ናይጄሪያ በዜጎቿ ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ለማነጋገር የደቡብ አፍሪካን አምባሳደር ጠራች

የፎቶው ባለመብት, KIM LUDBROOK/EPA/Shutterstock
ናይጄሪያ በደቡብ አፍሪካ በቅርቡ በውጭ ዜጎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ዙሪያ ለማነጋገር የአገሪቱን ተጠባባቂ ከፍተኛ ኮሚሽነር ጠራች።
ናይጄሪያ ሰኞ ዕለት በደቡብ አፍሪካ በተከሰቱት ጉዳዮች ላይ ያላትን "ጥልቅ ስጋት" በይፋ ታቀርባለች ተብሏል። ጉዳዩ በአገሮቹ መካከል ያለውን ግንኙነት ሊጎዳ እንደሚችል እንደምትገልጽ ይጠበቃል።
ስብሰባው በቅርቡ ጸረ-ስደተኛ ቡድኖች ባደረጓቸው ሰልፎች እና "በናይጄሪያ ዜጎች ላይ በደረሰ በደል እና በንግዶቻቸው ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች" ላይ ያተኩራል ተብሏል።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ናይጄሪያውያን እና አራት ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። በተመሳሳይ ጊዜ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ዜጎች ላይ ጥቃቶች ተሰንዝረዋል።
በአህጉሪቱ ውስጥ ካሉ ሌሎች አካባቢዎች የሚነሱ ሰዎች ለሥራ ፍለጋ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናሉ።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጥቃቶቹን አውግዘው የውጭ ዜጎች የአገሪቱን ሕጎች እንዲያከብሩም አስጠንቅቀዋል።
በ1994 የአገሪቱን የመጀመሪያውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማስመልከት ባቀረቡት የነጻነት ቀን ንግግራቸውን ደቡብ አፍሪካውያንን የአፓርታይድ ስርዓትን በሚቃወሙበት ወቅት ሌሎች የአፍሪካ አገራት የሰጡትን ድጋፍ አስታውሰዋል።
አንዳንድ የደቡብ አፍሪካውያን ግን የውጭ ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ መግባታቸውን፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሥራ እየወሰዱ እና ከወንጀል ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በተለይም ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋር ግንኙነት አላቸው ሲሉ ይከሳሉ።
ጸረ-ስደተኛ ቡድኖች ሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች ደጃፍ ላይ ሆነው የሰዎችን ማንነት ለመለየት እያስቆሙ ወረቀቶቻቸውን ሲጠይቁ ነበር።
ባለፈው ሳምንት በዋና ከተማዋ ፕሪቶሪያ አንድ ቡድን ባደረገው ሰልፍ ወቅት የውጭ አገር ዜጎች ዓመጽ ሊኖር ስለሚችል ንግዶቻቸውን እንዲዘጉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
በወቅቱ አንድ የናይጄሪያዊ ለቢቢሲ ፒጂን "ነገሮች ደስ አይሉም፤ ሁላችንም ጥቁር ስለሆንን ወንድማማቾች ነን... ሁሉም እዚህ የሚመጣው ለመሥራት ብቻ ነው" ብሏል
በተቃውሞው ምክንያት ወደ ሥራ መሄድ ያልቻለ አንድ የጥበቃ ሥራተኛ "ከአፍሪካውያን ወገኖቻችን የጠበቅነው ነገር አይደለም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"እያስፈራን ነው። አፍሪካ ውስጥ እንዲህ ከፈራን አስቡት ወደ አውሮፓ ብንሄድስ?" ሲል ጠይቋል።
ባለፈው ወር አንድ ጋናዊ ትክክለኛ የኢሚግሬሽን ወረቀቶች እንዳሉት ለማረጋገጥ ሲጠየቅ የሚያሳይ ቪዲዮ በስፋት ከተጋራ በኋላ ጋና የደቡብ አፍሪካን አምባሳደር ጠርታ ነበር።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በኩጎምፖ የወደብ ከተማ የሚገኙት የናይጄሪያ ማኅበረሰብ ሰዎች ኃላፊያቸውን "ንጉሥ" ተብሎ ሊተረጎም በሚችል ባህላዊ ስርዓት እንደሾሙት ከተዘገበ በኋላ ጸረ-ስደተኞች ተቆጥተዋል። በአካባቢው ያሉ አንዳንድ ደቡብ አፍሪካውያን ይህንን የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ እንደሚደረግ ሙከራ አድርገው ቆጥረውታል።
ደቡብ አፍሪካ ወደ 2.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች መኖሪያ ስትሆን ይህም ከጠቅላላው ሕዝብ ከአራት በመቶ ያነሰ ነው። ሆኖም ግን ብዙዎቹ በአገሪቱ ውስጥ በህገወጥ መንገድ እንደሚገኙ ይገመታል።
አብዛኛዎቹ የመጡት እንደ ሌሶቶ፣ ዚምባብዌ እና ሞዛምቢክ ካሉ ጎረቤት አገሮች ሲሆን እነዚህም ለሃብታም ጎረቤታቸው የስደተኛ የጉልበት ሠራተኞችን የማቅረብ ታሪክ አላቸው። አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ናይጄሪያዊያን ናቸው።














