ቀጥታ , የሶማሊያ የባህር ላይ ወንበዴዎች የኢራንን መርከብ በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉ

የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች 23 ሰዎችን የጫነች የኢራን አሳ አጥማጅ መርከብ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰማ። የሕንድ ውቅያኖስ የባሕር ላይ ደህንንት ማዕከል የባሕር ላይ ወንበዴዎቹ የንግድ መርከቦችን በመጠጋት ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላለ ሲል አስጠንቅቋል። አዚኒ የተባለችው የአሳ አጥማጅ መርከብ የታገተችው ሐሙስ ዕለት መሆኑ ታውቋል። መርከቧ በሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ በባንዳር ባይላ እና ሀፉን ከተሞች መካከል እየቀዘፈች እንደነበር የፑንትላንድ የባሕር ላይ ፖሊስ እሁድ ዕለት አስታውቋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ በየመን የድርጅቱ ሠራተኛ በሁቲዎች እጅ እያለ መሞቱን አወገዙ

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በየመን በሁቲ ቁጥጥር ሥር የነበረ የድርጅቱ ሠራተኛ መሞቱን ተከትሎ “እጅግ ማዘናቸውን” ገለጹ።

    ሟቹ መሐመድ ኢብራሂም አል-ሻሚ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ ውስጥ ይሰራ የነበረ ሲሆን፣ ከሰኔ 6 ቀን 2024 ጀምሮ በሁቲዎች ምንም ክስ ሳይመሰረትበት ታስሮ ቆይቷል።

    ጉተሬዝ ቅዳሜ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መግለጫ፣ አል-ሻሚ በሁቲዎች እስር ውስጥ የሞተ ሁለተኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኛእንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ በፊት እንደ አውሮፓውያኑ በየካቲት 2025 የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሠራተኛ በእስር ላይ ሳለ ሕይወቱ አልፎ ነበር።

    “አሁንም በእስር ላይ ስላሉት የተመድ ሠራተኞች፣ የቀድሞ የተመድ ሠራተኞች እና የሰብዓዊ ድርጅቶችና የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ሠራተኞች የደህንነት እና የጤና ሁኔታ እጅግ ያሳስበኛል” ሲሉ ጉተሬዝ ተናግረዋል።

    በሁቲዎች እስር ውስጥ የሞተው የመጀመሪያው የተመድ ሠራተኛ አህመድ ባአላዊ ሲሆን፣ እሱም የዓለም የምግብ ፕሮግራም የአገር ሠራተኛ ነበር። እአአ ከጥር 23 2025 ጀምሮ በሰሜን የመን በአካባቢው ባለሥልጣናት በዘፈቀደ ታስሮ ከቆየ በኋላ በየካቲት 11 2025 ሕይወቱ አልፏል።

    የመን እአአ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በግጭት ውስጥ ትገኛለች። በዚያ ዓመት የሁቲ ታጣቂዎች ዋና ከተማዋን ሰነዓን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን መንግሥት ለመደገፍ በሳዑዲ አረቢያ የሚመራ ወታደራዊ ጥምረት በመጋቢት 2015 ጣልቃ ገብቷል።

    ግጭቱ በዓለም ላይ እጅግ ከባድ የሰብዓዊ ቀውሶች ካስከተሉ መካከል አንዱ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ ሆነው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።

    • ተያያዥ ዜናዎች
  2. በፍሎሪዳ የንግድ አውሮፕላን ተከስክሶ በውስጡ የነበሩ 9 ሰዎች ሞቱ

    በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት አንድ የንግድ አውሮፕላን እሁድ ዕለት በመኖሪያ ሰፈር ተከስክሶ በውስጡ የነበሩ ዘጠኝ ሰዎች በሙሉ መሞታቸውን የአሜሪካ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

    አደጋው የተከሰተው ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመዝናኛ ስፍራ ማር-አ-ላጎ 14 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።

    ከአደጋው በኋላ የተነሱ ምስሎች በመኖሪያ አካባቢ በሚገኝ መንገድ መሀል ትልቅ ጉድጓድ መፈጠሩን፣ እሳት መነሳቱን እና የከሊርጀት 60 (Learjet 60) አውሮፕላን ስብርባሪዎችን አሳይተዋል።

    የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር እንዳስታወቀው፣ አውሮፕላኑ ከአውስቲን ቴክሳስ ተነስቶ ወደ ባሃማስ እየተጓዘ ነበር።

    የአሜሪካ ሚዲያዎች እና የበረራ መረጃ ትንተናዎች እንደሚያመለክቱት፣ አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት በሰከንድ መቶዎች የሚቆጠሩ ጫማዎችን እየተምዘገዘገ እየወረደ ነበር።

    ከአደጋው ቀደም ብሎ በተቀዳ የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ድምጽ ውስጥ፣ አብራሪው አውሮፕላኑ በደቂቃ 10,000 ጫማ እየወረደ መሆኑን ሲገልጽ ይሰማል።

