ ድባቴ፣ እንቅልፍ ማጣት እና የሰውነት ክብደት መጨመር ያመራል።
ጭንቀት እና ምግብ ምን ያገናኛቸዋል?
ጭንቀት እና ምግብ ያላቸውን ትስስር የሚገልጹት የሥነ ልቦና እና አመጋገብ ባለሙያ ዶ/ር ሚቱ ስትሮኒ ናቸው።
"ለፈተና ሳጠና እታመም ነበር" ሲሉ የራሳቸውን ተሞክሮ ይጠቅሳሉ።
የሰውነት ምግብ ማብላያ ክፍል እና አእምሮ መካከል ትስስር እንዳለ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
ጭንቀት ከአንጎል ወደ ሆድ የሚሄደው ነርቭ (vagus nerve) ላይ ጫና ያሳድራል።
ይህ የነርቭ አካል ከአንጎል ወደ ሆድ መልዕክት ያስተላልፋል። ሰውነት አስፈላጊውን የምግብ መጠን ሲያገኝ (ስንጠግብ) ወይም ከምግብ ኃይል ማግኘት ሲያስፈልገን መረጃ ይሰጣል።
ባለሙያዋ እንደሚያስረዱት ሰውነት ጭንቀት ሲገጥመው የሚፈልገው የስኳር መጠን ይጨምራል።
"ልክ ሲጨንቀን አእምሯችን የሚፈልገው የስኳር መጠን ከፍ ይላል" በማለት የሥነ ልቦና እና አመጋገብ ባለሙያ ዶ/ር ሚቱ ስትሮኒ ያስዳሉ።
አንዳች ነገር ሊከሰት ይችላል ብሎ በማሰብ ሰውነት ቅርመ ጥንቃቄ ሊያደርግም እንደሚችልም ይገልጻሉ።
ከባድ ጭንቀት አመጋገብን ይለውጣል?
ከባድ ጭንቀት ሰውነት ላይ ያለው ጫና ከማቅለሽለሽ እና ስኳር በብዛት ከመፈለግም በላይ ነው።
ሰውነት ሲጨነቅ የደም ሕዋስ በስኳር ይሞላል። ስለዚህም የሚመረተው የኢንሱሊን መጠን ይጨምራል።
የግሉኮስን መጠን የሚያስተካክለው ሆርሞን ውጤታማነቱ እንደሚቀንስ የሥነ ልቦና ባለሙያ እና በዬል ዩኒቨርስቲ የጭንቀት ጥናት ምርምር ማዕከል የከፈቱት ፕ/ር ራጂታ ሳናሀ ያስረዳሉ።
ግሉኮስ በደም ሕዋስ ሲቆይ ኃይል ከማመንጨት ይለቅ የደም የስኳር መጠን ያለልክ ከፍ እንዲል ምክንያት ይሆናል።
ከፍተኛ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ለስኳር ሕመም የሚጋለጡትም ለዚህ ነው። የሰውነት ልብደታቸውም እየጨመረ ይሄዳል።የሰውነት ክብደት ሲጨምር ተከትለው የሚመጡ ለውጦችም አሉ። ከልክ ያለፈ ስብ በሰውነታቸው ውስጥ ያለ ሰዎች ኢንሱሊንን ይቋቋማሉ።
ስለዚህም ሲጨነቁ አእምሯቸው የሚፈልገው የስኳር መጠን ይጨምራል።
"አንደኛወ እክል ሌላውን ያስከትላል። እሽክርክሪት ነው። የሰውነት ስብ ሲጨምር ኢንሱሊን መቋቋም ይከሰታል። ስንጨነቅ ደግሞ የበለጠ ስኳር ያስፈልገናል" ሲሉ ባለሙያዋ ያስረዳሉ።
በጭንቀት ምክንያት ብዙ ላለመብላት ምን እናድርግ?
ጭንቀት የሚከሰትበትን ወቅት ቀድሞ በመለየት ከመጠን ያለፈ ላለመመገብ መብላትን እንደ መፍትሔ ባለሙያዎቹ ያስቀምጣሉ።
"ዋናው ትኩረት መሆን ያለበት እንቅልፍ ነው። እንቅልፍ የሰውነት እንቅስቃሴን መልሶ እንደ አዲስ ስለሚያስጀምር ጭንቀትን ለመቆጣጠር ይረዳል" ሲሉ ዶ/ር ሚቱ ስትሮኒ ይናገራሉ።
የጭንቀት ሆርሞንን በመቀነስ፤ በአእምሯችን ውስጥ የሚገኘውን ሀይፖታላሙስ (hypothalamus) እንዲሁም ሌሎችም የሰውነት ክፍሎች በሚዛናዊ መንገድ እንዲንቀሳቁ ያደርጋል።
"እንቅልፍ ካልተኛን የስኳር ፍላጎታችን ይባባሳል" ይላሉ ባለሙያዋ።
የጭንቀት መጠንን ለመቀነስ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግም ይመከራል።
ስንጨነቅ የትኞቹን ምግቦች እናቁም?
ስንጨነቅ መቀነስ ካለብን ምግቦች አንደኛው ስኳር እንደሆነ ፕ/ር ራጂታ ሳናሀ ይናገራሉ።
በፍጥነት የሚሠሩ የተቀነባበሩ ምግቦች (junk foods) አለመመገብም ይመከራል።
"እነዚህን ምግቦች አለመግዛት ወይም በቅርብ የሚገኙበት ቦታ አለማስቀመጥ የተሻለው መንገድ ነው" ይላሉ።
ረሃብ እና አምሮት የሚያስታግሱ ቀላል ምግቦችን መመገብን ባለሙያዋ ይመክራሉ።
የግሉኮስ መጠን የሚጨምሩ ምግቦችን መቀነስ ይመከራል። ካርቦሃይድሬት የበዛባቸው እንደ ፒዛ ያሉ ምግቦችን ማስወገድም ያስፈልጋል።
ፕሮቲን የበዛባቸው እንደ ሥጋ እና ዓሣ ያሉ ምግቦች እንዲሁም ያልተፈተጉ ጥራጥሬዎችን መመገብን ባለሙያዋ ይመክራሉ።
"ሲጨንቃቸው አልኮል መጠጥ የሚያዘወተሩ ሰዎችም መቆጠብ አለባቸው" ይላሉ።
"የማኅበራዊ ጥናት ባለሙያዎች ከጭንቀት የሚመነጭ የአመጋገብ ለውጥን ለማስተካል ጥናቶች አድርገዋል። ከወዳጅ ዘመዶች ጋር አብሮ ማብሰል እና መመገብ አንድ መንገድ ነው" ሲሉ ባለሙያዋ ያብራራሉ።