ባይናንስ ግዙፍ የተባለ የሳይበር ጥቃት ከተፈፀመበት በኋላ ተጠቃሚዎቹ 3.6 ቢሊዮን ዶላር አወጡ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዓለም ግዙፉ የክሪፕቶ ከረንሲ ኩባንያ ባይናንስ በታሪክ ትልቁ የሳይበር ጥቃት ከተፈፀመበት በኋላ እሑድ ዕለት አገልግሎቱን ሲጀምር ደንበኞች 3.6 ቢሊዮን ዶላር ማውጣታቸውን ገለፀ።

ኩባንያው በደረሰበት ጥቃት 6.3 ቢሊዮን ዶላር የዲጂታል ሃብቱ የተጎዳ ሲሆን፤ ከጥቃቱ በኋላ ሁሉንም የገንዘብ ልውውጦች አግዷል።

እንደ አሜሪካ የፌደራል ምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ ያሉ ትላልቅ ድርጅቶች ለሳይበር ጥቃቱ ሰሜን ኮሪያን ከስሰዋል።

ኩባንያው 95 በመቶ የሚሆነው የተዘረፈውን ሀብቱን ማስመለሱን ሲናገር፤ ቀሪውን ለማስመለስ ግን ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ተናግሯል።

ባይናንስ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ የደረሰውን ጉዳት እንደሚሸፍን በተደጋጋሚ ተናግሯል።

ባይናንስ ትናንትና ባወጣው መግለጫ አገልግሎቱን ዳግም ሲጀምሮ ደንበኞቹ 4.649 ቢሊዮን ዶላር ሲያወጡ፤ 1.01 ቢሊዮን የሚሆን የዲጂታል ገንዘብ ደግሞ ወደ ኩባንያው ተቀማጭ ሆኗል። ይህም ደንበኞቹ 3.64 ቢሊዮን ዶላር አውጥተዋል ማለት እንደሆነ ጠቁሟል።

በፍጥነት ከፍተኛ ወጪ የማውጣት አዝማሚያ አንደነበር ጠቁሞ፤ ከቆይታ በኋላ "እንደተጠበቀው" መረጋጋቱን ገልጿል።

የእሑዱ ወጪ ኩባንያው ከሚያስተዳድረው 171 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ውስጥ ሁለት በመቶ በላይ የሚሆነው እንደሆነም ባይናንስ አክሎ ተናግሯል።

ኩባንያው ባለፈው ሣምንት በጥቃቱ የደረሰበትን ጉዳት ለመሸፈን 6.3 ቢሊዮን ዶላር ተቀማመጭ ማድረጉን አስታውቋል።

ባይናንስ በጥቃቱ ምክንያት በጥርጣሬ ታግደው የነበሩ ከኩባንያ ኩባንያ የሚደረጉ የክሪፕቶ ከረንሲ ልውውጦች መጀመራቸውን ገልጿል።

'ቼንአናሊሲስ' በተባለው የገንዘብ አስተዳደር ተቋም ዓለም አቀፍ አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አሌክ ዝብሪክ ከባይናንስ ጥቃት ጋር የተያያዙ ሃብቶች "መታጠቡን" ቀጥሏል ብሏል።

የተዘረፈውን ገንዘብ ለማስመለስ ከባይናንስ እና ከመንግሥት ጋር እየሰሩ ያሉት ባለሙያው "በጣም በፍጥነት ገንዘቡ እየታጠበ እንደሆነ ማየታችንን ቀጥለናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አጥቂዎቹ ገንዘቡን በበርካታ ሺዎች አድራሻ፤ በበርካታ ሺዎች ተቀማጭ በኩል አድርገው እያንቀሳቀሱ ነው" ሲልም አክለዋል።

ባይናንስ ላይ የተፈፀመው ጥቃት 'ትሬደር ትሬተር' ከተባለ የሰሜን ኮሪያ የሳይበር ወንጀለኛ ቡድን ጋር ተያይዟል። 'ላዘርስ ግሩፕ' የሚል ሌላ መጠሪያ ያለው ቡድኑ ከ'ባይባይት' እ.አ.አ በ2025 በታሪክ ትልቁ የተባለ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ዘርፈዋል።

እሑድ ዕለት ኤፍቢአይ ከቡድኑ ጋር ትስስር ያላቸውን የክሪፕቶ ቦርሳዎች ይፋ ያደረገ ሲሆን በኢንዱስትሪው ያሉ አጋሮች የገንዘብ ልውውጦችን በማገድ እገዛ እንዲያደርጉ አሳስቧል።