    በመቀጠልም አብራሪው የድንገተኛ አደጋ መከሰቱን አስጠንቅቆ “በከፍተኛ ፍጥነት እየወረድን ነው፤ በደቂቃ 20,000 ጫማ እየወረድን ነው” ብሎ መጮሁ ተገልጿል።

    “ልንከሰከስነው... ጊዜ የለንም” ሲልም ለመቆጣጠሪያው ማማ መናገሩ ተዘግቧል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቀ እና ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ ቪዲዮ፣ የአደጋውን ቅጽበት ያሳያል። በቪዲዮው ላይ መኪኖች በመኖሪያ አካባቢ በሚገኝ መንገድ ላይ ሲጓዙ ይታያሉ፤ ከዚያም አውሮፕላኑ በቀጥታ ወደ መሬት ተቀልብሶ ሲወድቅ እና ትልቅ ፍንዳታ ሲፈጥር ይታያል።

    የፍሎሪዳ ገዢ ሮን ዴሳንቲስ ከአደጋው በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ያንን ቪዲዮ ስታይ በጣም የሚያስደነግጥ ነው። እንደ ሚሳይል እየተምዘገዘገ ወደ ታች እየመጣ ይመስላል፣ ከዚያም ግዙፍ ፍንዳታ ይከሰታል፤ ፍርስራሹም በየአቅጣጫው ይበተናል” ብለዋል።

    እስካሁን በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ማንነት በይፋ አልተገለጸም። ዴሳንቲስ በበኩላቸው “እስካሁን ድረስ መሬት ላይ የነበረ ተጎድቶ ወይም ሞቶ የተገኘ ሰው ስለመኖሩ ሪፖርት የለንም” ብለዋል።

    • ተያያዥ ዜናዎች
  3. አሜሪካ የኢራንን ቅድመ ሁኔታዎች ከተቀበለች የሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ በሁለት ቀናት ውስጥ ሊከፈት ይችላል- አራግቺ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አሜሪካ በቴህራን የቀረቡትን ቅድመ ሁኔታዎች ከተቀበለች ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለው የሆርሙዝ ወሽመጥ በሁለት ቀናት ውስጥ እንደገና ሊከፈት ይችላል አሉ።

    አራግቺ እንደገለፁት፣ ከኳታር አደራዳሪዎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች የእቅዱን ማስፈጸሚያ ጊዜ ከአምስት ቀናት ወደ ሁለት ቀናት አሳጥረውታል።

    ሚኒስትሩ አክለውም ቴህራን ከኢዝላማባድ ስምምነት በኋላ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ፣ በቀጠናው የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይሎች እንዲቀነሱ፣ ለነዳጅ ሽያጭ የተቀመጡ ገደቦች እንደገና እንዲከለሱ እና በኳታር የሚገኙትን ጨምሮ የታገዱ የኢራን ንብረቶች እንዲለቀቁ ትጠይቃለች።

    ኢራን ከኦማን ጋር በተወያየችባቸው የመርከብ መጓጓዣ መስመሮች ላይ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲሰጥላትም ትፈልጋለች።

    አራግቺ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በዋሽንግተንና በቴህራን መካከል በሌሎች እስካሁን ያልተፈቱ ጉዳዮች ላይ አዲስ ድርድር ለመጀመር መንገድ ይከፍታል ብለዋል።

    ይህ ሃሳብ የቀረበው በባሕር ማጓጓዣና በኤነርጂ ገበያዎች ላይ ተጽእኖ ያሳደረውን ውጥረት ለመቀነስ የዲፕሎማሲ ጥረቶች በቀጠሉበት ወቅት ነው። የዓለም የነዳጅ ንግድ አንድ አምስተኛ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ አሁንም ለዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ መተላለፊያ ሆኖ እያገለገለ ነው።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር “በጥሩ ሁኔታ እየሄደ” መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ደግሞ ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት ለማድረስ ገና እንዳልወሰኑ ጠቁመዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት በበኩላቸው አሜሪካ ጥቃት ከፈጸመች የከፋ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ አስጠንቅቀዋል።

    • ተያያዥ ዜናዎች
  4. ሩሲያ እና ዩክሬን የሳይበር ጥቃት ተፈጸመባቸው

    ሩሲያ እና ዩክሬን የአደጋ ጊዜ ማንቂያ መተግበሪያቸው ላይ ግዙፍ የሳይበር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አስታወቁ።

    የሳይበር ጥቃቱን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል የዲጂታል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ተቀስቅሷል።

    የዩክሬን ባለሥልጣናት ለዜጎቻቸው የጨረር ስጋት መኖሩን የሚገልጽ ሐሰተኛ መልዕክት ከተላከ በኋላ የአየር ጥቃት ማሳወቂያ መተግበሪያቸው የሳይበር ጥቃት እንደደረሰበት ተናግረዋል።

