በኔፓል እና ፓኪስታን ላበረከቱት የግብርና ሥራ ታላቁን ሽልማት ያሸነፉት ኢትዮጵያዊ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ለፊልም ኦስካር፣ ለሰላም ኖቤል ካልን ለእርሻ ምን እንላለን?

የድማሚት ፈጣሪው ስዊድናዊ አልፍሬድ ኖቤል፣ የኖቤል ሽልማትን እንደጀመረው ሁሉ የምግብ ሽልማትን የጀመሩት ዶ/ር ኖርማን ቦርሎግ ናቸው።

'ዎርልድ ፉድ ፕራይዝ' ይባላል ሽልማታቸው። የዓለም የምግብ ፋውንዴሽን ነው ተቋሙ። በአሜሪካ፣ አዮዋ ግዛት ነው መገኛው።

ዶ/ር አብዱረሕማንም እዚያው ናቸው። ይህ ተቋም 'የእርሻና ምግብ ኖቤል' እንደማለት ነው ይላሉ።

በየዓመቱ ለፈር ቀዳጅ የግብርና ተመራማሪዎች ሽልማት ይሰጣል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ቀንቷት ያውቃል። ዕድሜ ለፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጄታ።

ፕሮፌሰር ገቢሳ በማሽላ ሰብል ባደረጉት ምርምር ነው ለሎሬትነት የበቁት፤ በ2001 ዓ/ም። ከርሳቸው በኋላ ይህን ሽልማት የወሰደ ኢትዮጵያዊ የለም።

ዘንድሮ ግን ዶ/ር አብዱረሕማን በሽር ለዚያ ተጠግተዋል። ዋናውን የሎሬትነት ሽልማት ባይወስዱም ከዚሁ ተቋም በሌላ ዘርፍ አሸናፊ ሆነዋል።

የዘንድሮው ሎሬት ግን ኔዘርላንዳዊው ሁብ ሌሊቬልድ ናቸው።

ዶ/ር አብዱረሕማን ያሸነፉት በፈር ቀዳጆች ዘርፍ ነው። በኦስካር የተለያዩ ዘርፎች እንዳሉት ሁሉ ለዚህም የዓለም ምግብ ሽልማት ፋውንዴሽን በርካታ ዘርፎች አሉት።

ዓመታዊ የሎሬት ሽልማቱ 250ሺህ ዶላር የሚያሸልም ነው።

ሌሎች ዘርፎች ግን የገንዘብ ሽልማት አያስገኙም። ሆኖም ከገንዘብ ያልተናነሰ ትልቅ ሙያዊ ዋጋ ያላቸው ናቸው።

ዶ/ር አብዱረሕማን በዓለም ላይ ከ40 ቀዳሚ የግብርና እና ምግብ ፈር ቀዳጆች (Top Agri-food Pioneers – TAP) ዘርፍ አንዱ ሆነው ነው የተመረጡት።

ዶ/ር አብዱረሕማን በሽር ማን ናቸው?

አዲስ አበባ ነው የተወለዱት። ሐረማያ ዩኒቨርስቲ ነው የተማሩት። በፅጽዋት ሳይንስ ነው የተመረቁት።

የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከደቡብ አፍሪካው ፍሪስቴትስ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። በዕፅዋት ማዳቀል (Plant Breeding) የሠሩት ምርምር ብዙ ተወድሷል። የማዕረግ ተመራቂም ነበሩ።

"የተለያዩ ዘሮች የተለያየ ቦታ ሲበቅሉ ለምን የተለያየ ብቃት ይኖራቸዋል የሚል ጥናት ነበር የሠራሁት" ይላሉ።

ይህን የዛሬውን ዕውቅናቸውን ተከትሎም ቀድሞ የተማሩበት የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ደስታውን ገልጿል። 'የቀድሞ ተማሪዬ ስኬት' ብሎ የርሳቸውን ታሪክ በድረ-ገጹ አትሟል።

"ምርምርን ለለውጥ ያዋሉ የኛው ፍሬ" ሲልም አሞግሷቸዋል።

የዩኒቨርስቲው ምክትል ቻንስለር ቫሱ ሬዲ፣ "ዩኒቨርስቲያችን ባንተ ዕውቅና ማግኘት ኮርቷል፤ ሳይንሳዊ ምርምር ለማኅበረሰብ ለውጥ እንዴት መዋል እንደሚችል ያሳየህ ጀግና ነህ" ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።

