በሦስት አገራት ሲጓዝ ያልተለየው ኬንያዊ የኢቦላ ታማሚ እያነጋገረ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
በኢቦላ ወረርሽኝ ክፉኛ ከተጎዱ አካባቢዎች በአንዱ የቆየው ኬንያዊ ነጋዴ ሕመሙ ከመታወቁ በፊት ወደ ሁለት ተጨማሪ አገራት መጓዝ ችሏል።
የ40 ዓመቱ ግለሰብ በናይሮቢ ሆስፒታል በጠና ከታመመ በኋላ ገዳይ የሆነ ተላላፊ በሽታ እንዳለበት ተረጋግጧል።
የግለሰቡ ሕመም የኬንያ የመጀመሪያ የተረጋገጠ የኢቦላ ኬዝ ሆኗል። ቫይረሱ ከተገኘበት ከሁለት ቀናት በኋላም ሕይወቱ አልፏል።
ቫይረሱ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሚገኙ በርካታ የጤና ተቋማት እና በኡጋንዳ እና ኬንያ ሁለት የአየር ማረፊያ የጤና ምርመራ ጣቢያዎች ሳይለይ መቅረቱ ትልቅ ጥያቄ አስነስቷል።
በአውሮፓውያኑ 2026 ዓመት ብቻ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 4,000 ሰዎች በኢቦላ ቫይረስ ሕይወታቸው አልፏል። ይህም እስካሁን ከተቀሰቀሱ ከባድ ወረርሽኞች ውስጥ ሁለተኛው ገዳይ አድርጎታል።
የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል የኬንያዊውን ታማሚ የስድስት ሳምንታት እንቅስቃሴ ተከታትሎ ቫይረሱን ለመለየት በርካታ እድሎች እንዳመለጡ ገልጿል።
የተቋሙ የድንገተኛ በሽታዎች ዳይሬክተር ዶ/ር ውሳም ማንኮላ ነጋዴው ግለሰብ ታማሚ ሆኖ እንዴት በሺዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትሮችን ሊጓዝ እንደቻለ ግልፅ ስዕል ሰጥተዋል።
ማንነቱ ለሕዝብ ይፋ ያልሆነው ግለሰብ ለሰባት ዓመታት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኖረ እና በሦስት ግዛቶች ውስጥ ለንግድ የተጓዘ ነው።
በኢቦላ ቫይረስ መቼ እና የት እንደተያዘ እስካሁን ግልፅ ባይሆንም በተጓዘባቸው ሦስቱም ግዛቶች ግን ወረርሽኙ እንደነበር የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል።
ግለሰቡ ሕመም ከተሰማው ከሁለት ሳምንት በኋላ ኡጋንዳ ገብቷል።
ኡጋንዳ ኢቦላ መጋቢት ወር እንደተቀሰቀሰ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር በሚያዋስናት ድንበር የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች።
በአገሪቱ በሽታው ቢገኝም ባለፈው ነሐሴ ከኢቦላ ነፃ መሆኗ ታውጇል።
ኬንያዊው ግለሰብ ድንበሩን ሲሻገር በይፋዊ የጤና ፍተሻ ማለፉ ግልፅ አይደለም።
ድንበሩን ከተሻገረ በኋላ በተሽከርካሪ ተጉዞ ወደ ዋና ከተማዋ ካማፓላ ከደረሰ በኋላ ወደ እንተቤ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደርሷል። ከዚያም ወደ ናይሮቢ በአየር ተጉዟል።
የኡጋንዳ ባለሥልጣናት በአየር መንገዱ የጤና ክትትል ሲያልፍ ሙቀቱ መደበኛ እንደነበር ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያዎች በሙቀት እና በራስ መረጃ ላይ የተደገፈ ልየታ ብቻ ግድፈቶች እንዳሉበት ይናገራሉ።
በተመሳሳይ ሁኔታ በናይሮቢ ጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ ቫይረሱ ያልተለየ ሲሆን፤ ቤተሰቦቹ ከአየር ማረፊያው ተቀብለው ወደ ሆስፒታል እንደወሰዱት ታውቋል።
በሆስፒታሉ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የጡንቻ ሕመም፣ የጉሮሮ ሕመም እና በደም መፍሰስ እየተሰቃየ ነበር።
የላብራቶሪ ምርመራ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተቀሰቀሰው ቡንዲቡጎዮ ዝርያ በሆነው ኢቦላ ቫይረስ እንደተያዘ አረጋግጧል።
የጤና ሁኔታው ከመባባሱ በፊት በለይቶ ማቆያ እንዲቆይ ከተደረገ ከቀናት በኋላ ሕይወቱ አልፏል።
የኬንያ መንግሥት ግለሰቡ አገር ቤት ከገባ ጀምሮ ንክኪ አድርገዋል የተባሉ 66 ሰዎች መለየታቸውን አስታውቋል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በኡጋንዳ ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች ለመለየት ጥረቱ በመቀጠሉ የዓለም የጤና ድርጅት ይህ ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ገልጿል።




