    የዩክሬን አየር ኃይል ወዲያውኑ መልዕክቱ ሐሰተኛ መሆኑን በመግለጽ ምንም ዓይነት የጨረር ስጋት የለም ብሏል።

    አክሎም ዜጎች በአገሪቱ ባለሥልጣናት በይፋ የሚሰጡ መረጃዎች ላይ ብቻ እንዲተማመኑ አሳስቧል።

    ከሰዓታት በኋላ የሩሲያ ድንገተኛ አደጋ ሚኒስቴር የአደጋ ማስጠንቀቂያ መተግበሪያው ላይ “ግዙፍ የሳይበር ጥቃት መፈጸሙን” ገልጾ የመረጃ መንታፊዎች ሐሰተኛ መረጃ እያሰራጩ መሆኑን ገልጿል።

    የአገሪቱ ባለሥልጣናት ለድንገተኛ አደጋ ማስጠንቂያ የሚያገለግሉት ሳይረኖች፣ ቴሌቪዥኖች እና የራዲዮ ስርጭቶች የጥቃቱ ሰላባ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

    የሳይበር ጥቃቱ የተፈጸመው በኬርሶን ግዛት ላይ ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ካበቃ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።

    ዩክሬን ጥቃቱን የፈጸመችው ሩሲያ ናት ስትል የወነጀለች ሲሆን ሞስኮ ግን ለጥቃቱ ተጠያቂ ናቸው ያለቻቸውን አካላት አላሳወቀችም።

    በሁለቱም አገራት ያሉ ባለሥልጣናት ክስተቶቹ የተገናኙ መሆን አለመሆናቸውን እየመረመሩ ነው።

  5. የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች የኢራንን አሳ አጥማጅ መርከብ በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉ

    የሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች 23 ሰዎችን የጫነች የኢራን አሳ አጥማጅ መርከብ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰማ።

    የሕንድ ውቅያኖስ የባሕር ላይ ደህንንት ማዕከል የባሕር ላይ ወንበዴዎቹ የንግድ መርከቦችን በመጠጋት ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ ሲል አስጠንቅቋል።

    አዚኒ የተባለችው የአሳ አጥማጅ መርከብ የታገተችው ሐሙስ ዕለት መሆኑ ታውቋል።

    መርከቧ በሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ በባንዳር ባይላ እና ሀፉን ከተሞች መካከል እየቀዘፈች እንደነበር የፑንትላንድ የባሕር ላይ ፖሊስ እሁድ ዕለት አስታውቋል።

    የፖሊስ ባልደረባው የፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) እነደተናገረው 12 የባሕር ላይ ወንበዴዎች 21 ኢራናውያንን እና ሁለት ሶማሊያውያን ጸጥታ ባልደረቦችንን ያሳፈረችውን መርከቧን አግተዋል።

    ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ለመስጠት ኃላፊነት እንዳልተሰጠው በመግለጽ ስሙ አንዳይገለጽ የጠየቀው ይህ ግለሰብ የመርከበኞቹ ደህንነት በምን ሁኔታ ላይ እንደሆነ አይታወቅም ብሏል።

    የባሕር ኃይል ደህንነት ማዕከሉ ባወጣው ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ወንበዴዎቹ ያገቱትን መርከብ ተጠቅመው በንግድ መርከቦች ላይ ተጨማሪ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ ብሏል።

    የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ኃይል ዘመቻ ጉዳዩን እየመረመረ መሆኑን ገልጾ በአካባቢው የሚገኙ መርከቦች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን እንዲያሳውቁ ጥሪ አቅርቧል።

    ይህ የመርከብ እገታ የተከሰተው በኤደን ባሕረ ሰላጤና በምዕራባዊ ሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ የሶማሊያ ባሕር ወንበዴዎች እንደገና ካንሰራሩ በኋላ ነው።

    ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ይፋ በተደረገ መረጃ መሠረት ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ስድስት የንግድ መርከቦች ታግተዋል።

    ከእነዚህም ጥቃቶች አንዳንዶቹ ከሶማሊያ የባሕር ዳርቻ በጣም ርቀው በሚገኙ ስፍራዎች የተፈጸሙ ናቸው።

    በመስከረም ወር የፑንትላንድ ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ ወንበዴዎቹ ኤምቲ ኦነር 25 በመባል የምትጠራውን ነዳጅ ጫኝ መርከብ ካገቱ በኋላ የጸጥታ አባላት ከመድረሳቸው በፊት አምስት ባሕረተኞችን ገድለዋል።

    የነዳጅ ጫኝ መርከቡ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በወንበዴዎች እጅ ነበር። ባለሥልጣናት 16 በባሕር ላይ ውንብድና የተጠረጠሩ ግለሰቦች መታሰራቸውን ገልጸዋል።

    ባለፉት አስር ዓመታት ዓለም አቀፍ የባሕር ኃይል ጥበቃዎች እና የባሕር ደህንነት ማሻሻያዎች በሶማሊያ አካባቢ የባሕር ላይ ውንብድናን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰውት ነበር። ነገር ግን በቅርቡ የተፈጸሙት የመርከብ እገታዎች በአገሪቱ ረዥም የባሕር ዳርቻ አካባቢ በሚያልፉ መርከቦች ላይ የደህንነት ስጋት ደቅነዋል።