ዶ/ር አብዱረሕማን ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት ለዚህ ዕውቅና ያበቃቸውም ይኸው ነው። ሳይንሳዊ ምርምርን፣ ወደ ተግባር መለወጡ፣ ለውጦ ደግሞ የአርሶ አደርን ሕይወት መለ'ወጡ እንደሆነ አብራርተዋል።

ዶ/ር አብዱረሕማን ከረዥም የትምህርት ዓመታት ቆይታ ወደ ሥራው ዓለም ከገቡ በኋላ የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው የተለያዩ አገራት ለሁለት ዐሥርታት በምርምር ሥራ ቆይተዋል።

ዋናው ሥራቸው ግን ኢሲያ ነው። በተለይ በደቡብ ኢሲያ፣ በኔፓልና ፓኪስታን በሠሯቸው ተግባራት ትልቅ ስም ተጎናጽፈዋል።

የተሸለሙት ምን ሠርተው ነው?

ዶ/ር አብዱረሕማን በኃላፊነት የሚሠሩበት መሥሪያ ቤት 'የዓለም አቀፍ የበቆሎና የስንዴ ማሻሻያ ማዕከል'፣ በምህጻሩ ስሚት (CIMMYT) ይባላል። ዋና መሥሪያ ቤቱ ሜክሲኮ አገር ነው። ይሁንና በላቲን አሜሪካም፣ በአፍሪካም፣ በኢሲያም ቢሮዎች አሉት።

እሳቸው የኢሲያውን ቢሮ ይመራሉ። የኢስያ ቀጠና የዘር ሥርዓት መሪ በመሆን ያገለግላሉ።

የሚገርመው የታሪክ ግጥምጥሞሽ፣ ይህን 'የእርሻ ኦስካር' ተብሎ የሚጠራውን የዓለም የምግብ ሽልማት የጀመሩት ሰው ድሮ (በ1960ዎቹ)፣ አሁን ዶ/ር አብዱረሕማን በሚያገለግሉበት መሥሪያ ቤት ምርምር ሥራ ይሠሩ ነበር።

ይህ ዶ/ር አብዱረሕማን የሚመሩት ተቋም በደቡባዊ ኢሲያ አገሮች ይንቀሳቀሳል።

በተለይ በኔፓልና በፓኪስታን የገበሬዎችን ሕይወት አሻሻሏል ተብሎ ይወደሳል። እንዴት አድርጎ?

በዘር ላይ ሳይንሳዊ ምርምርን አደረገና፣ ከግልና ከግብርና ሚኒስትሮች ጋር ተባብሮ፣ ምርጥ ዘር ገበሬዎች እጅ እንዲደርስ አስቻለ። በአጭሩ ስኬታማ የዘር ሰንሰለት (Seed Systems) ዘረጋ።

ዶ/ር አብዱረህማን የሚመሩት ተቋም ይህን በማሳካቱ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ሸላሚው ድርጅት ገልጿል።

ለምሳሌ ዶ/ር አብዱረሕማን በኔፓል ገበሬዎች የተሻሻለ ዘር ከውጭ ማስገባት እንዲያቆሙ በማድረጋቸው በዓመት 25 ሚሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል።ይህ በሠሩበት ዘመን ሲባዛ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይሆናል።

ሌላስ ምን አሳክተዋል?

አገር በቀል የዘር ምርት አስፋፍተው የሴት ገበሬዎች ሕይወት እንዲሻሻል፣ የሸማች ማኅበራት ገቢ እንዲያደግ አድርገዋል። በ10ሺህ ሄክታር የሚዘራ የተሻሻለ የበቆሎ አገር በቀል ዝርያ ተጨባጭ ውጤትን አስገኝቷል።

ይህ ብቻ አይደለም፤ ዶ/ር አብዱረሕማን በኔፓል መንግሥት በብሔራዊ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው ዘመናዊ የዘር መረጃ ሥርዓት (Digitally Enabled Seed Information System) እንዲበለጽግ አድርገዋል።

