የኦፕንኤአይ ኃላፊ ዓለም ሰው ሠራሽ አስተውሎትን "መፍራቱ ተገቢ ቢሆንም" ኩባንያዎችን ግን "ማመን አለበት" አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኦፕንኤአይ ኃላፊ ሳም አልትማን ሰዎች የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በሚመለከት የእርሳቸውን እና ሌሎች ኩባንያዎችን ሊያምኑ እንደሚገባ ተናገሩ።
ኃላፊው ይህን ያሉት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) በከፍተኛ ፍጥነት መዘመን በበርካቶች ዘንድ ስጋት ከፈጠረ ወዲህ ነው።
አልትማን ማክሰኞ ዕለት በሳን ፍራንሲስኮ በተካሄደው ጉባዔ ላይ "ዓለም ትክክለኛውን ነገር እንደምናደርግ ማመን አለበት፤ ምክንያቱም ትክክለኛው ነገር ስለሆነ እና በዚያ መጠን ኃላፊነት ስለሚሰማን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ይኹን እንጂ አልትማን ሰዎች የኤአይ አቅም በፍጥነት እያደገ ሲመጣ መፍራታቸው ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
"አሁን ኤአይ ችግሮችን እንደሚፈጥር ለመገመት እንደ ከዚህ በፊቱ ከባድ አይደለም" ያሉት ኃላፊው " ሲመስለኝ ዓለም ይህንን መፍራቱ ተገቢ ነው" ብለዋል።
አልትማን ይህንን ያሉት ሴልስፎርስ በሚባል የሶፍትዌር ኩባንያ ባዘጋጀው ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ነው።
የኦፕንኤአይ ኃላፊ የሆኑት አልትማን ባለፈው ሳምንት አንትሮፒክን የለቀቀ ተመራማሪ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ያጋራው መልዕክት በሰፊው መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ በይፋ አስተያየት ሲሰጡ ይህ የመጀመርያቸው ነው።
ተመራማሪው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቁጥጥር ካልተደረገበት የሰው ልጅን ከአስር ዓመት በኋላ ሙሉ በሙሉ ያጠፋል ብሎ ነበር።
በርካታ የኤአይ ኩባንያ ኃላፊዎች በተመራማሪው ሃሳብ የተስማሙ ቢሆንም እዚህ ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ የቻሉት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ይህንን የሚያደርገው በምን መልኩ እንደሆነ አላብራሩም።
የተመራማሪውን አስተያየት ተከትሎ በሕዘብ ዘንድ ከፍተኛ መነጋገሪያ በመሆኑ ሠው ሠራሽ አስተውሎትን የማበልጸግ ፍጥነት እንዲቀንስ ጥሪ ቀርቧል።
የአንትሮፒክ ኃላፊ የሆኑት አሞዴይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ማበልጸግ ፍጥነት እንዲቀንስ እና መንግሥት ኢንዱስትሪውን እንዲቆጣጠር ጥሪ አቅርበዋል።
አልትማን፣ የጎግል ዲፕማይንድ መስራች የሆኑት ዴሚስ ሃሳቢስ፣ የኤክስ እና ግሮክ ባለቤት የሆነው ኤለን መስክ ተመራማሪው ይፋ ያደረገውን መረጃ አድንቀዋል።
ማክሰኞ ዕለት ተጨማሪ የኤአይ ኩባንያ ኃላፊዎች መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ከሚቆጣጠር ኩባንያዎቹ ራሳቸውን እንዲፈትሹ ጥሪ አቅርበዋል።
አልትማን እንደ ኦፕንኤአይ ያሉ ኩባንያዎች ራሳቸውን መቆጣጠር እንደሚችሉ ተናግረዋል።
"ወደ ትክክለኛው መስመር እንመጣለን፣ ይህንን በጥንቃቄ ማድረግ እንደምንችል በኩባንያችን እና በኢንዱስትሪው አቅም እተማመናለሁ" ብለዋል።
አክለውም "ከኤአይ አቅም በፊት ደህንነቱን እንደሚያስቀድሙ" እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረው፣ ያንን ማድረግ ካልቻሉ ግን የሚያበለጽጉበትን "ፍጥነት እንደሚቀንሱ አልያም እንደሚያቆሙ" አስረድተዋል።
ከአልትማን አስተያየት በኋላ የሜታ ሃላፊ ማርክ ዙከርበርግ በኤክስ ገጹ ላይ እያንዳንዱ የኤአይ ቤተሙከራ የሰው ሠራሽ ሞዴሎች እና መሣሪያዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ "የራሱን እርምጃ ለመውሰድ" አቅም እና ተነሳሽነት አላቸው ብሏል።
ዙከርበርግ አክሎም "ይህንን ማድረግ ያልቻለ ማንኛውም ቤተሙከራ ወደ ኋላ መቅረቱ አይቀርም" ብሏል።
"ቤተሙከራዎች ሞዴሎቻቸው ጉዳት የሚያደርሱ ከሆነ ከባድ ተጠያቂነት ይገጥማቸዋል፤ ስለዚህ ይህንን ለመከላከል ጠንካራ ተነሳሽነት አላቸው።"
የናቪዲያ ኃላፊ ጄንሰን ሁዋንግ በተመሳሳይ ማክሰኞ በተካሄደው ጉባዔ ላይ የአይቲ ኩባንያዎች አዳዲስ የቴክኖሎጂ ስሪቶች በውጭ ኃይሎች መተዳደር የለባቸውም የሚለውን መወሰን አለባቸው ብለዋል።
"አዲስ ሕጎች ወይም ደንቦች አያስፈልጉንም" ያሉት ሁዋንግ አክለውም በፈጠራ ፍጥነት እና በኤአይ ምርቶች ደህንነት መካከል "የተሳሳተ ምርጫ" ሊኖር አይገባም ብለዋል።
ኔቪዲያ በዓለም ላይ ትልቁ ኩባንያ ሲሆን ትርፉ እየጨመረ የመጣው በኤአይ ኮምፒውተር ቺፖች ላይ ከፍተኛ ፍላጎት በመኖሩ ነው።
"ደህንነት ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ደህንነት የምህንድስና ችግር ነው" ሲሉ ሁዋንግ ተናግረዋል።
አክለውም የአይቲ ኩባንያ መሪ በማንኛውም ጊዜ በምርታቸው ላይ እምነት ከሌላቸው ምርታቸውን ላለመልቀቅ መምረጥ እንዳለባቸው አክለዋል።
"ይህ በጣም ግልፅ የሆነ ነገር ነው" ያሉት ሁዋንግ "በተቻለህ ፍጥነት መሮጥ፣ ነገር ግን በማንኛውም ጊዜ ተቋሙ ቁጥጥር እያደረገ እንዳልሆነ ከተሰማን ቆም ማለት አለብን" ብለዋል።



![ቀነኒ አዱኛ፣ ሜላት ተሰማ፣ ፀጋ በላቸው፣ ዘውዱ ሃፍቱ፣ ሃይማኖት በዳዳ [ከቀኝ ወደ ግራ]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/660/cpsprodpb/1f2f/live/fcf8c5a0-b109-11f1-bc1f-3f186ca4140c.png.webp)