ይህ ሥርዓት በግብርና ውስጥ የተሳሰሩ ባለድርሻ አካላት የተሻለ የዘር መረጃ፣ ዕቅድና ትግበራ እንዲኖራቸው አስችሏል።

ሽልማቱ ይህን ሁሉ ከግምት በማስገባት ነው ዶ/ር አብዱረሕማንን ዕውቅና የሰጣቸው።

"እኔ ብቻዬን እንዳልመስልህ፤ በብዙዎች ተሳትፎ የተገኘ ታላቅ ስኬት ነው" ይላሉ።

ይህ ስኬት ታዲያ በአየር ንብረት ለውጥ በምትናጠው ኔፓል አገር ብቻ አይደለም። በፓኪስታንም ተሳክቶላቸዋል።

ከ15 አዳዲስ የበቆሎ ዝርያዎቸን ለገበሬዎች እንዲሰራጩ አድርገዋል። ዝርያዎቹ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ ናቸው።

በአጭሩ ዶ/ር አብዱረሕማን ምርምርና በተግባር ወደ ገበሬው እንዲደርስና የአርስ አደሮች ሕይወት እንዲለወጥ በማድረጋቸው የተሰጣቸው ዕውቅና ነው።

"አንድ አዲስ ዝርያ በምርምር ቢገኝ ገበሬዎች እጅ ካልገባ፣ ገበሬው ካላመነው፣ ገበሬው ካልተጠቀመው፣ በትክክለኛው ጊዜ ካላገኘው ምን ትርጉም አለው?" ይላሉ።

ዘር የሁሉ ነገር መነሻ ነው የሚሉት አብዱረሕማን "ጠረጴዛው ላይ ሽሮ ወጥ የበላ ሰው ሽንብራውን መርሳት የለበትም" ይላሉ።

"ለምትጣፍጥ ሽሮ የምትሆነው ዘር ምን ምን ዓይነት ናት። እንዴት ብትዘራ ምርታማ ትሆናለች፣ የዝርያው ባህሪ ምን ቢሆን ነው ስንበላው እንዲጣፍጠን ማድረግ የሚቻለው? እንዴት በትንሽ ወጪ ብዙ ሰው ጋር ደርሳ የምግብ ዋስትናን ልታረጋግጥ ትችላለች..." እያሉ በሽሮ ሰንሰለት ነገሩን ለማስረዳት ይሞክራሉ።

የርሳቸው ሥራ የዘር ምርምር ላይ ብቻ አያበቃም። ምርጥ የተባለው ዘር ከምርት ጀምሮ እስከ ሽያጭ በሰንሰለቱ ውስጥ አስገብቶ ውጤቱን ማየትን ይጨምራል።

"ለኔ ሳይንሳዊ ምርምና ጥናትን የምለካው ሕይወትን ባሻሻለበት ልክ ነው" ይላሉ ደጋግመው።

የተማሩበት የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲም ዕውቅና የሰጣቸው ለዚሁ ነው። ምርምርን ከሼልፍ አውጥቶ ማሳ ላይ ስኬት በመዝራታቸው።

"የሳይንስ ምርምር የገበሬዎችን ሕይወት በተጨባጭ ሲለውጥ እንደማየት ምን ደስ የሚያሰኝ ነገር አለ?" ይላሉ ዶክተር አብዱረሕማን።

ሽልማቱን ከመቀበላቸው በፊት ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት አገራቸው ኢትዮጵያ ለግብርና ባለሙያዎች ዋጋም ቦታም ዕውቅናም ስትሰጥ ማየት ምኞቻቸው እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ለቲክቶከሮች ታላቅ ዕውቅና በምታጎናጽፍ አገር፣ ኢትዮጵያ፣ በልቶ ማደር 'ስኬት' ተደርጎ በሚቆጠርባት ኢትዮጵያ፣ ለግብርና ለእርሻ ሳይንቲስቶች ይህ ነው የሚባል ዕውቅና አትሰጥም።

አገር ቤት፣ ሚዲያውም ሌላውም ለአርስቲስቶች፣ ለሌሎች ጉዳዮች የሚሰጠውን ሽፋን በትንሹ እንኳ ለግብርናና ለእርሻ ቢሰጥ ደስ እሰኝ ነበር።" ይላሉ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በምትተጋው ኢትዮጵያ ተወልደው በኢሲያ ማሳዎች ውስጥ የሚኳትኑት ዶ/ር አብዱረሕማን በሽር።